tgoop.com/Tfanos/2585
Last Update:
አንድ ሰው ስንት ነው?
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *
አንዳንዶች "ጠቅላይ ሚኒስተሩ አንድ ግለሰብ ነው። እሱ ላይ ትችት ማብዛት ለውጥ አያመጣም። አንድ ሰው ቢቀየር የሚለወጥ ነገር የለም" ይላሉ።
በእርግጥ ጠቅላዩ አንድ ሰው ብቻ ነው? በፍፁም አይደለም። በግለሰብ ደረጃ አንድ ግለሰብ ነው። በስልጣን ደረጃ ግን ብዙ ነው።
ዝርዝር ጉዳዮችን ትተን የሐገሪቱን ሕገመንግሥት እናጣቅስ።
የጠቅላይ ሚኒስተሩን ስልጣን እና ሃላፊነት የሚዘረዝረው የሕገመንግስት ክፍል አንቀፅ 74 ነው። የኢፌድሪን ሕገመንግሥት ያነበበ ሰው በቀላሉ እንደሚገነዘበው ጠቅላይ ሚኒስተር የሚሆን ሰው የተከማቸ ስልጣን ይኖረዋል። የተከማቸ ስልጣን እና ከፍተኛ ሃላፊነት ከፍ ያለ ተጠያቂነትን ቢወልድ አግባብ ነው!
ሕገመንግስታችን በአንቀጽ 74 ንዑስ አንቀፅ 1 እንደሚናገረው ከሆነ ጠሚው ጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው። ይህን በልባችን አኑረን ሌሎች አንቀፆችን እንመልከት።
የሚኒስተሮች ምክር ቤት አባላትን በእጩነት አቅርቦ እንዲያስመርጥ ስልጣን አለው። ደግሞም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ፥ የሚኒስተሮች ምክር ቤት መሪ፥ የሚኒስተሮች አስተባባሪ እና ወካይ ነው።
አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 የውጭ ፖሊሲን ጠቅላይ ሚኒስተሩ በበላይነት እንደሚያስፈፅም ስልጣን ይሰጠዋል። ይህ ማለት የሐገሪቱ ቀዳሚ ዲፕሎማት እንደማለት ጭምር ነው።
ዋና ኦዲተር ፥ ኮምሽነሮች ፥ የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንትን መርጦ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያፀድቃል። (ንዑስ አንቀፅ 7)
በንዑስ አንቀፅ ሁለት እና ንዑስ አንቀፅ ሰባት ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሲቪል ሹመቶችን የመስጠት ስልጣን አለው። (ንዑስ አንቀፅ ዘጠኝ)
ከለይ የተጠቀሱ ነጥቦች ምን ይነግሩናል?
በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስተሩ አንድ ግለሰብ ነው። ነገር ግን ሚኒስተሮችን የሚሾም ፥ ጦሩን የሚያዝ ፥ ከፍተኛ ሹመቶችን የሚሰጥ ፥ የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ አስፈፃሚ ፥ሚኒስተሮችን የሚሰበስብ ደግሞም የሚወክል ፥ ከዋና ኦዲተር እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሚሾም ግለሰብ ነው። ይህን ሁሉ እንዲያደርግ ሕግ ይፈቅድለታል።
እውነት ነው፥ ጠሚው አንድ ሰው ብቻ ነው። ነገር ግን በሕገመንግስቱ መሰረት ከብዙ ሰዎች የላቀ ስልጣን እና ሃላፊነት ያለበት ግለሰብ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስተርነት መንበር በሚሊየኖች ሕይወት እና በቢሊዮን ገንዘቦች የሚወስንበት ቦታ ነው።
"እሱ ምን ያድርግ?" የሚል የየዋህ ጥያቄ ላላቸው ሰዎች ሕገመንግስት መልስ አለው። አድራጊ ፈጣሪዎችን እንዲሾም እና እንዲያዝ ስልጣን የተሰጠው ግለሰብ ምን ያድርግ አይባልም።
ምናልባት "ሕገመንግስቱ በስርኣቱ አልተከበረም" የሚል ክርክር መግጠም ለሚወድ ሰው ሕገመንግሥት መልስ ይሰጣል።
በአንቀፅ 74 ንዑስ አንቀጽ 13 መሰረት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሕገመንግሥት የማክበር እና የማስከበር ሃላፊነት አለበት። ስለዚህ መሰረታዊ የሕገመንግስት ጥሰት ቢፈፀም በንዑስ አንቀፅ 13 የተሰጠውን ሃላፊነት ጠቅላዩ አልተወጣም ማለት ነው።
በእርግጥ ጠሚው አንድ ሰው ነው። ነገር ግን የተከማቸ ስልጣን እና ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት ግለሰብ ነው። ትልቅ ሃላፊነት ትልልቅ ተጠያቂነት ቢያስከትል ተፈጥሯዊ ስለሆነ "እሱ ምን ያድርግ?" የሚለውን አይረቤ ሙግት ማቆም ያስፈልጋል!
@Tfanos
@Tfanos
BY Tesfaab Teshome
Share with your friend now:
tgoop.com/Tfanos/2585