Telegram Web
✞ ቅዱስ ቁርባን - የሕይወት እንጀራ ✞

(እነሆ የዘመቻችን የመጨረሻ ምዕራፍ)

እውቀት ንጋት ናት ጨለማን ታበራለች! ስለዚህ .. ጊዜ ወስዳችሁ አንብቡ!
3•  ቅዱስ ቁርባን

     3.1•  ቅዱስ ቁርባን ምንድነው ?

ክፍል - ፩

          ✞ በልተን እንደወጣን በልተን እንመለሳለን

   "ለአዳም ሦስት ዕፅዋት ተሰጥተውት ነበር፤ አንዱን ሊጠብቀው፣ አንዱን ሊመገበው፣ አንዱን ሺሕ ዓመት ኖሮ ሊታደስበት፣ አትብላ ያለውን ዕፀ በለስ በበላ ጊዜ የሚታደስበት ዕፅ ተነሥቶታል፡፡ በሚታደስበት ዕፅ ሕይወትም ፈንታ ዛሬ ሥጋውና ደሙ ገብቶልናል፤ ሥጋውን ደሙን ተቀብለን፤ በልጅነት ታድሰን መንግሥተ ሰማያት የምንገባ ሆነናል፡፡"

                             (ኦሪት ዘልደት አንድምታ)


በአባት ዘንድ ታስበን ተፈጥረናል፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም በእግዚአብሔር ልቦና ተጸንሶ፤ ሰው የተባለ ፍጥረት ሊሆን ሲወለድ፤ የባሕሪይ ዕድገቱን እንዲጨርስ ዔድን ገነት በተባለች ቦታ ገብቶአል፡፡ ማለት አዳም የተባለ እግዚአብሔር በፈቃዱ ጸንሶ ያስገኘው ልጅ፤ ገነት በተባለች ማኅፀን ውስጥ በባሕሪይ ያድግ ነበር፡፡

አዳም አካሉና ባሕሪዩ ከተፈጠረባት ጊዜ አንስቶ፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ወዳዘጋጀለት ከፍታ በባሕሪዩ ያድግ ነበር፡፡ ይሄ የዕድገት ቆይታ ደግሞ በገነት ሥርዓት አንድ ቀን ያህል ይፈጃል፡፡ በምድር (ከፀሐይ በታች ባለ ሥርዓት) ሲሆን አንድ ሺሕ ያህል ዓመት ይሆናል (2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፥8)፡፡

አዳም በስድስተኛው ቀን አጋማሽ (አርብ 6:00) ላይ ተጸንሶ በመቀጠል ወደሚያድግበት ቦታ ወደ ገነት ገብቶአል፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 2፥8) በገነትም አንዱን ቀን (ሺሕውን ዓመት) ቆይቶ ሲጨርስ ከዕፀ ሕይወት ዛፍ ይበላና ይታደሳል፡፡ በሌላ አነጋገር ሰባተኛው ቀን (ቅዳሜ) ሲገባ፤ አዳም ዕድገቱን ጨርሶ ሕያው በመሆን በእውቀትና በጥበብ ይወለዳል፡፡ ወደ ፍጹም የባሕሪይ ልዕልና ይደርሳል፤ ይረቃል፤ ወደ ቀጣዩ ቀን ሥርዓት ይሄዳል፡፡

እግዚአብሔር እንደዚህ አስቦ፥ አዳምም በታሰበለት ውስጥ እየሄደ ሳለ፤ የገነቱን ሥርዓት የሚረብሽ አንድ ድምፅ ወደ ሔዋን መጣ፡፡ መጥቶም የባሕሪይ ዕድገታችሁን ሳትጨርሱ እንዳትነኩት የተባሉትን የዛፍ ፍሬ ያለ ቀኑ እንዲነኩት አግባባቸው፡፡ በሴቲቱ አሳቦች መካከል አማራጭ የሚሆንን "ባዕድ አሳብ" ዲያቢሎስ አጫወተ፡፡ ተቀበለቺው፤ በላች፤ ለአዳምም ሰጠቺውና በላ፡፡ ከበሉም በኋላ፤ ከአትብሉ ሕግ የወጣው የሰው ልጅ ባሕሪይ ከአምላኩ ፈቃድ ተለይቶ መጓዝ በመጀመሩ፤ አዳምና ሔዋን ከዚህ በፊት ተስምቶአቸው የማይታወቅ ሌላ ስሜት ተሰማቸው፡፡ ፍርሃት፣ ባዶነትና ጭንቀት ውስጣቸውን አገኘው፡፡ የጸጋ ብርሃናቸውን አጡ፡፡

በመለኮት ቤት ውስጥ ብርሃን ብቻ ነው ያለው፡፡ ጨለማ የለም፡፡ ስለዚህ ከብርሃን ኃይል ጠፍተው የጨለሙት እነ አዳም ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት አልቻሉም፤ እርሱ ወዳለበት መሄድ አቃታቸው፡፡ ከላይ በተነሣንበት አንቀጽ ስናወራ፤ የሰው ልጅ ባሕሪይ አምላክ አስቦ ወዳዘጋጀለት ከፍታ ማደግ መቀጠል አልቻለም፡፡ እንኪያስ እኛ ወደርሱ "አሳብ" (አባት) መሄድ እንዳቃተን ሲያይ፤ እርሱ ወደኛ "በቃሉ" (በልጁ) መጣ፡፡ አዳምና ሔዋን ጠፍተው ወዳሉበት ቦታ ሰኮና ብእሲ (የሰው ኮቴ) እያሰማ መጣና "አዳምን ጠርቶ። ወዴት ነህ? አለው፡፡" (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥9)

ተርጓሚዎች የእግዚአብሔር ቃል (ወልድ) "ወዴት ነህ?" ሲል መናገሩ አዳም ያለበት ጠፍቶት አልነበረም፤ "በኋላ ዘመን ሥጋን ተዋሕጄ አድንሃለው" ሲለው ነው ይላሉ፡፡ ይሄ ማለት "ወዴት ነህ" የምትለዋ የፍለጋ ጥሪ በአዳም ባሕሪይ ውስጥ የተጻፈች ረቂቅ ተስፋ ሆና ተቀምጣለች፡፡ በሆነ ጊዜ በሆነ ቦታ ላይ አዳም ከጠፋበት ስፍራ ላይ መጥቶ የሚያገኘው አንድ ኃይል እንዳለ እዛው በገነት ሳለ በውስጡ (በባሕሪዩ) አውቆታል፡፡

ባሕሪያችን ተስፋ እንደሰነቀ አልቀረም፡፡ ራሱን "የሰው ልጅ" እያለ የሚጠራ የእግዚአብሔር ልጅ "የጠፋውን ልፈልግ መጥቼያለሁ" ሲል በገነት የጠራን መለኮታዊ ቃል እርሱ እንደነበረ ተናገረ፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 18፥11) ወዴት ነህ ያለ ያ "ቃል ሥጋ ሆነና"፤ ሕልውናችን ጠፍቶ የነበረበትን ነጥብ አገኘው፡፡ ከአባቱ (ከአሳቡ) ተለይተን በመውጣታችን ምክንያት የመጡብንን ባዕድ ስሜቶች፣ ጠባያቶችና የክፉ መንፈስ እውቀቶች እያጠፋና የእርሱን እያስተማረ በመካከላችን ተመላለሰ፡፡ አገልግሎቱ ወደ ዋናው ክፍል ላይ የሚደርስበት ደረጃ ላይ ሲቃረብም በአይሁድ ምኩራብ ሳለ የሚከተለውን ተናገረ ፦

   "የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱ፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው

                        (የዮሐንስ ወንጌል 6፥44-51)

ሺሕውን ዓመት በመጨረስ ወደ ሰባተኛው ቀን በመግባት፤ በነፍስና በሥጋችን ላይ የምትሠርፅ የሕይወት ዕፅን በልተን ከገነት ማኅፀን መወለድ ሲገባን፤ ነገር ግን ያለ ቀኑና ያለ ሥርዓቱ ከእውቀት ዛፍ በልተን ያለ ጊዜያችን ተወለድን፡፡ በተለመደው የመጽሐፍ አገላለጽ ከገነት ተባረርን፡፡ በእናቱ ማኅፀን ያለ ጽንስ እውቀትን ከውጪ መቀበል ከጀመረ ተወልዷል ማለት ነው፡፡ ያለ ጊዜው የተወለደ ልጅ ደግሞ ይሞታልና፤ በአካል ወደ አፈር፥ በባሕሪይ ከእግዚአብሔር አሳብ ወደ መለየት፥ በነፍስ አድራሻው ወደማይታወቅ ጨለማ መውረድ ጀመርን፡፡ ይሄ ወደታች የመውረድ ጉዞ ጠቅለል ባለ ቃል "ሞት" ይባላል፡፡

በመብል የተነሣ ሞት የሚባለው ውድቀት ወደ ተፈጥሮአችን መጣ፡፡ ከወደቅንበት ለመነሣት ብዙ ብንጥርም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ አለመሞትን ብንፈልግም እንደምንፈልገው ግን አልሆነልንም፡፡ ውስጣችን ማደግ፣ መርቀቅና ከፍ ከፍ ማለትን ይመኛል፡፡ ሆኖም አካላችን ወደተፈጠረበት አፈር ይጓዛል፡፡ ከእርሱነቱ ተክፍላ በእኛ ውስጥ ያለች ነፍስ ወደ ፈጣሪ ፈቃድ መሄድን ትፈቅዳለች፤ ሥጋ ግን ወደ ራሱ ፈቃድ ያዘነብላል፡፡ በአጭሩ ከራሳችንም ከእግዚአብሔርም ተጣላን፡፡

ስለዚህ? እርቅ ያስፈልጋል፡፡ እርቁ እንዲኖር ደግሞ በመጀመሪያ ከጠፋንበት መገኘት ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ይፈልገን ዘንድ ተሰደን ወደሄድንበት ምድር ተከትሎን መጣ፡፡ ባገኘንም ጊዜ ከወገናችን እንደ አንዱ ሆነና በሥጋ ተዛመደን፡፡ ጉድለታችንን እየሞላ፣ ጥያቄያችንን እየመለሰ፣ መንገዳችንን እያቀና ውስጣችንን እየገነባ ቆየና፤ ወደኛ የመጣበትን ዋናውን ሥራ አከናወነልን፡፡ ከራቅነው እግዚአብሔር የምንቀርብበትን መንገድ ሰጠን፡፡ እንዴት?

ቁርባን በቁሙ የሱርስት (የሶርያ ቋንቋ) ቃል ነው፡፡ አምኃ ወይንም እጃ መንሻ ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ በግእዙ ትርጉም ደግሞ መቀራረቢያ፣ መገናኛ ማለት ነው ይሉታል፡፡ ሦስተኛ በሚስጢር ትርጓሜው መሥዋዕት ማለት ነው፡፡

የመድኃኒቱ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ቅዱስ ቁርባን በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡ በላይኛው አንቀጽ በቃል ፍቺው እንዳየነው ቁርባን የተለያዩ የስም ትርጉሞች አሉት፡፡ እነዚህ ትርጉሞች በየራሳቸው ከጌታችን ሥጋና ደም ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ እስቲ እንመልከታቸው፡፡
    "ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።"

                                      (2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፥19
)

አትብሉ የሚል ትእዛዝ ያሰመረው እግዚአብሔር፤ መስመሩ ተጥሶበታል፡፡ አዳም ሕግ በማፍረስ በደል ፈጽሞአል፡፡ ስለዛ ካሳ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ለንጉሥ እግዚአብሔር የሚሆን እጅ መንሻ መስጠት ይገባዋል፡፡ ሆኖም ይህንን አምኃ ችሎ ሊከፍል አልተቻለውም፡፡ ሞትን የሚክስ ሕይወት፣ ውድቀትን የሚሽር ትንሣኤ፣ የተዘጋውን ማኅተም የሚከፍት ቁልፍ ከፍጥረት ዘንድ አልተገኘም፡፡ ዮሐንስ ፦

     "በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። "ከሽማግሌዎቹም አንዱ። አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል አለኝ።"

                                             (የዮሐንስ ራእይ 5፥3-5)

አበው በሰባት ማኅተሞች የተዘጋው መጽሐፍ አንድም ሰው ((ሰ)ብእ-(ሰ)ባት) ነው ይላሉ፡፡ ከነዚህ ማኅተሞች አንዱ ሞት ነው፡፡ "አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ" የሚለውን ድምፅ ያደመጠ ባሕሪያችን ሞትን መሻገር ቢፈልግም አልሆነለትም፡፡ አለመሞት የሚባለውን ገጽ ሊዘረጋና ገልጦ ሊያነበው ማንም አልቻለም፡፡

ይህንን ያወቀቺው የባለ ራእዩ ነፍስ፤ ስለ ሁሉ የሰው ልጅ ሕይወት ተወክላ ስለተዘጉባት ማኅተሞችና ሊከፈቱም ስላለመቻላቸው አስባ አምርራ አለቀሰች፡፡ በዚህን ጊዜ አንድ የሚያጽናና ድምፅ "ከይሁዳ ወገን የሆነ አንበሳ እርሱም የዳዊት ልጅ" የተባለ ማኅተሞቹን ሊተረትራቸውና መጽሐፉን ሊገልጠው እንደቻለ ተናገረ፡፡ ይሄ ድል ነሺ መድኃኒቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!

ለእጅ መንሻ የሚቀርብ ንጹሕ በግ፣ እጅ መንሻውን የሚያቀርብ ሊቀ ካህን፣ እጅ መንሻውን የሚቀበል ንጉሥ ራሱ ሆኖ፤ መድኃኒቱ በመስቀል ላይ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ እንከፍለው ዘንድ የሚገባውን ዕዳ በእኛ ቦታ ሆኖ ከፈለልን፡፡ ሞት የማይገባውን ሥጋውን ለሞት አሳልፎ በመስጠት፣ መፍሰስ የሌለበት ቅዱስ ደሙን ስለ ኃጢአታችን ቤዛ በማፍሰስ፤ ለመተላለፋችን ካሳ የሚሆን ንጹሕ አምኃን ሰጠ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ሥጋና ደሙን ቅዱስ ቁርባን እየተባለ እንዲጠራ ያደረገው ቀዳሚ ምክንያት፡፡

ሌላውና ዋነኛው ደግሞ ቁርባን በግእዙ አቻ ፍቺ መቀራረቢያ፣ መገናኛ ማለት ነው ተባብለናል፡፡ ይህም ትርጉም እንዲሁ ለመድኃኒቱ ሥጋና ደም የሚስማማ ነው፡፡ በወደፊት ክፍሎች ላይ በሰፊው ስለምንመለስበት ለመግቢያ ያህል በሚሆን እናብራራው፡፡

ባሳለፍነው የንስሐ ምዕራፍ ላይ ከአምላክ ፈቃድ ከተለየን በኋላ ፊታችን ወደ ዓለም ጀርባችን ወደ እግዚአብሔር ዞሮ እንደምንኖር አይተናል፡፡ ይሄን በሌላ አገላለጽ ከእግዚአብሔር ርቀን ለዲያቢሎስ ቀርበን በምድር መመላለስ ጀመርን ልንለው እንችላለን፡፡

በዚህ አኗኗር ውስጥ ሳለን፤ ዘመን ምሕረትን ባመጣልን የመዳን ጊዜ ላይ "አማኑኤል" በተባለ ስሙ ከእኛ ጋር ሊሆን ያፈቀረ ክርስቶስ፤ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋና ደሙን ለእኛ በመስጠት ከእግዚአብሔር ለያይቶን የነበረውን የመራራቅ ግድግዳ አፍርሶ አንድነትን አምጥቶአል፡፡

    "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ (አንድነት!)።"

                                                 (የዮሐንስ ወንጌል 6፥56)


እግዚአብሔር በእኛ ከሚኖርበት እኛ ደግሞ በእግዚአብሔር ከምንኖርበት ክሂል ወጥተን ለዘላለሙ እንዳንጠፋ፤ መድኃኒቱ ሥጋውን መብል ደሙን መጠጥ በማድረግ ራሱን በውስጣችን እኛን ደግሞ በውስጡ በማኖር፤ ከራሱ ጋር አቀራረበን፣ አገናኘን፡፡ ይህን የእውነት መሠረት ስናውቅም፤ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ቁርባን መባሉ ትክክለኛ ሃይማኖታዊ አተረጓገም ስለመሆኑ ግንዛቤ እንወስዳለን፡፡

ሦስተኛ ቁርባን ማለት መሥዋዕት ማለት እንደሆነ አይተናል፡፡ በተስፋና በቃል ስለ እግዚአብሔር ልጅ መወለድ ሲናገር የቆየው ብሉዩ ዘመን፤ ቁርባንን በመሥዋዕትነቱ ሲገለገልበት ቆይቷል፡፡ በሐዲስ ኪዳኑ ጊዜ ላይ አማናዊ መሥዋዕት ሆኖ ስለሚቀርበው የክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ያደረጉ፤ በትንቢትነት የተገለጡ፤ የተለያዩ የእንስሳትና የዕፅዋት መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር ሲቀርቡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ፦

የልዑል እግዚአብሔር ካህንና የሳሌም ንጉሥ ያቀረበው የኅብስትና የወይን መሥዋዕት ለክርስቶስ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናትነትና ለሥጋው ወደሙ ዓይነተኛ ምሳሌ ሆኖ ይነገራል (ዘፍ 14፤18 ዕብ 5፣6 እና 10፣7፥17)። ሁለተኛ፤ ከቀሳፊ የሞት መልአክ አድኖ ከግብጽ ባርነት ነፃ ያወጣቸው የፋሲካ በግ ደም መረጨትና ሥጋውም ተጠብሶ መበላቱ የእግዚአብሔር በግ ለተባለው ለመድኃኒቱ አዳኝነትና ለምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ ሆኗል (ዘፀ 12፤1:51 1ኛ ቆሮ 4፣7)። ሦስተኛ፤ እሥራኤላውያን በምድረ በዳ ይመገቡት የነበረው ከሰማይ የወረደው መና ዛሬ ምእመናን ለነፍሳቸው ምግብ የሚቀበሉት የሥጋውና የደሙ ምሳሌ ነው (ዘፀ 16፣16፥23 ዮሐ 6፣49፥51)። አራተኛ፤ ጥበብ ያዘጋጀችው ማዕድ፣ ያረደችው ፍሪዳ፣ የጠመቀችው የወይን ጠጅ፣ የላከቻቸው አገልጋዮቿ የተጠሩት ሰዎች ሁሉ ምሳሌነት እንዳላቸው ይነገራል። ጥበብ የክርስቶስ፣ ማዕድ የሥጋው የደሙ፣ አገልጋዮች የካህናት፣ ተጋባዦች የምእመናን ምሳሌ ናቸው ተብሎ ይተረጎማል (ምሳ 9፤1፥5)። ይህን የመሳሰሉ ሌሎች ምሳሌዎችም አሉ (ዘሌዋ 2፤ 23፣13፥14 ሲራክ 24፣19፥21)።

ለአካሉ ጥላ ሆኖ የነበረው ዘመን ሲያበቃ፤ የብሉይ ዓመታትን መሥዋዕት የሚጠቀልል አንድ የመሥዋዕት ሥርዓት በመድኃኒቱ አማካኝነት ከስቅለት ቀን በፊት በነበረው የመጨረሻው እራት በሚሰኘው ዕለተ ሐሙስ ላይ ተመሠረተ፡፡

   "ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።"

                                               (የማቴዎስ ወንጌል 26፥28)

ከጠፋንበት ፈልጎ ያገኘን መድኃኒታችን ወደኛ ሥጋን ለብሶ የመጣበት ትልቁ፣ መሠረታዊና መጨረሻ ምክንያት ስለዚህ ኃጢአትን የሚያስተሠረይ ዘላለማዊ መሥዋዕት ሲል ነው፡፡ የአርብ ሥጋውን በሐሙስ ኅብስት፥ የአርብ ደሙን በሐሙስ ወይን አድርጎ ባርኮ እንበላው እንጠጣው ዘንድ ራሱን መሥዋዕት ያደረገ ቅዱስ በግ፤ ለበጎቹ ራሱን የሚመግብ ቅዱስ እረኛ!

እናስታውስ! ከእግዚአብሔር የተለየነው በመብል ምክንያት ነው ብለናል፡፡ እህሳ ወደ እግዚአብሔር የመመለሻው መንገድም የተዘረጋልን እንዲሁ በመብል በኩል ነው፡፡ በልተን ትተነው እንደወጣን፤ እንደገና በልተን ደግሞ ወደተውነው አምላክ እንመለሳለን፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን . . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
3•  ቅዱስ ቁርባን      3.1•  ቅዱስ ቁርባን ምንድነው ? ክፍል - ፩           ✞ በልተን እንደወጣን በልተን እንመለሳለን ✞    "ለአዳም ሦስት ዕፅዋት ተሰጥተውት ነበር፤ አንዱን ሊጠብቀው፣ አንዱን ሊመገበው፣ አንዱን ሺሕ ዓመት ኖሮ ሊታደስበት፣ አትብላ ያለውን ዕፀ በለስ በበላ ጊዜ የሚታደስበት ዕፅ ተነሥቶታል፡፡ በሚታደስበት ዕፅ ሕይወትም ፈንታ ዛሬ ሥጋውና ደሙ ገብቶልናል፤ ሥጋውን…
3•  ቅዱስ ቁርባን

ክፍል - ፪

      3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?

           3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል

               ✞ ፫ተኛው ቤተ መቅደስ (ትንሣኤ)

   "ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።"

                                            (የዮሐንስ ወንጌል 2፥21)

አዳም ባሕሪያችን የተሠራበት "የሰውነት" መዝገብ ነው፡፡ (፲፮፤ በደመወዝ ጎሽሜ) ወይም አዳም ማለት ሰብአዊ ማንነትን የሚወክል አንድ ታላቅ ወንዝ ነው እንበለው፡፡ ከዚህ ወንዝ ውስጥ ሁላችን የሰው ልጆች ተገኝተናል፡፡ ስለዚህ ስለ አዳም ባሕሪይ ስናወጋ ስለ አንድ ዘፍጥረት ላይ ታሪኩ ስለሚዘከርለት ሰው ብቻ ሳይሆን ስለራሳችን ባሕሪይም ጭምር ነው የምናወሳው ማለት ነው፡፡

ይሄ አዳም የተባለ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር ልዩ ፈቃድ ነው፡፡ በመውለድ አንቀጽ ስናወራ አዳም የተወለደው ከእግዚአብሔር የፈቃድ ማኅፀን ነው፡፡ ይሄ በእግዚአብሔር ታስቦ የተገኘ ፍጡር "ቤተ መቅደስ" ተብሎም ይጠራል፡፡ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፥16) እነሆ የአምላክ ቤተ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ተሠርቶ በሚፈጸምበት በገነት እየታነጸ ሳለ፤ ከወላጁ ከእግዚአብሔር የሚለየው የዲያቢሎስን ፈቃድ በመፍቀዱ ምክንያት ቤተ መቅደሱ ሳይጠናቀቅ (እግዚአብሔር ያሰበው ሳይሆን) ፈረሰ፡፡ "ከአፈር ተሠርተሃልና ወደ አፈር ተመለስ" የሚል የመፍረስን ትእዛዝ በባሕሪዩ አደመጠ፡፡

አዳም የሚባለው ሰው ሞትን አወቀ የሚለውን አነጋገር በቤተ መቅደስ በኩል ብንደግመው ፈረሰ የሚለው ቃል ነው የሚስማማው፡፡ መፍረስ የሚለውን ቃል በአቻ ፍቺዎች ሲበየን፤ መበታተን፣ መበስበስ፣ ወደ ታች መመለስ ልንለው እንችላለን፡፡ በጥንት የዕብራውያን የሃይማኖት ትምህርት አጥኚዎች ዘንድ "ሞት" የሚለውን ቃል ሲተነትኑ፤ በውኃና በአፈር ውህዶች መካከል የሚከሰት የመበስበስ ሂደት ሲሉ ይተረጉሙታል፡፡ (አባዶን፤ መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ)

የፈረሰው ቤተ መቅደስ የተገነባው በስድስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ እያንዳንዱ የዘፍጥረት ቀናት (ከእሁድ እስከ አርብ ያሉት) አዳምን ለማስገኘት የፍጡርን ባሕሪይ ያዋጡ ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰው ማለት የስድስቱ ቀን ፍጡራን ባሕሪያት መጥቅሊያና መካተቻ የሆነ ፍጡር ነው /ሰው የተፈጠረው በዕለተ አርብ ነው፤ አርብ ደግሞ ማለት ማካተቻ፤ መደምደሚያ ማለት ነው/፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረ በኋላ አርፏል፡፡ ወይንም ሌላ መፍጠሩን አቁሟል፡፡ በመሆኑ በዚህ መሠረት ከተናገርን፤ የሰው ልጅ የአምላክ ማረፊያ ቤተ መቅደስ ነው መባሉ ልክ ይሆናል፡፡

ሞት ወደ አዳም ባሕሪይ ከመጣ በኋላ ግን፤ በስድስቱ ቀናት "ድምርነት" የተሠራው ሰው ወደኋላ (ወደ መጀመሪያው) ቀን መልሶ ፈርሷል፡፡ "ወደ አፈር ተመለስ" የሚል ትእዛዝ የተሰጠው የሰው ልጅ፤ ከስድስተኛው ቀን (የአርብ) የፍጡር ሥርዓት "ሰውነት" እየፈረሰ ሄዶ ወደ አንደኛው ቀን (የእሁድ) የፍጡር ሥርዓት "አፈርነት" ይመለሳል፡፡ በአጭሩ፤ አዳም የተከለከለውን ካደረገ በኋላ፤ በውስጡ ተሰብስበው ሰው ያሰኙት የስድስቱ ቀን ፍጡራን ባሕሪያት ተጣሉበት፡፡ ፍጥረት ሁሉ በባሕሪይ አዳምን ለማስገኘት ወደፊት በሚቆጥሩ ቀናት እየተሰበሰቡ እንዲሄዱ ተሠርተው ሳለ፤ አዳም ግን ከዚህ ሕግ ተፋልሶ ወጥቶ የዛፉን ፍሬ ከበላ በኋላ "ወደ አፈር ተመለስ" ስለተባለ፤ ከፍጡራን ባሕሪይ በተቃራኒ እየተጓዘ ወደ አንደኛው ቀን በመመለስ፤ ከራሱም ከተፈጥሮም ጋር ጸብ ጀምሯል፡፡ /የዛፉን ፍሬ ከወሰድን በኋላ ከቀን ስድስት ወደ ቀን አንድ በባሕሪይ በመውደቅ መጥተናል እያልን ነው/ የሰው ልጅ ከገነቱ ስህተት አስከትሎ ጉስቅልና ያገኘው ለዚህ ነው፡፡ ማለት አዳም ከእግዚአብሔር ተለይቶ ሲወጣ፤ ውስጡ ካሉት የፍጥረታት ባሕሪይ ጋር ቀውስ ጀምሯልና፤ ይህ የውስጥ የባሕሪያት ተቃርኖ ወደ ውጪ ወጥቶ ሲገለጽ፤ ፀሐይ ታተኩሰው፣ ዝናብ ይቀጠቅጠው፣ እሳት ያቃጥለው፣ ውኃ ይጠማው፣ ርሃብ ይይዘው፣ በሽታ ያገኘው፣ ድካም ይሰማው፣ ጉንዳን ይቆነጥጠው፣ ጊንጥ ይነድፈው፣ አራዊት ያሳድዱት፣ ወዘተ... ጀመር፡፡

እግዚአብሔር አዳም የተባለን ቤተ መቅደስ ከፍጡራን ባሕሪያት ሰብስቦ በመጀመሪያ ሲሠራው እንዲፈርስ አስቦ አልነበረም፡፡ ይልቅ አስቀድሞ አስቦ ያዘጋጀለት (መልካም እንደሆነ ያየለት) የከፍታ ሥርዓት አለ፡፡ ይሄ መለኮታዊ አሳብ በራሱ "ሕያው" ከመሆኑ የተነሳ ከመፈጸም አይቀርምና፤ አሳቡ እንዲሳካ ከፈቃዱ ውጥቶ የፈረሰው አዳም እንደገና በፈቃዱ መሠራት አለበት፡፡ ደግሞም ቀድሞውኑም የሠራን እርሱ ስለሆነ፤ ከፈረስንበትም ቦታ ላይ አንስቶ እንደገና ሊገነባን የሚችለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ "እንደገና" የምንገነባ ከሆነ ደግሞ፤ "መጀመሪያ የተሠራንበት መንፈሳዊ አካሄድ መደገም" ይኖርበታል፡፡ ማለትም በኦሪት መግቢያ ላይ ተዘርዝረው ያሉት ስድስቱ ቀናት ዳግም ተሰብስበው የፈረሰውን ማንነታችንን መልሰው ሊገነቡት ይገባል፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ባሕሪያችንን አስቀድሞ ላየው ልዕልና ለማብቃት "እንደገና ስድስቱን ቀናት እየጠራ ይሠራን ጀመር"፡፡

እንደገና ይሠራናል ሲባል፤ አንድ መገንዘብ ያለብን ወሳኝ ጉዳይ አለ፡፡ መጀመሪያ ስንሠራ በስድስቱ የዘልደት ቀናት ስብስብነት እንደነበር ከላይ ጠቅሰናል፡፡ እነዚያ ቀናት ደግሞ በእግዚአብሔር ጊዜ የተሰሉ "ሰማያዊ ቀኖች" ናቸው፡፡ ከመነሻ እስከ መድረሻ የሚዘልቀው የፍጥረታት "ባሕሪይ" የተቀረጸባቸው ረቂቅ ሥርዓቶች ናቸው፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ እንደገና በነዚህ ስድስት ቀናት ውጤትነት የምንሠራበት ሂደት ከቀን አንድ /ከዛፉ በልተን ወደ ቀን አንድ እንደተመለስን ያስታውሷል/ ጀምሮ ሲደገም፤ ዳግም የመሥራት ሂደቱ ስፍራ እንደለወጠ ማስተዋል ይገባናል፡፡ ማለትም እኛ መጀመሪያ ከተሠራንበት የእግዚአብሔር ሥርዓት ተለይተን ወጥተን ወደ ምድር ወርደናል (ቦታ ቀየረናል)፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ የተሠራንባቸው እነዚያ ስድስቱ ሰማያዊ ቀናት ድጋሚ ይሠሩን ዘንድ ሲሰበሰቡ፤ አቆጣጠራቸው ተሰደን በመጣንበት በምድር ሥርዓት በኩል የሚሰላ ይሆናል (በቀየረነው ቦታ መሠረት ማለት ነው)፡፡ በደንብ ለማብራራት፤ በገነት ሳለን የጊዜ ልኬት የሚለካው በእግዚአብሔር በኩል ባለ ስሌት ነበር፡፡ ወደ ምድር ከመጣን በኋላ ግን ጊዜያት የሚሰፈሩት በመውጣት በመግባታቸው ምክንያት ዘመናትን እንዲያስታውቁን በተሰጡን የሦስተኛው ቀን ፍጥረታት (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት) በኩል ነው፡፡ በመሆኑም ተከትሎን ወደ ምድር የመጣው እግዚአብሔር ስድስቱን ቀናት እየሰበሰበ ዳግም ሲሠራን በሰውኛ አቆጣጠር እየለካ ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር (በገነት ሳለን) የነበረው አንድ ቀን፤ በእኛ (በምድር ሆነን) አንድ ሺሕ ያህል ዓመት ይሆናልና፤ ወደኋላ (ወደ አፈርነት) በመመለስ የፈረስንባቸው ስድስቱ ሰማያዊ ቀናት ወደፊት እንደገና እኛን ለመመለስ በምድር ሲሰበሰቡ ስድስት ሺሕ ያህል ዓመታት ይቆጥራሉ፡፡
አንጓ ክስተቶችን እየመዘዙ ከመተረክ አንጻር፤ ይሄ "ዳግም" የመገንባት ሥራው "አብራምን ለይቶ በመጥራት" ጀመረ እንበል፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 12፥1) እንደሚታወቀው አዳም የወደቀው በሴት ፈቃድ አማካኝነት ነው፡፡ ወይንም ወደ ምድር እንዲወርድ ምክንያት የሆነቺው ሔዋን ናት፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ዓለም በሴት በኩል እየተወለድን እንመጣለን፡፡ (ዝኒ ከማሁ) እንኪያስ ቤተ መቅደሱ እንደገና መገንባት አለበት ስንል፤ አያይዘን ለመፍረሱ ምክንያት የሆነቺው ሔዋንም "እንደገና" መቀረጽ ይገባታል እያልን ነው፡፡ ("እንደገና" እየሠራን ነው ካልን፤ የመጀመሪያው የተፈጠርንበት የሰማዩ ሥርዓት በምድር ራሱው እየተደገመ እንደሚሄድ ልብ እንበል!)

እናም ለመፍረስ የሆነቺው ምክንያት፥ ለመገንባትም ምክንያት ትሆን ዘንድ፤ ይህቺ [አዲሲቱ] ምክንያት በአብራም ባሕሪይ ውስጥ መሠራት ጀመረች፡፡ በገነቱ ሥርዓት አዳምን አስተኝቶ ሔዋንን ከጎኑ በወጣች አጥንት እንደሠራት፤ በመሬቱም ሥርዓት ሌላውን ሕዝብ አስተኝቶ አብራምን ለይቶ እንደ አጥንት በማውጣት ይሠራ ጀመረ፡፡ ማለትም ሴቲቱ (ሔዋን) በአብራም ተለይቶ የመውጣት አጥንትነት እንደገና መሠራት ጀመረች፡፡ በገነቱ የአፈጣጠር ሥርዓት ስናወራ፤ አብራም ማለት ከአዳም ጎን የወጣው ሔዋን የተሠራችበት አጥንት ነው ማለት ነው፡፡

የብሉይ ዘመን የምንላቸው ስድስት ሺሕው ዓመታት (ስድስቱ ቀናት) ወንዱን ልጅ (አዳምን) ዳግም ለመውለድ ያማጡ ዓመታት ናቸው፡፡ በአብርሃም ተለይቶ የመውጣት የቃልኪዳን ትውልድነት ስትገነባ የቆየቺው ሴቲቱም፤ በምጥ ዘመኑ መድረሻ ላይ በተጨባጭ ተገልጣ ትታያለች፤ ድንግል ማርያም ሆና!

ከአዳም አስጀምረን እያየን የመጣነውን እውነታ፤ በሉቃስ ጽሕፈት (የሉቃስ ወንጌል 1፥28-35) ላይ በተቀመጠው፤ በገብርኤል ሰላምታ ውስጥ በአንኳር አገላለጽ ተጠቅልሎ እናገኘዋለን፡፡ መልአኩ ንግግሩን ሲጀምር "ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ" አላት። ከተወዳጂቱ በፊት የነበሩት ዘመናት (ብሉይ ዓመታት) የአዳም ባሕሪይ ወድቆ ያለበት ጊዜ እንደመሆኑ መጠን ሐዘን በሰዎች ላይ ነግሧል፡፡ አሁን የፈረሰው ቤተ መቅደስ እንደገና ተሠርቶ የሚገለጽበት አዲስ ዘመን መጥቶአልና "ደስ ይበልሽ" ሲል አበሠራት፡፡ በተጨማሪ አዳም ከልዕልናው ተለየ፤ ወደቀ፤ ስንል ጸጋን ስለማጣቱም እያወራን ነውና፤ ይሄ የተገፈፈው ጸጋ ወደ ሰዎች ስለመመለሱ "ጸጋ የሞላብሽ ሆይ" በማለት አሳወቃት፡፡ ቀጠለና "ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ (የተለየሽ) ነሽ" አላት፡፡

ከአካሉ የተሠራች በመሆኗ ምክንያት አዳም ሲፈርስ አብራ የፈረሰቺው ሔዋንን፤ በአብርሃም ተለይቶ የመውጣት አጥንትነት እንደገና እርሷንም ሊሠራት ጀመረ አላልንም? .. ስለዚህ ይህቺ "ሴት" ሆና በመጨረሻ በሥጋ የምትገለጸዋ የወንዱ ልጅ አጥንት፤ በአብርሃም የቃልኪዳን ትውልድ (በወንዶቹ) ውስጥ ስትገነባ.. ስትገነባ ትቆይና ጊዜው ሲደርስ ሥጋ ለብሳ ስትገለጽ፤ ድንግል ማርያም ሆናለች፡፡

እመቤቲቱ በሥጋ ከመገለጧ በፊት በነ'አብርሃም ተለይቶ የመውጣት የትውልድ ቅብብሎሽ ስትሠራ ቆይታለች፡፡ ተለይተው ከወጡት አባቶቿ የተወለደቺው ብላቴናይቱ፤ ይሄ የመለየት ኃይል፤ ሥጋ ሆና ከገብርኤል ጋር በተነጋገረችበት ጊዜ ላይ እንዲህ ሲመሰከርላት እንሰማለን፤ "አንቺ ከሴቶች መካከል የተለየሽ ነሽ"!

የመዳን ምክንያት ትሆን ዘንድ ተለይታ የወጣቺው ዳግማዊቱ አጥንት ሥጋ (ሔዋን) በሆነች ጊዜ፤ የሰማዩ ሥርዓት በምድር እየተደገመ ነው ብለናልና፤ አዳም የገነቱን ድምፅ ዳግም ይናገረዋል፡፡ "ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት" ይላል፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 2፥23) በሐዲስ ኪዳንኛ አገላለጽ፤ አዳም ከሥጋዋ ሥጋ፥ ከነፍሷ ነፍሷ ሊነሣ ከሔዋኒቱ "በመዋሐድ" ይወለዳል፡፡ ዘመኑ በተስፋ ሲነገሩ የነበሩ እውነታዎች በሥጋ የሚገለጡበት የጸጋ ዘመን ነውና፤ ዳግማዊው አዳም ተጨባጭ ሆኖ በዚህ ዓለም ይገለጻል፡፡ ስሙም ኢየሱስ (መፍረሳችንን የሚፈውስልን መድኃኒት) ሲባል ይሰየማል፡፡

አሁን ወደኋላ የወደቀው ቤተ መቅደስ ወደቦታው ተመለሰ፡፡ የፈረሰው ባሕሪይ ዳግም ተገነባ፡፡ በእግዚአብሔር ታስቦ፥ በስድስት ቀኖች ተሠርቶ፥ ሆኖም ወደ አንደኛው ቀን በመመለስ አፈር የሚሆነው ስብእና፤ እስከ አሁን ባየነው አካሄድ መሠረት እንደገና ከቀን አንድ ወደ ቀን ስድስት (ከመጀመሪያው ወደ ስድስተኛው ሺሕ ዘመን) እየተሰበሰበ ተሠራ፡፡

በሰማይ የተሠራው አዳም ስለፈረሰ፤ በምድር ድጋሚ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሠራና ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ ባሕሪያችንን ተዋሕዶ ተወለደ፡፡ ባሕሪያችንን ሲዋሐደው፤ የኛ ባሕሪይ ሞትን አስቀድሞ ሰምቶት ነበር፡፡ እግዚአብሔር አንዴ የተናገረው ቃል እስከ ዓለም ምፅዓት ድረስ የሚቀጥል ነውና፤ "ሞትን ትሞታለህ" የሚለው ድምፅ እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ ለባሕሪያችን የሚደመጥ ይሆናል፡፡ በሌላ አባባል፤ ሞትን ከሰሙት አዳምና ሔዋን ሁላችን በሥጋ እንወለድ ዘንድ ግድ ነውና፤ ሞትን መሞታችን የማይቀር ነው፡፡

በሥጋ የተወለደው ዳግማዊው አዳምም፤ ንጹሕና ቅዱስ የሆነውን አካል ይዞ ቢመጣም፤ ለሞት የታዘዘ ባሕሪያችንን ስለተዋሐደ፤ በሥጋ ይሞት ዘንድ ግድ ይሆናል፡፡

ሆኖም ግን ሁለተኛው አዳም እንደ መጀመሪያው አዳም ያልሆነበት አንድ ሌላ ልዩ ነገር አለ፡፡ እርሱ ባሕሪይው የሰው ባሕሪይ ብቻ አልነበረም፤ ፍጹም አምላክ የሆነ የመለኮትም ባሕሪይ ነው፡፡ ተዋሕዶ በሚለው ዶግማ ውስጥ የምንናገረው እውነት ይህ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ልጅ (ወልድ) እስከሞት ድረስ የሚሄደውን ባሕሪያችንን ገንዘብ አድርጎ በሥጋው ወራት ሲመላለስ፤ ወደ አይሁድ ቤተ መቅደስ በሄደበት አንዱ ጊዜ ላይ የሚከተለውን ተናገረ ይላል ዮሐንስ ፦

   "ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።"

                                            (የዮሐንስ ወንጌል 2፥21)

መድኃኒቱ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ  "በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤" በዚህም ተቆጥቶ ጅራፍ አነሳ፡፡ ነጋዴዎቹንም ከመቅደሱ አባረረ፡፡ አይሁዳውያኑም "ይህን ለማድረግ አንተ ምን ሥልጣን አለህ?" ሲሉ ጠየቁት፡፡ ጌታም መለሰና "ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱ፤ በሦስተኛው ቀንም እገነባዋለሁ" አላቸው፡፡

በዚህ መልስ ጠያቂዎቹ ተገረሙ፤ እንደ ድፍረትም ሳይቆጥሩት አይቀርም፡፡ "46 ዓመታትን የፈጀ ሕንጻን በ3 ቀን ሠራዋለሁ ትላለህን?" ሲሉም ተናገሩት፡፡ የመድኃኒቱ መልስ በኋላ የገባው ሐዋሪያ ግን "አፍርሱት፤ እኔም አነሣዋለሁ" ስላለው ቤተ መቅደስ ምንነት ሲረዳ፤ ከኢየሱስ ምላሽ ለጥቆ "እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር" ብሎ በመጻፍ የተረዳውን ሚሥጢር አካፍሎናል፡፡

እንደተነጋገርነው አዳም የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ሰውነት ቤተ መቅደስነት ነው (ያልገባን ትልቅ ክብር!)፡፡ መድኃኒቱ አፍርሱት ሲል ለአይሁዶቹ የሚነግራቸው ስለ ሰውነቱ ነበር፡፡ በሌላ አባባል "የሚፈርስ ሥጋ (ሞትን የሰማ ባሕሪይ) ተዋሕጄያለሁና ጊዜው ሲደርስ ልትገድሉኝ አላችሁ" እያለ የሚመጣውን ተነብዮአል፡፡
ስለዚህ ዓለም በዚህ ዘመኗ አርጅታብናለች፡፡ ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም የሚለው የሕይወት ጽሑፍ በገሐድ እንደጋራ ይነበበን ጀምሯል፡፡ ሁሉ ነገር ጥለነው የምንሄደው ከንቱ ድካም እንደሆነ ሲገባን ተስፋ መቁረጥን በምድራችን ላይ አንግሠነዋል፡፡ እንኪያስ መልካም ብለን ስንከባከባቸው በቆዩ የሰውነት እሴቶች ላይ ማመፅ ጀምረናል፡፡ መኖርን አሁን በምናየው ልክ እየለካን አፍንጫችን ሥር ባሉ ጉዳዮች ጭልጥ ብለን መጥፋትን አማራጭ አድርገናል፡፡ ወዴት እንደምንሄድ፣ አድራሻችን የት እንደሚያደርስ፣ አቅጣጫችን ወደ ምን እንደሚመራ አናውቅም፤ የነፍስ ካርታ የለንም!

ሦስተኛውን ቤተ መቅደስ አላወቅነውም፤ ለማወቅም ፈቃድ ያለን አይመስልም፡፡ ከማመን አለማመን ተሽሎናል፡፡ ባሕሪያችን ወደ ዘላለም እረፍት ለመሄድ ይታገለናል፤ ግን መንገዱን ስለማናውቀው የምናደርገውን አጥተን፤ በሌላ በመሰለን መንገድ ስንባዝን ይኸው ዙሪያው ተዘግቶብን አለን፡፡ ወደ ዕፀ ሕይወት እንዳንደርስ የተጋረደው ኪሩብ፤ በሐዲስ ኪዳንም ዘመን ከፊታችን እስከ ሰይፉ ቆሞ የሚታየን ሰዎች ብዙ እንሆናለን፡፡

እስኪ ዝም ብለን እንጠይቅ፡፡ ምንድነው የመኖራችን ዋጋ? ምንድነው የሕይወት ትርጉም? የምንሠራውና የምናውቀው ሁሉ ከሞት ባሻገር ካልተከተለን እንግዲያው ልፋታችን የቱን ሚዛን ይደፋል? ፍጻሜያችን ምንድነው? .. እሺ የምንመኘው ሁሉ ሆነ፡፡ ገንዘቡ ገባ፤ ሒሳቡም ተከማቸ፡፡ ከዛስ? ምንድነው መጨረሻው? ተደሰቶ የመኖርን ብያኔ በውል አውቀነዋል ወይ? ከመብላት፣ ከመጠጣትና ከመዝናኛ ያለፈ ፍጡርነት በኛነት ውስጥ የለም? ካለስ ምንድነው? በእግዚአብሔር ሕልውና ካመንን እህሳ የተናገራቸውን ቃላት እንቀበላቸዋለን? ወይስ አንቀበላቸውም? ሳንወለድ የነበረውን ጊዜ አናውቀውም፤ አናውቀውም ማለት ግን የለም ማለት አልነበረም፡፡ እናስ ከሞትን በኋላ የሚኖረውን ጊዜ ስናስብ ምን እናስባለን? አሊያስ ቀድሞውኑ አናስብም? .. እስኪ ዝም ብለን እንጠይቅ!

መጠየቅና ተረጋግተን ማሰብ ስንጀምር፤ የእውነትን ፈለግ ለመከተል ዕድል እናገኛለን፡፡ መድኃኒቱ "ሕይወትም፣ መንገድም፣ እውነትም" ነው፡፡ ያገኘናል፤ ከተዘጋብን ቅርቃር ያወጣናል፤ ባሕሪያችንን ባሕሪይ አድርጎ በአባት ቀኝ ተቀምጦአልና የምንበላወስበትን ድካም ሁሉ ያውቀዋል! ስላወቀም ይሸከመዋል፤ የእርሱን ቀሊል ቀንበርም ይሰጠናል፡፡ "አሳርፋችኋለሁ" ሲል በወንጌላዊ ማቴዎስ ዘመን የተናገረው ቃል ያለአንዳች ጥርጥር ዛሬም የታመነ ነው፡፡ ይሄም ያረፈ ሰው የሚጽፈው ምስክርነት ነው፡፡ አዎ፤ ሦስተኛውን ቤተመቅደስ ይገነባ ዘንድ ውድ ሥጋውን የቆረሰ ንጹሕ ደሙን ያፈሰሰ አባትየው፤ የታመነ ነው፡፡ ስለ እዚህ ስለተከበረ ሥጋና ደም፤ ስለ ቤተ መቅደስነታችን ማሰብ እንጀምር!


(ጽሑፉ ረዝሞዋል፤ ቢሆንም አንብቡ! እንደተሰጠኝ አቀብያለሁ፤ የቀረው ድርሻ የእጃችሁ ነው፤ "በጎቹ" ድምፁን ይሰሙታል! ይቀበሉ ዘንድ ራሳቸውን ለአባትየው ያቀበሉ ሁሉ የሚገባቸውን ያገኙታል!)

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
3•  ቅዱስ ቁርባን ክፍል - ፪       3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?            3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል                ✞ ፫ተኛው ቤተ መቅደስ (ትንሣኤ) ✞    "ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን?…
3•  ቅዱስ ቁርባን

ክፍል - ፫

      3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?

           3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል

                  ✞ ሥርየተ ኃጢአት

   "ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።"

                                      (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፥10)

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ካየልን መድረሻና ንጹሕ ፈቃድ ወጥተን፤ ከ"አትንኩ!" ትእዛዝ ተላልፈን ያልተፈቀደልንን በመንካታችን ከአምላክ አሳብና ባሕሪይ ተለይተናል፡፡ ፍጹሙን ሕግ ጥሰን ሥርዓት አፋልሰናል፡፡ ይህም ባሕሪያችን በገነት ሳለ የፈጸመው ቀዳሚው ጥፋት "የአዳም ኃጢአት" ሲባል ይጠራል፡፡

የሰው ልጅ የተከለከለውን የእውቀት ዛፍ ያለ ጊዜው ከበላ በኋላ መልካሙን እና ክፉውን ለማወቅ የሚችልበት የአእምሮው ኃይል ነቅቶአል፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 3፥22) ይሄ እውነት የሚነግረን እውቀት የሚባለው ጉዳይ መልካምና ክፉ የሚባል ሁለት መልክ እንዳለው ነው፡፡ በመልካሙ እውቀት መንፈስ ቅዱስ ይገለጻል፤ በክፉው እውቀት ደግሞ መንፈስ ርኩስ ይገለጻል፡፡ ስለዚህ በሌላ አነጋገር እያልን ያለነው፤ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ በተቀደሰና ባልተቀደሰ መንፈስ መካከል የሚዋትት ሕይወት ይኖረዋል ነው፡፡

የአዳም ባሕሪይ የእውቀትን ዛፍ ከወሰደ በኋላ፤ በአእምሮ ታውቀው የሚገለጡ ግንዛቤዎቹ በመልካም (በጽድቅ) እና በክፉ (በኃጢአት) መካከል የሚመላለሱ ሆነዋል፡፡ ከዚህ የተነሣም፥ የሰው ልጅ ኃጢአትን አውቆ፥ በመቀጠል የሚፈጽምበት፥ ሁኔታ መጥቶአል፡፡ ይሄም ነገር በመጀመሪያ በአዳም ልጅ በቃየን ሕይወት ላይ ሊረጋገጥ ችሎአል፡፡

ባሕሪያችን ኃጢአትን ለይቶ አውቆ መሥራት ጀመረ ማለት፤ ከፈጣሪ ጋር የነበረን የአንድነት ቅርበት እየሰፋ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ አዳም ከገነት (የእግዚአብሔር ፈቃድ ከነበረው ቦታ) ወጣ የሚለውን አሳብ፤ የሰው ልጅ ባሕሪይ የአምላክን ፈቃድና እውነት ከሚከተልበት መንገድ እየራቀ እየራቀ ወጣ በሚል አተረጓጎም መረዳት ይኖርብናል፡፡ የዚህም ትንታኔ ማስረጃ፤ አዳም ወደ መሬት ተመልሶ ከመጣበት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለው የአኗኗራችን ገጽታ ነው፡፡ ጊዜ ጊዜን እየተካ ዘመናት ወደፊት በቆጠሩ ቁጥር፤ የሰው ልጆችም በኃጢአትና በዓመፃ ሕይወት የምንመላለስበት አኳኋንም ጨምሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለያይተን የምንኖርበት ሁኔታ ከቀን ቀን እያደገ ሄዶ ዛሬ የምንገኝበት ከባድ የክፋት ዘመን ላይ አድርሶናል፡፡

በኛ እና በአምላክ መካከል ገብቶ መለያየትን ያመጣው ኃጢአትና የኃጢአት ኃይል (ዲያቢሎስ) እንዲወጣ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ወገናችን ሆኖ ወደኛ መጣ፡፡ ኃጢአትን የማያውቅ፣ ንጹሕና ቅዱስ የሆነ ሰብአዊ ሥጋና ባሕሪይ ለብሶ፤ የኛን፥ በኃጢአት እሾህ እየተወጋ፣ በእርግማን አሜኬላ እየታነቀ፣ በስሕተት እውቀት እየተመራ ለረቂቅ ባርነት ተገዝቶ ያለ ሕልውናችንን ነጻ ሊያደርግልን ኑሮአችንን በትሕትና ሆኖ ኖረ፡፡ ጳውሎስ ሲናገር ፦

    "እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።"

                                             (ወደ ዕብራውያን 2፥14-17)

በእርሱ ቅድስና ሊቀድሰን የወደደ ቅዱስ ጌታ፤ በባሕሪይና በዘራችን ተጣብቶ ወደ ውድቀት ሲመራን የነበረውን የገነቱን ጥፋት ሊያጠፋልን፤ ጥፋትን የማያውቅ ሥጋውን እንጀራ አድርጎ በማቅረብ፤ በመብላት እንደወደቅን በመብላት ደሞ ከወደቅንበት እንድንነሣ ራሱን "እንካችሁ" አለን፡፡

   "ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።"

                                             (የማቴዎስ ወንጌል 26፥26-28)


የምንነጋገርበት ጉዳይ "ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው" የሚለው የመድኃኒቱ የምሕረት ድምፅ ላይ አለ፡፡

ኃጢአት ፈጽመን ከእግዚአብሔር እየራቅን መኖር ከጀመርን በኋላ፤ ስሕተታችንን የምናርምበትን መንገድ ልናገኘው አልቻልንም ነበር፡፡ ይልቁንም ከስሕተት ላይ ሌላ ስሕተት እየደረብን፤ ከዓመፃ ላይ ዓመፃ እየጨመርን፤ ከነባር ኃጢአት ላይ አዲስ ኃጢአት እየፈጸምን፤ ከክፉ መናፍስት ጋር በአንድም በሌላም አቅጣጫ እየተባበርን መኖርን መረጥን፡፡

ይሄ ምርጫችን ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም፡፡ እርሱ በቀዳማዊው አሳቡ ሲፈጥረን ለዚህ አይነት ሕይወት ፈጽሞ አላሰበንም፡፡ በመጀመሪያ መልካም እንደሆነ ያየልን የስብእና ከፍታ ከሥጋ ፈቃዳችን የተነሣ ወደኛ ሳይመጣ ቀርቶአል፡፡ ይሄ አሳብ ደግሞ ሕያው በሆነ መለኮት የታሰበ ሕያው አሳብ ነውና ከመፈጸም ሊቀር አይችልም፡፡ ስለዚህ ያሰበልንን ሊነግረን በቃሉ በኩል እርሱ ወደኛ መጣ፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ወደኛ የመጣው ከጠፋንበት (ከአምላክ ከራቅንበት) ቦታ ያገኘን ዘንድ እንደሆነ እናስታውስ፡፡ የጠፋነው ደግሞ በኃጢአት ነው፡፡ ስለሆነ ከጠፋንበት የምንገኘው ለኃጢአታችን ሥርየት ሲከናወንልን ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ፈላጊያችን ቃል ሥጋ (ዘመድ) ሆነና የራቀ ሕልውናችንን ወደርሱ አቀረበው፡፡ በሌላ አነጋገር "ወንድማችን" እስከሆነበት ጥግ ድረስ ከሸሸንበት ጎሬ ገብቶ ሊወዳጀን ፈቀደ፡፡

አዳም ከወደቀበት ስፍራ ላይ በመገኘት አዳምን የሆነው ተወዳጁ፤ የሰውን ባሕሪይ ከወደቀበት አንስቶ ወደ አባቱ መንግሥት ለመመለስ ዋጋ መክፈል ነበረበት (በእርግጥም መነሣት እንጂ መውደቅ ዋጋ አያስከፍልም)፡፡ ይህም ዋጋ እስከ ሞት ድረስ የሚሄድ ታላቅ ዋጋ ነው፡፡ ከሞትም ደግሞ ለከባድ ሕማምና ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳርግ ቁስልን የሚጠይቅ ሞት!

     "እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።"

                                                       (ትንቢተ ኢሳይያስ 53፥5)

እኛ እንገረፈው ዘንድ የተገባ ጅራፍን በጀርባው አስተናገደ፡፡ እኛ እንቀበለው ዘንድ የሚያስፈልግ ድብደባን በሰውነቱ ታገሰ፡፡ እኛ እንሸከመው ዘንድ የተስማማ መከራን በትከሻው አኖረ፡፡ እኛ እንታመመው ዘንድ የታዘዘ ቁስልን እርሱ ተቀበለ፡፡ በብያኔ ደረጃ፤ ቁስል ማለት የሥጋ መቆረስ ማለት ነው ብንል እንችላለን፡፡ እነሆም ስለኛ ስለሁላችን ኃጢአት ሲል አንዱ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውን በመስቀል ላይ ቆረሰ፡፡

መድኃኒቱ በመስቀል ላይ ሆኖ መሥዋዕት ከመሆኑ አንድ ዕለት አስቀድሞ፤ ለተማሪዎቹ ሥጋውን እንዲበሉ እንደሰጣቸው በወንጌል ተጽፎልናል፡፡ ይሄ ሥጋ የተቆረሰው ግን በቀጣዩ ዕለት በአርብ ነበር፡፡ እስቲ በቀላል በምሳሌ እንየው፡፡
አንድን በግ በሕይወት ወይንም በተለምዶ አገላለጽ ከነነፍሱ እያለ ልንበላው አንችልም፡፡ ሊታረድና ሥጋው በአግባቡ ለመብልነት እንዲሆን ተዘጋጅቶ ሊወጣ ግድ ይላል፡፡ እንዲሁ የእግዚአብሔር በግ ክርስቶስም በሐሙስ ማታ ሥጋዬን ብሉ፥ ደሜንም ጠጡ በሚልበት ሰዓት በመስቀል ላይ ገና አልታረደም ነበር፡፡ በሌላ አባባል አልሞተም ነበር፡፡ ስለዚህ ሥጋውን በመለኮት ጥበብ የተቀደሰ ሕብስት፥ ደሙንም ወይን አድርጎ ሲሰጣቸው፤ የሥጋና ደሙ ኃጢአትን የማስተሠረይ ኃይል የሚፈጸመው በአርብ መሰቀሉ እንዲሆን መንክር ሥርዓት አበጅቶ ነው፡፡ "ስለ ብዙዎች የሚፈስ ደሜ" ያለውም ለዚህ ነው፡፡ ደሙ የፈሰሰው አርብ ነው፡፡ እንኪያስ የዳንነው (ኃጢአታችን የተፈወሰው) በቁስሉ (በፈሰሰ ደሙ) ነው መባሉ እውነት ነው፡፡

በክርስቲያኖች ዘንድ ዝነኛ የሆነውና የተወደደው "በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን" የሚለው የጥቅስ ቃል ሲነበብ አሊያ በአንደበት ሲነገር ደስ ይላል፡፡ በእምነት ተቀብለን በሕይወት የሚገለጥ "ኑሮ" የምናደርገው ግን፤ በመበላቱ ይፈውሰን ዘንድ ለቁስል ተላልፎ የተሰጠ ሥጋውን ስንወስድ የተገኘን እንደሆነ ነው፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ምእመን፤ "በእርሱ ቁስሉ እኔ ተፈወስኩ" የሚል ንግግር ሲያሰማ፤ ለቁስል የተዳረገን የጌታን ሥጋ ስለመቀበሉ እርግጠኛ መሆን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ቁስሉ እኛን ሊፈውስ የቻለው፤ "ሥጋዬን ብሉ፥ ደሜንም ጠጡ" ሲል፤ መድኃኒት እርሱነቱን ከውስጣችን እንዲኖር የሚያደርግ አማናዊ ኪዳን ስለተሠራልን ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ጌታ አርብ ላይ በመስቀል ሥጋውን የቆረሰው፥ ደሙን ያፈሰሰው፤ የሐሙሱ የሥርየት ቃልኪዳን ወደ ፍጻሜ እንዲመጣ ነውና፤ ቅዱስ ቁርባንን ትቶ እንዲሁ በደፈናው በጌታ ተፈውስኩ ማለት፤ የታዘዘ መድኃኒትን ሳይውጡ ከሕመሜ ዳንኩ እንደማለት ነው፡፡

ቅዱስ ቁርባን ስለ ሰዎች ልጆች ኃጢአት ሥርየት ተብሎ የተሰናዳ ሰማያዊ ሥርዓት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ አምነን በስሙ የሚዘጋጀውን ማዕድ ስንካፈል፤ በመጀመሪያው ከአንዱ የአዳም ዘር በመሆናችን ምክንያትነት በመወለድ የሚከተለንን የእርግማን ገመድ እንበጥሳለን፡፡ በመቀጠል ከአዳም ኃጢአት ብቻ ሳይሆን፤ ከእውቀት ዛፍ በመብላታችን ክፉና ደጉን በጊዜያችን ውስጥ ስለምንሠራ፤ በክፉ እውቀት (በመንፈስ ርኩስ) የሚመራውን ኃጢአት እንድንደመስስ፤ በመልካም እውቀት (በመንፈስ ቅዱስ) የሚመራውን ጽድቅ ደግሞ እንድናጠነክር ኃይል እናገኛለን፡፡

የክርስቶስን ሥጋና ደም እየተቀበልን ስንኖር በሚከተሉት መንገዶች የኃጢአት ሥርየት ይከሰታል ፦

፩•  በሥጋ ከአዳም ቤተሰብ ሁላችን ተወልደናልና በባሕርየ ሰብ ውስጥ ከሚከተለን ከገነቱ ጥፋት ነጻ እንወጣለን (ይሄን በ40 እና በ80 ቀን የጥምቀት ቁርባን ላይ ብዙዎቻችን አግኝተነዋል)
፪•  በትውልዳችን የዘር ሐረግ ውስጥ የነበሩ የዓመፃ መዝገቦችና የበደል ሥራዎች ሁሉ ከነታሪካቸው ይፋቃሉ
፫•  በየጊዜው ኑሮአችን ውስጥ ስፍራ ይዘው ለመቆየት የሚታገሉ የአሳብ (ሐልዮ)፣ የቃል (ነቢር) እና የድርጊት (ገቢር) ኃጢአቶች ሥርየት ያገኛሉ

ስምዖን የሚባል አንድ ፈሪሳዊ በመድኃኒቱ ዘመን ነበረ አሉ፡፡ ይህም ሰው ጌታ ወደርሱ ቤት መጥቶ እንዲጋበዝ አጥብቆ ይወተውታል፡፡ ጥያቄውም ተቀባይነት ያገኝና መድኃኒቱ በጠሪው ቤት ለማዕድ ይሰየማል፡፡ ይህንን ሁሉ በርቀት ትከታተል የነበረች በከተማው ውስጥ የምትኖር አንዲት በኃጢአት አሽክላ የተያዘች ሴት፤ መድኃኒቱ የገባበትን ቤት ለይታ ካወቀች በኋላ ሽቱ የሞላበት ውድ የሆነ የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ ወደ ፈሪሳዊው መኖሪያ ዘለቀች፡፡ ከገባችም በኋላ ከመድኃኒቱ "በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች።" (የሉቃስ ወንጌል 7፥38) ይህንን ያየው ጋባዡ ባለቤትም፤ የሴትየዋ ኃጢአት በጌታ ፊት ሳይገለጥ በመቅረቱ እየታዘበ በልቡ ነገር ያመላልሳል፡፡ መድኃኒቱም የውስጡን አውቆ ለሰውየው የሚሆን ምላሽ ሰጠና ከበታቹ ወድቃ የምታለቅሰውን ሴት ደግፎ አነሣት፡፡ በስተመጨረሻም እንዲህ አላት "ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል"፡፡ (የሉቃስ ወንጌል 7፥48)

እንግዲህ ክርስቲያኖች እንዲህ ነው የምናምነው፡፡ ተወዳጁ ወደ ሕይወታችን ይመጣ ዘንድ የወደደው ስለ ኃጢአታችን እንደሆነ እናምናለን፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት ፍዳ ሊያድነንም ከመካከላችን እንደገባ እናምናለን፡፡ ግን እጅግ ብዙዎቻችን ያመንነውን የምንኖር አይመስልም፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ምስኪኒቱን ሴት "ከኃጢአት ማሠሪያ ተፈትተሻልና በሰላም ሂጂ" ሲል የተናገረ ጌታ፤ ዛሬም ይህንኑ የምሕረት ድምፅ በሥጋውና በደሙ ውስጥ አኑሮልን ወደ አባቱ እንደተመለሰ አልገባንም፤ ወይንም የገባንን በሕይወት መተርጎም አልፈለግንም፡፡

ስለዚህ የኃጢአት ሥርየትን ያላገኘ ሰውነታችን፤ ተገልጾ በማይወጣ የነፍስ ጭንቀት መተንፈሻ እያጣ፤ ይህንንም ያልተገለጸ ጭንቀት በሌሎች የተገለጹ ሥጋዊ ጭንቀቶች ለመርሳት እየዳከረ፤ አሁን ታይቶ አሁን የሚጠፋ ቅጽበታዊ ደስታን ለማቆየት ብዙ እየደከመ ቀናቱን ይገፋል፡፡ በመድኃኒቱ ትእዛዝ ዝም እንዲል ያልታዘዘው፥ ከውስጣችን የሚናወጠው፥ የኃጢአት ማዕበል፤ የሰከነ እፎይታንና አስተማማኝ እረፍትን ነስቶን፤ ስሜትና ትርጉም በሌለው የመኖር ጉዞ እንድንባዝን አስገድዶናል፡፡ የኃጢአትን ሰንሰለት ከበጠሰ በኋላ፤ እውነተኛ ሰላሙን ከሚታይ አካላችን ሥር ላለ የማይታይ ሕይወታችን ሊያካፍለን እጁን ወደኛ የዘረጋውን ጌታ፤ እንዴት ወደ ውስጣችን እንደምንይዘው ስላላወቅን፤ ብናውቅም እንኳ የተለያየ ሰበብ እየሰጠን መዳፉን ከመጨበጥ ሰለዘገየን፤ በክፉ እውቀት የሚገለጸው ዲያቢሎስ በሁሉም መንገድ አኗኗራችንን ከንቱ ሊያደርግ እርሱ አስቀድሞ እኛን ጨበጠን፡፡ በመሆኑም "በሰላም ሂዱ!" የሚለው የአምላክ ቃል ለሕልውናችን ስላልተደመጠ፤ በትንሹም መረበሽ፥ በትልቁም መረበሽ ዕጣችን ሆኖ፤ በየደረስንበት ቦታ ተጠራጣሪና ድንጉጥ ሆነን ችግርን በሰቀቀን እንጠባበቃለን፡፡

በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች በክርስቶስ ቁስል አልተፈወስንም፡፡ ለምን፤ ከኃጢአት ደዌ የሚያድነው የመድኃኒቱ ሥጋና ደም በብዙ ምክንያቶች ወደ ሥጋና ደማችን አልገባም፡፡ ይልቁኑ ወደ ውስጥ ሰውነታችን እንዲገባ የፈቀድነው የሚፈርሰውን እህልና ውኃ ብቻ ስለሆነ፤ ውጨኛው ኑሮአችንም እንዲሁ ይህንን የመፈረስ ገጽታ ይዞ፤ ተምረን ተምረን ባዶ፣ ሠርተን ሠርተን ባዶ፣ አቅደን አቅደን ባዶ በሆነብን ጊዜ ላይ በዘወትር ምሬት እንመላለሳለን፡፡

እናም፤ እንዲፈወስ ዕድል ያልተሰጠው ቁስላችን፤ ከዓመት ወደ ዓመት እያመረቀዘና እየሰፋ ሄዶ፤ አሁን በነኩን አካል ላይ ሁሉ ሕመም እየተሰማን፤ ውኃ ሲቀጥን ሲወፍር እየከፋን፣ በሆነ ባልሆነው ቶሎ ሆድ እየባሰን፣ በመጣ ባልመጣው እየተደናገርን፣ በሚሳካ በማይሳካው እየተብሰከሰክን፤ በውድ ዋጋ ተሠርቶ በነጻ የተሰጠ መድኃኒት እያለን፤ በርካሽ ዋጋ ተሠርቶ በውድ ዋጋ የሚገዛ ክኒን ለጭንቀት ማቅለያ እንውጣለን፡፡ ኸረ እስከ ዘላለም የታመነው፥ ታምኖም በሕልውና የሚነበበው፥ መጽሐፍ እንዲህ ነው የሚለው፤ "በእርሱም ቍስል (በተቆረሰ ክቡር ሥጋና በፈሰሰ ቅዱስ ደም) እኛ ተፈወስን (የኃጢአት ሥርየት አገኘን)።"

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
3•  ቅዱስ ቁርባን ክፍል - ፫       3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?            3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል                   ✞ ሥርየተ ኃጢአት ✞    "ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።"                               …
3•  ቅዱስ ቁርባን

ክፍል - ፬

         3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?

                3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል

                         ✞ ዘላለማዊነት

ሰባተኛዋን ቀን ሳንደርስባት ወድቀናል፡፡ ቀኒቱ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ ያረፈባት ናት፡፡ ፍጹም ሰላምን፣ ዕረፍትን፣ ዘላለማዊነትን ምልክት ታደርጋለች፡፡

አዳም በገነት አንድ ሺሕ ዓመት (አንድ ቀን) ኖሮ ቢጨርስ፤ ወደ አዲሱ ሥርዓት ይገባና ከዕፀ ሕይወት በመብላት ለዘላለማዊ ሕልውና ይታደስ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ አሳች ምክር ሰምቶ ወድቆአል፡፡ ወደ ዕረፍቲቱ ቀን ከመሄድ ይልቅ ወደኋላው ተመልሶ ወደ አንደኛው የዘፍጥረት ቀን ወርዶ ጎስቁሏል፡፡ ከዕፀ ሕይወት ዛፍ እንዳይደርስም ተከልክሎአል፡፡ ዘላለማዊነት ከነፍስ ባሕሪዩ ውስጥ ተደብቆ ቀረ፡፡

"አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ" የሚልን ትእዛዝ ሰብአዊ ማንነታችን ሰምቶአል፡፡ ከአፈር የተሠራው ሥጋችን ነው፡፡ አፈር ደግሞ የአንደኛው ቀን ፍጥረት ነው፡፡ ስለዚህ ሥጋችን ወደ አንደኛው ቀን፥ ወደኋላው ይገሰግሳል፡፡ ለመሞት እንኖራለን፡፡ ነፍስ ግን የመለኮት እፍታ ናት፡፡ ከማይለወጥ፣ ከማይጠፋ ሕልውና ተከፍላ የተገኘች ናት፡፡ በመሆኑ እርሷም የማትለወጥ፣ የማትጠፋ ዘላለማዊ አካል ናት፡፡ ወደ ሰባተኛው ቀን የመሄድ ፈቃድ በባሕሪይዋ ውስጥ ታትሞአል፡፡ ሥጋ ወደ አንደኛው ቀን፥ ነፍስ ወደ ሰባተኛው ቀን ይጓዛሉ፡፡

መሞትን አንፈልገውም፡፡ ከሞት ለመራቅ ማንኛውም አይነት ዋጋ ለመክፈል እንስማማለን፡፡ ሆኖም ግን እንሞታለን፡፡ አለመሞትን ብንመርጥም፥ አለመሞት አልቻልንም፡፡ ነፍስና ሥጋ ተጣልተውብናል፡፡ ከዕፀ ሕይወት ዛፍ ብንበላ ኖሮ፤ የዘላለማዊነት ኃይል በነፍስና በሥጋችን ላይ ይሠርጽልን ነበር፡፡ ግን ወደ ዛፉ እንዳንደርስ የሚጋርድ ኪሩብ ተሹሞብናል፡፡ ይሄ በባሕሪያችን ሲገለጽ፤ ዘላለማዊነትን ከውስጣችን ብናስሰውም እንዳንደርስበት መንገዱ ተዘግቶብናል፡፡ ወይንም ጠፍቶብናል፡፡ ሥጋ ወደታች ይዞን እየወረደ ከዕረፍቲቱ ቀን አርቆናል፡፡ አዳም (የሰው ልጅ ሁሉ) ወደ ሰባተኛው መግባትና ከፍ ከፍ ማለት አልቻለም፡፡

ወንዱ ልጅ እንደገና ሊወለድ ያስፈልገዋል፡፡ በሌለ አባባል ከወደቀበት ከአንደኛው ቀን ሥርዓት ተነሥቶ ወደ ስድስተኛው ቀን ሥርዓት በመሄድ ከፈረሰበት መሠራት አለበት፡፡ ከዛ በመቀጠል ወደ ሰባተኛው የዕረፍት ቀን መግባት ያስፈልገዋል፡፡ ገና ስንፈጠር ወደዚህ ቀን እንድንደርስ በአምላክ ታስበን ስለሆነ፤ የፈጣሪ ፈቃዱ በባሕሪያችን አለ፡፡ አውቀነውም ሆነ ሳናውቀው ወደ ቀኒቱ ለመድረስ ስንጣጣር እንኖራለን፡፡ ወንዱን ልጅ ለማግኘት እናምጣለን፡፡

አዳምን እንደገና ለመውለድ /የሰውን ልጅ እንደገና ለማደስ/ በባሕሪይ ያማጥንባቸው ዓመታት በክርስትናው አስተምህሮ የብሉይ ኪዳን ዘመናት ይባላሉ፡፡ እነዚያ 5500 ዓመታት ሲፈጸሙ፤ ስድስተኛው ሺሕ ዘመን ላይ ወይንም በዘፈጥረት አገላለጽ በተፈጠርንበት ስድስተኛው ቀን አጋማሽ ላይ (አርብ 6:00) ወንዱ ልጅ ተወለደ፡፡ ፍጹሙ ስብእና፥ አዳም ከጠፋበት ተገኘ፡፡ እነሆ፥ የሰው ልጅ ከመውደቅ የሚነሣበት አዲሱ ዘመን፤ ሐዲስ ኪዳን መጣ!

ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግማዊው አዳም ነው፡፡ በእግዚአብሔር ልቦና የተጸነሰው፣ ንጹሑና ቅዱሱ "ሰው' ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰው በእግዚአብሔር ፈቃድ በስድስቱ ቀናት የፍጥረታት ባሕሪይ ድምርነት ተሠርቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከፈቃዱ ወጥቶ ፈርሶአል፡፡ እንደገና በእግዚአብሔር ፈቃድ የፈረሰው ባሕሪይ ሲገነባ፤ ሁለተኛው አዳም በስድስቱ ሺሕ ዓመታት በኩል ተሠርቶ ተወለደ፡፡ እናስታውስ! አዳም ወደ ዘላለማዊ ሕልውና እንዲደርሰ ታስቦ ነው የተፈጠረው፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው አዳም ዳግም የተወለደው ወደዚህ ወደታሰበልን የዕረፍት ቀን፥ የዘላለም ሕይወት ይዞን እንዲሄድ ነው፡፡ ወይንም ከዕፀ ሕይወት ፍሬ ይሰጠን ዘንድ ነው ወደኛ መጥቶ ባሕሪያችንን የተዋሐደው፡፡ ከዕፀ ሕይወት? እንዴት? .. ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ፦

      "ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን። ይኸውም እኛን ስለመውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው"

ወደ ዘላለማዊነት የሚወስደው መንገድ ተዘግቶብን ነበር ብለናል፡፡ ሕያው ሆነን ለመኖር እንዳንችል ከአምላክ ፈቃድ ርቀን ጠፍተናል፡፡ በራሳችን ሕያው ለመሆን በብዙ አይነት መንገዶች እየተጓዝን ብንደክምም፤ ከመቃብር የሚያልፍ ኑሮን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ከዚህም የተነሣ ስናስብ፣ ስንፈልግ፣ ስናቅድና ስንሠራ ሞትን መጨረሻ አድርገን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ወደኛ በመጣ ጊዜ ግን፤ ይሄ እስከ ሞት ድረስ የሚረዝመው ታሪካችን ሊለወጥ ችሏል፡፡ የዘላለማዊነትን ድምፅ ከዘላለም ጌታ አድምጠናል፡፡

       "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።" (ተመስገን!)

                                                       (የዮሐንስ ወንጌል 6፥54)

የዳግማዊው አዳም የሚሞት ሥጋና ደም ከማይሞት የመለኮት ባሕሪይ ጋር የተዋሐደ ነው፡፡ ስለሆነ፤ ሁለተኛው አዳም የማይሞትን ባሕሪይ ተዋሕዶ አለና ከሞት ባሻገር የሚቀጥል ሕልውና አለው፡፡

እኛ ግን የተወለድነው፥ አዳም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ከተሰደደ በኋላ ነው፡፡ ማለት፤ የመጀመሪያው ሰው፥ ሞትን በሰማ ባሕሪዩ በኩል ነው ይዋለድ ዘንድ የሆነው፡፡ ስለዚህ ልጆቹ እኛም ሟቾች ነን፡፡ ከሚፈርሰው ሥጋ ተገኝተናልና እንፈርሳለን፡፡

የአምላክ የባሕሪይ ልጅ ታዲያ፤ የሰው ልጆች ሁሉ የሚወለዱበትን የአዳምን ባሕሪይ ሲዋሐደው፤ ከማይጠፋ፣ ከማይሞት መለኮታዊ ባሕሪዩ ጋር አንድ አደረገው፡፡ ይህን ዘላለማዊ ባሕሪይን የተዋሐደ ሥጋውን እና ደሙን መብል አድርጎ ሲሰጠን፤ የኛም ሥጋና ደም ዘላለማዊነትን ያገኝ ዘንድ ሆነለት፡፡ ከዕፅ ሕይወት እንድንበላ አደለን የሚያሰኘው እንግዲህ ይሄ ነው፡፡

የክርስቶስ ሥጋና ደም ስለ ዘላለማዊ ሕልውና ሲባል የተሰጠን ዕፀ ሕይወታችን ነው፡፡ በመብላታችን ምክንያት ከዘላለም ሕይወት (ከሰባተኛው ቀን) እንደተለየን፤ በመብላታችን ምክንያት ወደ ዘላለም ሕይወት እንድንመለስ ቅዱስ ቁርባንን በምሕረቱ ዘመን ተቀብለናል፡፡ ቅዱስ ቁርባን ስለ ዘላለም እውነት፣ ስለ ዘላለም ሰላም፣ ስለ ዘላለም ዕረፍት የምንቀበለው የሕያውነት ኃይል ነው፡፡

ከሚጠፋው አዳም ሥጋና ደም የተወለድን ሰዎች፤ ከማይጠፋው አዳም ሥጋና ደም ስንርቅ፤ የነፍሳችን የዘላለማዊነት ባሕሪይ ከሥጋችን መሠረት ሥር የሚያርፍበትን ስፍራ አጥቶ ኑሮአችን እስከሞት ድረስ በሚዘልቁ ቅጽበቶች ይሞላ ዘንድ ግድ ይሆንበታል፡፡

የዘላለም ሕይወትን የሚያድለው የክርስቶስ ሥጋና ደም ከሰውነትና ከዘመናችን ከተለየ፤ የሚጠብቀን ነገር ቢኖር እንዲሁ ትርኪ ሚርኪ የሆነ በብልጭታ ሁነቶችና በአጋጣሚዎች ላይ የቆመ ጊዜያዊ ኑሮ ነው፡፡ በወረት ቅጽበቶች የላመና ወዲያው ወዲያው የሚለዋወጥ አኗኗር የዛሬዋ ዓለም አገራት ዜጎች ሁሉ የሚጋሩት የአንድነት ገጽታ ሆኗል፡፡

ዓለም፤ በሳይንስ አስተንትኖቷና በቁስ እውቀት ሚዛን ልኬቷ በመስፈር የሕይወትን መርህ ደንግጋ ስታበቃ፤ "ሥጋዬ የተቀበለ ደሜን የተቀበለ ዘላለማዊ ነው" ያለውን ሕያው ቃል በጊዜያዊ ቃላቶች በመለወጥ ሰዎችን ለረጅም ዘመናት ያለማቋረጥ ስለሰበከች፤ የዘመናችን ትውልድ በተለይ ዘላለማዊነት የሚባለውን የሕያውነት አካል ሊያውቀውና ሊኖረው ቀርቶ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይገባውም፡፡
ዘላለማዊነትን ከፊደል ትምህርት ሰነዶቿና ፍኖተ ካርታዎቿ፣ ከሥራ መዋቅሯና የመሥሪያ ደንቦቿ፣ ከዜጎች የሕይወት መርህና የአኗኗር ሥርዓት፣ ከቴክሎኖጂ ውጤቶቿና ከምርምር ግኝቶቿ፣ ከፖለቲካዊ መርሆቿና ሕጓቿ አርቃ ያወጣቺው ይህቺ ዓለም፤ የሕያውነትን ኃይል ከብዙ ሰዎች ግንዛቤ ውስጥ አሽሽታዋለች፡፡

ለዘላለም ተፈጥረን ለጊዜዎች እንድንኖር የሚሸብበን የዓለም ወጥመድ ላይ ንቃተ ሕሊና የሌለን አማኞችም፤ በደረስንባቸው የኑሮ ሁኔታዎችና ቆይታዎች ላይ የሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ ጊዜያዊ ሆነው አረፉ፡፡ አልሆኑም? .. ከደስታም ጊዜያዊ፣ ከእፎይታም ጊዜያዊ፣ ከዕረፍትም ጊዜያዊ፣ ከተስፋም ጊዜያዊ፣ ከጸጋና ከበረከትም ጊዜያዊ፣ ከሞገስና ከማስተዋልም ጊዜያዊ፣ ከጥበብና ከችሎታም ጊዜያዊ ቆይታ ያለን ታይቶ ጠፊዎች አልሆንም?

አዳማዊያን ስንፈጠር ጊዜዎች ወደ ሕይወታችን የሚያመጧቸውን ነገራት ወደ ራሳችን የመኖር ውህደትና የመስመር ስምምነት ከማምጣታችን በፊት 'ምን መጣ?' የሚለውን ለማጥለል እንድንችል፤ ከመጣው ጉዳይ አሊያ አጋጣሚ መካከል ክፋትን ለይተን፥ መልካሙን አስቀርተን፤ አንጥረን፤ እንጠቀም ዘንድ አእምሮ ከግራ ቀኝ የማጤኛ ልቦና ጋራ ታድለን የነበረን ቢሆንም፤ ሰዎች ዛሬ ከተሰጣቸው በታች የሚኖሩ ሲሆን፤ ጊዜ እንዳመጣው የሚመጡ፣ ጊዜ እንደሚወስደው የሚሄዱ እየሆኑ፤ ወደ ዓለም በጊዜ እንደመጡ ከዓለምም ተለይተው በጊዜያቸው ይሄዳሉ፡፡ የዘላለም ሕይወት ከውስጣችን የሚጀምርበት የእምነት ጥበብ ስለጠፋን፤ ጊዜ ጀምሮ፤ ጊዜ እንዳደረገን አድርጎ፤ ጊዜ ይጨርስናል፡፡ በዕድሜያችን ጊዜዎች መካከል ልዩ ማንነታችንን ሳንፈልገውና አግኘተን ሳንጠቀምበት፤ ጊዜው ለኛ የሚስማማውን እንዲያቆይልን፥ የማይጠቅምንን እንዲወስድልን በመንፈሳዊ ኃይል ሳንቆጣጠረው፤ ሳንሞት በጊዜዎች ውስጥ በኑሮ ሞተን ደግሞ እንደገና በአካል የምንሞትበት ጊዜ ሲደርስ ወደ መቃብር እንሸኛለን፡፡

ዮሐንስ 6፥27 ላይ "ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና" ይላል፡፡ ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ተብለን ግን ለዕለት እንጀራ ብቻ ስንባዝን ዕድሜያችን ሄደ፡፡ እንጀራ ብቻ ስናሳድድ፥ ሥጋችንም በዛው እንደ ባሕሪዩ ከነፍሳችን ርቆ ተሰደደ፡፡ በየቀኑ ለእንጀራ ኑሮ ብቻ የምንወጣ የምንገባ ፍጡሮች ሆነን፤ ሌሎች መንፈሳዊ እውነታዎችና ሰማያዊ ሚስጢሮች ከጉያችንም ሆነው እየተሸሸጉብን፤ የሕይወትን በረከት ያዝነው ስንል እያመለጠን፣ ልናድግ ነው ስል እየደከምን፣ ልናርፍ ነው ስንል ተጨማሪ እየሮጥን፣ ተረጋጋን ስንል አዲስ ችግር እያስጨነቀን፤ አልባረክ ባለ ጊዜ ውስጥ አልበረክት ያለ ዘመንን ተሸክመን ተቸገርን፡፡ አልፎም ተርፎ የመኖር ወዝ ተሟጥጦ እስከሚደበዝዝብን ድረስ ተፈተንን፡፡ አየህ? ለምድር እንጀራ ብቻ የመሮጥን ውጤት? የምድርን እንጀራ፣ የምድርን መብል፣ የምድርን ምቾት ፍለጋ ስትሮጥ መንገዱ ማለቂያ አይኖረውም፡፡ አጋመስኩት ብትል ዞረህ ከተነሣህበት ጅማሮ ላይ ትመለሳለህ፡፡ ደረስኩበት ብትል የሚቀርህን አስበህ በአእምሮም በአካልም አንድ ጊዜ ትዝላለህ፡፡ እንደዚህ ነው የሚለው በቃ "ለሚጠፋ መብል አትሥሩ!"

እሺ ታዲያ ለምን እንሥራ? ቃሉን መለስ ስናነበው እንደዚህ የሚል ምላሽ ይሰጠናል፤ "ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፡፡" ለዘላለም የሚኖር፡፡ ዛሬ ተበልቶ ነገ የሚርብ መብል አይደለም፡፡ ወሩን ሙሉ ተደክሞበት፣ ከክፉዎች ጋር በመታገል፣ ብዙ በመውጣትና በመድከም የሚመጣ መብል አይደለም፡፡ ይሄ የዘላለም መብል ነው፡፡ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደሙ ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን፡፡

የዘላለም ሕይወትን አጥተው የጊዜዎች ሕይወትን ይመሩ ዘንድ ሰዎች እንዳይገደዱ አምላክ ሰው ሆኖ የዘላለም ቃሉን አሰማን፡፡ "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው" አለን፡፡

የክርስቶስን ሥጋና ደም መውሰድ ስንጀምር፤ ሥጋችን ከነፍስ ፈቃዳችን ጋር ተናብቦ ጉዞውን ወደ ሰባተኛው የዕረፍት ቀን ስለሚያቀናው፤ የእኛ እና የዓለም ጊዜዎች ቅርጻቸውን ወደ ዘላለማዊነት እየቀየሩ እየቀየሩ ይመጣሉ፡፡ የዕድሜ ሰዓቶቻችንና የምንኖርበት ዘመን ሰዓቶች ቅጽበታዊ የሆነ ኲነታቸውን እየለቀቁ ሊቆይ የሚችለውን፥ ሊጸና የሚችለውን ለማምጣት ሲሉ መሄድ ይጀምራሉ፡፡ ቅዱስ ቁርባን ስንወስድ ዘላለማዊነትን መኖር የምንጀምረው በሚከተሉት ሁለት ውስጣዊና ውጪያዊ መንገዶች ነው፡፡

በአንደኛው፥ እግዚአብሔር አምላክ ከምድር አፈር አበጅቶን ሰው ሊያደረገን ሕያው እስትንፋሱን ነፍስ አድርጎ በውስጣችን ሲያኖራት፤ ከውጪ የምንቀበለው የእግዚአብሔር አምላክ ሕያው ሥጋውና ሕያው ደሙ ለነፍሳችን ምግብና መጠጥ ይሆንላታል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ቁርባን የሕይወትህ ክፍል በሚሆንበት ጊዜ ዘላለማዊነት ከነፍስህ ውስጥ ስለሚጀምርና እየገዘፈ እየገዘፈ ስለሚመጣ ውስጣዊ ሕይወትህ ዝም ይላል፡፡

ዝምታው የሐዘን፣ የመቆዘም፣ የመባዘንና የመቆራመድ ሳይሆን የመረጋጋት ዝምታ ነው፡፡ የእፎይታ ዝምታ ከውስጥ በኩል በጥልቀት ይሰማሃል፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ላንተ ምንም የማይሞቅ የማይበርድ አይነት ሆኖ ማዕበል ቢመታው የማይናወጽ እንደ ሐይቅ ጠለል በዝግታ የሚንሸዋሸው ዝምታ ከውስጥ ይሰማሃል፡፡ ከውስጥህ ያለው በሥጋና ደሙ መቀደስ በኩል የመጣው የዘላለማዊነትን መንፈስ ያዘለ ዝምታ፤ ብትታመም የማይደነግጥ፣ ብታጣ የማይሰጋ፣ ብትራብ የማይጨነቅ፣ ቢሞላልህ የማይፈነጥዝ፣ ቢተረፈረፍህ የማይኮፍስ፣ ብትጠግብ የማይወጣጠር ሰው አድርጎ ይቀርጽሃል፡፡ ቢመችህም ባይመችህም ዘወትር የውስጥ መደላደልና የማይሸበር ጸጥታ ያለው ሰው ትሆናለህ፡፡

ሁለተኛው፤ ሥጋና ደሙን በተደጋጋሚ በመቀበል የሕይወት ልምድ ውስጥ ሰውነትህን ስትቀድሰው ተፈጥሮ ወዳንተ እያዘነበለ፤ ላንተ እየታዘዘ፣ አንተን እያገዘ፣ የምትለውን እየሰማህ የምትኖርበትን ዘላለማዊነት ከውጪ ባለው ገጽታ በሚታይ እውነት ውስጥ ይገልጥልሃል፡፡

እግዚአብሔር ተፈጥሮን አንጾና አስተካክሎ ከፍጥረታት ጋር ሲያኖራት፤ የሰው ልጆችን እንደ አባትነቱ በፍጹም ፍቅሩ ለይቶ ሲፈጥር በነፍስ ሥልጣንነት በኩል እግዚአብሔርነት አካፍሎናልና ተፈጥሮ እንድታገለግለን ፍጥረታትን እንድንገዛ አክብሮ ቀረጸን፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 1፥28)
   
ይሄ ድንቅ ነገር ነው፡፡ የምድር ፍጥረታትን ሁሉ በየወገን ወገናቸውና በየነገድ ነገዳቸው ካበጃቸው በኋላ ስም የማውጣት ኃላፊነት ለሰው ልጅ ተሰጠው፡፡ አዳምም ለእንስሳትና ፍጡራኑ ሁሉ ስም ሲሰጣቸው፤ ስማቸውም ጸድቆላቸው እንዲታዘዙትና እንዲያገልግሉት ሆኑ፡፡ በፍጥረታቱም ሳያበቃ ተፈጥሮን አዳም እንዳሻው እንዲያበጃትና እንዲጠብቃት ተሰጠቺው፡፡

     "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።"

                                                         (ኦሪት ዘፍጥረት 2፥15)

ዛሬ ይሄ ታላቅ ስጦታ ከሰብአዊነታችን ውስጥ ከነአካቴው ርቆ፤ እንኳንስ ተፈጥሮን ልናበጃትና ልንጠብቃት ይቅርና የራሳችንን የግል ሕይወት ማስተካከልና መጠበቅ ተስኖን ከተፈጠርንበት ኃያል ጸጋ ሸሽተን የምንኖር ድኩማኖች በመሆን ዝምብለን እንገላወዳለን፡፡
ስንጀምረው ተፈጥሮ ለኛ ትሠራ ዘንድ ነበረ የተፈጠረቺው፡፡ መጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 10'ን ስናይ፤ ኢያሱ በእግዚአብሔር ፊት ፀሐይን በገባዖን ምድር አቁሟታል፡፡ ጨረቃንም አዘግይቷታል፡፡ እኛ አሁን እግዚአብሔር ፊት መቆም ስላቃተን ለተፈጥሮ ብቻ ለመሥራት ተገድደናል፡፡ አልፎም ተርፎ አንዳንዴ ተፈጥሮ ስትከዳን ለመኖራችን አደጋም ጭምር ታመጣብናለች፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ባሕር ከፍለው ተሻገሩ የሚለውን ታሪክ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ይዘው፤ ዛሬ ከአገር ሊወጡ ሲሹለከለኩ፣ እንደ ዕቃ ሲጫኑ ሲወርዱ፤ ባሕር ደርምሷቸው ስንቶች የዓሳ እራት ሆነው እንደቀሩ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ስንቶች አለቁ? መሬት ሲንሸራተት የስንት ሰዎች ሕይወት አብሮ ተንሸራተተ? የጎርፍ ውኃ ስንቶችን እያላተመ ወሰደ? የእሳት ሰደድ የስንቶችን ሕይወትና ኑሮ አነደደ? የአውሎ ነፋስ ወጀብ ስንቶችን ለሥርዓተ ቀብር አስክሬናቸው እንኳ እንዳይገኝ አርቆ ቀበረ?

እግዚአብሔር የሌለው የሰው ልጅ በተፈጥሮ ሥር ነው፡፡ አሁን በዚህ በምዕራባውያኑ እና ሩቅ ምሥራቃውያኑ ውስጥ ያሉ አገሮች ከአሁን አሁን መሬት ከዳችን እያሉ ከሚመጣው አደጋና ሰቆቃ ለመትረፍ ቤት ሲሠሩ፣ መንገድ ሲገነቡ፣ ኢንደስትሪ ሲተክሉ የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም እንዲችል አድርገው ነው፡፡ ለዘመናትም በዚህ የተፈጥሮ ግብ ግብ መካከል የኖሩ ዜጎችም ተፈጥሮን እየፈሩ፣ ተፈጥሮን ባለማመን እየጠበቁ፣ ተፈጥሮን አጨንቁረው እያዩ ይኖራሉ፡፡

በዘመነ ፍዳ የዲያቢሎስ ክንድና አገዛዙ ሰልጥኖ ከሕግ በታች አድርጎ የሰው ልጆችን በዘር ጉዳትና ውድቀት ውስጥ አስሮ፤ ስጦታችንን ሲፋለም የኖረበትን ዘመን ወደ ምሕረት ሊለውጠው እግዚአብሔር ቃል ፍቅር ይዞት ሥጋ ሆነና ጸጋንና እውነትን ተመልቶ ወደ ጊዜና ወደ ሕይወታችን መጣ፡፡ ሲመጣ ከሰጠን ታላላቅ ሰማያዊ በረከቶች መካከል አንደኛው ንጹሕ ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነው፡፡

ታዲያ ይሄን ክቡር ሥጋና ደም ስንቀበል ተፈጥሮን ማገልገላችን ይቀርና ተፈጥሮ እኛን ለማገልገል ወደ ኑሮአችን ትታዘዛለች፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያውን ንጹሑን የአዳም ስብእና እያገኘነው እያገኘነው ስለምንሄድ፤ በነፍስ ወረቀታችን ላይ የተጻፈው ተፈጥሮን የማዘዝ ሥልጣን መገለጥ ይጀምራል፡፡ እነሆ፥ ተፈጥሮ ላንተ እንድትስማማ የክርስቶስ ሥጋና ደም ያስፈልግሃል፡፡ "የሰማይ አባታችን ሆይ፥ ለአዳም የሰጠኸውን ቀዳሚ ጸጋና ሞገስ እንዲሁ በኔ ሕይወትም ስጠኝ፡፡ ጊዜና ዘመን እንዳይገዛኝ የሕይወቴን መግቢያ መውጪያ ተቆጣጠረው፡፡ የመኖርን ሚስጢር ከሰማያዊ ስጦታዎችህ ጋር ግለጥልኝ፡፡ የዕረፍቲቱን ቀን ኃይል በባሕሪዬ ውስጥ አኑርልኝ፡፡ ሕያው እውነትህ በኑሮዬ ውስጥ ይጀምር" እያልክ ቅዱስ ቁርባን ስትወስድ ..  ያን ጊዜ የተፈጥሮ ባለቤት መሆን ትጀምራለህ፡፡ ጊዜ አንተ ስለለፋህ ብቻ ሳይሆን ጊዜው አንተን ሊያግዝህ የማያቋርጡ ዕድሎችን እየያዘ ወዳንተ ይመጣል፡፡ ሁኔታዎች አንተ ስለተጨነቅላቸው ሳይሆን ሁኔታዎች ላንተ ሊጨነቁልህ ወዳንተ ይገሰግሳሉ፡፡ በረከት አንተ ስለደከምክለት ብቻ ሳይሆን፤ ስለወጣህ ስለወረድክለት ሳይሆን፤ በረከት ካንተ ጋር ለመሆን ወዳንተ ይመጣል፡፡ የሚደግፉህና የሚያበረቱህ ልበ ቀና ሰዎች ሳትጠራቸው ወዳንተ ይመጣሉ፡፡ የሚያስፈልግህን ሁሉ በጊዜ ጊዜው እንድትሰጥህ ተፈጥሮ ከሰማይ አምላካችን ትእዛዝ ትቀበላለች፡፡ ከዛ በኋላ ሰውና ዲያቢሎስ የቱንም ደረጃ ያህል ቢሮጡ አይቀድሙህም፡፡ ክፉዎች የዘጉት በር ሁሉ እየተከፈተ፥ የከፈቱትም ሁሉ እየተዘጋ፤ የበረከትና የሰላም ገባር ወንዞች ወዳንተ የሕይወት ወንዝ ያለማቋረጥ እየመጡ ይቀላቀላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን

ይሄ የሚሆነው ግን በመጀመሪያው አቋም ሲኖረን ነው፡፡ በተሰበረ ልብና የእውነት ፍቅር ወደ እግዚአብሔር የመጠጋት ቁርጠኝነት ሲኖረን ነው፡፡ በቅዱስ ቁርባኑ በመቀደስ ከውስጥም ከውጪም የዘላለማዊነትን ቅርጽና ገጽታ መያዝ ስንጀምር ተፈጥሮ ለአዳም እንደታዘዘቺውና እንዲጠብቃትም እንደተሰጠቺው ወዳንተ እርዳታዎችን ልታደርግልህ ትመጣለች፡፡ የዛሬው ትውልድ ተፈጥሮ የሸሸቺው ትውልድ ነው፡፡ ዓለም ሲደነግጥ አብሮ የሚደነግጥ፣ ዓለም ሲፈራ አብሮ የሚፈራ፣ ዓለም ሲሸወድ አብሮ የሚሸወድ ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህ የሕይወት ምሪቱንና የራእይ መረጃዎቹን ከቴሌቪዥን፣ ከኢንተርኔት፣ ከጋዜጣና ከመገናኛ አውታሮች ብቻ የሚጠብቅ እየሆነ፤ ዜናዎች ሲጨክኑ እየተሳቀቀ፣ ዜናዎች ሲያበስሩ እየፈነጠዘ፣ ዜናዎች ሲወሳሰቡ ግራ እየተጋባ የሚኖር ሆኖ ይገኛል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
2•  ንስሐ    2.4•  ለንስሐ እንዴት እንዘጋጅ? ክፍል - ፰                  ✞ ለማንና እንዴት እንናዘዝ ✞    ከንስሐ ሂደት ውስጥ ወደ መጨረሻው አከባቢ የምናገኘው ክፍል "ኃጢአትን የመናዘዝ" ክፍል ነው፡፡ መናዘዝ በጥሬ ቃሉ አደራን መናገር፣ ሚስጢርን ማውጣት፣ ጥፋትን ማስረዳት፣ ስሕተትን መግለጥ ከሚሉ ግሶች ጋር አቻ ይገጥማል፡፡    መናዘዝ የንስሐ መሠረታዊ አምድ ተደርጎ…
3•  ቅዱስ ቁርባን

ክፍል - ፭

         3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?

                3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል

                         ✞ ሀበነ ንኅበር

     "ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ ከመ ብከ ንሕያው ዘለኩሉ ዓለም ወለዓለመ ዓለም፡፡"

     "የአንተ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ ስጠን በዚህም በሥጋው በደሙ አድነን ለዓለሙ ሁሉ በምትሆን በአንተ ለዘላለሙ ሕያዋን እንሆን ዘንድ"

                                                               መጽሐፈ ቅዳሴ

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር አንድ አዳምን ነው የፈጠረው፡፡ የሰው ልጆች ሁላችን የተገኘነውና የምንገኘው ከዚህ አንድ ሰው ነው፡፡ አዳምን እንደ አንድ ትልቅ ወንዝ ማየት እንችላለን፡፡ አስቀድሞ ሔዋን የተባለች ሴት ከዚህ ወንዝ ተቀድታ ወጣች፡፡ በመቀጠል አቤልና ቃየን ወጡ፡፡ እያለ እያለ ..

ሁላችን ከአዳም ተገኝተናል ካልን፤ በአዳም የሆነው ሁሉ በኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከደፈረሰ ወንዝ የደፈረሰ ወንዝ እንዲቀዳ፤ የአዳም ባሕሪይ ለሞት በመታዘዙ ምክንያት፤ እኛም የምንሞት ሆነናል፡፡ ሞትን ለምሳሌ ያህል ጠቀስን እንጂ፤ አዳም የገነቱን ስሕተት በመፈጸሙ ምክንያት የመጡበትን ጉስቅልናዎች ሁሉ ተካፍለናቸዋል፡፡ መራብ፣ መጠማት፣ መታመም፣ ማርጀት፣ መድከም፣ .. የሚባሉ የጸጋ መገፈፍ ውጤቶችን ከአባታችን አዳም ሁላችን ተቀብለናል፡፡

አዳም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጣሰ ጊዜ፤ የተጣላው ከአምላኩ ጋር ብቻ አልነበረም፡፡ ከእራሱ ጋርም ተጋጭቷል፡፡ ነፍስና ሥጋው በተለያየ መሻትና ስበት የሚቃረኑ ሆነውበታል፡፡ በውስጡ ከተጻፉት የተፈጥሮና የፍጥረታት ባሕሪያት ሁሉ ጋር ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይሄም የውስጥ ጸብ በውጪኛው ገጽታ በተጨባጭ ሲገለጽ፤ ሰውን ፀሐይ ታተኩሰው፣ ዝናብ ይቀጠቅጠው፣ እሳት ያቃጥለው፣ ድንጋይ ይፈነክተው፣ ጉንዳን ይቆነጥጠው፣ ጃርት ይወጋው፣ ጊንጥ ይነድፈው፣ ውሻ ይነክሰው፣ ድመት ትቧጥጠው፣ .. ጀመር፡፡

ይሄ የውስጥ ቅዋሜ በውስጠኛው ማንነታችን ላይም የሚነበብበት የራሱ ገጽ አለው፡፡ በዝርዝር እንየው፡፡

በኦሪት ዘልደት መግቢያ ምዕራፍ ላይ የምናገኛቸው ተፈጥሮና ፍጥረታት የተፈጠሩበት ስድስት ተከታታይ ቀናት አሉ፡፡ እነዚህ ቀናት አንድን ፍጥረት በአካል ሲያስገኙ፤ ያ አካል ደግሞ ከሌሎች ፍጥረታት ራሱን የሚለይበት ልዩ ባሕሪይ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው የቀን ሥርዓት የተገኘውን እሳት ብንመለከት፤ እሳት የውዕይት (የማቃጠል፣ የመተኮስ፣ የመንደድ) ባሕሪይ አለው፡፡ ይሄ ባሕሪዩ የራሱን የእሳትነት አካል መልክና መገለጫ ያደርጋል፡፡

ስድስቱ ቀናት ተከታታይ ሲሆኑ፤ የአንዱ ቀን ፍጡራን ባሕሪያት ለሚከተለው ቀን ተፈጣሪ አካል መጋቢ ባሕሪይ ይሆናሉ፡፡ ይህም ማለት ፍጡራኑ በቅደም ተከተል እንደተፈጠሩበት አደራደር ቀዳሚው ባሕሪይ በተከታዩ አካል ውስጥ መዋቅር ሆኖ ይገባል፡፡ ፀሐይን እንመልከት፡፡ በሦስተኛው የቀን ሥርዓት የተፈጠረቺው ፀሐይ የአንደኛው ቀን ፍጡራን የሆኑትን እሳትና ብርሃን በባሕሪይዋ ውስጥ ተደምረው አሉ፡፡ አስቀድመው በተገኙ አካላት ላይ የተጻፉ ባሕሪያት በቀን ወደፊት ውስጥ እየተሰበሰቡ የቀጣዩን ቀን ፍጡር ባሕሪያት ይቀርጻሉ ነው በአጭሩ፡፡

የሰው ልጅ በስድስተኛው ቀን ላይ የተፈጠረ የመጨረሻው ፍጡር ነው፡፡ ስለዚህ ከአዳም በፊት ተፈጥረው የተገኙ ባሕሪያት ሁሉ ተሰብስበው ከውስጡ አሉ (የሰው ልጅ ተነብቦ የማያልቅ መጽሐፍ መባሉ በነዚህ የባሕሪያት ስብጥርነት የተነሣ ነው)፡፡

በግ የዋህ እንስሳ ነው፡፡ አጠገቡ አንድ በግ አርደህ ይህኛውንም ልትደግመው ብትጠጋው አይሸሸህም፡፡ ፍየል ላይ ይሄ አይሠራም፡፡ ብልጥ ናት፡፡ ውሻ ለባለቤቱ ታማኝ ነው፡፡ ተንከባከበው አልተንከባከበው ጌታውን አይከዳም፡፡ ድመት በቤት የምትቆይበት ጊዜ እንደ ምቾቷ ይወሰናል፡፡ ካልተስማማት አለፍ ብላ ጎረቤት ስትጠጋ አንዳች ቅር አይላትም፡፡ ተኩላ ነጣቂ ነው፡፡ የሚሆነውንም የማይሆነውም መንትፎ መሄድ ምርጫው ነው፡፡ ጉዳን ታታሪ ነው፡፡ የጀመረውን ሥራ ሳይፈጽም ማረፍን አይፈልግም፡፡ እስስት አከባቢዋን ቶሎ ትለምዳለች፡፡ ራሷን ታመሳስላለች፡፡ ሣር ለተነፈጠበት መልክአ ምድር ውበት ነው፡፡ ዙሪያውን ያደምቃል፡፡ ነፋስ ወዳጅ የለውም፡፡ ወዳገኘበት ስፍራ በነጻነት ይሄዳል፡፡ ከዋክብት በማታው ክፍለ ጊዜ ያሸበርቃሉ፡፡ በአንድነት ሲታዩ ይደምቃሉ፡፡ እነዚህ ባሕሪያት በኛም የማንነት መዝገብ ላይ ድርሻ ይዘው የሰፈሩ ጠባያቶቻችን ናቸው፡፡

የባሕሪያቱ ስብስብ (እንደ ሕዝብ ብናያቸው) የበላይ የሆነ ገዢ ባሕሪይ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለበዚያ አንዱ ባሕሪይ ከአንዱ ባሕሪይ ጋር በተቃረነ ቁጥር ቀውስ ይፈጠራል፡፡ አራዊቱ እንስሳቱን ካሳደዱ ሰላም አይኖርም፡፡ ውኃው እሳቱን ካጠፋው ችግር ይኖራል፡፡ ድንጋይ የነፋሱን መውጪያ ከደፈነበት ባርነት ይከሰታል፡፡ በመሆኑም ባሕሪያቱን ሁሉ ተቆጣጥሮ የሚገዛ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ በየረድፋቸው፣ በየፈረቃቸውና በየቦታቸው እንዲገለጡ የሚያዝዝ አስተዳዳሪ ሊኖር ግድ ይላል፡፡

የባሕሪያትን መገለጥ ልክ ሰጥቶ የሚገዛቸው ታላቁ ባሕሪይ የነፍስ ባሕሪይ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር አካል ተከፍሎ ወደ ሰው የገባው መለኮታዊው እስትንፋስ፤ የተገኘው ከእግዚአብሔር ነውና ባሕሪዩም የእግዚአብሔር ነው፡፡ እንኪያስ "የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ" የሚለው የሥልጣን ዙፋን የተዘረጋው ለነፍስ መቀመጫነት ነው፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት 1፥26)

ይሄ ውስጣዊ ተቋም ወደ ውጨኛው ገሐድ ሲገለጥ በባሕሪያት ላይ የታየው መስማማትና መፈቃቀድ በአዳምና በፍጡራን መካከል ይታያል፡፡ አገላለጹን ሌላ ገጽታ ስንሰጠው፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮንና ፍጥረታትን እንዲያስተዳድር ነፍሱ በባሕሪያቱ ሁሉ ላይ መንገሥ አለባት፡፡

የላይኛውን አንቀጽ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ዋቢ እናድርገው፡፡ "አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው" ኖኅ፤ የፍጡራን ሕይወት በጥፋት ውኃ ምክያትነት ከምድር ጠፍቶ እንዳይቀር ወደ ገነባው ግዙፍ መርከብ እንዲያስገባቸው ታዝዞአል፡፡ ታዲያ ፍየሉና ነብሩ፣ አይጥና ድመቱ፣ ሚዳቋና ነብሩ እንዴት ሳይቀዋወሙ ሰልፋቸው ጠብቀው እንደገቡ ሰልፋቸው ተከትለው ወጡ?

በኖኅ ማንነት ላይ ሠልጥና ያለቺው የእግዚአብሔር እፍታ ከውስጡ ያሉትን ባሕሪያት ተቆጣጥራ ስለገዛቻቸው፤ እንስሳቱና አራዊቱ በኖኅ ፊት ሳሉ አይጣሉም፡፡ ተደጋግፈው እንጂ ተገፋፍተው አይቆሙም፡፡ አካሄዳቸውን "ከዓለም ጋር አድርገው" የነበሩት የኖኅ ጎረቤቶች ቢሆኑ ኖሮ ግን መርከቢቱን የሚመሩት፤ እንስሳቱ ተበልተው አራዊቱ ብቻ ይቀሩ ነበረ፡፡

ወደ ነጥባችን ስንመጣ፤ አካሄዳችንን ከዲያቢሎስ ምክር እንጂ ከእግዚአብሔር አሳብ ጋር ባለማድረጋችን ምክንያት ነፍስ በሰውነት ላይ ከነበራት ኃይል ፈረሰች፡፡ ባለሥልጣን መሆኗ ቀረና እንደሌሎቹ ባሕሪያት ወደ ውስጥ ተሻጠች፡፡ በዚህ ጊዜ ሌሎቹ ባሕሪያት ድብልቅልቃቸው ስለወጣ፤ አዳም ውሳጣዊ ማንነቱን መግራት የማይችል ሆነ፡፡

        "አቤቱ፥ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፥ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።"

                                                  (ትንቢተ ኤርምያስ 10፥23)
በቁጥር እጅግ ብዙ የሚባል ሰው፤ የሕይወት ጎዳናውን በራሱ የባለቤትነት ሥልጣን ተቆጣጥሮ በመኖር መንገዱ ላይ በውሳኔ እርምጃ ሲጓዝ አይታይም፡፡ ሰዎች በውስጣቸው ሌሎች ሰዎች ደባል ሆነው የሚኖሩ ያህል፤ በተቃራኒ ፍላጎቶች ሲንገላቱ፣ በተለያዩ ስሜቶች ሲዋዥቁ፣ በተሰበጣጠሩ አሳቦች ሲምታቱ፣ ባልተናበቡ እቅዶች ሲንከላወሱ፣ በሚነቃቀፉ ምግባሮች ሲደናገሩ፣ በሚለዋወጡ ጠባዮች ሲገለጡ ይስተዋላሉ፡፡ አንዳንዴሞ በተራራቁ የዋልታ ጥጎች ላይ በቆሙ ማንነቶች ከራሳቸው ጋር ክፉኛ እየተጋጩ፤ የኑሮ ገጠመኝ ባደረሳቸው ቦታ ላይ እንዴት እንደደረሱ ሳያውቁትና ሳይገነዘቡት ያለ'መኖርን ቀን እየቆጠሩ የሚኖሩ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አሉ፡፡ ነብዩ ምን አለ? .. "የሰው አካሄዱ ከራሱ ጋር እንዳይደለ አውቃለሁ"፡፡ ከራሱ ካልሆነ ታዲያ ከማን ጋር ነው?

ዲያቢሎስ ኃጢአት መፈጸማችንን ተከትሎ የመጣብን የውስጥ መደበላለቅ ውድቀታችን ላይ ይመካል፡፡ አንድ መሆን ያቃታቸው ውስጣዊ መገለጫዎቻችንን እንደ ጥሩ ዕድልና መሣሪያ በመጠቀም፤ የአእምሮ ሹክሹክታዎችን ከእኛ ለእኛ በማስደመጥ፣ በስሜት ግፊቶች ጀርባ ሆኖ ስሜቶችን በማዘባረቅ፣ ጠባያት በወጥነት መልክና ቅርጽ ተገኝተው የሰከነ ሁለንተና እንዳንይዝ የራሱን ጠባያት በተጻፉብን ባሕሪያቶቻችን በኩል በመግለጥ፣ ፍላጎትና የአኗኗር ዘይቤዎችን ተጋርቶ መስመር በማስለወጥ፣ ፍቃድና ውሳኔን ከፊት ቀድሞ በመምራትና ከኋላ ተከትሎ በመቆጣጠር፤ አካሄዳችን ከእግዚአብሔር ጋር ሳይሆን ከእርሱ ጋር እንዲሆን አድርጎ ወደ ወደደው መድረሻ በዝግታም በፍጥነትም ይመራናል፡፡ /አካሄዳችን ከእግዚአብሔር ጋር ሲሆን እንደ ኖኅ ከራሳችን ጋር አንድ እንሆናለን/

በዚህ ስለዚህ፤ አንዳንዶቻችን የአመላችን በተደጋጋሚ መቀያየርና አንዳች የጸና አቋም አለመያዝ ገርሞን እንዲሁ ራሳችንን እየታዘብን ተቀምጠናል፡፡ አንዳንዶቻችን የእኛነት መገለጫ አንድ ክፍል እንደሆነ አድርገን ተቀብለነው ከጊዜያዊ ሁነቶች ጋር ተሳስረን ከቅጽበት ጋር እንደ ቅጽበት የምንመላለስ ሰዎች ሆነናል፡፡ አንዳንዶቻችን ከራሳችን ጠባያትና አልረጋጋ የሚሉ ስሜቶች ጋር የግብግብ እልህ ተያይዘን፤ አንድ መሠረታዊ ገጽታ ያለው ማንነት ለመያዝ የምናደርገው ጥረት በተደጋጋሚ እየከሸፈ ግራ ሲያጋባን፤ ተስፋ ባለመቁረጥና በመቁረጥ መካከል ስንዋትት እንገኛለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ፤ ከላይ የተገለጹትን አይነት ሰዎች ሁሉ በመሆን፤ አንዳንድ ቀን ራሳችንን የምንታዘብ፣ አንዳንድ ቀን እንደ ልዩ ማንነታችን የምንቀበል፣ በሌላ ቀን ከራሳችን ጋር የምንጣላና የምንፋለም ቀለም አልባ ሰዎች በመሆን እየተዘበራረቅን ዕድሜያችንን ቀጥለናል፡፡
 
ይሄ የጋራ ሐቃችን ሆኖ ሳለ፤ የሰው ልጅ የውስጣዊ ማንነት መተረማመረስና አልጨበጥ ማለት ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር በቀጥታ እንደሚያያዝ፤ የክፉ መናፍስት አንዱ የውጊያ አዝመራ ስለመሆኑም፤ በጣም ለብዙዎቻችን ገና ሊገባን እንኳ አልጀመረም፡፡ ምክንያቱም ርኩሳን መናፍስት ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚሄዱበትን ሚስጢራዊ አካሄድ፣ ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር ያላቸው ጥብቅ ትስስር፣ የማጥፋት አሠራር ጥበባቸውን እና ወደ ግባቸው ለመድረስ የሚጓዙበትን ሂደት፤ በሚገባ ለመገንዘብ የምናሳየው መሻት አነስተኛ በመሆኑ፤ ስውራኑ አጥቂዎቻችን በቸልተኝነታችን በኩል የተቀዳጁትን ኃይል የበለጠ ከዘመን ዘመን እያጠነከሩ፤ የእስራት ገመዳቸውን በማጥበቅ የሰብአዊነት ሕልውና ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ በብርቱ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
 
በአንድ ሰው ውስጥ ብዙ እርስ በእርስ የሚጋጩ ማንነቶች ሊከሰቱ የቻሉት፤ ከላይ ባስቀመጥነው የአዳም ታሪክ ውስጥ በተፈጠረው ከእግዚአብሔር ፈቃድ አፈንግጦ የመውጣት ስሕተትነት እንደሆነ አንስተናል፡፡ በዚህ ጥፋታችን ላይም በመመካት ዲያቢሎስ ውሳጣዊ አንድነት እንዳናገኝ በተለያዩ ረቂቅ መንገዶች ተጠቅሞ እንደሚፋለም በአጭሩ ዳስሰናል፡፡ የበለጠ ግልጽ እይታ እንዲኖረን እነዚህን መንገዶቹን በሦስት ጎራዎች ከፍለን እንመልከታቸው፡፡
 
              ሀ] ሰው እና ሰው ውስጥ ያለ መንፈሱ ሲጋጩ
 
የአብዛኞቻችን የተለመደ ችግር ነው፡፡ ከውስጥ ተቃራኒ ግፊት ሆኖ የሚመራን፣ የጥል አሳብ ሆኖ የሚወተውተን፣ ምሪት ሆኖ ወደማንፈልገው የሚወስደን ኃይል ሲቆጣጠረን ብዙ ጊዜ ይገኛል፡፡ ይሄ ለምን ሆነ ስንል፤ የኛ የሰብአዊ ማንነት እና የመናፍስቱ ማንነት በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም፣ የተለያየ አመለካከት፣ የተለያየ አካሄድና የተለያየ እቅድ ሲኖረን፤ መናፍስቱ ከውስጥ እኛን መስለው እኛን ይጣሉ ዘንድ ስልት ይቀይሳሉ፡፡
 
ምሳሌ እንመልከት፡፡ የሰላቢ፣ የዛር፣ የጣዖት፣ ስግብግብ የቡዳ መንፈሶች፤ ሰዎች ዐሥራት በኩራት ሲያወጡ አይወዱም፡፡ ስለዚህ ሠርተው የሚያገኙት ገንዘብ ወደ ቤተክርስቲያን ዐሥራት ሆኖ እንዳይደርስ፤ የውስጥ ጫና በመፍጠር፤ ዐሥራቱ እንዳይወጣ በራሳችን የአሳብ ልክ አሳብ ሆነው ይጣሉናል፡፡ "ኸረ ብዙ ቀዳዳዎች ያሉብህ ሰው ነህ ቀጣዩን ወር ታወጣለህ፤ አሁን ለዚህ ጉዳይ አውለውና በቶሎ ተክተህ ትሰጣለህ፤ ምንም በረከት ላታገኚ ዝም ብለሽ ነው ተይው ባክሽ፤ እግዚአብሔር ያንቺን ችግር ያውቃል ሲመችሽ ታወጪያለሽ" እና ወዘተ... የአሳብ ግፊቶችን በኛ ውስጠኛ ሕሊና ውስጥ በማመላለስ ዐሥራት ማውጣት የፈለገውን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ይዋጉታል፡፡
 
ታዲያ እጅግ በቁጥር የበዙ ሰዎች ውሳኔያቸው ከመለዋወጡ በፊት፤ ውሳኔ እንዲለወጥ ከውስጥ የሚገፋ ሁለተኛ ኃይል እንዳለባቸው ልብ አይሉትም፡፡ ምክንያቱም፤ መናፍስቱ ከውስጥ ሆነው ከኛ አሳብ ተደብቀው ሲጣሉን፤ ራሳችንን በራሳችን የምናወራ እንጂ ከሌላ ባዕድ ፍጡር ጋር እየተከራከርን እንደሆነ እንድናስተውል አይፈቅዱልንም፡፡
 
የክፋት መናፍስት የጥፋት አሳባቸውን ወደ ጥፋት ግብር ከመቀየራቸው በፊት ሁልጊዜ መቼት የሚባለውን "መቼ" እና "የት" የሚለውን የሥነ ጥበብ ሕግ ይጠቀሙታል፡፡ ይኸውም፤ መቼ የጥፋት አሳብ ማመንጨት፣ መቼ የጥፋት ግፊት መጨመር፣ መቼ የጥፋት ግብርን ማጽደቅ የሚል፤ ጊዜን ከውስጥ ወደ ውጪና ከውጪ ወደ ውስጥ የመጠበቅን ነገር ይጠነቀቁለታል፡፡ የት ብለው በሚጠብቁት የቦታ መምረጥ አሠራር ውስጥ ደግሞ፤ የት ስፍራ ላይ ጥፋቱን እንደሚመሩ፣ የት የውስጥ ተጽዕኖውን በጉልበት እንደሚፈጥሩ፣ የት የዓለማ ሥራቸውን እንደሚያስፈጽሙ ከውስጥ ሆነው ያቅዳሉ፡፡ ማለት ለምሳሌ፤ በመንፈሳዊ ጥንካሬና እውቀት ውስጥ ባለንበት ሰዓትና ቦታ ላይ መናፍስቱ የሌሉ ያህል ዝም ይላሉ፡፡ ከጊዜያት ቆይታ በኋላም ወደ ሥጋዊ አኗኗርና መንፈሳዊ ድክመት የምናዘነብልበት መቼና የት ሲመጣ፤ ከውስጥ ሆነው የመጣላት እቅዳቸውን ከውጪ በመጣው አጋጣሚ አስታክከው ለመፈጸም ይንቀሳቀሳሉ፡፡
ስለዚህ ሥጋውንና ደሙን ስንወስድ፤ እስከ ቀራኒዮ ተከትለነው በመስቀሉ አብረን ሞተን፥ በአዲሱ መቃብር አብረነው እንቀበራለን፡፡ ሆኖም መድኃኒቱ "ላንቀላፉት ሁሉ በኩራት ሆኖ በመነሣቱ" እኛም ውስጥ ተቀብሮ ያለውን፥ ሥጋውን ያስነሣዋል፡፡ ይሄ ከሞት የተነሣው የክርስቶስ ሥጋ ደግሞ፤ በባሕሪያቶቻችን መካከል ቆሞ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" የሚል ነው፡፡ ባሕሪያቶቻችንም "ምስለ መንፈስከ" ይሉታል፡፡ ከዛም ወደ ኖኅ መርከብ ለመግባት እጅ ለእጅ ይያያዛሉ፡፡ ሰልፋቸውንና ረድፋቸውን ጠብቀው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ "ክርስቶስ በኛ ነውና ማን ይቃወመናል" የሚለው የጳውሎስ ቃል በኛ ሕይወት ውስጥ ሥጋ ሆኖ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል ይገለጣል፡፡ እንወቅበት .. እንቁረብ!


ሀበነ ንኅበር በቀጣዩ ክፍሎች ይቀጥላል.. ከቤተሰባችን ጋራ፣ ከቤተክርስቲያን ጋራ፣ ከአገራችን ጋራ!

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባዖት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪
3•  ቅዱስ ቁርባን ክፍል - ፭          3.2•  ቅዱስ ቁርባን ለምን እንውሰድ ?                 3.2.1•  በእግዚአብሔር በኩል                          ✞ ሀበነ ንኅበር ✞      "ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ ከመ ብከ ንሕያው ዘለኩሉ ዓለም ወለዓለመ ዓለም፡፡"      "የአንተ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ…
3•  ቅዱስ ቁርባን

ክፍል - ፭ የቀጠለ..

            ✞ አንድ አድርገን ከራሳችን ጋር

   "ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።"

                                       (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፥18
)

ባሳለፍነው ክፍል፥ ከእግዚአብሔር ስንጣላ ከራሳችንም እንደተጣላን አውስተናል፡፡ በዚህ ውስጣዊና ውጪያዊ ጥል ዲያቢሎስ ተመክቶ፤ ከውስጥ ያለው የባሕሪያትን ቀውስ ተገን በማድረግ የሕይወት አካሄዳችን ከራሳችን ጋር እንዳይሆን ያደርጋል ስንልም ተነጋግረናል፡፡ አሁን ወደ መፍትሔው እንምጣ፥ አንድ ወደ ማድረጊያው!

አዳም ራሱንም ፍጥረታትንም ሲገዛ የነበረው ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዝቶ በቆየበት ጊዜያት ሳለ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አዳም ውሳጣዊና አፍአዊ ሰላም ከኃይል ጋር የነበረው ከእግዚአብሔር ጋር እያለ ነው፡፡

የሰው ልጅ ከአምላኩ ሲለይ ከራሱም ተለየ ካልን፥ ወደ ፈጣሪ ሲመለስ ወደራሱም ተመለሰ ማለት ይሆናል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶሰ ዳግማዊው አዳም ነው፡፡ ዳግም የተወለደው አዳም ማለት ነው፡፡ "ዳግም" ተወለደ ከተባለ፥ የነበረው በድጋሚ ተወልዷል እየተባለ ነው፡፡ በዘፍጥረት በእግዚአብሔር ፈቃድ ተጸንሶ በገነት ማኅፀንነት ያድግ የነበረውን የሰው ልጅ ባሕሪይ፥ ሳይለውጥ ሳይጨምርበትገንዘብ አድርጎት መሢሑ በሥጋ መጥቶአል፡፡

ነገሩን በስብዕና አንቀጽ ብቻ ስናየው፤ የመድኃኒቱ ሥጋ በዘፍጥረት የነበረውን የአዳምን ንጹሕና ቅዱስ ባሕሪይ ባሕሪዩ ካደረገ፤ ልክ እንደ መጀመሪያው የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ያልተለየ፥ ኃጢአትን የማያውቅ፥ የመለኮትን ጸጋና እውነት የተመላ ነው ማለት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሥጋ ላይ ተፈጥሮና ፍጥረታት አይጣሉም፡፡ ባሕሪያት ቀውስ ውስጥ አይገቡም፡፡ ከዚህም የተነሣ ክፉው መንፈስ እንክርዳዱን የሚዘራበት የጸብ አዝመራ አያገኝም፡፡

ይሄ ሥጋ፥ የሁላችን ሥጋ ይሆን ዘንድ፤ መድኃኒቱ ሥጋውን የሚበላ ደሙን የሚጠጣ አድርጎ በስሙ ለምናምነው ሁላችን ሰጥቶናል፡፡ ብቻም ሳይሆን፥ በእኛና በእርሱ መካከል ያለውን የዓመፃ ግድግዳ በመስቀል ላይ አፍርሶታል፡፡ በዚህም አማናዊ ኪዳን በኩል፥ ዐማኑኤል፥ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ሆነ የሚለው ቃልኪዳን በሥጋው መቆረስ በደሙ መፍሰስ ቤዛነት ታትሞልናል፡፡

ስለዚህ የክርስቶስን (የዳግማዊውን አዳም) ንጹሕ ሥጋና ቅዱስ ደም መውሰድ ስንጀምር፥ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እየሆንን እንመጣለን፡፡ ከእርሱ ጋር አንድ ስንሆን ከራሳችንም ጋር [እንደ ቀደማዊው አዳም] አንድ እንሆናለን፡፡ ከራሳችን ጋር አንድ ከሆንን፥ መጽሐፍ እንዳለ የሚቃወመን ኃይል (ዲያቢሎስ) ተቃውሞው አይሳካለትም፡፡ ጥቅሱን ላንብበው ፦

    "እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?"

                                               (ወደ ሮሜ ሰዎች 8፥31)


በእርግጥም እግዚአብሔር ካለ የሚቃወመን "የለም"፡፡ የለም ማለት ተቃዋሚው ወገን የለም ማለት ሳይሆን፤ ከእግዚአብሔር ጋር እስከሆንን ድረስ ተቃውሞ በራሱ ተቃውሞ ሆኖ ሊያሸንፈን አይቻለውም፡፡ በሌላ አባባል፥ ችግሩ አለ ነገር ግን አንቸገርም፤ እሳቱ ይነዳል ነገር ግን አንቃጠልም፤ በረዶ ውስጥ ነን ሆኖሞ ግን አንቀዘቅዝም፤ ወደታች እየጣሉን ነው ሆኖም ግን አንወድቅም፡፡ ስለዚህ ትክክል ነው ጥያቄው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ 'ማን' ይቃወመናል?

ወደ ርእሳችን ጽንሰ አሳብ ጥቅሱን ስናስገባው፤ ክርስቶስ በኛ ካለ፥ እርስ በእርስ የሚቀዋወሙ ውስጣዊ ባሕሪያት አይኖሩብንም፡፡ ምክንያቱም እርሱ "መልካሙ እረኛ" ነው፡፡ ሁሉን የፈጠረና ያለ እርሱም አንዳች የማይሆን የሌለ ነው፡፡ ስለዚህ .. በጎቹ በተኩላው እንዳይበሉ ይጠብቃል፤ አእዋፋቱ በነጻነት እንዲበሩ ይፈቅዳል፤ ውኃው እሳቱን እንዳያጠፋ ያስማማል፤ ነፋሱ አፈሩን እንዳይገለብጠው ያደርጋል፣ .. /የተፈጥሮና የፍጥረታት ባሕሪያት በኛ እንደተጻፉ ያስታውሷል/፡፡

እያልኩ ያለሁት፤ የክርስቶስ ሥጋና ደም ከእኛ ሥጋና ደም ጋር ሲዋሐድ፤ የውስጥ ጉስቁልና ውጤት ሆነው የመጡት የቀውስ ባሕሪያት፥ በሰላም አለቃው ድምፅ መሰማት ይሰክናሉ፡፡ በመሆኑ ጭንቀት፥ ጭንቀት ሆኖ አይቃወመንም፡፡ ፍርሃት፥ ፍርሃት ሆኖ አይረብሸንም፡፡ አሳቦቻችን እርስ በእርስ እየተጋጩ አያናውጡንም፡፡ ፍላጎቶቻችን እየተጣሉ ግራ አያጋቡንም፡፡ ጠባያቶቻችን እየተለዋወጡ አያዘባርቁንም፡፡ ፈቃዶቻችን እየተቃረኑ አያምታቱንም፡፡ ምክንያቱም በተወዳጁ ጌታ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡

ታዲያ ልብ እንበል! "ማነው የሚቃወመን?" ብለን በጠላታችን ፊት በእምነት ድፍረት ከመቆማችን በፊት፤ "እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ" የሚለው ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ትኩረት መስጠት እንደሚገባን ልብ እንበል፡፡ ሐዋሪያውም መልእክቱ ሲጽፍ ያስቀደመው "እግዚአብሔር ከኛ ቢሆን" የሚለውን ንባብ ነው፡፡
 
"እሺ እንዴት ነው እግዚአብሔር ከኛ ጋር የሚሆነው?" የሚለውን አስፈላጊ ጥያቄ ስናነሳ፤ ዮሐንስ መልስ አለኝ ይለናል፡፡ እንስማው ፦

     "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።"

                                                 (የዮሐንስ ወንጌል 6፥56)

ይሄ ነገር ድንቅ ነው! ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበል ምእመናን አለ ጌታ፥ "እርሱ በእኔ ይኖራል፥ እኔም ደግሞ በእርሱ እኖራለሁ" አለ፡፡ እውነትም ኢየሱስ ክርስቶስ ዐማኑኤል ነው፡፡ እኛ በእርሱ፥ እርሱም በእኛ እንዲኖር በማድረግ፤ ከእግዚአብሔርነቱ ጋር አንድ የሚያደርገን ዐማኑኤል!

ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ማለት ቅዱስ ክርስቶስን መቀበል ማለት ነው፡፡ "አምላክ ሰው ሆነ፥ ሰውም አምላክ ሆነ" የሚለውን ከቤተልሔም (ልደት) እስከ ቢታንያ (ዕርገት) ያለውን የሕይወት መንገድ (እውነት) የሰማን ሰዎች የምናምነው እንደዚህ ነው፡፡ በተዋሕዶ ዓለት ላይ ቆመን ነገሮቻችንን ሁሉ መልክና ቅርጽ የሰጠናቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዋሐድ ዘንድ ነው፡፡ ከአምላክ ጋር ተዋሕደን ደግሞ በዚህ ዓለም የምንመላለሰው ስሙን ብቻ በመጥራት ሳይሆን፤ በሚስጥረ መለኮት የሰጠን እርሱነቱን በሰውነታችን ውስጥ በማኖር ጭምር ነው፡፡

የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች፤ ከቅዱስ ቁርባን በተለያየ ሰበብ ርቀን እኛ በእርሱ፥ እርሱ በእኛ የምንኖርበት አንድነት ሲጠፋ፤ ወደ ነውጥና ወደ አለመረጋጋት ሄደን፥ እነርሱም እኛን ፈልገው ወደኛ መጡና ከችግሮች ጋር አንድ ሆነን ቁጭ አልን፡፡ ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበል ክርስቶስን የተዋሐደ ኑሮ ስሌለን፤ በአንጻሩ መከራዎችን ወደ ጊዜያችን ለማምጣት ያለ ዕረፍት የሚተጋው ክፉ መንፈስ በኛ ተዋሕዶ፥ እኛም የእርሱ ፈቃድና ዓለማ ተዋሕደን፤ ይኸውና መኖር በራሱ የሚቃወመን ፍጥረቶች ሆነን አለን፡፡

እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ስላልሆን፤ የሮሜው መልእክት በጀርባው ተጽፎ ሲነበብብን፤ በባሕሪያቸው የመቃወም ባሕሪይ የሌላቸው ወይንም እንዲቃወሙን የማንፈልጋቸው ነገራት እንኳ ይቃወሙናል፡፡ አሉ እኮ ስኬት የሚቃወማቸው፣ ደስታ የሚያጠፋቸው፣ ሰላም የሚረብሻቸው፣ ዕረፍት የሚበጠብጣቸው፣ ሐብት እንቅልፍ የሚነሳቸው፣ እውነት የሚያስጨንቃቸው ሰዎች፡፡ አየህ.. አምላክ ከኛ ካልሆነ የማይቃወመን ደግሞ የለም፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርገው የክርስቶስ ሥጋና ደም ስሌለን፤ የማይቃወሙትም የሚቃወሙትም ነገሮች ሁሉ ይቃወሙናል፡፡ ብዙዎቻችን በኑሮ ገመናችን ውስጥ ማጣትም ማግኘትም፣ መሳቅም ማልቀስም፣ መራብም መጥገብም፣ ብቸኝነትም ወዳጅነትም እየተቃወሙን ይገኛሉ፡፡ ወደግራም ብንሄድ የሚቃወመን አለ፤ ወደቀኙም አቅጣጫ ያው ተጻራሪው አለ፡፡ የውስጥ ማዕበሎቻችን በመድኃኒቱ ቃል ዝም እንዲሉ ስላልተገሠጹ፤ የሕይወት መርከባችን ከመናወጥ ማቆም አልቻለም፡፡

ቅዱስ ቁርባን የማይወስድ አማኝ፤ እግዚአብሔር በኔ ስላልሆነ ማን ይቃወመኛል ብሎ ከጠየቀ፤ ምላሽ አንድ "እራስህ" የሚል መልስ ማግኘት አለበት፡፡ አምላክ በኛ ከሌለ፥ እኛን የምንቃወመው እኛው እንሆናለን፡፡ ቅድም ያሰብነውን አሳብ አሁን የምንቃወም፣ ዛሬ ያቀድነውን በጎ እቅድ ነገ የምናፈረስ፣ ትናንት የተሰማን ፍላጎት አሁን የሚጣላን ሆኖ፤ ራሳችንን የምናስቸግረው ራሳችን ሆነን እናርፈዋለን፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ያልሆነ ሰውነት፤ ከውስጡ ያሉትን የባሕሪይ ተቋሞች ተቆጣጥሮ ከራሱ ጋር አንድ የሚሆንበት ክሂል ይለየዋል፡፡ የዚህ ክሂል አለመኖር ደግሞ ለክፉው መንፈስ ጉልበትና አቅም ስለሚሆን፤ በእግራችን ወደፊት እየተራመድን በአእምሮአችን ወደኋላ የምንጓዝ፣ በእጃችን ያነሳነውን በአሳባችን የምንጥል፣ በጭንቅላታችን የወደድነውን በተግባራችን የምንጠላ፣ በፍላጎታችን የቀረብነውን በጊዜያችን የምንሸሽ የተቃውሞ መጽሐፍ ሆነን፤ ኑሮአችን ሲታይ ትርምስ የሚነበብብን የውጥንቅጥ መገለጫዎች ለመሆን እንገደዳለን፡፡

ከቅዱስ ቁርባን የተለየን ክርስቲያኖች፥ በመጀመሪያ ከክርስቶስ ቀጥሎ ከራሳችን ጋር ተለያይተን፤ አንድ መሆን ማለት አንድ አካል መያዝ ብቻ መስሎን፥ ነገር ግን በአንድ አካላችን ውስጥ በተሰበጣጠሩ ማንነቶች እየተቀዣበርን፤ ፈለግ የሌለን ዱካ አልባ ሰዎች ሆነን ፍዝዝ ብለን ወደሞት ቀን እንራመዳለን፡፡ ኸረ እንዴት ነው ነገሩ? .. ሥርዓተ ቅዳሴያችን ሥጋውና ደሙን ቀድሶ ምእመናንን ከመቀደሱ በፊት "ሀበነ ንኅበር.. " ሲል በየዕለቱ ያውጃል፤ አንድ እንሆን ዘንድ ስጠን!

ሳይንሳዊና ተጨባጭ እውቀቶች የከፍታን ጫፍ በነኩበት በዚህ በልህቀት ዘመን፤ ብዙ ሰዎች ከራሳቸው ጋር አንድ መሆን ተስኗቸው የውዥንብር ወለል ላይ ቁጭ ብለዋል፡፡ የሚያማምሩ አልጋዎችን የሠራ ዘመናችን ሰላም ያለው እንቅልፍን ለትውልዶቹ መስጠት አላወቀበትም፡፡ የመዝናኛ አንዲስትሪዎች ቁጥር ቢበዛም የሰዎች የውስጥ ዋይታ እንዲሁ በዝቷል፡፡ የአንድ አድራጊው ክርስቶስ ሰማያዊ ቅኝት ለነፍስ ጆሮአችን ስለማይደመጥ፤ የሥጋን ድክመት ተገን ያደረገው የአንድነት ተቃዋሚው ዲያቢሎስ፥ የመለያየት ድምፆችን ከውስጥም ከውጪም በኩል እያሰማ ያለማቋረጥ ይበጠብጠናል፡፡

የአስታራቂው ሥጋ ሥጋችን እንዲሆን ከቅዱሱ ማዕድ ስላልተካፈልን፤ ስሜቶቻችንና አመለካከቶቻችን ሊታረቁልን አልቻሉም፡፡ በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለት ተቃዋሚ ጠባያትን ስናንጸባርቅ፤ "ሀበነ ንኅበር" እያልን ከሰማያዊው እንጀራ አልበላንም፡፡ ስለሆነም፤ ከሰማይ ስፍራ የተለየው ዲያቢሎስ ከሰማያዊ እውነቶች ለይቶን በምድር ወከባ ተከበን እንድንበላወስ ቢያስገድደን የሚያስገርም አይደለም፡፡

ሰዎች ከራሳቸው ጋር መስማማት ሲያቅታቸው፤ የሥነ ልቦና አማካሪዎችን፣ የሕክምና ባለሙያዎችን በማነጋገር ምድራዊ መፍትሔዎችን ለማግኘት ይታትራሉ፡፡ ነገር ግን አንድ የሚያደርገው መድኃኒት ከሰማይ የወረደ መሆኑን ዘንግተዋል፡፡ ስለዚህ ክኒኖችን ቢውጡም፣ መርፌዎችን ቢወጉም መደንዘዝን እንጂ መረጋጋትን አላገኙትም፡፡ ምክንያቱም አንድ አድራጊው እንዲህ ብሎን ነበር ፦

      "ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።"

                                                  (የዮሐንስ ወንጌል 14፥27)

አበው "እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም" የምትለዋን የጥቅስ ክፍል ሲተረጉሙ ፦

       "እኔ የምሰጠው ሰው እንደሚሰጠው ያለ አይደለም፡፡ ሰው ቢሰጥ ያንዱን ለአንዱ ኃላፊውን ነው እርሱ ግን የባሕሪዩን ነውና፡፡ አንድም ሰው የሚሰጠው ግዙፉን ነው እርሱ ግን ረቂቁን ነውና፡፡"

                                               (የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ
)

መድኃኒቱ ለባሕሪያችን የሚያሰማው ሰላም፤ አልኮን ጠጥተን፣ የአጋንንት ጢስ ታጥነን፣ ለስላሳ ሙዚቃ አድምጠን፣ የሚያስቅ መዝናኛ ተመልክተን እንደሚገኘው ሰላም ያለ አይደለም፡፡ የምንኖርባት ዓለም በሐሰት አምባ ላይ ቆማ የተመሠረተች ናት፡፡ (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፥15-16) ሐሰት ደግሞ በራሷ ሁለተኛ ናት፤ ቀዳሚ የሆነቺይቱን፥ እውነትን የምትከተል ሁለተኛ ናት፡፡

እንዲህ ካልን፤ ዓለም የሚሰጠን ሰላም ሐሰተኛውን ሰላም ነው ማለት ነው፡፡ ሰላምን የሚመስል ሰላም ብንለው ይቻላል፡፡ በእርግጥም ሲታይ ከዓለም የተቀበልናቸው ሰላሞች በሰላም ካባ ያጌጡ ረብሻዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅመን የምናመጣው ሰላም፤ በሌላ ጎኑ የሚረብሸው ጤና፣ ሥነልቦና፣ ኢኮኖሚ አለ፡፡

ሌላው ይሄ ዓለም ልስጣችሁ እያለ የሚያማልልበት ሰላም በውስጠኛው ሕይወት ላይ የሚያርፍ አይደለም፡፡ በመሆኑ አለመረጋጋትን የሚያሰክን ሳይሆን የሚያስረሳ ሰላም ነው፡፡ ወይንም ከልብ መዝገብ ላይ ሄዶ በማይፋቅ ጽሕፈት ስለማይታተም ዛሬም ነገም መደጋገም የሚፈልግ ጊዜያዊ ሰላም ነው፡፡ ማለት፤ ቅድም ያየኸው የሚያንከተክት ቀልድ ከሰዓታት በኋላ አያስቅህም፡፡ ትናንት የተጎነጨኸው ውስኪ ዛሬም ካልተቀዳ "ሰላሙን" አይሰጥህም፡፡

ከሰማይ ያለ የቃሉን ሕልውና በምድር ያለ ሥጋ ያደረገው ክርስቶስ የሚሰጠውን ሰላም አንዴ ካደመጥከው ግን፤ ደጋግመህ ስማኝ አይልህም፡፡ ይሄን ሰላም አንዴ ከሰማኸው፤ በምንም አይነት ጫጫታና ሁከት ምክንያትነት የማይበጠበጥ የዕረፍት ጸጥታ ይሰማሃል፡፡ ሰላም የሚባለው ነገር ደግሞ የሚመጣው የሚቃወሙ አካላት (ባሕሪያት በኛ ጽሑፍ) ተስማምተው ሲቀመጡ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሲሆኑ ነው፡፡ አንድነት የሰላም ጥብቅ ባልንጀራ ናት፡፡

ማስገንዘቢያ ይሆን ዘንድ የማስተላልፈው ጭብጥ አሳብ፥ ከራሳችን ጋር አንድ እሆን ዘንድ ከወደድን ከክርስቶስ ሥጋና ደም እንቀበል የሚል ነው፡፡ ራሳችንን ለማረጋጋትና አኗኗራችንን ለመሰብሰብ የምንሄድባቸው ዓለማዊ መፍትሔዎች እውነተኛውን አንድነት አይሰጡንም፥ አልሰጡንምም፡፡ የዚህ ማረጋገጫ ምስክር ራሳችን ነን፡፡ በሥጋ ዘዴዎችና ጥበቦች እናምጣው ያልነው የውስጥ አንድነት ከእንቅልፍ ክኒን የተሻለ ዘላቂ መፍትሔ አልሰጠንም፡፡

የእግዚአብሔርን በግ ሥጋ በልተን የምንሰማው ሰላም ግን ከዚህ ዓለም ሰላም ይለያል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የውስጥ ሕይወት መስፍን ነው፡፡ ከመስቀል ባሻገር ያለው፥ ከሞት የተነሣው ክርስቶስ በነፍስም በሥጋም ላይ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 28፥18) በትንሣኤ ያለው ክርስቶስ በርቅቀት ያለ ግዝፈት፥ በግዝፈትም ያለ ረቂቅ ነው፡፡ ስለዚህ በረቂቅነቱ የተዘጋ በርን አልፎ ይገባል፡፡ በኛም የተዘጋ ሥጋ ውስጥ አልፎ ለመግባት የፍቅሩ ፈቃድ ዛሬም ሳይቀዘቅዝ አለ፡፡
ባለፉት ክፍሎቻችን በተደጋጋሚ እንዳወሳነው፤ የክርስቶስን ሥጋና ደም ከምንወስድበት ብዙ ምክንያቶች መካከል አንድነትን የተመለከተው ርእስ ይጠቀሳል፡፡ የኛን ሥጋን ተዋሕዶ ከእኛ ጋር አንድ የሆነ የእግዚአብሔር የባሕሪይ ልጅ፤ እኛን የሆነበትን የእርሱን ሥጋ ተዋሕደን ከእርሱ ጋር በአንድነት የምንኖርበት መንክር ጥበብ በተቀደሰው ማዕድ በኩል አካፍሎናል፡፡

ቤተሰቦች በሥጋና በደም ተዋልደው መዛመዳቸው በፍቅርና በአንድነት ስለመኖራቸው ዋስትና አይሆንም፡፡ ለዚህ ማስረጃው ማንም ሳይሆን እኛና ኑሮአችን ነን፡፡ በመልክ የተመሳሰሉ ሰዎች በቅራኔ ጠባያት ተለያይተው ለጸብ የሚፈላለጉ ሲሆኑ ማየት የጊዜያችን አንዱ ልማድ ሆኗል፡፡ ወንድማማቾች ከአንድ ማኅፀን የተወለዱ ጠላቶች ሆነው እርስ በእርስ ሲበላሉ መስማት የማይገርም ጉዳይ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ዘመዳማቾች በርስትና በንብረት ምክንያት ተጣልተው ፍርድ ቤት ሲመላለሱ መመልከት ከጀመርን ምን ያህል ጊዜ አልፎ ይሁን?

በቤተሰብ ውስጥ መተሳሰብ ሲጠፋ፣ መተጋገዝ ሲቀንስ፣ መስማማት ሲርቅ፣ መከባበር ሲለይ ወደ ቅዱስ ቁርባን እንጠጋለን፡፡ "አቤቱ የቤት ሰላም አጣሁ፣ አንድነትም ሸሸን" እያልን በጌታ ሥጋና ደም በኩል እንማጸናለን፡፡ ከሕይወት እንጀራ እየበላን ስለ ሕይወት መፍትሔ እንዲሰጠን እንለምናለን፡፡ እርሱ ከዛ በኋላ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ከጓዳችን የራቀውን ፍቅር ይመልሰዋል፡፡ ከቤተሰባችን ውስጥ ቤተሰብ ሆኖ ክፋት የሚፈጽመውን ኃይል ዝም እንዲል ያዘዋል፡፡ አሁን፥ ቤትን ብቻ ሳይሆን መዋደድን፣ መቻቻልን፣ መደማመጥን፣ መጠባበቅን የምንጋራ በሥጋም በመንፈስም የተሳሰርን ሰዎች እንሆናለን፡፡

ሚስቶችም ባሎች አመል ሲለውጡ፣ ጠባይ ሲቀይሩ፣ መዋሸት ሲያበዙ፣ መደበቅ ሲያመጡ፣ መረበሽ ሲጀምሩ እጃቸውን በመቅደሱ መሥዋዕት በኩል ይዘረጋሉ፡፡ ትዳራቸውን ይታደግ ዘንድ የአምላክን እርዳታ ይጠይቃሉ፡፡ እግዚአብሔርም ጩኸታቸውን ይሰማል፡፡

ዛሬ ይሄ መንፈሳዊ ኃይልና ብልሃት ከግንዛቤ ዝርዝራችን ጠፍቶ፤ የቤተሰባችንን ችግር ለማቅለል ስንል የምንወስነው ውሳኔ በራሱ ባለ ችግር ሆኖ፤ ለሰላም ያወራነው ጸብ፣ ለአንድነት ያቀድነው መለያየት እየፈጠረ ግራ ያጋባናል፡፡ አለ እግዚአብሔር መንፈስ የምንከተለው መፍትሔ፥ መፍትሔ መሆን ስለማይችል፤ ትሕትና ስናሳይ ንቀት፣ ዝምታ ስንመርጥ ጥፋት፣ እሺ ስናበዛ ስሕተት ምላሽ ሆኖ እየተገለጠ በቁዘማና በብስጭት የምንኖር ብሶተኞች አድርጎናል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው ሲያስቸግሩአቸው፣ ምክር አሻፈረኝ ሲሉአቸው ወደ ጭቅጭቅና ቁጣ እንጂ ወደ እግዚአብሔር ኃይል አይሄዱም፡፡ ወጣቶችም ውስጣቸውን ባልተረዱበት መንፈሳዊ ስቃይ እየባተቱ፤ ከሥነ ምግባርና ግብረ ገብ ዕሴቶች በመሸሽ ስሜታዊነትን ያስቀደመ አስተሳሰብ እየተከተሉ ከቤተሰቦቻቸው ሀሳብና ፈቃድ ርቀው ይጓዛሉ፡፡ አባትና ልጅ፣ እናት ልጅ በሥጋና በደም ተካፈሉ እንጂ ከክርስቶስ ሥጋና ደም በአንድነት ስላልተካፈሉ፤ የኑሮና የጊዜ ክስተት በሚያመጧቸው ውጣ ውረዶች ምክንያትነት ተከፋፍለው ይነካከሳሉ፡፡ በአካል ተመሳስለው በሕይወት ተለያይተው ይኖራሉ፡፡

ብቻም ሳይሆን፥ ከክርስቶስ ጋር አንድ ሳይሆን በአንድ ቤት የሚኖር ቤተሰብ ወጥ የሆነ የወገናዊነት መተሳሰብ ያለበት ማኅበረሰብን፤ ከፍ ሲል አገርን ሊያስገኝ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር በሌለበት የተሰበሰቡ ሰዎች ሰይጣን ባለበት መለያየት ይበታተኑ ዘንድ ግድ ነውና፡፡ እሺ ምን ይሻላል? ሀበነ ንኀበር ይሻላል.. አንድ እንሆን ዘንድ ከሥጋና ደምህ ስጠን!

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን...
#ጸባዖት_ይከተላችሁ
@bemaledanek
​​#ሕዳር_ሚካኤል !

#እንኳን_ለመላእክት_አለቃ_ለቅዱስ_ሚካኤል #በዓለ_ሲመት_በሠላም_አደረሰን !

በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል (ሕዳር 12)
(አንብባችሁ ስትጨርሱ ለሌሎችም ታሪኩን እንዲያዉቁ #SHARE_SHARE_SHARE
ብታደርጉ ብዙ አተረፋችሁ፡፡)

ቤተ ክርስቲያን ልጆቹዋ የመላእክትን ተራዳኢነት አውቀው እንዲጠቀሙና የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን እንዲበቁ ስትል ለቅዱሳን መላእክት የመታሰቢያ ቀን በመስጠት በእነርሱ የምናገኛቸውን እርዳታዎች እንዲታወሱ ታደርጋለች፡፡

በዚህም መሠረት በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው፡፡

እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል። ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2 እንደሆነ አክሲማሮስ በተሰኘው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት
አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” (ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው፣ በጸሎትም ይራዳቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት” (ዘጸ.23፡21) ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር፡፡

ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለ “መልአክ” የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡- ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ስለመሾሙ ሲመሰክር “በእውነት በመጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም
የለም”(ዳን.10፡21) ብሎአል፡፡

ስለዚህም ለኢያሱ የተገለጠውና እስራኤላውያንንም የመራው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን እንረዳለን፡፡

የቅዱስ ሚካኤል ረድኤት እና በረከት በሁላችን ላይ ይደር
#ጾመ_ነቢያት_ (#የገና_ጾም_)
የ2015 ዓ.ም. የገና (የነቢያት) ጾም፤
#ጾሙ_ኅዳር_15_ይጀምራል_!!
#Share

፠ ከ7ቱ አጽዋማት (ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ፍልሠታ፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ድኅነት፣ ጾመ ነነዌ ና ጾመ ገሃድ) መካከል አንዱ ነው፡፡
፠ ኅዳር 15 ቀን ተጀምሮ እስከ ልደት ዋዜማ ለአርባ ሦስት ቀናት የሚጾም ጾም ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ፤ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ፤ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ፤ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፤ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ፤ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል፤ ትንቢቱ ደርሶ፣ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡
፠ ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡
እነርሱም፤
† ፩. #ጾመ_አዳም_፤ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገት ከተባረረ በኋላ; በፈጸመው በደል አዝኖ ፥ ተክዞ፤ አለቀሰ (እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ) ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በደጅህ ድኼ፣ በዕፀ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡›› የሚል ነው፡፡ /ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ/ ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት ‹‹ጾመ አዳም›› ይባላል፡፡

† ፪. #ጾመ_ነቢያት_፤ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች: ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም: ቅዱስ ሙሴ: ቅዱስ ኤልያስ፣ ቅዱስ ዳንኤል ና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: (ዘዳ 9:19, ነገ. 19:8, ዳን. 9:3፣ መዝ. 68:10, 108:24) ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል::

† ፫. #ጾመ_ሐዋርያት_፤ ሐዋርያት ‹‹ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?›› ብለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡
† ፬. #ጾመ_ማርያም_፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ‹‹ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?›› ብላ ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና ‹‹ጾመ ማርያም›› ይባላል፡፡

† ፭. #ጾመ_ፊልጶስ_፤ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ እያስተማረ ሳለ በሰማዕትነት ሲሞት፤ አስክሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ፤ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስክሬን እንዲገለጽላቸው ከኅዳር ፲፮ ጀምረው ጾመው በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስክሬን ተመልሶላቸዋል፤ ነገር ግን አስከሬኑ ቢመለስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡

† ፮. #ጾመ_ስብከት_፤ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡

† ፯. #ጾመ_ልደት_፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት ስለሆነ ‹‹ጾመ ልደት›› ይባላል፡፡

   ጾምን ትእዛዝ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንጾመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል፡፡
ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡


ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE

💚  •✥@bemaledanek •✥•💚
💛  •✥@bemaledanek •✥•💛
💖 •✥•@bemaledanek •✥• 💖
2024/06/29 00:32:47
Back to Top
HTML Embed Code: