tgoop.com/Tfanos/2590
Last Update:
"ጅብ ቢያነክስ ፥ እስኪነክስ"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *
አንዳንዴ ደግነት የማታለያ ወጥመድ ይሆናል፥ ታማኝ መስሎ መታየት የጠንቃቆችን ትጥቅ ያስፈታል ፥ አንዴ ያመነን እንዲጠራጠር ማድረግ ብዙ አቅምን ይጠይቃል።
አንዳንድ ቸርነቶች ወጥመድ ናቸው፥ አንዳንድ በጎነቶች ከክፋት ይመነጫሉ ፥ አንዳንድ ጥሩነቶች የመጨረሻ ግባቸው ጥፋት ነው።
ሮበርት ግሪን "The 48 Laws of Power" የሚል መፅሐፍ አለው። መፅሐፉ ሰዎችን አታሎ በስልጣን መገኘትን ፥ አጭበርብሮ መከበርን ፥ በተንኮል መንገድ ተፅዕኖ መፍጠርን ይሰብካል። የማታለያ መንገዶችን የሚሰብክ መፅሐፍ ነው። ፖለቲከኞችን መረዳት ለሚፈልግ ሰው ጥሩ ትምህርት ይሰጣል።
መፅሐፉ ላይ ከሰፈሩ 48 ሕጎች መካከል 12ኛው ሰዎችን በልግስና ተግባር እንዴት ማታለል እንደሚቻል ያትታል። "አንድ የቅንነት እርምጃ ብዙ የጥፋት እርምጃን ይሸፍንልሃል" ይላል።
ከመፅሐፉ 2 ምሳሌዎችን እንምዘዝ
ሀ፥ ፍራንቼስሶ ቦሪ በ1695 አ.ም የሞተ የተዋጣለት አስመሳይ ሰው ነው።የሚላን ሰው ሲሆን በአንድ ወቅት ወደ አምስተርዳም አቀና። ለታማሚዎች እርዳታ በማድረግ ይታወቃል ፥ ያለ ምንም ክፍያ ምክር ይለግሳል ፥ ለድሆች ገንዘብ ያድላል፥ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ክፊያ አይቀበልም። በአጭሩ ባለ ግርማ-ሞገስ ደግሞም ቸር ሰው ነበር።
ክእለታት በአንዱ ይህ ደግ ሰው ጠፋ። ሰዎች ፈልገው አጡት።
ከመጥፋቱ በፊት ግን በርካታ ሰዎች ገንዘባቸውን እና ውድ አልማዞቻቸውን በአደራ እርሱ ዘንድ አስቀምጠው ነበር። ምክኒያቱም እርሱ በጎ ሰው ስለሆነ እምነት ይጣልበታል። ሲጠፋ እምነቱን ይዞ ኮበለለ። በአደራ የተቀመጠውን ሀብት ይዞ ተሰወረ።
ደግ ሰው መስሎ ከርሞ ሌባ ሆኖ ጨረሰ!
ጅብ ቢያነክስ ፥ እስኪነክስ!
ምሳሌ ለ
ግሪኮች በትሮይ ጦርነት ጊዜ ጠላታቸውን ድል የነሱት በስጦታ በኩል ነው።
ብዙ ጀግኖቻቸውን ሰውተው የትሮይን ግንብ ማፍረስ አልቻሉም። ከበባቸው ድልን አላዋለደላቸውም ነበር። ከእላታት በአንዱ መፍትሔ ፈጠሩ፥ ስጦታን እንደ ወጥመድ የመጠቀም መፍትሔ!
ለትሮጃኖች በስጦታ የሚቀርብ ግዙፍ የእንጨት ፈረስ ገነቡ። ፈረሱ በውስጡ ወታደሮችን መደበቅ የሚችል ነው። ፈረሱን በከተማው መግቢያ በር ላይ አቆሙት ፥ ትሮዮች ፈረሱን ሲመለከቱ ከአማልክት የተላከላቸው ስጦታ መሰሏቸው ወደ ውስጥ አስገቡት።... ከዚህ በኋላ ትሮጃኖች ሀሴት አደረጉ። በሉ ፥ ጠጡ ሰከሩም። ሲተኙ ከፈረሱ ውስጥ የተደበቁ ወታደሮች ወጥተው አጠቋቸው።
አንዲት ስጦታ የጦርነትን አቅጣጫ ወሰነች። በብዙ መስዋዕትነት ያልተፈታ ወገብ ተፈታ ፥ የማይሸነፍ የመሰለው ተሸነፈ... የስጦታ ወጥመድ!
ተገዳዳሪ ጠላት በስጦታ ይታለላል። ስጦታን እንቢ ማለት ለጥቂት ሰዎች ብቻ የተሰጠ ፀጋ ሳይሆን አይቀርም።
አንዳንዴ ደግነት የማታለያ ወጥመድ ይሆናል፥ ታማኝ መስሎ መታየት የጠንቃቆችን ትጥቅ ያስፈታል ፥ አንዴ ያመነን እንዲጠራጠር ማድረግ ብዙ አቅምን ይጠይቃል።
እርግጥ የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም። ነገር ግን የፈረሱ ሰጪ ልብ መታየት አለበት።
የስጦታ ፈረስን ጥርስ አለማየት ጨዋነት ሲሆን ፥ የሰጪውን የልብ ዝንባሌ መመርመር ደግሞ ብልሃት ነው። ብልሃት እና ጨዋነት አብረው ይሄዳሉ!
@Tfanos
BY Tesfaab Teshome
Share with your friend now:
tgoop.com/Tfanos/2590