tgoop.com/Terbinos/12731
Last Update:
አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ፡፡ አብርሃም እግራቸውን አጠበ፡፡ በጀርባውም አዘላቸው፡፡ ምሳቸውንም አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም እንደሚበሉ ሆኑለት፡፡ በዚያው ዕለትም የይስሃቅን መወለድ አበሠሩት፡፡ አብርሃም ከደግነቱና እንግዳ ከመውደዱ የተነሣ በተመሳቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ የወጣ የመረደውን፣ የመጣ የሄደውን ሁሉ እየተቀበለ እግዚአብሔርን እያገለገለ የሚኖር ጻድቅ ነበር፡፡ ለዚህም ነው አብርሃም በወይራ ግራር (በመምሬ) ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠለት፡፡ ዘፍ 18፡1-25፣ ሮሜ 4፡-3፡፡ ቀትር ሰዓት ላይ በድንኳኑ ደጅ ተቀምጦ እንግዳ ሲጠብቅ እግዚአብሔር ታየው ተነጋገረው፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ ዐይኑን አራምዶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች ከበላዩ ባለ ተራራ ላይ ቆመው አያቸው፣ ወደ እርሱም ሲወርዱ አይቶ ፈጥኖ ሄዶ ከሰግደላቸው በኋላ ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ…›› እያለ በትሕትና በመጋበዝ ወደ ድንኳኑ አስገብቶ በሚገባ ጋበዛቸው፡፡ ‹‹በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ›› ብሎ አንድነታቸውን፣ ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ›› ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡
••
ያች ሥላሴ የገቡባት የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደገቡ ሁሉ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋዋን ለመዋሐድ የማደራቸው ምሳሌ በመሆኑ አማናዊቷ የሥላሴ ማደሪያ የአብርሃም ድንኳን እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ 1፡35፡፡
••
እግዚአብሔርም አብርሃምን የዛሬ ዓመት ልጅ እንደሚወልድ ነግሮት በዓመቱ ይስሐቅን ወልዷል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ከአብርሃም ድንኳን ወጥተው ወደ ሰዶም ወደ ገሞራ ሄዱ፣ አብርሃምም ይሸኛቸው ዘንድ አብሯቸው ሄደ፡፡ የሄዱትም ሁለቱ ሰዎች አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወልድ በአብርሃም ቤት ቀርቷል ይኸውም ከቤተ አብርሃም ሰው እንደሚሆን ለማጠየቅ ነው፡፡ አብርሃምም ተመልሶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፡፡ እግዚአብሔርም የሚሠራውን ሁሉ ከአብርሃም አይሠውርም ነበርና የሰዶምን የገሞራን ጥፋት ነገረው፡፡ አብርሃምም ይቅር እንዲላቸው አብዝቶ ለመነላቸው፡፡ ሥሉስ ቅዱስን የአብርሃሙ ሥላሴን በምግባር በሃይማኖት ሆነን እናገለግል ዘንድ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን!
••
(ስንክሳር ዘተዋሕዶ ፌስቡክ ገጽ የተወሰደ )
••••
👉🏼 የፌስቡኩ ገፃችን - https://www.facebook.com/terbinos
👉🏼 የቲክ ቶክ የገፃችን - https://www.tiktok.com/@yeamanuelljochi
👉🏼 የቴሌ ግራም ቻናላችን - https://www.tgoop.com/Terbinos
BY ❤️ የአማኑኤል ልጆች ❤️
Share with your friend now:
tgoop.com/Terbinos/12731