tgoop.com/TheHabesha0/1737
Last Update:
ሰላም እንዴት ናችሁ ውድ ቤተሰቦች ዛሬ ስለ #ኢትዮጵያ_እና_ኢትዮጵያዊነት በሚል አርዕስት የጀመርኩላችሁን ጥናታዊ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍል ይዤ መጥቻለው እንደተለመደው በልዩ ትኩረትና ማስተዋል ይነበብ መልካም ቆይታ።
ክፍል ፪ ( ሁለት ) ወሰነ ክልል
የጥንቷን ኢትዮጵያ ወሰነ ክልል በተመለከተ ከዚህ እስከዚህ ድረስ ነበር ብሎ በትክክል ለመናገር አያስደፍርም፡፡ እንደ ጥንታዊ መዛግብቱ ከሆነ እጅግ ሰፊ የሆነና በተለያየ ዘመናት አንዴ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ጠበብ ሲል የነበረ ሆኖም ግን የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማዕከል ያደረገ እንደነበር መረዳት አያዳግትም:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 1400 ዓ.ም. ገደማ የተጻፈው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ (ኦሪት ዘፍጥረት) ከኤደን ገነት የሚመነጨው ሁለተኛው ወንዝ ጊዮን የኢትዮጵያን መሬት ይከባል በማለት የዛን ጊዜዋ ኢትዮጵያ መሠረቷ የአሁኗን ኢትዮጵያን ጭምር እንደሚያካትት ይጠቁማል (ዘፍ. 2÷1)::
በሌላ የብሉይ ኪዳን የዕብራውያን መጽሐፍ ‹‹አርጤክስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በ127 አገሮች ላይ ነገሠ (አስቴር 1÷1÷8÷9) በማለት መልክዓ ምድራዊ ፍንጭ ሰጥቷል:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 687 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረው ነብዩ ኢሳያስ ደግሞ ቲርሐቅ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ግብፅ ድረስ ያስተዳድር እንደነበረ ገልጿል (ኢሳ. 37 ÷9-11፣ 1ኛ ነገሥት 19:9)፡፡ የዚህ ጥቁሩ ፈርኦን በመባል የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ንጉስ በአርኪኦሎጂ ጥናትም የተረጋገጠ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ690-664 ዓ.ዓ. ግብፅን ያስተዳድር አንደነበር ተመዝግቧል፡፡
የጥንት ግሪኮች ኢትዮጵያ ደግሞ ሰፊ መልከዓ ምድራዊ ግዛትን ያካለለ ሲሆን ከግብፅ በስተደቡብ ያለውን አጠቃላይ የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ክፍል ‹‹ኢትዮጵያ›› በማለት ይጠሩት ነበር፡፡ ሆሜር በድርሰቶቹ ኢትዮጵያ ትሮይንና የዓረቡን ምድር ትገዛ እንደነበር ገልጿል፡፡ ሄሮዱቱስ ስለኢትዮጵያ ሲያነሳ የአባይ ወንዝና ትልቁን ሐይቅ በማመልከት የመልከዓ ምድራዊ ጥቆማ ሰጥቷል፡፡ ፕሊኒ የተባለው ሌላው ግራካዊ ኢትዮጵያ በጥንቱ ዘመን ሃያልና ዝነኛ እንደነበረችና ሶሪያንና እስከ ሜድትራኒያን የባህር ዳርቻ ድረስ ትቆጣጠር እንደነበር ጽፏል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት 60 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረ ዲኦዶረስ ሲኩለስ የተባለ ጸሐፊ ደግሞ ኢትዮጵያ የግብፅ ትውፊትና ስልጣኔ መነሻ መሆኗንና ኢትዮጵያውያን እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ ያስተዳድሩ እንደነበር ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን የነበረ ትራቦ የተባለ ሌላኛው የግሪክ ጸሐፊ የኢትዮጵያ ግዛት ዓረብን ብቻ ሳይሆን እስከ አውሮፓ ድረስ እንደሚዘልቅ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የግዛት ክልል ቀይ ባህርን ተሻግሮ ደቡብ ዓረቢያ ድረስ ይዘልቅ እንደነበር የታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመኑ ኢዛናና የ6ኛው መቶ ክ/ዘመኑ ካሌብ የመታሰቢያ ሃውልት ጽሑፎች አይነተኛና ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ አስቀድሞ እንደተገለጸው ምንም እንኳ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ወሰነ ክልል በትክክል ለመናገር ባይቻልም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ3ኛውና ከ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ያሉ ማስረጃዎች የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ አክሱምን ማዕከል ያደረገና ከአሁኑ ኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደነበር ያመለክታሉ፡፡
ለዛሬ በዚሁ አበቃሁ በቀጣይ ክፍል እስክመለስ መልካም ቆይታ 👐
• ኢትዮጵያዊነት ሳንፈልገው በግድ የተጫነብን ዕዳ ሳይሆን የተዋብንበት ጌጣችን፣ የከበርንበት
ዘውዳችን፣ የወረስነው ቅርሳችን ነው፡፡
ፍቅር አንድነትን ከጥንት ከመሰረቱ ከታሪካችን እንማር ፍቅር ያሸንፋል ጥላቻንም ያጠፋል!
♥ ኢትዮጵያ ሁን
♥ አፍሪካሁን
♥ ሰው ሁን
🔊 ይህንን ድህረ-ገጽ ለመቀላቀል👇
@TheHabesha0 @TheHabesha0
@TheHabesha0 @TheHabesha0
BY የካሌብ ጽሑፎች
Share with your friend now:
tgoop.com/TheHabesha0/1737