tgoop.com/bemaledanek/2427
Last Update:
የዛሬው የዘመን ትውልዶች የ60'ዎቹ ትውልዶች ልጆች ነን፡፡ በግልጽ ቋንቋ አምላክ የለም ሲሉ አዲስ ርዕዮት ያመጡት ሰዎች አባቶቻችን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የለም የተባለበት ጊዜ ፍሬዎች ነን፡፡ ነን አይደለንም?
አባቶች በእውነተኛ ሰማያዊ ሞገስና ጸጋ ያቆዩትን ቃልኪዳን፤ በፍጹም መሥዋዕትነትና ተጋድሎ ያስረከቡትን የእምነት ስጦታ፤ አክብረውና ጠብቀው ያቆዩት የተስፋና የመገለጥ በረከት፤ ሐሰትን በአንድ ኅብረት ተቃውመውና አውግዘው መልካሙን ያቆዩበት የእውነት ክብር፤ አንዱ ለአንዱ ድክመቱ በታየበት ቦታ ላይ ለድጋፍና ለመተባበር የተከፈተው ስብዕና፤ አንደበታቸውንና ምግባራቸውን ከመንፈሳዊ ጉድለትና ሙላት አንጻር እየመዘኑ የእግዚአብሔርን የረድኤት እጆች የያዙበትን ዘመን፤ ባለጊዜዎች ተነሡና "ይውደም" አሉት፡፡
ከዚህ የይውደም የፍልስፍናው አምባ የተነሣው አፍራሽነታችን፥ አጥፊነቱን በቀጥታ ለቀጣዩ ትውልድ በሚያስተላልፍበት ጊዜ፥ ይውደም ያልንበት የቃል እርግማን በእያንዳንዳችን ልብና ቤት ውስጥ ዘልቆ ሲገባ፤ በመጀመሪያው ውድመት አንድ ሲል ውስጣችንን ከእግዚአብሔር እውነት ለይቶ አወደመው፡፡ ውስጣችን በሚወድምበት ጊዜ፤ የትናንት ማንነቶቻችን ተስማምተውን መቆየት አቃታቸውና ወዳስጠጓቸው ልቦች ሄደው ተሸሸጉ፡፡
ከኮሚኒስቱ ዘመን ርዕዮት ወዲህ በመጣንባቸው የሕይወት ምዕራፎች ውስጥ፤ ያዋጡናል ብለን የተከተልናቸው ሀገራዊ አስተሳሰቦች፣ ትክክል ናቸው ብለን የተቀበልናቸው የሕብረተሰብ ፖሊሲዎች፣ ይሻሉናል ብለን የሰበሰብናቸው የፍልስፍና ዕውቀቶች፤ የአባቶችን የእምነት ፍቅርና ኃይል እንደ ባሕላዊ ጎታች ሥርዓት ተመልክቶ ከመናቁም በተጨማሪ፤ የራሱን የታሪክ ዘውግና እውነት በእንግዳ አመለካከት በማጉደፍ በዓለም ፊት ማንነቱን ያዋረደ፣ ነገሥታትን ያንቋሸሸ፣ ጳጳሳትን ያሳደደ፣ ሃይማኖታዊ አሻራዎችን ያወደመ፤ አረማዊ ጠባይ በሀገር አቀፍ ሰፊ ሽፋን የተንጸባረቀበት ጊዜ ነበረ፡፡
"ሥርዓቱንም ከአባቶቻቸውም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን፥ ያጸናላቸውንም ምስክሩን ናቁ፤ ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፥ ምናምንቴዎችም ሆኑ፥ እግዚአብሔርም እንደ እነርሱ እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብን ተከተሉ።"
(መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 17፥15)
በዘመኑ ከነበረው የፖለቲካ ቅዠት-ወለድ ሀሳብ ጋር ተጣምረው፤ ጊዜን ከትውልድ ፍጥነትና ለውጥ ጋር ለማስኬድ ያደረግናቸው ጥረቶች የእግዚአብሔርን መሪነት አፍርሰንና እንዲሁም ክደን ስለተጓዝንባቸው፤ ስመ መለኮት በሌለበት ቦታ ላይ የጀመረነው ባልተጨበጠ የመመሪያ አጀንዳ የናወዘ ግስጋሴ የታሪክ ከፍታዎችን እንዳልነበሩ ያህል ደምስሶ ለመጣል ቀላል ሆኖለታል፡፡ ቀደምቶቻችን ደምና ዋጋ ከፍለው ባቆዩት መንፈሳዊ ቀለም ላይ የፍልስፍና እርሾ ቀይጠን ስንደባልቅ፤ በግማሽ ሕሊናችን አማኞች በቀረው ግማሽ ሕሊናችን አፈንጋጮች በመሆን፤ በቀደመው የእምነት ትውልድ ተሸንፎ የነበረው የዲያብሎስ ሠራዊት በኛ ዘመን ላይ ለጥፋት ቁጥጥር እንዲያንሰራራ ምቹ አጋጣሚ ስላገኘ፤ ቀጥሎ የተተካውን ባለተራ ትውልድ በጥቁር ሥልጣን ጨፍልቆ በመግዛት፤ በአስተሳሰብ ጨለምተኝነት ሃይማኖታዊ እውነታዎችን የሚንቅ፣ ባሕላዊ ሥነ ምግባራትን የሚጠየፍ፣ ማኅበረሰባዊ ዕሴቶችን የሚያሸማቅቅ፣ የእምነት ታሪኮቹንና የአባቶቹን የተጋድሎ መሥዋዕትነት የሚያጥላላ፣ በዘርና በጎሳ ልዩነት የሚነቃቀፍ፣ ሥጋዊ እሳቦቶችንና መሻቶቹን የሕይወቱ ብቸኛ እቅድ የሚያደርግ፣ አርቆ የማስተዋልን የሥነ ልቦና አቅም የተነጠቀና በተለያዩ ዘመን አመጣሽ የለውጥ እስራቶች የተጠፈነገ፥ የርኩሰት ዳፍንት እንደ ወረርሺን ያጠቃው ትውልድ ተከተለ፡፡
አሁን ያለውን ትውልድ ያስገኘው ትውልድ፤ በየግል በየግል ስናየው፥ ከሞላ ጎደል በንጽጽሮሽ መልኩ የተሻለ እርሱን ባስገኙት ቤተሰቦች ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ አጥር የተከለለ ስለነበረ፤ ከማኅበረሰቡ ባሕል ሲወጣ ቢንገዳገድም፤ አኗኗሩን ርኩሳን መናፍስት ቢያበላሹትም፤ ፈሪሐ አምላክ ያላቸው ስለነበሩ ቢያንስ በሀገራዊ ደረጃ የትውልድ መጥመምን አላስተናገዱም፡፡ ግን ታዲያ ትዳር መሥርተው አብዛኛዎቹ ልጅ ሲወልዱ እንደዛው በተንገዳገዱበት የሕይወት ልክ ሆነውና የሰማይ አምላክን ጸጋ አርቀው በአንጻሩ የዘመንን ምርቃና ይዘው ከነበረ፥ የተወለደውም ከልጅነቱ በአመልና በሱስ ግንፍልተኝነት የመረቀነ፤ የአስተዳደግ ሕጉም የተንገዳገደ እንዲሆን ይገደዳል፡፡ የዛሬ የወጣቱ ትውልድ ወላጆች በወጣትነት ዘመናቸው ቃማዊች የነበሩ፣ ጠጪዎች የነበሩ፣ የፖለቲካ ግፈኞች የነበሩ፣ በዝሙት የወደቁ፣ የጣዖትና የባዕድ አምልኮት ግብር የሚገብሩ "የነበሩ" ሲሆን፤ ንስሐ ሳይገቡና ቅዱስ ቁርባን ሳይቀበሉ ከፊሉ ልባቸው መለስ ባለጊዜም ይሁን እዛው ውስጥ በቆዩበት ጊዜ የሚወልዱት ልጅ፥ የእነርሱን "የነበሩ" ታሪክ ገጽታውን አዘምኖ እንዲቀጥል፤ ገና ከማለዳው በመናፍስቱ የውርስ ኃይል ተይዞ መኖር መጀመር ዕድሉ ሆኖ፥ ከቅድስና የሚዋልል ቢሆን በእውነት የሚጠብቅ ነው፡፡
አዎ.. ኃጢአት በንስሐ ባልተሠረየበትና ከጌታ ጋር መኖር እንድንችል ቅዱስ ቁርባን ባልተወሰደበት ሁኔታ የተወለድን ትውልዶች ነንና እኛም ዘራችንን ዘሩ ካደረገው ከአባታችን ከዲያቢሎስ ስለመሆናችን ሕይወታችን ማረጋገጫ የማያስፈለገው መታያ ይሆናል፡፡ በሥጋ የአኗኗር ውጥረት መካከል በጠበበ የማስተዋል መስመር ላይ ወድቀን፤ የቅርብ ቅርቡን ብቻ እያየን ጊዜያችንን በትምህርትና በሥራ ብቻ አጥረን ይዘነው፤ ውስጣችን መቼ እንደታመመ እንኳ መረጃውን አጥተን ቀስ በቀስ በመጀመሪያ ከውስጥ ቀጥሎም በውጪ ገጽታችን እየተበላን መጣን፡፡ እየተበላን መጣንና ወደ ኋላችን ዞረን የመጣንበትን አቅጣጫ ቆመን የምናስተውልበትን አእምሮና ጊዜ አጥተን፤ ከባሰ ወደ ባሰ፣ ከጨነቀ ወደ ጨነቀ፣ ግራ ከተጋባ ወደ ተስፋ የቆረጠ የሕይወት እርከን እየተሸጋገርን ዕለቶቻችን ለማሳለፍ ብቻ የምንኖር ሆንን፡፡
እንግዲህ ስንወለድ ጀምሮ በመናፍስት ተጋቦት ውስጥ ሆነን ከነፍስና ከሥጋችን ተጨማሪ አጥፊ ኃይልን ከማኅፀን ወርሰን ስለተወለድን፤ እግዚአብሔር የፈጠረልን ንጹሕ ሕሊናና ልቦና ላይ አብሮ የተወለደው ክፉ መንፈስ የአሉታዊ ሀሳቦችና ምሪቶች ምንጭ ሆኖ፤ በሥጋዊ ዕውቀት ብቻ የምንሄድበት የኑሮአችን ጓዳና ተስማሚ ምሽግ ሠርቶለት ብዙ ጥፋትና ኪሣራ እያደረሰ፤ የዘመን ክፉ እንዲፈጥን የጋራ እርግማንን ለሕይወታችን አሰልጥኖ የመቅሠፍት ትውልዶች አድርጎናል፡፡ በእርግጥ ክፉ መናፍስት በዘራችን ውስጥ እየተዳበሉ አብረው በመወለድ ያጠፉን ነበር፥ ግና ክርስቶስ ልጆቹ እንድንሆን በመሥዋዕትነት ኪዳን ቃልኪዳን ሰጥቶ ከጥፋት ታደገን፥ ዳሩ ግን በጥፋት ዘመን ላይ የደረስነው የአሁን ጊዜ ትውልዶች ከተሰጠን ኪዳን አፈንግጠን ስንወጣ መናፍስቱ እንደገና በቤተሰባችን ሐረግ ውስጥ ዘልቀው ገቡ፤ እነሆም መናፍስት አብረው እንደሚወለዱ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ስንሰማ ግርምት ሆኖብን እናደንቃለን፡፡ ቃሉ ምን አለ? "..አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ።"
ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባዖት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
BY በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
Share with your friend now:
tgoop.com/bemaledanek/2427