tgoop.com/Tfanos/2597
Last Update:
ያየ ሰው ሽመልስ ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ደራሲ ነው። 'ጎቲም ሲሞን' የሚል የልብ ወለድ መፅሐፍ አለው። የዛሬ 10 አመት አከባቢ ነው ያነበብኩት። በዛ መፅሐፍ ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ያለውን ፍላጎት በደንብ አሳይቷል።
ከፋና ሬዲዮ ጀምሮ እከታተለው ነበር። ትንታኔዎችን የሚያቀርብበት መንገድ ደስ ይለኛል። ENN ሲገባ ቋሚ ተከታታዩ ሆንኩ። አብይ ወደ ስልንጣን ሲመጣ ከመንጋው ጋር አልተነዳም። ነገሮችን በጥንቃቄ ለመከታተል ሞክሯል። ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ቀድሞ ተገንዝቧል።
ENN ሲዘጋ ወደ ናሁ ቴሌቪዥን ገባ። እዛም እከታተለው ነበር።
ኢትዮ ፎረም ገና ጥቂት ተከታይ እያለው ጀምሮ እከታተላለሁ። (ኢትዮ ፎረም ላይ ከአበበ ባዩ ይልቅ በብዛት የምሰማው የያሰውን ነው)
በነገራችን ላይ በሐገራችን ያሉትን የሁሉንም ፅንፍ ሚዲያዎች በተቻለኝ መጠን እከታተላለሁ።
Omn፥ ርዕዮት ፥ ኢትዮ ፎረም ፥ ኢቲቪ ፥ ኢትዮ 360 ፥ የሃሳብ ገበታ ፥ ኩሽ ማዲያ፥ ምንግዜም ሚዲያ... ወዘተ። ሁሉንም እሰማለሁ። ከሁሉም የምቀበለው ደግሞም የማልቀበለው አለ።
ያየሰው ሽመልስ መፅሔት ላይ ሲፅፍ ብዕር ይታዘዝለታል። ቴድሮስ ፀጋዬ እና ያየሰው ሽመልስ ከሚጋሩት ፀጋዮች መካከል አንዱ የፅሐፍ ችሎታ ይመስለኛል። ሁለቱም ጥሩ ፀሐፊ ፥ ጥሩ ተናገሪ ፥ ጥሩ ጠያቂ ናቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሩ የህዝብ ግኑኝነት ባለሞያ ያስፈልጋቸዋል። እንደ ያየሰው አይነቱ ሰው ለእንዲህ አይነት ስራ የሚመች ይመስለኛል።
ብልፅግና ፓርቲ በማህበራዊ ሚዲያ ፥ በሜይንስትሪም ሚዲያ ወዘተ ብዙ ፕሮፖጋንዲስቶች አሉት። እኒያ ሁሉ ቢጨመቁ የያየሰውን ሩብ ያህል ተፅዕኖ አይፈጥሩም። በእሱ ፊት ሁሉም ደካማ ናቸው። ምክኒያቱም እሱ በማንበብ አቅም ፥ በፅሉፍ ችሎታ ፥ በስል አንደበት ፥ ሃሳቡን በማደራጀት አቅም ይበልጣቸዋል።
አንዳንድ ሰዎች ያየ ሰውን በወገንተኝነት ይከሱታል። ለምን እንደሚከሰስ ይገባኛል። ግን ያየሰውን በወገንተኝነት የሚከሱ ሰዎች ከእሱ መማር ያለባቸው ቁም ነገር አለ። እሱ በሚሰራበት አቅም ልክ እነሱ ለሚወግኑለት አካል ለመስራት ይጣሩ።
መውጫ ፥
ያየሰው ፈገግ የሚያሰኙኝ አገላለፆች አሉት።
1፥ አብይ አህመድ በሙስሊሙ ኢድ ጊዜ እንደ ሙስሊም በክርስቲያኑ በዓል ጊዜ እንደ ክርስቲያን መሆን መለያው ነው። ይሄን አይቶ ያየሰው "ለፋሲካ ጊዜ የኢየሱስ ወታደር ፥ ለአረፋ ጊዜ የአሏህ ወዛደር" ብሎታል።
2፥ አብይ ወደ ስልጣን የመጣ ጊዜ ከእግሩ ስር መነጠፍ የፈለጉ የአማራ ኤሊቶች ነበሩ። የአብን ሰዎች ፥ የብአዴን ሰዎች ፥ ዛሬ ተቃዋሚ የሆኑ አክቲቪስቶች ወዘተ። እኚህ ሰዎች ያኔ አብይ ሲጋራ ሲያጬስ ቢመለከቱ 'የኔን መዳፍ መተርኮሻ አድርገው' ይሉት ነበር። ያየሰው እኚህን አደር ባዮች "የአብይ አማራ" ብሎ ይጠራቸዋል።
3፥ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ላይ በብዛት ይወድቃሉ። ለወደቁ ተማሪዎች ቀጣይ እጣ ፋንታ ማንም ግድ አይሰጠውም። ይሄን የታዘበው ያየ ሰው "ብርሃኑ ነጋ ሲጥላቸው ብርሃኑ ጁላ ያነሳቸዋል" አለ።
ዞሮ ዞሮ ፥ ፕሮፖጋንዳ መስራት የምትፈልጉ ፥ ዜና መስራት የምትወዱ ወዘተ ከያየሰው ተማሩ።
@Tfanos
BY Tesfaab Teshome
Share with your friend now:
tgoop.com/Tfanos/2597