tgoop.com/The_ProphetAB/554
Last Update:
አባት የመጀመርያም የመጨረሻም የሆነ ብቸኛ ልጁን ሊድር ድል ያለ ሰርግ ደግሶ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆቹን ጠርቶ የምሳ ግብዣውን እየተዟዟረ ይመለከታል።
‹‹ማን ቀረ ማን መጣ›› የሚለውን በትኩረት እየተመለከተ ሳለ የቅርብ ጎረቤቱን ከእይታው ያጣዋል። ግራ በመጋባት እየተዟዟረ ቢመለከትም ጎረቤቱንም ሆነ የጎረቤቱን ልጆች ሊያይ አልቻለም።
‹‹የልብ ወዳጄ በዛሬ ቀን እንዴት ከጎኔ ይጠፋል›› እያለ በንዴት ስሜት በመብሰልሰል ላይ ሳለ ድንገት የጎረቤቱ ልጅ ብቅ አለና በፍጥነት ትንሽ ምግብ ቀማምሶ ትቶ ወጣ።
ይህን ትዕይንት የተመለከተው ደጋሽ በንዴት ተብከነከነ። የአባቱ በደስታው ግዜ አለመገኘት ሳያንሰው ልጁ መጥቶ በምግቡ አላግጦ መውጣቱ አበሳጨው።
በዚህ መሀል የሙሽራው አጃቢዎች ሙሽራውን ይዘው ወደ ሙሽሪት ቤት ጉዞ ሊጀምሩ መኪናቸውን ማንቀሳቀስ ሲጀምሩ ምግቡን ቀማምሶ በፍጥነት የወጣው የጎረቤቱ ልጅ ሙሽራውን ለማጀብ ከግቢ መኪናውን ይዞ ይወጣል።
አባት ተበሳጨ፣ ንዴቱን መቆጣጠር ቢያቅተው በቁጣ መንፈስ ተሞልቶ ወደ ጎረቤቱ ልጅ በመሄድ፦‹‹አባትህ ጎረቤቴ ሁኖ ደስታዬ ላይ አልተገኘም፣ ታላላቅ ወንድሞችህም እንደዝያው፤:ታድያ አንተ ምን አስበህ ነው በምግብ አላግጠህ ትተህ የወጣኸው? አሁን ተመለስ ያንተን አጃቢነት አንፈልግም›› ብሎ መለሰው። ልጁም እቤቱ ገባ፤ ሰርገኛዎችም ሙሽራውን ይዘው ወደ ሙሽሪት ቤት አቀኑ።
በመጨረሻም አጃቢዎች ሙሽሮችን ይዘው ወደ ቤት በመግባት የደስታቸው ተካፋይ ከሆኑ በኋላ ቀኑ ሲጨልም ሁሉም ተበታትኖ ሰርግ ቤቱ በሙሽሪት እና በሙሽራው ጭር አለ።
አባት አሁንም በጎረቤቶቹ ንዴት እየተብሰለሰለ ነው። ድንገት ከመሸ ያለ ወትሮው የጎረቤቱ ጊቢ ተከፈተ። የሙሽራው አባት እየተመለከተ ነው።
የጎረቤቱ ልጆች በትከሻቸው አንዳች ነገር ተሸክመው ከቤታቸው ሲወጡም ተመለከተ። ፍፁም ዝግታ እና እርጋታም በሚስተዋልበት እርምጃ ልጆቹ ይራመዱ ጀመር።
የሙሽራው አባት ጠጋ አለ። ፦‹‹ምንድነው?ማንን ነው የተሸከማችሁት ›› ሲልም ጠየቃቸው።
‹‹አባታችን ጠዋት ሞቶ ነው፤ ሲሞትም በሱ ለቅሶ ምክንያት ያንተ ደስታ እንዳይስተጓጎል መሞቱን ከሰርግህ በፊት ለማንም እንዳንናገር እና ድምፅ አውጥተን እንዳናለቅስ ተናዞልን ነበር። ለዝያ ነው ድግሱ ላይ መገኘት ያልቻልነው። ›› በማለት አባታቸውን የተሸከሙት ልጆች ጉዳያቸውን አስረዱ።
ደጋሽ ተፀፀተ፦ ‹‹እኔ በሱ ቦታ ብሆን ይህን የማድረግ አቅም አይኖረኝም ነበር›› ሲልም የቁጭት እንባ ያነባ ጀመር።
በህይወታችን ችላ ያሉ እየመሰሉ በቁስላቸው ደስታችንን ላለማበላሸት ሲሉ ከአከባቢያችን የሚርቁ ሰዎች አሉና ልብ ያለው ልብ ይበል።
Sefwan Ahmedin
አሻም
getu wendesen🙏🙏🙏🙏
BY የተሰበሩ አክናፍ🖤💔
Share with your friend now:
tgoop.com/The_ProphetAB/554