tgoop.com/bemaledanek/2758
Last Update:
"እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ" የሚለው ቃልም እንደሚነግረን፤ በጨለማው ዓለም ላይ ብርሃን በተገለጠ ጊዜ አብረው በቅድስና የተገለጡት መላእክት መልካም(ታማኝ፣ ታዣዥ፣ ንጹሕና ጽኑ) እንደሆኑ እግዚአብሔር አየ፡፡ ስለዚህም ለእነርሱ የመንፈሱን ኃይልና ግርማ አካፍሎ አገልጋዩ ሲያደርጋቸው፤ በጨለማው ጊዜ የካዱት መላእክት ከዚህ ሹመት የተለዩ ሆኑ፡፡ ይህንንም መለየት መጽሐፍ "ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም" በማለት ይገልጸዋል፡፡ (የዮሐንስ ራእይ 12፥8)
መላእክትን እንዲመራ አክብሮ የፈጠረው ሳጥናኤል በክፉነት ፍላጎቱን ገልጾ ርኩስ በመሆን ከሰማይ ቅድስና ሲለይ፤ ከድቶ ባፈነገጠው ነገድ ፋንታ፤ ፍጥረታትን የሚያስተዳድር፣ እንደ ተቀደሱት መላእክት በብርሃን ጸጋ የሚመላለስ፣ በክብርም ከፍ ያለ ፍጡር መቶኛው ሙሉ ነገድ ይሆን ዘንድ "እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር(በፍቅር) መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።" (ኦሪት ዘፍጥረት 1፥27)
"ከሰማይ(ከብርሃን) ስፍራ ያልተገኘለት" ጨለማው ዲያቢሎስ፤ እርሱ በተዋረደበት ቦታ ላይ እኛ ባለ ክብር ሆነን መፈጠራችን በእጅጉ ያስቀናዋል፡፡ ይባስ ብሎ በእግዚአብሔር ምሳሌ ተፈጥረን በብርሃን ጸጋ በመክበር አስተዳዳሪ መሆናችን ደግሞ ተመኝቶ ያጣውን ገዢነት በኛ ተፈጥሮ ላይ ስላየው መገመት በማንችለው የጥላቻ ጥግ አምርሮ እንዲጠላን አደረገው፡፡ (የተፈጠርንበት ቀን 6፥ ዲያቢሎስ ጥላቻን ያለማቋረጥ ወደኛ እንዲገልጽ የአሳቺነት መታወቂያን ያተመበት ቀን ነው)
በፍጥረት ወገኖቹ ከሆኑት መላእክት ጋር በመጀመሪያ ተዋግቶ የተሸነፈው ዲያቢሎስ፤ ከመላእክትም በላቀ ክብርና ግርማ የተፈጠረውን የሰው ልጅ በቀጥታ ተፋልሞ ሊጥለው እንደማይችል ከቀደመ ሽንፈቱ ተሞክሮ ወስዶአል፡፡ በአዳምና በሔዋን ላይ መልቶ የነበረውም የብርሃን ጸጋ ጨለማነቱን በመቃወም ማንነቱን እንደሚገልጥበት ያውቃል፡፡ ስለዚህ እውነተኛ መልኩን(ጥላቻውን) በሥጋ ደብቆ በእንስሳ አካል ተሰውሮ ወደ ሔዋን ሄደ፡፡ (ይሄ በሥጋ የመደበቅ ጉዳይ፥ ዘግይቶ ክፉው መንፈስ በኛ የሥጋ ባሕሪይ ላይ የርሱን መለያ እንዲያስቀመጥ ፈለግ የተወ ምሪት ሆኖአል፡፡ ጥላቻንም በባሕሪያችን የማፍለቅ ግፊት የመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ የመጀመሪያው ጥላቻን በሰው አካል የመግለጥ የመናፍስት ሴራ በቃየን ባሕሪይ ላይ ተጀመረ)
እዚህ ጋር ያለው እቅድ ተነድፎለት የታለመው የእባቡ ምኞት፤ አዳምና ሔዋን በራሳቸው ፈቃድ ወስነው ከራሳቸው ላይ ያለውን የብርሃን ጸጋ እንዲገፍፉት ነው፡፡ የተሰጣቸውን መልክ እንዳይኖሩት ሌላ በር መክፈት ነው፡፡ እንዲህ የሚሆነው ደግሞ ከእግዚአብሔር አምላካቸው ፈቃድ ሲለዩ እንደሆኑ ገልጽ ስለሆነ፤ ከሴቲቱ ጠጋ ብሎ "በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።" (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥1)
ዲያቢሎስ ወደ ሔዋን እንደደረሰ ተቀዳሚ ሥራው ያደረገው የእግዚአብሔር የሆነውን አሳብ ከውስጧ መለወጥ ነው፡፡ "በውኑ አትብሉ ብሎአልን?" ሲል በአንጻራዊ ጎን ያለውን፥ ትእዛዝ ተላልፎ የመብላትን አሳብ፥ እንደታውጠነጥን ዕድል አመቻቸላት፡፡ ሔዋንም የእግዚአብሔር መልክ ያላት የፍጥረታት ንግሥት ከመሆን ባለፈ፥ እግዚአብሔርነት አገኛለሁ በሚል ዲያቢሎሳዊ ቅዠት አትንኩ የተባለውን የዛፍ ፍሬ ከባልዋ ጋር ወስዳ በላች፡፡
በዚህ ጊዜ ከእነርሱ መልክ ውጪ ያለውን፥ የነፍስ ባሕሪይ የማታውቀውን፥ በልዑል አምላክ እቅድ ውስጥ ያልተቀመጠውን፥ "ክፋትን" የማገናዘቢያ ዓይኖቻቸው ሲከፈቱ፤ ከሰውነታቸው ላይ የብርሃናቸው ጸዳል ተገፍፎ "ዕራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ" (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥6)፡፡ (ባዕድ አምልኮት የሚባለው ገለጻ ይህንን ያመለክተናል፡፡ ነፍስ ባሕሪይዋ ከተሠራበት ውጪ ያለውን መልክ አታውቀውምና የጣዖታት አምላክነት ለርሷ ባዕድ ይሆናሉ)
ብርሃናዊነታቸው ከሥጋዊ አካላቸው ላይ የተነሣው አዳምና ሔዋን፤ የተፈጥሮአቸው ጸዳል ተሰብስቦ በለስ የቀጠፉበት የእጅ ጣታቸው ላይ የወቀሳ ማስታወሻ ሊሆን ጥፍር ሆኖ በቀለ፡፡ ነፍስም በሥጋ ላይ የነበራት ቁጥጥር ተነሥቶ ከአፈርማው ተክለ ቁመና በታች ተሸሸገች፡፡ የዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን ተስምቶአቸው የማይታወቅ አዲስ ሥጋዊ ስሜትን አስተናገዱ፡፡ ፈሩም፡፡ ስለዚህም ወደ ጫካው ዘልቀው ገቡና ከብርሃን እግዚአብሔር ፊት ተሸሸጉ፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥8)
እነሆም አዳም በባሕሪይው ከእንግዲህ ብርሃንን በመፍራትና ባለመፍራት መካከል የሚዋልል አዲስ ጠባይ ያለው ሰው ሆነ ማለት ነው፡፡ መልኩን በመግለጥና ባለመግለጥ ፈንታ የሚዋትት ሕይወትን ጀመረ ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ነፍሱ በሥጋው ላይ እንድትሰለጥን መንገዱን በእምነት ጎዳና አድርጎ ከከፈተላት፤ እስትንፋሲቱም ከእግዚአብሔር የተካፈለቺውን መለኮት በሥጋ ላይ በመግለጽ መንፈሳዊ ጠባያቶቿን ታስነብባለች፡፡ ሰው ፍቅርን ፍጹም አጽንቶ ሲመላለስበት፤ ከሞት ቅጣት ጋር ተያይዞ የመጣበትን የቀደመውን ፍርሃት አውጥቶ ይጥላል፡፡ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥18)
ቅዱሳን ሰማእታት ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ተገደው፤ እሳት ውስጥ የሚገቡት፣ በመጋዝ የሚሰነጠቁት፣ ወደ ገደል የሚወረወሩት፣ በፈላ ውኃ የሚቀቀሉት፣ በሰይፍ የሚታረዱት፣ በጦር የሚወጉት ለዚህ ነው፡፡ በጽድቅ አኗኗር ዘመናቸውን ሲያሳልፉት፤ የነፍስ ተፈጥሮአቸው እንደ ቀደመው የአዳም ገጽታ በሥጋ ላይ ብርሃን ሆኖ ስለሚሰለጥን፤ ከነፍስ ወደ ውጨኛው አካል የሚፈልቀው ፍቅር በዓለም ላይ ዲያቢሎስ የሚነዛውን ፍርሃት ሁሉ ገርስሶ ይጥልላቸዋል፡፡
ሰዎች እንግዲህ ፍቅርን በመኖርና ባለመኖር መካከል ዕለቶቻችን እየዋዠቁ የሚገኙት፤ ነፍስ ከአካሏ እግዚአብሔር ጋር በመሆን ባሕሪያቶቿን እንዳታንጸባርቅ ርኩሳን መናፍስት በብዙ መስመሮች አልፈው ወደ ኑሮአችን እየመጡ የጥላቻን ገጽታ እንድናውቀው በሥጋ ምሽግነት ስለሚዋጉን ነው፡፡
ሔዋን ስለ ዛፉ ፍሬ እያሰበች ያላትን መለኮታዊ መልክ እንዳታስተውል መንፈሱ የመጤ እውቀት ጥላ ሆኖ ከፊት ወደኋላ እንደሸፈናት፤ ሁላችን የአዳም ዘሮች ትክክለኛውን የፍቅር ትርጉም በዓለማዊ ፍልስፍናዎችና ትንተናዎች አዛብተን መልካችንን እንድናጣ፤ በየዘመኑ በሚነሡ ርዕዮቶች፣ አመለካከቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ ንድፈ ሐሳቦች፣ የኑሮ ዘይቤዎችና ሳይንሳዊ አስተንትኖቶች ጀርባ ዲያቢሎስ የራሱን ጽልመታዊ አካሄድ እያስገባ፤ ተፈጥሮአችንን እያበላሸው ይገኛል፡፡
"ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና" ካልን፤ እግዚአብሔር ደግሞ ፍጹም መልካምና ቅዱስ ነው፡፡ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥8) ስለዚህ ፍቅርን የምናውቀው ቅዱስ በሆነው መልካም ነገር ሁሉ ውስጥ ነው ማለት ይሆናል፡፡
ከጥንት የሰዎች መነሻ ታሪክ አንስቶ እስከ ዛሬው ዘመናችን ድረስ ክፉ መናፍስት የተቀደሰውን መልካም ነገር ባላንጣ ሆነው የሚዋጉት ፍቅርን እንዳንኖረው ነው፡፡ እግዚአብሔርን የማያውቅ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ ትውልድ፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ ሕይወት፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ አሳብ፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ እውቀት፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ ጥበብ፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ ንብረት፣ እግዚአብሔርን የማያውቅ ሥልጣን በምድራችን ላይ እንዲንሰራፋ ሰፊውን ድርሾ ወስዶ ሚናውን በሚገባ የተጫወተው የዲያብሎስ ሠራዊት፤ የአዳም ልጆች መልካቸውን ማስታወስ አቅቶአቸው፤ የዘመኑን ሥጋዊ መልክ መስለው እንዲኖሩ የፍቅርን
BY በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
Share with your friend now:
tgoop.com/bemaledanek/2758