tgoop.com/eotcy/2234
Last Update:
[ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች ]
የብርሃን እናት ዛሬ ተወለደች
"ሐና አንቺን ያፈራችባት
ኢያቄምም አንቺን ለሕይወት ያፈራባት
የደስታ ሰዓት ምንኛ የተባረከች የተቀደሰች ናት
የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት አንቺ ነሽና
አንዲት ርግቤ ሆይ ተአምርሽን አመሰግናለው "
ማኅሌተ ጽጌ
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት ቀን ለክርስቲያኖች ሁሉ የደስታ ዕለት ናት ቅዱስ ያሬድ " ከኢያቄምና ከሐና ስለተወለደች ስለማርያም ልደት ዛሬ ደስታ ሆነ የብርሃን እናት በእውነት ተወለደች" እንዳለ ይህ ቀን የደስታችን ቀን ነው ለምን ቢሉ የመመኪያችን ዘውድ የንጽሕናችን መሠረት ድንግል ማርያም የተወለደችበት ዕለት ነውና፣ የነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ የዓለም ብርሃን የተባለ መድኃን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን የምትወልድን የብርሃን እናቱ ድንግል ማርያም የተወለደችበት ዕለት ነውና ነው ፡፡
የእመቤታችን ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ በድንገት የሆነ አይደለም አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረለት በአበው ሕይወት ውስጥ ምሳሌ የተመሰለለት ነው ለአብነትም
~ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት " መሠረቷቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው "መዝ 86፡-1 ብሎ በዝማሬው የተቀኘው ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች ንጽህና ነው የተቀደሱ ተራሮች ያለውም የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥትና ከቤተ ክህነት ከሆኑት ከተቀደሱት ከኢያቄምና ከሐና የመሆኑን ነገር ሲያመለክት ነው፡፡ ይህንን ትንቢትና እውነተኛውን የእመቤታችንን የትውልድ ሀረግ አስማምታ ቤተክርስቲያን ‹‹የእመቤታችን ማርያም ትውልዷ በአባቷ በኩል ከንጉሡ ከዳዊት ወገን ነው፤ በእናቷም በኩል ከካህኑ ከአሮን ወገን ነው፤ የአባቷ ስም ኢያቄም ነው፤ የእናቷም ስም ሐና ነው፡፡›› ብላ ታስተምራለች፡፡
~ ጠቢቡ ሰሎሞንም "ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ" መኃ 4፡8 ብሎ ሙሽራ የምትባል ድንግል ማርየም የት እንደምትወለድ ጭምር አስቀድሞ በትንቢት ነግሮናል
@eotcy
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት መሰረት የእመቤታችን የትውልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለው ተራራማ ሀገር ነው፡፡ የዚህ ትንቢት ምስጢርም የእመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን ያስረዳሉ ትንቢቱም ሲፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች
~ እናት እና አባቷ እርሷን ከመውለዳቸው በፊት በተቀደሰ ትዳር እየኖሩ ልጅ አጥተው እግዚአብሔርን ደጅ በመጥናት የሚኖሩ ቅዱሳን ነበሩ እግዚአብሔር ከልጅ ሁሉ በላይ የሆነች አምላክን የምትወልድ ልጅን ሰጣቸው ስሟንም ማርያም ብለው ጠርተዋታል ጸጋ ወ ሐብት ማለት አስቀድማ ጸጋ /ስጦታ፣ ሐብት /በረከት ሆና ለእናት እና አባቷ ተሰጥታለች በፍጻሜ ግን መድኃኒት የተባለ ክርስቶስን ወልዳለች እና ለሰው ሁሉ ስጦታ ናት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳያስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር እንዳለ ጠፍተን እንዳንቀር ምክንያተ ድኂን የሆነችን ድንግል ማርያም ስጦታችን ናት ፡፡
ቅዱስ እንድርያስ የከበረ ስለሆነው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ታላቅነት ‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ ምሳሌዎቹ በእዉነታ፣ አሮጌው በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል፤ የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ ይህ ዕለት (ጌታ) መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነው፡፡” በማለት ገልጾታል፡፡ የእርሷ ልደት የልዑል ማደሪያው መቅደስ የተሰራበት ዕለት ነውና ሁላችን እናከብረዋለን፡፡ በዚህም ዕለት ‹‹ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም/ እነሆ ዛሬ በእመቤታችን ልደት ደስታ ሆነ›› እያልን እንዘምራለን
" ኢያቄምና ሐና በጸለዩ በአለቀሱ ጊዜ
ለሁላችን ምእመናን መጠጊያ የምትሆን
ኃጢአት ይቅር የምታስብል ሴት ልጅ አገኙ
ሁለቱ ሽማግሌዎች ሰማይን ወለዱ
ሰማያቸውም ጸሐይን አስገኘች "
ነግሥ ዘልደታ
@eotcy
BY ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
Share with your friend now:
tgoop.com/eotcy/2234