tgoop.com/ethyas/1273
Last Update:
................
🌹አንድ ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት እስከ ሞት ድረስ ታምኖ የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን ሊያከናውናቸው ከሚገቡ መንፈሳዊ ተግባራት ጥቂቶችን እንመለከታለን፡፡
👉🏽1. #የእግዚአብሔር_ስጦታዎች_ሁሉ_ለበጎ_መሆናቸውን_ማመን
🌹በማናቸውም ጊዜ እግዚአብሔር ሁሉን የሚሰጥ አምላከ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሌላው ቀርቶ ለእኛ ክፉ የሚመስሉን ነገሮችን እንኳን ለበጎ መሆናቸው ማመን አለብን፡፡ /ሮሜ.8.28/፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፉውን ወደ በጎ ሊለውጥ የሚችል ኃያል አምላክ ነውና፡፡ ብላቴናው ዮሴፍ ባሪያ አድርገው የሸጡትን ወንድሞቹን «እናንተ ክፉ ነገር አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው፡፡» ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ /ዘፍ.50.20/፡፡ አበ ብዙኃን አብርሃም እግዚአብሔር «ልጅህን ሠዋልኝ» ያለው ለበጎ እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡ ማወቅም ብቻ ሳይሆን እንደተባለው ልጁን ቢሠዋ እንኳን ከሞት አስነሥቶ በእርሱ በኩል ዘሩን እንደሚያበዛለት ያምን ነበር፡፡ /ዕብ.11.17/፡፡ ኢዮብም ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ አውቆ «እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን» ብሏል፡፡ /ኢዮ.1.21/፡፡
👉🏽2. #የእግዚአብሔርን_ቃል_ኪዳኖች_ማመን
🌹ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር የሰጣቸው ተስፋ ደርሶ ቃሉ የሚፈፀም አይመስላቸውም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ያለጥርጥር ይፈጸማል፡፡ ለአዳምና ለሔዋን የተሰጠው ተስፋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ተፈጽሟል፡፡ /ዘፍ.3.15/፡፡ ለኤልያስ የተሰጠው ተስፋ ምንድን ነው) የተሰጠው ተስፋ በሰራፕታዊቷ ሴት መጋቢነት ሲፈጸም ታይቷል፡፡ እንዲሁም በነቢዩ በኢዩኤል አንደበት የተነገረው ተስፋ የበዓለ ሃምሣ ዕለት ለቅዱሳን ሐዋርያት በመሰጠቱ ተፈጽሟል፡፡ /ኢዩ.2.28፤ ሐዋ.2.16/፡፡ በዚህ ዓይነት እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባውን ቃል ኪዳን እንደማይሽርና ከአፉ የወጣውን ቃል እንደማይለውጥ ማመን ይገባል፡፡/መዝ.88.34/፡፡ በቤተ ክርስቲያን በምንሰበሰብበት ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡት በዚያ እኔ በመካከላቸው እሆናለሁ ባለው መሠረት በመካከላችን እንደሚገኝ የታመነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከውስጥም ሆነ ከውጭ መከራ በሚበዛባት ጊዜ መከራ የሚያስነሣባትና የሚያጸናባት ዲያብሎስ መሆኑን አውቀን «የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም» በሚለው ቃል ኪዳን መጽናት ይገባል፡፡ /ማቴ.16.18/፡፡ መናፍቃን ከእውነት መንገድ ለማውጣት በሚከራከሩን ጊዜም «ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁ»የሚለውን ቃል ኪዳን በማሰብ መታመን ያስፈልጋል /ሉቃ.21.15/፡፡
👉🏽3. #በችግር_ጊዜ_የእግዚአብሔርን_ቸርነትና_ፈቃድ_ተስፋ_ማድረግ
🌹በመንፈሳዊ ጎዳና ስንጓዝ በየአቅጣጫው የሚከበንን መከራ አይተን ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር ተመልክተን አዳኝነቱን ተስፋ ማድረግ አለብን፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወገኖቹ እስራኤል ቀይ ባሕርን ከኋላ ደግሞ የፈርኦንን ሠራዊት ተመልክተው ተስፋ በቆረጡ ጊዜ «ቁሙ፣ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ፡፡» ያላቸው ለዚህ ነው፡፡ /ዘዳ.14.13ጠ14/፡፡
ብላቴናው ዳዊት የተመለከተው በአካሉ ግዙፍ ወደሆነው ወደ ጎልያድ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር አዳኝነት ነው፡፡ /1ሳሙ.17.46/፡፡በአጠቃላይ ዓለም ድብልቅልቅ ቢል ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡ ምክንያቱም «እግዚአብሔር በወጀብና በዓውሎ ነፋስ መካከል መንገድ አለውና»/ናሆ.1.3/፡፡
👉🏽4. #የቅዱሳንን_ገድል_ማሰብ
🌹ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጣቸው ሃይማኖት እሰከ መጨረሻው ተጋድለዋል፡፡ /2ጢሞ.4.7/፡፡ በሰይፍ ተመትተዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ ለአናብስት ተሰጥተዋል፣ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥለዋል፣ ይህም የሚያሳየን የእምነታቸውን ጥንካሬ ነው፡፡ በመሆኑም የቅዱሳንን ገድል በምናስብበት ጊዜ ከእነርሱ የምንማረው እምነታቸውን፣ ሥርዓታቸውንና ትውፊታቸውን ለመጠበቅ መጽናታቸውን ነው፡፡ መማርም ብቻ ሳይሆን በተሰጣቸው ቃል ኪዳንም እንጠቀማለን፡፡ እስራኤል ዘሥጋ «እናንተ ጽድቅን የምተከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ ስሙኝጠ ከእርሱ የተቆረጣችሁበትን ድንጋይ ከእርሱም የተቆፈራችሁበትን ጉድጓድ ተመልከቱ፣ ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፡፡ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፣ ባረኩትም፣ አበዛሁትም፡፡» የተባለለት ለዚህ ነው፡፡ /ኢሳ.51.1/፡፡
🌹ቅዱስ ጳውሎስም «የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው» ብሏል /ዕብ.13.7/፡፡ በአጠቃላይ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑንና ሥራችንን ሁሉ እንደሚከናውንልን፣ ከሁሉም በላይ እንደሚወደን ማመን ያስፈልጋል፡፡ /ዘፍ.15.21፤1.22፤ መሳ.16.3/፡፡ ምክንያቱም አንድ ልጁን እንኳን አልከለከለንምና /ዮሐ.3.16/፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱም በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና፡፡ /1ዮሐ.4.9/፡፡ እርሱም በትምህርቱ «ከእንግዲሀ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ወደጆች ግን ብያችኋለሁ» ብሎናልና፡፡ /ዮሐ.15.15/፡፡ በመጨረሻም ስለማናቸውም ነገር እንደምንጸልይ ሁሉ ስለ እምነታችንም ጽናት ልንጸልይ ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ እምነታችን ዕለት ዕለት እያደገ እየጠነከረ ይሄዳል፡፡
...............
BY ኢትዮጵያ የስላሴ የክብራቸው መገለጫና መመስገኛ ምድር
Share with your friend now:
tgoop.com/ethyas/1273