tgoop.com/eotcy/2272
Last Update:
ጉድለትህን ተጠቀምበት
ዘኪዎስ በማጠሩ ምክንያት በኢያሪኮ እያለፈ ያለውን ክርስቶሰን ለማግኘት ተቸገረ። ሕዝቡ ብዙ ነው የቆሙት ሁሉ ጌታን ከማየት ከለሉት። የሾላ ዛፍ ላይ ወጥቶ ጌታን ለማየት ሲሞክር ጌታ አሻቅቦ አየው።
እሱ ዛፍ ላይ ሊያይ እንጂ ሊታይ አልወጣም። ጌታ ሊታዩ ከሚሞክሩ ይልቅ ሊያዩት የሚሹትን ይወዳልና ዘኪዎስን ጠራው።
ከምድር ቆመን ዓይናችንን አንጋጥጠን ማረን የምንለው ጌታ ዘኪዎስን ከምድር ሆኖ ወደ ላይ እያየ ና ልማርህ አለው።
"ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛል" አለው። ጌታ ወደ ቤቱ ገባ ለዘኪዎስ ቤት መዳን ሆነለት።
ዘኪዎስ አጭር ባይሆን ኖሮ ከሰዎች ጋር እየተጋፋ ጌታን ያይ ይሆናል እንጂ በጌታው ዓይን ለመታየት የሚያበቃ ትጋት አያሳይም ነበር። ምናልባትም ሰዎችን ገለል በሉ እያለ በኩራት ሲጋፋ ከአንዱ ጋር ሊጣላ ሊቆይ ይችል ነበር።
ዘኪዎስ አጭር ባይሆን ኖሮ ከዛፍ ላይ አይወጣም ነበር።
ዘኪዎስ አጭር ባይሆን የሠራዊት አምላክ ወደ ቤቱ አይገባም ነበር። በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ንጉስ በቤቱ ወንበሮች ላይ የተቀመጠው ዘኪዎስ በማጠሩ ምክንያት ነው። የዘኪዎስ ነፍስ የዳነው በቁመቱ ማጠር ነበር።
እግዚአብሔር የማዳኑን ቀን የቆጠረለት ቁመቱን ሲያሳንሰው ነበር። በምድር በመጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ በሕይወት መዝገብ ስሙ የተጻፈው ዘኪዎስ አጭር በመሆኑ ነው።
ስለ ቁመቱ የማወራ እንዳይመስልህ።
ለነፍሳችን መዳን የሚያሳጥርብን ብዙ ነገር አለ። እንደ ዘኪዎስ ቁመትህ አጭር ባይሆን የሚያጥርህ ነገር ግን አይጠፋም።
ይሄ ጎደለኝ የምትለው ከሰዎች አነስኩበት የምትለው ነገር አንዳች ነገር የለም❓ እሱን ማለቴ ነው። ይሄ ይጎለኛል ከሰው አንሳለሁ እያልክ አትማረር እጥረትህ መክበሪያህ ነው። ጉድለትህም መዳኛህ ነው።
ችግሮችህ የእግዚአብሔርን ቸርነት ምታባቸው መስታዎቶችህ ናቸው
እግዚአብሔር ያጎደለብህ የመሰለህ ነገር ወደ ዛፍ እንድትወጣ ምክንያትህ ይሁን። በጉድለትህ እንደ ዘኪዎስ ከፍ በልበት። ያኔ ሰዎች አንተን አንጋጠው ከማየት ውጪ አማራጭ አይኖራቸውም።
ፈጣሪ በፍቅሩ ይይህ እንጂ ሰዎች ወዳንተ ያዘነብላሉ።
በቤትህ መዳን ይሆንልሀል፡፡ ከዚያም ስላጠረህ ስለተጎዳህ ነገር ፈጣሪህን ስታመሰግነው ትኖራለህ።
እመነኝ አንዳንድ ጉድለቶች እድሎች ናቸው። ዘኪዎስ አጭር ባይሆን ይሄኔ በሾላው ዛፍ ጥርሱን እየፋቀ ይቀር ነበር።
"...........እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ የመዳን ቀን አሁን ነው"
--2ኛ ቆሮ 6፥2
@eotcy
@eotcy
@eotcy
BY ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
Share with your friend now:
tgoop.com/eotcy/2272