tgoop.com/ethyas/1274
Last Update:
................
🌹በአንጻሩ ደግሞ እስከ ሞት ድረስ እንዳንታመን በእምነትና በምግባር እንዳንጸና የሚያደርጉን ፈተናዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ፡
👉🏽1. #የራስን_ክብር_መሻት
🌹ብዙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ክብር ትተው የራሳቸውን ምድራዊ ክብር ሲፈልጉ እምነታቸው ደክሞባቸዋል፡፡ ዲያብሎስ ከክብሩ የተዋረደው፣ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ያሳደደው፣ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ «እነሆ ዓለሙ ሁሉ በኋላው ተከትሎት ሄዷል፡፡» በማለት ይቃወሙት የነበረው የራስን ክብር በመሻት ነው፡፡ /ማቴ.2.17፤ ዮሐ.12.19/፡፡ ይሁን እንጂ ምድራዊ ክብር ፈጥኖ እንደ ሣር ይጠወልጋል፣ እንደ አበባም ይረግፋል፡፡ /ኢሳ.40.6፤1ጴጥ.1.24/፡፡ ስለሆነም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «ነፍሴን/ሰውነቴን/ በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ» ማለት ይገባል፡፡
2. #እምነትንና_ዕውቀትን_መደባለቅ
🌹የሰው ልጅ አእምሮው ውሱን፣ ዕውቀቱም የተገደበ ስለሆነ ነገረ ሃይማኖትን ከአቅሙ በላይ ለመተንተን ይከብደዋል፡፡ ስለሆነም የረቀቀውን የእግዚአብሔርን አሠራር ስፋቱንና ጥልቀቱን በሥጋዊ ዕውቀቱ እመረምራለሁ ሲል ከተሳሳተ ሀሳብ ላይ ደርሶ ይሰናከላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደምናየው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት ግኖስቲኮች ከሃይማኖት ተሳስተው የወደቁት፣ ሃይማኖትንና ዕውቀትን በመደባለቅ ለመጓዝ ባደረጉት ሙከራ ነው፡፡ ሥጋዊውን ዓለም ልንመረምር እንችላለን እንጂ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ልንመረምር አንችልም፡፡ በመሆኑም ሊቃውንት በእምነት ተራቅቀው ብዙ የሃይማኖትን ምሥጢር ባወቁ ቁጥር የሚያውቁት ገና አለማወቃቸውን ነው፡፡ ስለሆነም ውሱን የሆነ ዕውቀታችንን በትህትናና በትዕግሥት እግዚአብሔርን ከማገልገል ጋር ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
👉🏽3. #ክፉ_ባልንጀርነት
ከመናፍቃን ጋር በመወዳጀት የእነርሱን ስብከትና መዝሙር መስማት እምነትን ያደክማል፡፡ ምክንያቱም የመዝሙሩ መሣሪያና ስሜት ለሥጋዊ ሀሳብና ፈቃድ መጥፎ ጎን መነሣሣት ይፈጥራልና፡፡ ሃይማኖታዊ ሳይሆን ስሜታዊ ያደርጋል፡፡ የዜማው ስልተ አልባ መሆንና ከዘፈን ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ዓለማዊነት ጠባይ የለበትም መንፈሳዊ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ ለዚህም ነው «ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋዋል» የተባለው /1ቆሮ.15.33/፡፡ በሃይማኖት በሥርዓት ከማይመስል ጋር ለመመሳሰል መሞከር፣ አብሮ ማደርም ሆነ መዋል መልካሙን እምነት ያጠፋዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ «በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት ሰላምም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና፡፡» ብሏል፡፡ /2ዮሐ.1.10 – 12/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም «ከማያምን ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፡፡» ብሏል፡፡ ስለሆነም ብርሃን ከጨለማ ጋር ምንም አንድነት ስለሌለው መለየት ያስፈልጋል፡፡ /2ቆሮ. 6.14-16/፡፡
👉🏽4. #ክፉ_ወሬ
🌹ምእመናን ስለ ሃይማኖታቸው መስማት የሚገባቸው ቤተ ክርስቲያናቸው የምትነግራቸውን መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» እንዲሉ በወሬ የተፈቱ ብዙዎች ናቸውና፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስትን ከመውረስ የደከሙትና በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውም ተስፋ የጠወለገው፣ ዐሥሩ ሰላዮች ያወሩትን እምነት የጎደለው ወሬ እውነት ነው ብለው በመቀበላቸው ነበር፡፡ /ዘኁ.13. 28/፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ አይሁድ «ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ከመቃብር ሰርቀው ወሰዱት» ብለው አስወርተው ነበር፡፡ ይህም ወሬ መግደላዊት ማርያምን አሳምኗት ስለነበረ ከአንዴም ሦስት ጊዜ ጌታን ከመቃብር ወስደውታል እስከ ማለት ደርሳለች፡፡ /ዮሐ. 20.2-13፤15/፡፡ ጥንትም አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር የተጣሉት የሰይጣንን ወሬ እውነት ነው ብለው በመቀበላቸው ነበር፡፡ /ዘፍ.3.4/፡፡ ምክንያቱም የሐሰት ወሬ ከዲያብሎስ ነው፤ የሐሰት አባት እርሱ ነውና፡፡ /ዮሐ.8.44/፡፡ በእምነት መድከም በመጀመሪያ ሥርዓትን ትውፊትን ያስንቀናል፡፡ በሃይማኖት ለሚኖር ሰው ይህ ደግሞ አግባብ አይደለም፡፡ እንግዲህ ይህንን ሁሉ አውቀን በጊዜውም አለጊዜውም በሃይማኖት በምግባር ጸንተን ልንገኝ ይገባል፡፡ በእምነታችን እንድንጸና ምክንያት ሳናበዛ እምነታችንን ከሚያዳክሙ እኩይ ተግባራት በመራቅ እምነትን የሚያጠናክሩትን በጎ ተግባራት ሁሉ መያዝ አለብን፡፡ «በዓመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ» እንደተባለ በማንም ሳንወሰድ የቅዱሳን አባቶቻችንን ሃይማኖት ከምግባር አስተባብረን ልንይዝ ይገባናል፡፡ /2ጴጥ.3.17/፡፡
👉🏽5. #ሥጋዊ_መከራን_መፍራት
🌹ሥጋዊ መከራን መፍራት እምነትን ያደክማል፡፡ ይህም ለዘለዓለም ሞት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ /ራዕ.21.7/፡፡ እግዚአብሔር ግን የፍርሃትን መንፈስ አላሳደረብንም /2ጢሞ.1.7/፡፡ ለሥጋ ፍላጎት መገዛት ማለትም ለዝሙት፣ ለገንዘብና ለሥልጣን ወዘተ መገዛትም እምነትን ያዳክማል፡፡ /1ነገ.11.1፤ ማቴ.19.22፤ ዮሐ.5.4-9፤ ዕብ.4.4፤ 2ጴጥ.2.15፤3ዮሐ.10፤ ራዕ.2.14/፡፡ ምድራዊ ችግርም ሲያዩት የሚያልፍ ስለማይመስል እምነትን ያዳክማል፡፡ ጌዴዎን «ጌታዬ ሆይጠ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን)» ያለው በምድራዊ ችግር ብዛት እምነቱ ደክሞ ስለነበር ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የማዕበሉን ኃይል አይተው «ጌታ ሆይ ስንጠፋ አይገድህምን)» ያሉ ለዚህ ነው፡፡ /ማር.4.35/፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ልንጠነቀቅ የሚገባው ሰይጣን እንዳያታልለን ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው የብርሃን መልአክ እስከሚመስል ድረስ ራሱን ይለውጣልና፡፡ /2ቆሮ.11.14/፡፡ እንዳለ፡፡ ምትሐታዊ የሆኑ ድንቅ ምልክቶችንም ያደርጋልና፡፡ /2ተሰ.2.3-9/፡፡ ሌላው ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ካለው ነገር የምንጠራጠርበት ምንም ዓይነት ነገር መኖር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በዓይነ ሥጋ ብቻ በመመልከት ጥቃቅን መስለው በሚታዩን ነገሮች መጠራጠር ከጀመርን ነገ ደግሞ የእግዚአብሔርን አዳኝነት እስከ መጠራጠር እንደርሳለንና ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
BY ኢትዮጵያ የስላሴ የክብራቸው መገለጫና መመስገኛ ምድር
Share with your friend now:
tgoop.com/ethyas/1274