tgoop.com/eotcy/2208
Last Update:
+++ የአንድ ኃጢአተኛ ሰው ጸሎት ++
አቤቱ “በጎውን ነገር ማን ያሳየናል?” የምንልበት ዘመን አይደለም፤ እንኳን በእኛ ዘንድ ይቅርና ወንጌል በአሕዛብ ዘንድ ሳይቀር የተሰበከበት ዘመን ነውና። ነገር ግን የተሰበከውን ቃል በልቤ አኑሬ ሕይወቴን ሳልለውጥበት ብዙ ዘመናትና ዓመታት አለፉ። ቃልህን ሰምቶ አለማድረግ በአንተ መዘባበት መሆኑን አውቃለሁ፤ ቃልህን የምሰማ እንጅ የምፈጽም ባለመሆኔም ምክንያት በድቡሽት ላይ እንደተሠራ ቤት ሆኛለሁ።
ጥልቀት በሌለው አኗኗር ላይ የተገነባው መንፈሳዊነቴ ጎርፍ በጎረፈ፣ ነፋስ ባለፈ ጊዜ የሚናወጥ ደካማ ሆኖብኛል።
ዓለምን ለማሳለፍ ዳግመኛ መምጣትህን ባሰብሁ ጊዜ እደነግጣለሁ።
ጻድቃን “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና” እያሉ የምትመጣበትን ቀን ሙሽራዋን እንደምትጠብቅ ሴት በተስፋ ይጠባበቃሉ፤ እኔ ግን አሁንም ለንስሐ ዕድሜ እንድትጨምርልኝ እለምናለሁ።
በተራራው ስብከት ጊዜ ተገኝቼ ስታስተምር ባልሰማህም፤ በደብረ ታቦር በተገለጥህ ጊዜ ክብርህን ካዩት መካከል ባልሆንም፤ በደብረ ዘይት እጅህን ጭነህ ከሾምኻቸው ውስጥ ባልመደብም አንተ ግን ለእኔ ምሕረት ማድረግን አትሰለችም። ወደ አንተ ባልመጣ እንኳን በተኛሁበት መጥተህ “ልትድን ትወዳለህ?” ማለትህ አይቀርም።
ከሰማይ የወረድህልኝ ሆይ! ኢያሱ ለእስራኤል ርስታቸውን እስኪያወርሳቸው ፀሐይን እንዳቆምህለት በምድር ላይ ያለን ኃጥአን ልጆችህ ሰማያዊት ርስትህን ሳንወርሳት ፀሐይ አትጥለቅብን፤ ዕድሜአችን አይለቅብን። አሜን!
( ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ )
꧁ ይ🀄 ላ 🀄ሉ ꧂
https://www.tgoop.com/eotcy
BY ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች

Share with your friend now:
tgoop.com/eotcy/2208