tgoop.com/Tfanos/2542
Last Update:
"ተፈራ ሻሎም ሞተ" ተባለ። እንደዋዛ ሞቱን ፌስቡክ ላይ አነበብን።
የሻሸመኔ ልጅ ሆኖ ተፈራን የማያውቅ ማን አለ? በተለይ የዘጠናዎቹ ልጆች ሁሉም ያውቁታል ቢባል ነገሩ ትንሽ ማገነን ያለበት እውነት ይሆናል።
ሻሸመኔ ላይ ሻሎም ጁስ ቤት ስመ ጥር ጁስ ቤት ነው። ዛሬ ላይ ሻሎም ጁስ አቄጣጫ መጠቆሚያ ፥ የሰፈር መጠሪያ ፥ የባጃጅ ፌርማታ ወዘተ ሆኗል። ጁስ ቤቱ የተፈራ ነበር።
በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ጁስ የቀመስኩት ሻሎም ጁስ ቤት ነው። ከአንዱ ዘመዳችን ጋር ሻሸመኔ ሸዋበር ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ሄደን። በዛን ወቅት ወደ ሻሸመኔ በእንግድነት የመጣ ጴንጤ ማክሰኞ እለት ሸዋበር ቃለህይወት ቤተክርስቲያን መሄድ ልማዱ ነው። የፓስተር ጌቱ ዱሬሳ አገልግሎት ተናፋቂ ስለሆነ ሁላችንም በጉጉት አገልግሎቱን እንካፈላለን።
ያኔ እድሜዬ 10 ወይም 11 እያለ ከዘመዳችን ጋር ቃለ ህይወት ሄደን ስንመለስ ወደ ስመ ጥሩ ሻሎም ጁስ ቤት ሄድን። አስተናጋጅ መጥታ ትዕዛዝ ተቀበለችን። ነገሩ ግር አለኝ። ዘመዴ ስፕሪስ ሲል ሰመቼ እኔም ሰፕሪስ አልኳት። ጁሱን ጠጣን። ተፈራ ወደ እኛ መጥቶ "ምን ጎደለ?" አለን። አስገምጋሚ ድምፁ ፥ ወንዳወንድነቱ ታተመብኝ። የመጀመሪያዬ ጁስ የሻሎም ስፕሪስ ሆነ።
ተፈራ "ኪያን አገባት" ተባለ። ኪያ የጎረቤታችን እትዬ አስቴር ልጅ ናት። እትዬ አስቴርን አዴ እንላታለን። የቀበሌያችን ሊቀመንበር ነበረች። ደርባባ ሴት ናት። እንወዳታለን። በሰፈራችን ቴሌቪዥን ካላቸው ጥቂት ሰዎች መካከል አዴ አንዷ ናት። ቤታቸው ሄደን ቴሌቪዥን እናያለን። ሻይ ትሰጠናለች።
የአዴ ልጅ ሙሉ ጌታ የሰፈር ልጆችን ሰብስቦ ኳስ እና ሩጫ ያወዳድረናል። ላሸናፊዎቹ ደስታ ከረሜላ ይሸልማል።
የአዴ ልጅ ኪያ ደግሞ ሱቅ ትልከናለች። ኪያ አንዳንዴ ቸርች አብራኝ ትሄዳለች። ተፈራ መልከቀናዋን ጎረቤታችንን ኪያን አገባ። ያኔ ሰፈራችን መምጣት ጀመረ።
ከእለታት በአንዱ ተፈራ ቤታችን መጣ። ከአባቴ ጋር የተለያዩ ጉዳዮችን ማውራት ጀመሩ። ተፈራ ሲያወራ ግርማ ሞገስ ስላለው በተመስጥኦ እሰማቸዋለሁ።
ተፈራ በወቅቱ ይወቀስበት የነበረ ጉዳይ ነበር። ምን ያህል ብር እንዳተረፈ በሀቅ ለገቢዎች ስለ ሚያሳውቅ ጂ ል ይሉት ነበር። ትልልቅ ሆቴሎች ገቢ ቀንሰው ሲናገሩ እሱ እውነቱን ይናገራል። በዚህ የተነሳ ግብሩ ይጨምርበታል። አባቴ ለምን እንደዚህ እንደሚያደርግ ጠየቀው።
"ጌታ አይወድም። መፅሐፍ ቅዱስ ግብር እንዳጭበረብር አይፈቅድም። እግዚአብሔር ያለኝን ከባረከልኝ ይበቃኛል" አለ። ገረመኝ።
ስምንተኛ ክፍል ሆነን ተፈራ ጋር ሄደን። መዝሙር እየሰማ ደረስን። ተዋወቅነው። "የምህረት ልጅ ነህ አይደል?" አለኝ። ደስ አለኝ። "ምህረት የፀሎት ሰው ናት ፥ ጌታ ይባርካት" አለ። በደንብ ደስ አለኝ።
ጉዳያችንን ነገርነው። "ሰሊሆም የሚባል የስነ ፅሁፍ ህብረት አለን። መንፈሳዊ ፕሮግራም እናዘጋጃለን። ለፕሮግራማችን ትንሽ ገንዘብ እርዳን" አልነው።
ወደ ቢሮ ወሰደን። እጁን ጭኖ ፀለየልን። "እግዚአብሔር ወጣትነታችሁን ይጠብቀው፥ ዘመናችሁ ይለምልም" አለን። ቃል በቃል እንዲህ ነው ያለን። በሞገሳም ድምፁ ባረከን። ጁስ ጋበዘን። ከጠየቅነው በላይ ሰጠን።
"ለወደፊቱ ነጋዴ ከሆናችሁ ግብር እንዳታጭበረብሩ ፥ ለሐገራችሁም ለእግዚአብሔርም ታመኑ" አለን። ደስ አለን።
አንድ የማውቀው ሰው "ቸገረኝ" አለው። "ጊዚያዊ ነገር ከምሰጥህ እኔ ጋር ስራ ጀምር" አለው።
አንዳንድ ሰዎች ብር ሲጠይቁት በነፃ ከመስጠት ይልቅ ስራ ያሰራቸው ነበር።
የሆነ ጊዜ ተፈራ መክሰሩ ተነገረ። ብዙ ገመናዎች አደባባይ ላይ ዋሉበት። አሳዘነኝ። አንድ ቀን ፀጉሩ ድሬድ ሆኖ ፥ ፂሙ ጎፍሮ አየሁትና ደየገጥኩ። አቅፎ ሰላም ሱለኝ ሆድ ባሰኝ።
ከወራት በፊት ሻሸመኔ ስሄድ ካፌ ውስጥ አገኘሁት። በአክብሮት ሰላም ካለኝ በኋላ "እንደ ድሮው አሁንም ትፅፋለህ?" ብሎ ጠየቀኝ። ደስ አለኝ።
አንድ ቀን ልጁን መንገድ ላይ አገኘኋት። በደንብ ሰላም ተባባልን። "ምህረት እና ዳዊት ደህና ናቸው?" አለችኝ። "ኪያ ደህና ናት ወይ?" አልኳት። ከተለየኋት በኋላ "የተፈራን ስልክ ስጭኝ ባልኳት ምን አለ?" አልኩ።
የሆነ ቀን ደውዬለት ባወራው ብዬ አስብ ነበር። ዛሬ ጠዋት የኪያ ወንድም ሙሉ ጌታ ደወለልኝ። ስልኩን እንደ ዘጋሁት አጠገቤ ላለችው ስለ ቤተሰባቸው ነገርኳት። "ሰሞኑን ለተፈራ እደውላለሁ" ብዬ አሰብኩ።
ፌስቡክ ስገባ መሞቱን አየሁ። ተፈራ ሞቷል ተባለ እንደ ዋዛ
@Tfanos
BY Tesfaab Teshome
Share with your friend now:
tgoop.com/Tfanos/2542