tgoop.com/bemaledanek/2391
Last Update:
ስንጀምረው ተፈጥሮ ለኛ ትሠራ ዘንድ ነበረ የተፈጠረቺው፡፡ መጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 10'ን ስናይ፤ ኢያሱ በእግዚአብሔር ፊት ፀሐይን በገባዖን ምድር አቁሟታል፡፡ ጨረቃንም አዘግይቷታል፡፡ እኛ አሁን እግዚአብሔር ፊት መቆም ስላቃተን ለተፈጥሮ ብቻ ለመሥራት ተገድደናል፡፡ አልፎም ተርፎ አንዳንዴ ተፈጥሮ ስትከዳን ለመኖራችን አደጋም ጭምር ታመጣብናለች፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ባሕር ከፍለው ተሻገሩ የሚለውን ታሪክ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ይዘው፤ ዛሬ ከአገር ሊወጡ ሲሹለከለኩ፣ እንደ ዕቃ ሲጫኑ ሲወርዱ፤ ባሕር ደርምሷቸው ስንቶች የዓሳ እራት ሆነው እንደቀሩ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ስንቶች አለቁ? መሬት ሲንሸራተት የስንት ሰዎች ሕይወት አብሮ ተንሸራተተ? የጎርፍ ውኃ ስንቶችን እያላተመ ወሰደ? የእሳት ሰደድ የስንቶችን ሕይወትና ኑሮ አነደደ? የአውሎ ነፋስ ወጀብ ስንቶችን ለሥርዓተ ቀብር አስክሬናቸው እንኳ እንዳይገኝ አርቆ ቀበረ?
እግዚአብሔር የሌለው የሰው ልጅ በተፈጥሮ ሥር ነው፡፡ አሁን በዚህ በምዕራባውያኑ እና ሩቅ ምሥራቃውያኑ ውስጥ ያሉ አገሮች ከአሁን አሁን መሬት ከዳችን እያሉ ከሚመጣው አደጋና ሰቆቃ ለመትረፍ ቤት ሲሠሩ፣ መንገድ ሲገነቡ፣ ኢንደስትሪ ሲተክሉ የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም እንዲችል አድርገው ነው፡፡ ለዘመናትም በዚህ የተፈጥሮ ግብ ግብ መካከል የኖሩ ዜጎችም ተፈጥሮን እየፈሩ፣ ተፈጥሮን ባለማመን እየጠበቁ፣ ተፈጥሮን አጨንቁረው እያዩ ይኖራሉ፡፡
በዘመነ ፍዳ የዲያቢሎስ ክንድና አገዛዙ ሰልጥኖ ከሕግ በታች አድርጎ የሰው ልጆችን በዘር ጉዳትና ውድቀት ውስጥ አስሮ፤ ስጦታችንን ሲፋለም የኖረበትን ዘመን ወደ ምሕረት ሊለውጠው እግዚአብሔር ቃል ፍቅር ይዞት ሥጋ ሆነና ጸጋንና እውነትን ተመልቶ ወደ ጊዜና ወደ ሕይወታችን መጣ፡፡ ሲመጣ ከሰጠን ታላላቅ ሰማያዊ በረከቶች መካከል አንደኛው ንጹሕ ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነው፡፡
ታዲያ ይሄን ክቡር ሥጋና ደም ስንቀበል ተፈጥሮን ማገልገላችን ይቀርና ተፈጥሮ እኛን ለማገልገል ወደ ኑሮአችን ትታዘዛለች፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያውን ንጹሑን የአዳም ስብእና እያገኘነው እያገኘነው ስለምንሄድ፤ በነፍስ ወረቀታችን ላይ የተጻፈው ተፈጥሮን የማዘዝ ሥልጣን መገለጥ ይጀምራል፡፡ እነሆ፥ ተፈጥሮ ላንተ እንድትስማማ የክርስቶስ ሥጋና ደም ያስፈልግሃል፡፡ "የሰማይ አባታችን ሆይ፥ ለአዳም የሰጠኸውን ቀዳሚ ጸጋና ሞገስ እንዲሁ በኔ ሕይወትም ስጠኝ፡፡ ጊዜና ዘመን እንዳይገዛኝ የሕይወቴን መግቢያ መውጪያ ተቆጣጠረው፡፡ የመኖርን ሚስጢር ከሰማያዊ ስጦታዎችህ ጋር ግለጥልኝ፡፡ የዕረፍቲቱን ቀን ኃይል በባሕሪዬ ውስጥ አኑርልኝ፡፡ ሕያው እውነትህ በኑሮዬ ውስጥ ይጀምር" እያልክ ቅዱስ ቁርባን ስትወስድ .. ያን ጊዜ የተፈጥሮ ባለቤት መሆን ትጀምራለህ፡፡ ጊዜ አንተ ስለለፋህ ብቻ ሳይሆን ጊዜው አንተን ሊያግዝህ የማያቋርጡ ዕድሎችን እየያዘ ወዳንተ ይመጣል፡፡ ሁኔታዎች አንተ ስለተጨነቅላቸው ሳይሆን ሁኔታዎች ላንተ ሊጨነቁልህ ወዳንተ ይገሰግሳሉ፡፡ በረከት አንተ ስለደከምክለት ብቻ ሳይሆን፤ ስለወጣህ ስለወረድክለት ሳይሆን፤ በረከት ካንተ ጋር ለመሆን ወዳንተ ይመጣል፡፡ የሚደግፉህና የሚያበረቱህ ልበ ቀና ሰዎች ሳትጠራቸው ወዳንተ ይመጣሉ፡፡ የሚያስፈልግህን ሁሉ በጊዜ ጊዜው እንድትሰጥህ ተፈጥሮ ከሰማይ አምላካችን ትእዛዝ ትቀበላለች፡፡ ከዛ በኋላ ሰውና ዲያቢሎስ የቱንም ደረጃ ያህል ቢሮጡ አይቀድሙህም፡፡ ክፉዎች የዘጉት በር ሁሉ እየተከፈተ፥ የከፈቱትም ሁሉ እየተዘጋ፤ የበረከትና የሰላም ገባር ወንዞች ወዳንተ የሕይወት ወንዝ ያለማቋረጥ እየመጡ ይቀላቀላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን❕
ይሄ የሚሆነው ግን በመጀመሪያው አቋም ሲኖረን ነው፡፡ በተሰበረ ልብና የእውነት ፍቅር ወደ እግዚአብሔር የመጠጋት ቁርጠኝነት ሲኖረን ነው፡፡ በቅዱስ ቁርባኑ በመቀደስ ከውስጥም ከውጪም የዘላለማዊነትን ቅርጽና ገጽታ መያዝ ስንጀምር ተፈጥሮ ለአዳም እንደታዘዘቺውና እንዲጠብቃትም እንደተሰጠቺው ወዳንተ እርዳታዎችን ልታደርግልህ ትመጣለች፡፡ የዛሬው ትውልድ ተፈጥሮ የሸሸቺው ትውልድ ነው፡፡ ዓለም ሲደነግጥ አብሮ የሚደነግጥ፣ ዓለም ሲፈራ አብሮ የሚፈራ፣ ዓለም ሲሸወድ አብሮ የሚሸወድ ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህ የሕይወት ምሪቱንና የራእይ መረጃዎቹን ከቴሌቪዥን፣ ከኢንተርኔት፣ ከጋዜጣና ከመገናኛ አውታሮች ብቻ የሚጠብቅ እየሆነ፤ ዜናዎች ሲጨክኑ እየተሳቀቀ፣ ዜናዎች ሲያበስሩ እየፈነጠዘ፣ ዜናዎች ሲወሳሰቡ ግራ እየተጋባ የሚኖር ሆኖ ይገኛል፡፡
ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
BY በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
Share with your friend now:
tgoop.com/bemaledanek/2391