tgoop.com/bemaledanek/2397
Last Update:
3• ቅዱስ ቁርባን
ክፍል - ፭
3.2• ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?
3.2.1• በእግዚአብሔር በኩል
✞ ሀበነ ንኅበር ✞
"ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ ከመ ብከ ንሕያው ዘለኩሉ ዓለም ወለዓለመ ዓለም፡፡"
"የአንተ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ ስጠን በዚህም በሥጋው በደሙ አድነን ለዓለሙ ሁሉ በምትሆን በአንተ ለዘላለሙ ሕያዋን እንሆን ዘንድ"
መጽሐፈ ቅዳሴ
እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር አንድ አዳምን ነው የፈጠረው፡፡ የሰው ልጆች ሁላችን የተገኘነውና የምንገኘው ከዚህ አንድ ሰው ነው፡፡ አዳምን እንደ አንድ ትልቅ ወንዝ ማየት እንችላለን፡፡ አስቀድሞ ሔዋን የተባለች ሴት ከዚህ ወንዝ ተቀድታ ወጣች፡፡ በመቀጠል አቤልና ቃየን ወጡ፡፡ እያለ እያለ ..
ሁላችን ከአዳም ተገኝተናል ካልን፤ በአዳም የሆነው ሁሉ በኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከደፈረሰ ወንዝ የደፈረሰ ወንዝ እንዲቀዳ፤ የአዳም ባሕሪይ ለሞት በመታዘዙ ምክንያት፤ እኛም የምንሞት ሆነናል፡፡ ሞትን ለምሳሌ ያህል ጠቀስን እንጂ፤ አዳም የገነቱን ስሕተት በመፈጸሙ ምክንያት የመጡበትን ጉስቅልናዎች ሁሉ ተካፍለናቸዋል፡፡ መራብ፣ መጠማት፣ መታመም፣ ማርጀት፣ መድከም፣ .. የሚባሉ የጸጋ መገፈፍ ውጤቶችን ከአባታችን አዳም ሁላችን ተቀብለናል፡፡
አዳም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጣሰ ጊዜ፤ የተጣላው ከአምላኩ ጋር ብቻ አልነበረም፡፡ ከእራሱ ጋርም ተጋጭቷል፡፡ ነፍስና ሥጋው በተለያየ መሻትና ስበት የሚቃረኑ ሆነውበታል፡፡ በውስጡ ከተጻፉት የተፈጥሮና የፍጥረታት ባሕሪያት ሁሉ ጋር ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይሄም የውስጥ ጸብ በውጪኛው ገጽታ በተጨባጭ ሲገለጽ፤ ሰውን ፀሐይ ታተኩሰው፣ ዝናብ ይቀጠቅጠው፣ እሳት ያቃጥለው፣ ድንጋይ ይፈነክተው፣ ጉንዳን ይቆነጥጠው፣ ጃርት ይወጋው፣ ጊንጥ ይነድፈው፣ ውሻ ይነክሰው፣ ድመት ትቧጥጠው፣ .. ጀመር፡፡
ይሄ የውስጥ ቅዋሜ በውስጠኛው ማንነታችን ላይም የሚነበብበት የራሱ ገጽ አለው፡፡ በዝርዝር እንየው፡፡
በኦሪት ዘልደት መግቢያ ምዕራፍ ላይ የምናገኛቸው ተፈጥሮና ፍጥረታት የተፈጠሩበት ስድስት ተከታታይ ቀናት አሉ፡፡ እነዚህ ቀናት አንድን ፍጥረት በአካል ሲያስገኙ፤ ያ አካል ደግሞ ከሌሎች ፍጥረታት ራሱን የሚለይበት ልዩ ባሕሪይ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው የቀን ሥርዓት የተገኘውን እሳት ብንመለከት፤ እሳት የውዕይት (የማቃጠል፣ የመተኮስ፣ የመንደድ) ባሕሪይ አለው፡፡ ይሄ ባሕሪዩ የራሱን የእሳትነት አካል መልክና መገለጫ ያደርጋል፡፡
ስድስቱ ቀናት ተከታታይ ሲሆኑ፤ የአንዱ ቀን ፍጡራን ባሕሪያት ለሚከተለው ቀን ተፈጣሪ አካል መጋቢ ባሕሪይ ይሆናሉ፡፡ ይህም ማለት ፍጡራኑ በቅደም ተከተል እንደተፈጠሩበት አደራደር ቀዳሚው ባሕሪይ በተከታዩ አካል ውስጥ መዋቅር ሆኖ ይገባል፡፡ ፀሐይን እንመልከት፡፡ በሦስተኛው የቀን ሥርዓት የተፈጠረቺው ፀሐይ የአንደኛው ቀን ፍጡራን የሆኑትን እሳትና ብርሃን በባሕሪይዋ ውስጥ ተደምረው አሉ፡፡ አስቀድመው በተገኙ አካላት ላይ የተጻፉ ባሕሪያት በቀን ወደፊት ውስጥ እየተሰበሰቡ የቀጣዩን ቀን ፍጡር ባሕሪያት ይቀርጻሉ ነው በአጭሩ፡፡
የሰው ልጅ በስድስተኛው ቀን ላይ የተፈጠረ የመጨረሻው ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህ ከአዳም በፊት ተፈጥረው የተገኙ ባሕሪያት ሁሉ ተሰብስበው ከውስጡ አሉ (የሰው ልጅ ተነብቦ የማያልቅ መጽሐፍ መባሉ በነዚህ የባሕሪያት ስብጥርነት የተነሣ ነው)፡፡
በግ የዋህ እንስሳ ነው፡፡ አጠገቡ አንድ በግ አርደህ ይህኛውንም ልትደግመው ብትጠጋው አይሸሸህም፡፡ ፍየል ላይ ይሄ አይሠራም፡፡ ብልጥ ናት፡፡ ውሻ ለባለቤቱ ታማኝ ነው፡፡ ተንከባከበው አልተንከባከበው ጌታውን አይከዳም፡፡ ድመት በቤት የምትቆይበት ጊዜ እንደ ምቾቷ ይወሰናል፡፡ ካልተስማማት አለፍ ብላ ጎረቤት ስትጠጋ አንዳች ቅር አይላትም፡፡ ተኩላ ነጣቂ ነው፡፡ የሚሆነውንም የማይሆነውም መንትፎ መሄድ ምርጫው ነው፡፡ ጉዳን ታታሪ ነው፡፡ የጀመረውን ሥራ ሳይፈጽም ማረፍን አይፈልግም፡፡ እስስት አከባቢዋን ቶሎ ትለምዳለች፡፡ ራሷን ታመሳስላለች፡፡ ሣር ለተነፈጠበት መልክአ ምድር ውበት ነው፡፡ ዙሪያውን ያደምቃል፡፡ ነፋስ ወዳጅ የለውም፡፡ ወዳገኘበት ስፍራ በነጻነት ይሄዳል፡፡ ከዋክብት በማታው ክፍለ ጊዜ ያሸበርቃሉ፡፡ በአንድነት ሲታዩ ይደምቃሉ፡፡ እነዚህ ባሕሪያት በኛም የማንነት መዝገብ ላይ ድርሻ ይዘው የሰፈሩ ጠባያቶቻችን ናቸው፡፡
የባሕሪያቱ ስብስብ (እንደ ሕዝብ ብናያቸው) የበላይ የሆነ ገዢ ባሕሪይ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለበዚያ አንዱ ባሕሪይ ከአንዱ ባሕሪይ ጋር በተቃረነ ቁጥር ቀውስ ይፈጠራል፡፡ አራዊቱ እንስሳቱን ካሳደዱ ሰላም አይኖርም፡፡ ውኃው እሳቱን ካጠፋው ችግር ይኖራል፡፡ ድንጋይ የነፋሱን መውጪያ ከደፈነበት ባርነት ይከሰታል፡፡ በመሆኑም ባሕሪያቱን ሁሉ ተቆጣጥሮ የሚገዛ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ በየረድፋቸው፣ በየፈረቃቸውና በየቦታቸው እንዲገለጡ የሚያዝዝ አስተዳዳሪ ሊኖር ግድ ይላል፡፡
የባሕሪያትን መገለጥ ልክ ሰጥቶ የሚገዛቸው ታላቁ ባሕሪይ የነፍስ ባሕሪይ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር አካል ተከፍሎ ወደ ሰው የገባው መለኮታዊው እስትንፋስ፤ የተገኘው ከእግዚአብሔር ነውና ባሕሪዩም የእግዚአብሔር ነው፡፡ እንኪያስ "የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ" የሚለው የሥልጣን ዙፋን የተዘረጋው ለነፍስ መቀመጫነት ነው፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 1፥26)
ይሄ ውስጣዊ ተቋም ወደ ውጨኛው ገሐድ ሲገለጥ በባሕሪያት ላይ የታየው መስማማትና መፈቃቀድ በአዳምና በፍጡራን መካከል ይታያል፡፡ አገላለጹን ሌላ ገጽታ ስንሰጠው፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮንና ፍጥረታትን እንዲያስተዳድር ነፍሱ በባሕሪያቱ ሁሉ ላይ መንገሥ አለባት፡፡
የላይኛውን አንቀጽ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ዋቢ እናድርገው፡፡ "አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው" ኖኅ፤ የፍጡራን ሕይወት በጥፋት ውኃ ምክያትነት ከምድር ጠፍቶ እንዳይቀር ወደ ገነባው ግዙፍ መርከብ እንዲያስገባቸው ታዝዞአል፡፡ ታዲያ ፍየሉና ነብሩ፣ አይጥና ድመቱ፣ ሚዳቋና ነብሩ እንዴት ሳይቀዋወሙ ሰልፋቸው ጠብቀው እንደገቡ ሰልፋቸው ተከትለው ወጡ?
በኖኅ ማንነት ላይ ሠልጥና ያለቺው የእግዚአብሔር እፍታ ከውስጡ ያሉትን ባሕሪያት ተቆጣጥራ ስለገዛቻቸው፤ እንስሳቱና አራዊቱ በኖኅ ፊት ሳሉ አይጣሉም፡፡ ተደጋግፈው እንጂ ተገፋፍተው አይቆሙም፡፡ አካሄዳቸውን "ከዓለም ጋር አድርገው" የነበሩት የኖኅ ጎረቤቶች ቢሆኑ ኖሮ ግን መርከቢቱን የሚመሩት፤ እንስሳቱ ተበልተው አራዊቱ ብቻ ይቀሩ ነበረ፡፡
ወደ ነጥባችን ስንመጣ፤ አካሄዳችንን ከዲያቢሎስ ምክር እንጂ ከእግዚአብሔር አሳብ ጋር ባለማድረጋችን ምክንያት ነፍስ በሰውነት ላይ ከነበራት ኃይል ፈረሰች፡፡ ባለሥልጣን መሆኗ ቀረና እንደሌሎቹ ባሕሪያት ወደ ውስጥ ተሻጠች፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ባሕሪያት ድብልቅልቃቸው ስለወጣ፤ አዳም ውሳጣዊ ማንነቱን መግራት የማይችል ሆነ፡፡
"አቤቱ፥ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፥ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።"
(ትንቢተ ኤርምያስ 10፥23)
BY በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
Share with your friend now:
tgoop.com/bemaledanek/2397