tgoop.com/deacongetabalewamare/1836
Last Update:
“ነቢይ ዘከመ እሳት ⇨ እሳታዊ ነቢይ”
✥ °°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°° ✥
"ወተንስአ ኤልያስ ነቢይ ዘከመ እሳት ወቃሉኒ ከመ ነድ ያውኢ ⇨ እሳታዊው ነቢይ ኤልያስ ተነሣ ቃሉም እንደ እሳት ያቃጥል ነበር" 【ሲራ. ፵፰፥፩】
መነሻችን የሚሆነው ጥያቄ ነው?
☞ [መኑ ውእቱ] ዘዐርገ በነደ እሳት በሰረገላት ወበአፍራስ ዘእሳት ?
በእሳት ሰረገላና በእሳት ፈረስ ወደሰማይ የወጣ ማነው?
ይህን ጥያቄ የሚያነሳው ሲራክ ብለን የምንጠራው ኢያሱ ወልደ ሲራክ ወይም ኢያሱ ወልደ አልዓዛር በመጽሐፉ ፵፰ኛ ምዕራፍ ቁጥር ፱ ላይ ነው።
በመጽሐፈ ሲራክ መቅድም ሊቃውንቱ ይኽን ነግረውናል
ሲራክ፦ ፀሐፊ ማለት ነው፤ ፀሐፊው ኢያሱ ወልደ አልዓዛር ወልደ ሲራክ ይባላል።
፶፩ ምዕራፎች ፦ በአቀራረቡ ከሰሎሞን መጽሐፈ ምሳሌ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ይዘት ፦ ለመንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወታችን ጥበብና ምክር የሚሰጥ ነው።
ሲራክ ስለእሳታዊ ነቢይ ይጠይቃል፤
ማነው? በእሳት ተጠቅልሎ የተወለደ ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሦስት ጊዜ ከሰማይ እሳት ያወረደ ፣ በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረስ ተጭኖ ወደሰማይ የነጎደ ማነው?
በዘይቤ መንፈሳዊ ትምህርትነትና ምክር በስፋት የያዘው ይኽ መጽሐፈ ሲራክ የእሳትን አስተማሪ ምሳሌነ አጉልቶ በብዙ መንገድ ይነግረናል ለአብነት
☞ ወርቅን ወርቅ ለመሆኑ የሚፈትኑት በእሳት እንደሆነው ሁሉ ጻድቅም ችግር በሚያመጣ መከራ ተፈትኖ የሚያልፍ ነው 【፪፥፭】
☞ የሚነድ’ እሳት የሚጠፋው በውኃ እንደሆነው ኃጢዓት የሚሰረየው በምጽዋት ነው 【፫፥፳፰】
☞ ከተናጋሪ ሰው ጋር መከራከር በእሳት ላይ እንጨት እንደመከመር ነው 【፰፥፫】
☞ መልከ መልካምና ደምግባት ያላት ሴት ፍቅር የሚነድ’ እሳት ነው 【፱፥፰】
☞ በነጻ ፈቃድ እንዲመርጥ ለሰው እግዚአብሔር ያቀረበው የጽድቅና የኃጢዓት መንገድ እንደ እሳትና ውኃ ነው 【፲፭፥፲፮】
☞ ሰው በልቡ ሐሳብ መፈተኑ ሸክላ በእሳት እንደሚፈተነው ነው 【፳፯፥፭】
☞ የእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣው እሳት ነው 【፳፰፥፳፪】…
እሳት በጠባዩ ይቡስ (ደረቅ) ፣ ውዑይ (የሚያቃጥል) እና ብሩህ (የሚበራ) ነው። በፍጥረትነቱም ከዐራቱ አሥራው ፍጥረታትና ባሕርያት አንዱ ሆኖ በሁሉ የሚገኝ በይብስቱ ከነፋስ በውዕየቱ ከመሬት በብርሃኑ ከውሃ የሚስማማ ፍጥረት ነው።
ሲራክ ምዕራፉን የሚጀምረው የነቢዩን ማንነት እንዲህ ሲል ነግሮን ነው! "ወተንስአ ኤልያስ ነቢይ ዘከመ እሳት ወቃሉኒ ከመ ነድ ያውኢ ⇨ እሳታዊው ነቢይ ኤልያስ ተነሣ ቃሉም እንደ እሳት ያቃጥል ነበር" 【ሲራ. ፵፰፥፩】
አልያስ ማለት ቀናዒ
መደንግጸ አብዳን፡ ሕገ መነኮሳት ሠራዒ
ኤልያስ ማለት ድንግል
ብእሴ ሰላም ፡ መምህረ እስራኤል
ኤልያስ ማለት ቅብዓ ፍሥሐ
ለቤተክርስቲያን ፡ አንቀጸ ጽርሐ
ኤልያስ ማለት ካህነ ኦሪት
ምዑዘ ምግባር ፡ መዝገበ ሃይማኖት
ኤልያስ ማለት ጸዋሚ
ለእግዚአብሔር ቊልኤሁ ፡ ዝጉሐዊ ተሐራሚ
ኤልያስ ማለት…
ኤልያስ ቴስብያዊ ፣ ኤልያስ ቀርሜሎሳዊ ፣ ኤልያስ ታቦራዊ ፣ ኤልያስ ዘሰራጵታ፣ ኤልያስ ነቢየ ፋፃ … በኩረ ሐዋርያት ፣ ቢጸ ነቢያት ፣ ነቢየ ክርስቶስ ፣ ነቢየ ልዑል ባለብዙ ግብር ባለብዙ ስም …
የዚኽ እሳታዊ ነቢይ ስሙ እንዲህ የበዛው ሥራው ስለበዛ ነው "በአምጣነ ዕፁ ለእሳት የዐቢ ነዱ ⇨ በእንጨቱ ብዛት የእሳቱ ነዲዱ ይበዛል" እንዲል【ሲራ. ፳፰፥፲】
ወሬዛ በኃይሉ አረጋዊ በመዋዕሉ ተብሎ የተገለጠ ጸሐፌ ትዕዛዝ ቅዱስ ኤልያስ ጥር ፮ በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረስ ተጭኖ ወደሰማይ ያረገበት ቀን ፣ ታኅሳስ ፩ በአክአብ ፊት በኃይል ለዘለፋ የተገለጠበት(የናቡቴ ዕረፍት) ፣ «ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ልደቱ» ነው፤ በእነዚኽ ቀናት ልንዘክረውና ልናከብረው ይገባል!
እንኳን እሳት ያወረደውን ቀርቶ የወረደውን እሳት ማክበር ተገቢ ነው ፤ አበው እንዴት መያዝ እንደሚገባው ሲነግሩን «እሳትን በገል ውሃን በቅል» ብለዋል።
ሙሴ አንደበቱ ትብ የሆነው እሳት በልቶ ፣ መጻጉዕ እጁ የተኮማተረው እሳት ጸፍቶ መሆኑን እናውቃለን።
ሊቁ እንዲህ ተቀኝቷል
"መጻጉዕ ሕፃን ኢያእመረ ነፍሰ ዓዲ
አኮኑ ፈነወ እዴሁ መንገለ እሳት ነዳዲ
【 መጻጉዕ ሕጻን ነው ነፍስ ማወቅ መች ጀመረ ?
ቢበስልማ ኖሮ ወደሚነደው እሳት እጁን ባልጨመረ 】
ኤልያስ ማለት በእብራይስጡ (ኤል אֵל) እና (ያስ/ ያህ יָהּ)ከሚሉ ሁለት የፈጣሪያችን ስሞች የተገኘ ጥምረት ሆኖ "እግዚአብሔር ጌታዬ ነው" የሚለውን ፍቺ ይሠጣል። በቅዱሱ መጽሐፍም ከታላቁ ነቢይ ውጪ ሌሎች ሁለት እስራኤላውያን በዚህ የከበረ ታላቅ ስም ተጠርተዋል።
በግሪኩ ደግሞ ኤሊያ ἐλαία (አላህያህ) ማለት ወይራ ማለት ነው። ይህን ያዞ ጌታችን የወይራ ዛፍ በበዛበት ተራራ በደብረ ዘይት ሲጸልይበት የነበረውን ዋሻ የኤልዮን ዋሻ እያለ ይጠራዋል
“ወመዐልትሰ ይሜህር በምኵራብ ወሌሊተ ይወፅእ ወይበይት ውስተ ደብር ዘስሙ ኤሌዎን ⇛ዕለት ዕለትም በመቅደስ (በምኩራብ) ያስተምር ነበር፥ ሌሊት ግን [ኤሌዎን በሚባል] ደብረ ዘይት ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር ” 【ሉቃስ ፳፩፥፴፯】
መጽሐፍም ኤልያስ ማለት ወይራ ማለት ነው የሚለውን ልሳነ ጽርእ ይዞ የወይራን ተክል ፍሬና ዘይትን ኤልያስ እያለ ይገልጣል (The tree , the fruit or the oil ☞ ዕፀ ዘይት ፣ ፍሬ ዘይት ፣ ቅብዐ ዘይት)
【ኩፋ ፲፯፥፲】 "ወነሥአቶ እሙ ወሐራዊ ወገደፈቶ ታሕተ አሐቲ ኤልያስ ወሖረት ወነበረት አንጻሮ መጠነ አሐቲ ምንጻፍ እስመ ትቤ ኢይርአይ ሞት ለሕጻንየ ወነቢራ በከየት ⇨እናቱ አነሳችውና ሔዳ በአንዲት የወይራ/ዘይት እንጨት ሥር አኖረችው የልጁን ሞት አላይም ብላለችና በዚያ ተቀምጣ አለቀሰች" (13፥31)
【ሔኖ ፫፥፳፬】 "ወአሕቲ መስፈርተ ኤልያስ ትገብር ዐሠርተ ምክያደ ዘይት ⇨አንዲቱም መስፈሪያ ዘይት አስር የዘይት አውድማንበትመላለች "
የእኛ ሊቃውንት ስሙን በዘይቤና በምሥጢር እያራቀቁ «ዕፀ ዘይት ማኅቶት በቅድመ እግዚአብሔር ፣ ሥዩም ላዕለ ምድር ወሥሉጥ ላዕለ ሰማይ ወላዕለ ማይ » በማለት ገልጠውልናል። በ«መልኩ» መነሻ ላይም
ሰላም ለትርጓሜ ስምከ ዘተብህለ ዘይተ
… በጸውኦ ስምከ ኤልሳዕ ዮርዳኖስ አዕተተ" ይላል
የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ ቃልም ለእርሱ መነገሩን በምሥጢር አስማምተው ይተረጉማሉ።
"ዕፀ ዘይት ወመኃትው በቅድመ እግዚአብሔር "【ራዕ ፲፩፥፬】
አቡቀለምሲስ በዚህ የራእዩ ክፍል በአምላካቸው ፊት ወይራና መቅረዝ እያለ አክብሮ የጠራው ሔኖክና ኤልያስን ነው።
✧ ወክልኤ ዕፀ ዘይት እለ ቅድመ እግዚአብሔር
(በእግዚአብሔር ፊት ያሉ የእግዚአብሔር ባለሟሎች የሚሆኑ ሁለቱ የወይራ ዛፎች) መባላቸው
☞ ሄኖክ ማለት ተሐድሶ(አዲስ መሆን) ማለት ነው።
ተሐድሶ በዘይት ነውና
☞ ኤልያስም ማለት ከላይ እንዳየነው ዘይት ማለት ነው።
ወክልኤ መኃትው እለ ቅድመ እግዚአብሔር
(በእግዚአብሔር ፊት ያሉ የእግዚአብሔር ባለሟሎች የሚሆኑ ሁለቱ መብራቶች) መባላቸው
☞ በትምህርታቸው የሰውን ልቡና ብሩህ ያደርጋሉና
ነገረ ዘይት/ ወይራ ዛፍ (About Olive Tree)
ከዕለተ ሠሉስ ዕፀው መካከል ዕፀ ዘይት (የወይራ ዛፍ) አንዱ ነው! ቅባት የሚሰጥ ለመብልነት ለመብራትም የሚውል የወይራ ወገን ነው::
BY Dn Getabalew Amare Kibret /ሰዐሊ/
Share with your friend now:
tgoop.com/deacongetabalewamare/1836