tgoop.com/biryalew/835
Last Update:
#ዓድዋ_የምኒልክ_እጅ_ሥራ !!!
በIsho Bir
…ምኒልክን ልትጠላው ትችላለህ፤ ደግሞም ልትወደው ትችላለህ። ነገር ግን ምኒልክ ተራ ስብዕና እንዳልነበረ ለመረዳት አይከብድም።
… ምኒልክ ውስብስብ ሰው ነው። ረቂቅ ነው። ደግሞ አድማጭ ነው።
… ምኒልክ እንደ ገሞራ እሳት የሚፋጅ ነው። ደግሞ እንደ ምንጭ ውኃ ገር ነው። ሚኒልክ ሀገር መመስረት፣ ግዛት ማስተዳደር ያውቃል። ተራ የታሪክ ሰው አይደለም። ጉልህ ነው።
… የምኒልክን ነገር ለማጉላት ብዬ ከሌሎች ማወዳደር አልፈልግም። ዳግሞም ማሳነስ ሊሆን ይችላል።
… ውጫሌ ውል የዓድዋ ጦርነት መነሻ ነው ይላሉ። ፈፅሞ ስህተት ነው። የዓድዋ ጦርነት መነሻ የበርሊኑ የቅኝ ገዢዎች ውል ነው።
… አውሮጳ አፍሪካን ለመቀራመት የተስማማው በበርሊን ስምምነት ነው። ያን ለማስፈፀም አውሮጳውያን በውድም፣ በውልም፣ በግድም አድርገውታል። በውል ወደ ቅኝ ግዛት የገቡ ብዙ ናቸው።
… ጣሊያን ለምኒልክ የውጫሌን ውል ስታቀርብለት፣ ምኒልክ ሳይገባው ቀርቶ፣ ተሸውዶ፣ ወይ ገር ሆኖ ነው ማለት ደካማ የታሪክ ተማሪ ከመሆን የሚመጣ ነው።
…የውጫሌ ውል የተፈረመው አፄ ዮሐንስ በሞቱ በ 10 ቀናት ውስጥ ነው። የዓድዋ ጦርነት የተካሄደው ደግሞ አፄ ዮሐንስ ከሞቱ ከ 7 ዓመት በኋላ ነው።
… ምኒልክ የውጫሌን ውል በመፈረም የራሱን ጉልበት እስኪያጠናክር ግዜ መግዣ ነው ያደረገው። ሚኒልክ ከፍ ለማለት ዝቅ ማለትን ያውቃል።
… እንደ ጣይቱ የሚፋጅ እሳት፣ እንደ ልብ ወዳጁ ራስ መኮንን የረጋ ውኃ ብቻ ቢሆን፣ ሀገርም አይሠራም፣ መንግሥቱንም አያፀናም ነበር።
… ውጫሌ በተፈረመበት ወቅት ምኒልክ፣ ብዙ ጠላቶች ነበሩት። ተጨማሪ ጠላት ጣሊያንን ማድረግ ስላልወደደ የፈረመው ነው።
… የውጫሌ ውል ኖረ አልኖረ ጣሊያን እንደሁ ኢትዮጵያን መውረሯ እንደማይቀር የሚታወቀውማ፣ የትግራይና የኤርትራን መኳንንት ጥሩ አድርጋ ስትክድ በማየት ነው። ምኒልክ ግን ጦርነቱን ቢያንስ እሱ በመረጠው ግዜ እንዲሆን ማድረግ ችሏል።
… ሚኒልክ ሁሉን ያዳምጣል። በቅንም ይረዳል። ዓላማውን አይስትም። ብልሃተኛም ነው።
… የአምባላጄ ጦርነት፣ የመቀሌ ከበባን በአሸናፊነት ሲያልፍ፣ በምኒልክ ውሳኔ የሚቆጡ ብዙ ነበሩ። ጣሊያኖችን ቢማርክም መልሶ እንደውም ከመጋዣ (ፈረስና በቅሎ ) ጋር ላካቸው እያሉ የሚወቅሱት ነበሩ። ምኒልክ ግን ጦርነት የሚገጥምበትን ቦታ እየመረጠ ነበር። የሱ መኳንንት የሚያውቁትን ምኒልክ ጠፍቶት አይደለም። ከባድ ስትራቴጂስት ስለነበረ ነው።
… ምኒልክ ያሰለፈውን ኃይል ያውቀዋል። ከቴድሮስ እስከ ራስ ውቤ፣ ወርቂትና ተዋበች፣ እስከ ዮሐንስና ጎበና የነበሩ ጦርነቶችን፣ በአይኑ ያየና የሰለጠ ንጉሥ እና ብልህ ጦርነት አዋቂ ነው።
… የቻይናው ታዋቂ የጦር ጀነራል - ሱን ሱ " ኃይል እንዳለህ ስታዉቅ፣ ደካማ ምሰል" ያለውን ምኒልክ ፈፅሞታል።
… ጣሊያን ዓድዋ ላይ የዘላለም ውርደት እስክትከናነብ በዚህ የሚኒልክ ብልጠት ተሸውዳለች። ምኒልክም ዓድዋ እስኪደርስ ድረስ የሚፋጅ ነብር መሆኑን ደብቆ ቆይቷል።
… አምስት ወር የተደረገ ጉዞ፣ የስምንት ሰዓት አጭር ጦርነት የሆነው፣ በዚህች አስደናቂ የምኒልክ ብልሃት ነው።
… ምኒልክ ያደረጋቸው ነገሮች፣ የፈፀማቸው ታሪኮች፣ የሰበሰባቸው ሸንጎዎች፣ የወሰናቸው ውሳኔዎች በእርግጠኝነት የምኒልክን ልህቀት የሚያገኑ ናቸው።
… ዓድዋ - በምኒልክ ተመርጦ፣ በምኒልክ ታቅዶ፣ በምኒልክ ተመርቶ፣ የተፈፀመ ጀብዱ ነው።
… ለዚያም ነው ምኒልክ የሀገር መሪ ብቻ ሳይሆን ሀገር መሥራች ነው የሚባለው።
… ከዚህ መለስ ስላለው የታሪክ ፋይዳ፣ ውጤት፣ ጥቅምና ጉዳት እንነጋገር እንጂ ሁነቱ ዳግም ላይመለስ፣ በምኒልክ ተፈፅሟል ።
***
ይገርምሃል ሸዋ !!!
💚💛❤️
#ዓድዋ_125
#የኢትዮጵያውያን_ድል
#የጥቁር_ህዝብ_ኩራት
#ኢትዮጵያ
@biryalew
@biryalew
BY ✍✍✍ብዕር ያለው ያውጋ/bir yalew yawga✍✍✍
Share with your friend now:
tgoop.com/biryalew/835