tgoop.com/eotcy/2281
Last Update:
‹‹በእንተ አቡነ አቢብ!›› ለምን እንላለ❓
እነሆ ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ምእመናን በሚቀምሱት የዕለት ምግብ አማካኝነት በነፍስም በሥጋም እንዲድኑ አስገራሚ የምሕረት ቃልኪዳን እንደተቀበሉ የሚናገር የገድል ተአምራታቸው ይህ ነው፡- ብዙዎች ስማቸውን ጠርተው በሚቀምሱት ምግብ አማካኝነት ከተለያዩ በሽታዎች የተፈወሱ አሉ፡፡ ይህ ቃልኪዳናቸው ለኹላችን ይደረግን ዘንድ ከመመገባችን አስቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም እንጥራ (አቡነ ዘበሰማያትን ማለቱ ነው፡፡) ከተመገብን በኋላም የዕለት ምግባችንን ስለሰጠን እግዚአብሔርን እናመስግን፡፡ ዘወትር ከተመገብን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹ስለ ወዳጅህ ስለ አቡነ አቢብ›› እያልን ሦስት ጊዜ እንቅመስ፡፡ አስቀድሞ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ አቢብ ተገልጦላቸው ‹‹…ወዳጄ አቢብ ሆይ! የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበልኩትን ሕማማተ መስቀል እያሰብህ ይህንን ሁሉ ገድል ፈጽመሃልና ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› አላቸው፡፡ ንዑድ ክቡር ቅዱስ አባታችን አቡነ አቢብም ‹‹ጌታዬ አምላኬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! መቼም ሰው ሁሉ ሳይመገብ አይውልም አያድርምና በተመገበ ጊዜ ስሜን ጠርቶ የተማጸነውን ማርልኝ›› አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አባታችን አቡነ አቢብ ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅር ካደነቀ በኋላ ‹‹…ከማዕድ በኋላ ስብሃት ተብሎ የተረፈውን ‹በእንተ አቢብ› ብሎ ሦስት ጊዜ የተመሰገበውን ሰው ሁሉ እምርልሃለሁ›› በማለት ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ያልተጠመቀ አረማዊ አሕዛብም እንኳን ቢሆን "ስለ አቡነ አቢብ" ብሎ ከተማጸነ ጌታችንን ያንን ሰው ወደቀናች የእምነት መንገድ ሳይመራውና በንስኃ ሳይጠራው በሞት እንደማይወስደው ለአባታችን ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ለማዳን ትንሽ ምክንያትን የሚፈልግ ያለ ምክንያትም የማያድን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ እስከዘላለም ድረስ ይክበር ይመስገን!
ሰው ተመግቦ እንኳን መዳን እንዲችል ይህን ድንቅ ቃልኪዳን ለአባታችን ሰጥቷቸዋልና በየቀኑ በዚህ ቃልኪዳን እንጠቀምበት፡፡ ተመግበን ከጨረስንና ስብሃት ካልን በኋላ ሦስት ጊዜ ‹‹በእንተ አቡነ አቢብ›› ብለን እንቅመስ፡፡
በዛሬዋ ዕለት ጥቅምት 25 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው ታስበው የሚውሉት ጻድቁና ሰማዕቱ አቡነ አቢብ ከቃልኪዳናቸው ረድኤት በረከት ይክፈሉን!
‹‹በእንተ አቡነ አቢብ!››
(ምንጭ፡- ደብረ ሰላም ቃጭልቃ አቡነ አቢብ ገዳም ያሳተመው ገድለ አቡነ አቢብ፣ ገጽ 105)
https://www.tgoop.com/eotcy
BY ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
![](https://photo2.tgoop.com/u/cdn4.cdn-telegram.org/file/Eqih0Aq0mMNzTW4_vKLrSi0SmiupSGhdIcmcHRjwsfpBMD4EjTg4JwUO55zGfGBHZanjEQKRUFUdSW__j-LmoUYXSyBU0XS8QH8D8Iwz_tyUV-b5i6U-xxlA-anX-51S3c7413PRjKDv8U36ZiddVVxNAhsdcRAERpNRe7nwn36jWnp8IkOayC7rbUVpgJmh81BBjBaiXOkPBTToAHP-j5R4xXEvH4yoKvJpiaS_tbIwizIAOk0GmHSinrnb3Yq_M0TIrYt8KfqyC0c23gkOPABeN6Kt_9B1gQXASS5iCC8EnyAXGAYDQy2WGrMhlXL7XgNz8jlIPL7lH2EQZxb54g.jpg)
Share with your friend now:
tgoop.com/eotcy/2281