tgoop.com/Tfanos/2540
Last Update:
"ክፉ ቀኖች ያልፋሉ ፥ ፅኑ ሰዎች ያልፉታል"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *
ሀ፥ በህወሓት እና በኦነግ መካከል ያለው የፖለቲካ ሽኩቻ የመስዋዕት በግ ፈለገ። ሁለቱ እንዲሸናነፉ ያለ ሀጢያቱ የሚታረድ ሚስክን ተፈለጎ ተገኘ። ያ ምስክን በሀረርጌ ገጠራማ አከባቢ የተከበረ አባት ነው።ሰውዬው እንደዋዛ "ኦነግ ገደ*ለው" ተብሎ ተገ*ድሎ ተጣለ። የሰውዬው ሞት ቤተሰባዊ ምስቅልቅል ወለደ።
ጥላዬ ታደሰ የተባለ ሰቃይ ተማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበር። የአባቱን ሞት የሰማ ቀን ሰማይ ተደፋበት። ተስፋው ጨለመ፥ የመኖር ፍላጎቱ ትቶት ተሰደደ።
ጥላዬ ታደሰ ከአባቱ ሞት በኋላ ሌላ ሰው ሆነ። ሙሉ ለሙሉ ሱስ ውስጥ ተዘፈቀ። ጫት ፥ ሲጃራ እና አረቄ መደበቂያው ሆኑ። ሀዘኑን በአረቄ ሸሸገው።
ጥላዬ ሱሰኛ ሆነ ሲባል ዝም ብሎ ሱሰኛ አይደለም የሆነው። አንድ እሁድ እለት እስኪሰክር ጠጥቶ ተኛ። ከስካር ወለድ እንቅልፉ የነቃው ሰኞ ሳይሆን ማክሰኞ ነው። ከእሁድ እስከ ማክሰኞ በእንቅልፍ አሳለፈ። ሰኞ እለት ሳይኖርባት አለፈች። ጥላዬ ታደሰ ሲሰክር እዚህ ድረስ ነው።
የአባት ሞት ፥ ተስፋ መቁረጥ ፥ ሱሰኝነት ፥ ብተኝነት እየተፈራረቁ የደቁሱት ዶክተር ጥላዬ "ጥላዬ ቀደምኩት" የሚል ህይወቱን የሚናገር ግሩም መፅሐፍ አለው። "ይህ ሰው ማነው?" የሚል ጠያቂ ካለ ዶክተር ጥላዬ ዛሬ የተከበረ የናሳ ሳይንቲስት ነው። አዎን የናሳ ሳይቲስት!
ህይወቱ ከሱስ እስከ ናሳ በአስገራሚ ክስተቶች የተሞላ ነው። የዶክተር ጥላዬ ህይወት የሚነግረን ግሩም መልእክት አለ! ያም መልእክት "ክፉ ቀኖች ያልፋሉ፥ ፅኑ ሰዎች ያልፉታል" የሚል ነው።
ለ፥ ፓስተር ታምራት ሀይሌ "አባት" ብለን ብንጠራቸው ከማያሳፍሩን ጥቂት የሃይማኖት ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ እጅግ የከበረ ስም ካላቸው ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል አንዱ ፓስተር ታምራት ሀይሌ ነው።
የፓስተር ታምራት የትላንት ህይወቱ በብዙ ፈተና እና ውጣ ውረድ የታጨቀ ነበር።
አባቱ ታዋቂ ባለ ውቃቢ ነበር። ያ ብቻ ሳይሆን የአባቱ ውቃቢ እንዲያርፍበት ታምራት ተመረጠ። ከዚህ በኋላ ህይወቱ የሰቀቀን ሆነ። ገና በልጅነቱ ከእኩዮቹ ጋር በነፃነት መንቀሳቀስ የማይችል ሆነ። መናፍስት እየተገለፁለት ያሰቃዩት ነበር።
ቤተሰቦቹ ለሊት ለሊት ወንዝ ዳር እየወሰዱት የአምልኮ ስርኣት ፈፅመውበታል። ሰውነቱን እስኪቆስል በአሸዋ ከፈተጉት በኋላ በውሃ ይነከራል። የልጅ ሰውነቱ ላይ የተፈጠረው ቁስል ውሃ ሲያገኘው ስቃይ ቢፈጥርበትም ለውቃቢው ሲባል ደጋግሞ አድርጎታል።
ታምራት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በሰው ቤት ተቆጥሮ ሲሰራ ከሰው በታች ሆኖ ተዋርዷል፥ ስድብ እና ዱላን እንደዋዛ ተቀብሏል። ራሱን ስለማጥፋት አስቦም ያውቃል።
ዛሬ ላይ ፓስተር ታምራት የተከበረ ሰው ነው። "የታምራት አምላክ ተአምረኛ" የሚል የህይወት ታሪኩን የሚያወሳ መፅሐፍ አለው።
የታምራት ህይወት ምን ይነግረናል? "ክፉ ቀኖች ያልፋሉ!"
ሐ፥ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ጥቂት የላቁ አእምሮዎች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው በቀላሉ የማይደገሙ ሊቅ ናቸው። ብቻቸውን ብዙ ሰው!
ጌታቸው ገና ጨቅላ ሳለ የፋሽስት ወረራ ቤተሰባዊ ምስቅልቅልን ወለደ። ከዛ በኋላ ብዙ አስቸጋሪ ወቅቶችን አሳልፏል።
አባቱ ለትምህርት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ልጃቸው እንዲማር ዘመድ ዘንድ ሰደዱት። ውጤቱ ግን የተገላቢጦሾ ሆነ። ህፃኑ ጌታቸው መማር አልቻለም። እረኝነት እጣ ፈንታው ሆነ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የመማር መብቱን የተነፈገው ህፃን ሰብአዊ ክብሩንም ተቀማ። ሰውነቱ በእከክ ሲወረር አዛኝ አጣ። ሰውነቱ እስኪቆስል ድረስ ማከክ ግዴታው ሆነ።
ወደ አባቱ ሲመለስ የተከበረ ኑሮ አልጠበቀውም። ከአባቱ ጋር በመቃብር ቤት እየኖረ መማር እጣ ፋንታው ሆነ።
ጌታቸው ሀይሌ የእናቱን ፍቅር ሳይጠግብ ገና ጨቅላ ሳለ እናቱ ተለይታው ሄደለች። የእናት ናፍቆቱን የሚወጣበት በቂ እድል አልነበረውም።
አባቱ የጤና እክል ገጥሞት ከአልጋ መዋል ግዴታው ሲሆን ብቻውን ለአባቱ ቂጣ እየጋገረ ይኖር ነበር። እንደ እኩዮቹ መጫወት ሳያምረው አባቱን እያስታመመ እና ለአባቱ ምግብ እያበሰለ ልጅነቱን አሳልፏል።
ትዳር ከመሰረተ በኋላ ሐገር ለማገልገል በሚጥርበት ዘመን የደርግ ሰዎች ሊይዙት ቤቱ ድረስ ከመጡ በኋላ ተታኩሰው ጉዳት አድርሰውበታል። ፕሮፌሱሩ ለረጅም ዘመን በዊልቸር እንዲቀመጥ ያስገደደውን መዘዝ ያመጣው ያ ጉዳት ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ባለ ግርማ ሊቅ ሆነዋል። የስኬት ጫፍ ላይ ተገኝተዋል። ህይወታቸውን "አንዳፍታ ላውጋችሁ" በሚል መፅሐፍ ከትበውታል።
ህይወታቸው ምን ይነግረናል? ክፉ ቀኖች ያልፋሉ!
ሁላችንም በአንዳች አይነት መከራ እያለፍን ይሆናል። እጅ የማይሰጥ ፅኑ መሆን እንዳለብን የብዙዎች ህይወት ይነግረናል!
በእርግጥ ክፉ ቀኖች ያልፋሉ!
Nb፥ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለው "ክፉ ቀኖች ያልፋሉ ፥ ፅኑ ሰዎች ያልፉታል" የሚል የትርጉም መፅሐፍ አንብቤ ነበር። የመፅሐፉ ደራሲ ሮበርት ሹርለ ይመስለኛል።
@Tfanos
@Tfanos
BY Tesfaab Teshome
Share with your friend now:
tgoop.com/Tfanos/2540