tgoop.com/eotcy/2291
Last Update:
+++ " #ለዚህ_መቼ_ጸለይን❓" +++
በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰባዊ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲረዳ የተቋቋመ የካህናት (የቀሳውስት) ጉባኤ ነበረ። የቀድሞው የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሺኖዳም ይህን ስብስብ እንዲቀላቀሉ ለአባ ሚካኤል ባቀረቡላቸው ጥሪ መሠረት የዚህ ጉባኤ አባል ሆኑ። ታዲያ አንድ ቀን አባ ሚካኤልን ጨምሮ የጉባኤው የበላይ ኃላፊ የሆኑት ጳጳስና ሌሎችም ካህናት የተጣሉ ባልና ሚስትን ሊያስታርቁ ተሰበሰቡ። ይሁን እንጂ የባልና የሚስትየው ጠብ እንዲህ በቀላሉ ሊበርድ የሚችል አልነበረምና ጳጳሱም ሆኑ ቀሳውስቱም ሁለቱን ለማስማማት ብዙ ቢጥሩም ግን አልተሳካላቸውም።
በስተመጨረሻም ጳጳሱ ወደ አባ ሚካኤል እየጠቆሙ "አባ ሚካኤል ለምን ዝም ብለው ተቀመጡ? እስኪ እርሶ ይሻላል ብለው የሚያስቡትን ይንገሩን❓" አሏቸው። አባ ሚካኤልም "ብፁዕነትዎ፣ #እንጸልይበት❗" አሉ። ጳጳሱም " #ይህን_ጉባኤ_ከመጀመራችን_በፊት_እኮ_ጸልየናል" ቢሏቸው አባ ሚካኤል " #አዎን_አባታችን_ለዚህ_ችግር_ግን_አልጸለይንም" አሉ። ከዚያ ሁሉም ለጸሎት ተነሡ። በጳጳሱ ፈቃድ በአቡነ ሚካኤል መሪነት ጸሎት አደረጉ። ጸሎቱ እንዳለቀም እነዚያ የተጣሉት ባልና ሚስት ክርክራቸውን ሁሉ ትተው በጉባኤው ፊት በፍቅር ተቃቀፉ። ሰላም አወረዱ። ይህን ጊዜ ከቀሳውስቱ አንዱ "አባታችን ከመጀመሪያ እንዲህ ቢሉን ምን ነበር❓ #አሳረፉን_እኮ" ብለው ጉባኤውን ፈገግ አሰኙት።
እኛስ ያልጸለይንባቸው ስንት ችሮች አሉብን❓
ብዙ ቋጠሮ የሚፈታው ግን በብዙዎች የሚረሳው ትልቁ መፍትሔ፣ ጸሎት❗
(አባ ሚካኤል ኢብራሂም (1899-1975) የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ለበርካታ ዓመታት በትጋት ያገለገሉና እጅግ የሚያስቀና የጸሎት ሕይወት የነበራቸው አባት ናቸው። በእርሳቸው ጉዳይ ከሰሞኑን መመላለሳችን አይቀርም።
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
🟢 @eotcy 🟢
🟡 @eotcy 🟡
🔴 @eotcy 🔴
BY ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶች
Share with your friend now:
tgoop.com/eotcy/2291