tgoop.com/WinaGfx2/1392
Last Update:
ጥቅምት 27
"እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም፡ ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር"
እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የነበረ የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ኢየሩሳሌም ተሰቅሎ ባፈሰሰው ደሙ መድኃኒትን አደረገ ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት /መዝ. 73፡12/
ይህ በመጋቢትና በጥቅምት 27 ቀን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት የምናከብረው በዓላችን ዓመተ ፍዳው፤ ዓመተ ኲነኔው አክትሞ የሰው ዘር የሆነው ሁሉ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት፣ ከሲኦል ወደገነት፣ የተመለሰበትና የተሸጋገረበት ዕለት መሆኑን ለማዘከር ነው፡፡ አዳም በሥላሴ አርአያና አምሳል ተፈጥሮ ጸጋ እግዚአብሔርን ተጎናጽፎ ነጻ የኅሊና ፈቃድ ያለው ሰው ሁሉ ገነትን ያህል ቦታ ይዞ ሥዩመ እግዚአብሔር፡ ነቢየ እግዚአብሔር፣ ካህነ እግዚአብሔር ሁኖ ለሰባት ዓመታት በስነ ሥርዓት በገነት ይኖር ነበር፣ ይሁንና እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም እጅግ መልካም ሆነ /ዘፍ. 1፡31/ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደምንረዳው እግዚአብሔር አምላካችን በስድስቱ ቀናት የፈጠረው ሁሉ መልካም ሲሆን በተለይም በሥላሴ አርአያና አምሳል ለተፈጠረው ሰው የሕይወት እስትንፋስን ሰጥቶ በገነት በሕያውነት እንዲኖር ያስቀመጠው የከበረ ክቡር ፍጡር ነበር፡፡ "ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ ይላል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፡፡
እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ አድርጎ ቢፈጥረውና የጸጋ ገዥ ቢያደርገው ያልተሰጠውን የባህርይ አምላክነትን በመፈለጉ የገዥና የተገዥ፣ የፈጣሪና የፍጡር መለያ የሆነውን ትእዛዘ እግዚአብሔርን በመጣሱ በዚህ ምክንያት ሞተሥጋ፣ ሞተ ነፍስ ተፈረደበት፡፡ ከክብሩ ተዋርዶ ከገነት እንዲወጣ ተደረገ፡፡ ተመልሶ ወደገነት ገብቶ ተጨማሪ ኃጢአትን እንዳይሠራም ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ሜሎስን በእጃቸው የያዙ ኪሩቤልን በኤደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ ይላል የሙሴ መጽሐፍ፡፡ /ዘፍ. 3፡22-24/
አዳም ሳይቸገር በጠላት ከንቱ ስብከት እንደእግዚአብሔር ለመሆን ክፉውንና ደጉንም ፈጥኖ ለማወቅ ቸኩሎ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱ ወደቀ፣ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ፡፡ በሰው ሕይወት ላይ አሳፋሪ፣ አስፈሪና አስነዋሪ ታሪክ ፈጸመ፡፡ አዳም እግዚአብሔር አታድርግ ያለውን የአምላኩን ትእዛዝ በማፍረስ የሞተ ሞት ተፈረደበት፡፡ ከዚህ አሳፋሪና አስፈሪ ታሪክ በመነሣት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለሞት ማሰብ ለማንም ሰው ቢሆን ቀላል ነገር አልሆነም፡፡ ያ ሰው የኖረው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ የሁሉ እድል ፈንታ በሆነበት ጊዜ ነበርና ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞተ ከእርሱ በኋላ ፍርድ ተመደበባቸው ይላል፡፡ ዕብ. 9፡27
ነቢዩ ሕዝቅኤልም እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፣ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች፣ ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፣ ኃጢአትየምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች፡፡ /ሕዝ. 18፡4/ በማለት የዚህን ማስጠንቀቂያ፣ ኃይለኛነትና ጥብቅነት ያሳያል፡፡ በቀል የእኔ ነው እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና ደግሞም ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል፣ በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅም የሚያስፈራ ነው ያላል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ /ዕብ. 10፡30-31/፡፡
ስለዚህ፣ ሞት፣ የኃጢአት ዋጋ ሆኖ በኃጢአት ምክንያት የመጣ ቢሆንም በኃጢአት ላይ የተሰጠ የመጨረሻ ፍርድ /ቅጣት/ ባለመሆኑ ከሞት በኋላ ሌላ ፍርድ የሚጠበቀን መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ይሁንና ቀዳማዊ አዳም በስህተቱ ተጸጽቶ በማዘኑ፣ በማልቀሱና ንስሐ በመግባቱ ለቸርነቱ ወሰን የሌለው አምላክ ንስሐውን ተቀብሎ የተስፋ ቃል ሰጠው፡፡ የተሰጠውም የተስፋ ቃል አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋዬን ቆርሼ ደሜን አፍስሼ አድንኅለሁ የሚል ነበር፡፡ ይህ የተስፋ ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ፣ ትንቢት ሲነገር ሱባኤ ሲቆጠር ኖሮ አምስት ሺህ አምስት መቶ የተስፋው ዘመን ሲፈጸም የተናገረውን የማይረሳ፣ የሰጠውን ተስፋ የማይነሣ እግዚአብሔር "ክርስቶስኒ መጽአ በዕድሜሁ ይሙት በእንተ ኃጢአትነ እንዘ ኅጥአን ንሕነ" /ሮሜ. 5፡6/ ይላል ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ጊዜው ሲደርስ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጅ ኃጢአት ሊሞትመጣ፣ ሰው ሆነ በሥጋም ተወለደ፣ በተወለደ በ30 ዘመኑ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ጾመ፣ በሰይጣን ተፈተነ፣ ፈታኙ ሰይጣንም ባቀረበው ፈተና ድል ተመታ፣፣
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራውን የጀመረው በጥምቀት፣ በጾም በጸሎት በትምህርት በተአምራት ሲሆን ሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት በይሁዳ፣ በሰማርያና በገሊላ አውራጃዎች በቅድስት ሀገር እየተዘዋወረ ወንጌልን አስተማረ፡፡ ትምህርቱ እየሰፋና እየተዳረሰ ሲሔድ የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ለሕማም፣ ለሞት፣ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ተሰቀለ፣ በሥጋ ሞተ፣ ተቀበረ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ውሎና አድሮ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ሞትን ድል አደረገ፡፡
ስለሞተ ነፍስና ሞተ ሥጋ ብዙ ተብሏል፣ እየተባለም ነው፣ እነዚህ ሁለቱም በመጀመሪያው ሰው፣ ሕግ ተላላፊነት በአንድ ወቅት በሰው ሕይወት ላይ የደረሱ አሳዛኝ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ለማለት እንደሞከርነው በመጀመሪያው ሰው ሕግ ተላላፊነት ሞተ ነፍስና ሞተ ሥጋ በዚህ አጋጣሚ ሁለቱም በዚያን ጊዜተያየዘው የመጡ ሲሆን ሞተ ነፍስ በ34 ዓ.ም በማዕከለ ምድር ቀራንዮ በስግው ቃል ሞተ ሥጋ አክትሞለት ሁሉም የአዳም ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት፣ ከሲኦል ወደ ገነት ተመልሷል፣ ይሁንና ሞተ ሥጋው የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ትንሣኤ ዘጉባኤን በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በዚያን ጊዜ ሞተ ሥጋውም ያከትምለታል፡፡ በዚያን ጊዜ በማዕከለ ምድር ቀራንዮ፣ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል አናት ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ የሚል በእብራይስጥ በፅርዕና የሮማይስጥ ተጽፎና ተለጥፎ ይነበብ ነበር፡፡ የእነዚህ የሦስቱ መንግሥታት የሥልጣን፣ የሥልጣኔና የጥበብ ኃይል በአንድነት ቢተባበሩም የክርስቶስን ኃይል ሊቋቋሙት አለመቻላቸው በግልፅ ታይቷል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞት መደምሰሻ፣ የሰይጣን ድል መንሻ፣ የድኅነት ጋሻ ያደረገው መስቀል በክርስትና ሕይወት የላቀ ክብርና ቦታ ያለው ሆነ፡፡ሰውን በስቅላት መቅጣት የተጀመረው የፋርስ ባቢሎን እንደነበረ በታሪክ የሚታወቅ ሲሆን መስቀል ከዘመነ ሥጋዌ በፊት የወንጀለኞች፣ የኃጢአተኞችና የበደለኞች መቅጫ መሣሪያ መሆኑ የታወቀ ነበር፡፡ ጌታ በዚህ ዓለም በተገለጠበት ጊዜ በዓለም ግዛቱን አስፍቶና አስፋፍቶ የነበረው የሮሜው የቴሣሩ መንግሥት ይህን የስቅላት አሠራር ልምድ ከፋርስ ባቢሎን ወርሶ ምንም ዓይነት ኃጢአት ሳይኖርበት በኃጢአተኞች ይሙት በቃ የተፈረደበት ጌታችን፣ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሰቀልላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ፍርድን ሰጠ፡፡
BY ✝️ኦርቶዶክስ pictures by Wina Gfx
Share with your friend now:
tgoop.com/WinaGfx2/1392