tgoop.com/bemaledanek/2401
Last Update:
3• ቅዱስ ቁርባን
ክፍል - ፭ የቀጠለ..
✞ አንድ አድርገን ከራሳችን ጋር ✞
"ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።"
(ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፥18)
ባሳለፍነው ክፍል፥ ከእግዚአብሔር ስንጣላ ከራሳችንም እንደተጣላን አውስተናል፡፡ በዚህ ውስጣዊና ውጪያዊ ጥል ዲያቢሎስ ተመክቶ፤ ከውስጥ ያለው የባሕሪያትን ቀውስ ተገን በማድረግ የሕይወት አካሄዳችን ከራሳችን ጋር እንዳይሆን ያደርጋል ስንልም ተነጋግረናል፡፡ አሁን ወደ መፍትሔው እንምጣ፥ አንድ ወደ ማድረጊያው!
አዳም ራሱንም ፍጥረታትንም ሲገዛ የነበረው ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዝቶ በቆየበት ጊዜያት ሳለ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አዳም ውሳጣዊና አፍአዊ ሰላም ከኃይል ጋር የነበረው ከእግዚአብሔር ጋር እያለ ነው፡፡
የሰው ልጅ ከአምላኩ ሲለይ ከራሱም ተለየ ካልን፥ ወደ ፈጣሪ ሲመለስ ወደራሱም ተመለሰ ማለት ይሆናል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶሰ ዳግማዊው አዳም ነው፡፡ ዳግም የተወለደው አዳም ማለት ነው፡፡ "ዳግም" ተወለደ ከተባለ፥ የነበረው በድጋሚ ተወልዷል እየተባለ ነው፡፡ በዘፍጥረት በእግዚአብሔር ፈቃድ ተጸንሶ በገነት ማኅፀንነት ያድግ የነበረውን የሰው ልጅ ባሕሪይ፥ ሳይለውጥ ሳይጨምርበትገንዘብ አድርጎት መሢሑ በሥጋ መጥቶአል፡፡
ነገሩን በስብዕና አንቀጽ ብቻ ስናየው፤ የመድኃኒቱ ሥጋ በዘፍጥረት የነበረውን የአዳምን ንጹሕና ቅዱስ ባሕሪይ ባሕሪዩ ካደረገ፤ ልክ እንደ መጀመሪያው የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ያልተለየ፥ ኃጢአትን የማያውቅ፥ የመለኮትን ጸጋና እውነት የተመላ ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሥጋ ላይ ተፈጥሮና ፍጥረታት አይጣሉም፡፡ ባሕሪያት ቀውስ ውስጥ አይገቡም፡፡ ከዚህም የተነሣ ክፉው መንፈስ እንክርዳዱን የሚዘራበት የጸብ አዝመራ አያገኝም፡፡
ይሄ ሥጋ፥ የሁላችን ሥጋ ይሆን ዘንድ፤ መድኃኒቱ ሥጋውን የሚበላ ደሙን የሚጠጣ አድርጎ በስሙ ለምናምነው ሁላችን ሰጥቶናል፡፡ ብቻም ሳይሆን፥ በእኛና በእርሱ መካከል ያለውን የዓመፃ ግድግዳ በመስቀል ላይ አፍርሶታል፡፡ በዚህም አማናዊ ኪዳን በኩል፥ ዐማኑኤል፥ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ሆነ የሚለው ቃልኪዳን በሥጋው መቆረስ በደሙ መፍሰስ ቤዛነት ታትሞልናል፡፡
ስለዚህ የክርስቶስን (የዳግማዊውን አዳም) ንጹሕ ሥጋና ቅዱስ ደም መውሰድ ስንጀምር፥ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እየሆንን እንመጣለን፡፡ ከእርሱ ጋር አንድ ስንሆን ከራሳችንም ጋር [እንደ ቀደማዊው አዳም] አንድ እንሆናለን፡፡ ከራሳችን ጋር አንድ ከሆንን፥ መጽሐፍ እንዳለ የሚቃወመን ኃይል (ዲያቢሎስ) ተቃውሞው አይሳካለትም፡፡ ጥቅሱን ላንብበው ፦
"እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?"
(ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥31)
በእርግጥም እግዚአብሔር ካለ የሚቃወመን "የለም"፡፡ የለም ማለት ተቃዋሚው ወገን የለም ማለት ሳይሆን፤ ከእግዚአብሔር ጋር እስከሆንን ድረስ ተቃውሞ በራሱ ተቃውሞ ሆኖ ሊያሸንፈን አይቻለውም፡፡ በሌላ አባባል፥ ችግሩ አለ ነገር ግን አንቸገርም፤ እሳቱ ይነዳል ነገር ግን አንቃጠልም፤ በረዶ ውስጥ ነን ሆኖሞ ግን አንቀዘቅዝም፤ ወደታች እየጣሉን ነው ሆኖም ግን አንወድቅም፡፡ ስለዚህ ትክክል ነው ጥያቄው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ 'ማን' ይቃወመናል?
ወደ ርእሳችን ጽንሰ አሳብ ጥቅሱን ስናስገባው፤ ክርስቶስ በኛ ካለ፥ እርስ በእርስ የሚቀዋወሙ ውስጣዊ ባሕሪያት አይኖሩብንም፡፡ ምክንያቱም እርሱ "መልካሙ እረኛ" ነው፡፡ ሁሉን የፈጠረና ያለ እርሱም አንዳች የማይሆን የሌለ ነው፡፡ ስለዚህ .. በጎቹ በተኩላው እንዳይበሉ ይጠብቃል፤ አእዋፋቱ በነጻነት እንዲበሩ ይፈቅዳል፤ ውኃው እሳቱን እንዳያጠፋ ያስማማል፤ ነፋሱ አፈሩን እንዳይገለብጠው ያደርጋል፣ .. /የተፈጥሮና የፍጥረታት ባሕሪያት በኛ እንደተጻፉ ያስታውሷል/፡፡
እያልኩ ያለሁት፤ የክርስቶስ ሥጋና ደም ከእኛ ሥጋና ደም ጋር ሲዋሐድ፤ የውስጥ ጉስቁልና ውጤት ሆነው የመጡት የቀውስ ባሕሪያት፥ በሰላም አለቃው ድምፅ መሰማት ይሰክናሉ፡፡ በመሆኑ ጭንቀት፥ ጭንቀት ሆኖ አይቃወመንም፡፡ ፍርሃት፥ ፍርሃት ሆኖ አይረብሸንም፡፡ አሳቦቻችን እርስ በእርስ እየተጋጩ አያናውጡንም፡፡ ፍላጎቶቻችን እየተጣሉ ግራ አያጋቡንም፡፡ ጠባያቶቻችን እየተለዋወጡ አያዘባርቁንም፡፡ ፈቃዶቻችን እየተቃረኑ አያምታቱንም፡፡ ምክንያቱም በተወዳጁ ጌታ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡
ታዲያ ልብ እንበል! "ማነው የሚቃወመን?" ብለን በጠላታችን ፊት በእምነት ድፍረት ከመቆማችን በፊት፤ "እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ" የሚለው ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ትኩረት መስጠት እንደሚገባን ልብ እንበል፡፡ ሐዋሪያውም መልእክቱ ሲጽፍ ያስቀደመው "እግዚአብሔር ከኛ ቢሆን" የሚለውን ንባብ ነው፡፡
"እሺ እንዴት ነው እግዚአብሔር ከኛ ጋር የሚሆነው?" የሚለውን አስፈላጊ ጥያቄ ስናነሳ፤ ዮሐንስ መልስ አለኝ ይለናል፡፡ እንስማው ፦
"ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።"
(የዮሐንስ ወንጌል 6፥56)
ይሄ ነገር ድንቅ ነው! ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበል ምእመናን አለ ጌታ፥ "እርሱ በእኔ ይኖራል፥ እኔም ደግሞ በእርሱ እኖራለሁ" አለ፡፡ እውነትም ኢየሱስ ክርስቶስ ዐማኑኤል ነው፡፡ እኛ በእርሱ፥ እርሱም በእኛ እንዲኖር በማድረግ፤ ከእግዚአብሔርነቱ ጋር አንድ የሚያደርገን ዐማኑኤል!
ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ማለት ቅዱስ ክርስቶስን መቀበል ማለት ነው፡፡ "አምላክ ሰው ሆነ፥ ሰውም አምላክ ሆነ" የሚለውን ከቤተልሔም (ልደት) እስከ ቢታንያ (ዕርገት) ያለውን የሕይወት መንገድ (እውነት) የሰማን ሰዎች የምናምነው እንደዚህ ነው፡፡ በተዋሕዶ ዓለት ላይ ቆመን ነገሮቻችንን ሁሉ መልክና ቅርጽ የሰጠናቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዋሐድ ዘንድ ነው፡፡ ከአምላክ ጋር ተዋሕደን ደግሞ በዚህ ዓለም የምንመላለሰው ስሙን ብቻ በመጥራት ሳይሆን፤ በሚስጥረ መለኮት የሰጠን እርሱነቱን በሰውነታችን ውስጥ በማኖር ጭምር ነው፡፡
የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች፤ ከቅዱስ ቁርባን በተለያየ ሰበብ ርቀን እኛ በእርሱ፥ እርሱ በእኛ የምንኖርበት አንድነት ሲጠፋ፤ ወደ ነውጥና ወደ አለመረጋጋት ሄደን፥ እነርሱም እኛን ፈልገው ወደኛ መጡና ከችግሮች ጋር አንድ ሆነን ቁጭ አልን፡፡ ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበል ክርስቶስን የተዋሐደ ኑሮ ስሌለን፤ በአንጻሩ መከራዎችን ወደ ጊዜያችን ለማምጣት ያለ ዕረፍት የሚተጋው ክፉ መንፈስ በኛ ተዋሕዶ፥ እኛም የእርሱ ፈቃድና ዓለማ ተዋሕደን፤ ይኸውና መኖር በራሱ የሚቃወመን ፍጥረቶች ሆነን አለን፡፡
እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስላልሆን፤ የሮሜው መልእክት በጀርባው ተጽፎ ሲነበብብን፤ በባሕሪያቸው የመቃወም ባሕሪይ የሌላቸው ወይንም እንዲቃወሙን የማንፈልጋቸው ነገራት እንኳ ይቃወሙናል፡፡ አሉ እኮ ስኬት የሚቃወማቸው፣ ደስታ የሚያጠፋቸው፣ ሰላም የሚረብሻቸው፣ ዕረፍት የሚበጠብጣቸው፣ ሐብት እንቅልፍ የሚነሳቸው፣ እውነት የሚያስጨንቃቸው ሰዎች፡፡ አየህ.. አምላክ ከኛ ካልሆነ የማይቃወመን ደግሞ የለም፡፡
BY በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
Share with your friend now:
tgoop.com/bemaledanek/2401