Telegram Web
እምነት
""""""""""

ስለሳምሽኝ ብቻ
ፈፅሞ አላምንሽም
ተወዳጅ ነኝ ብዬ
ራሴን አልዋሽም፤

የተሳመ ሁሉ የተፈቀረ ነው
ብሎ ያለው ማነው፥
ጌታንስ ይሁዳ
ስሞ አይደል የሸጠው!?


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ተሳድቦ ሃጅ
"""""""""""""""
አፍንጫ ጎራዳ ፥ፀጉሯ ቁርንጫጭ
ቁመናዋ አጭር ፥ ገላዋም ባለቦርጭ
አካሄዷል ስንኩል ፥ ተረከዟ ስንጥቅ
ጥርሷም ውበት አልባ ፥ ገዷም ኮቴ ደረቅ

ከሰው ያልተሰራች ፥ ብያለሁ አታምርም
ማፍቀሬም ስህተት ነው
ማለቴን አልክድም፤

ይህ ሁሉ ማጣጣል
ይሄ ሁሉ ሃሜት ፥ ካንደበቴ የወጣው

ወደድኩሽ ያሉኩ ቀን
እምቢየው ሂድ ከዚህ ስላልሽኝ እኮ ነው!
ድሮስ ቢሆን ፍቅሬ
ያጣ ለማኝ አይደል ፥ ተሳድቦ ሚሄደው!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
አትፍራ
""""'""""

ይሄ ሁሉ ስቃይ ፥ ይህ ሁሉ መከራ
እንዴት ያልፋል እያልክ ፥
ፈፅሞ እንዳትፈራ።

ተለየኝ ያልከው ሰው ፥
ሸሸኝ ያልከው ንብረት
ያልተፈቀደልህ ፥ ቢሆንስ ምናልባት?

ስለዚህ...

ትቶህ የኼደውን
ባይበጀኝ ነው ብለህ ፥ ለራስህ ንገረው
ሲነፍግም ሲፈቅድም
እግዚያብሔር ልክ ነው!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
* አሃ ዱቢን አካሲ? *
--------------------
የ"ይቅር አይቅር" እንኪ እንካ ሠላምታ
በማለዳ ፀሐይ አጓጊ ሞቅታ
የጣመው እፍታ ፥
ልብ የለመደውን መማለድ ስንፈታ
የቀትሯ ፀሐይ አናት ስትመታ
መታገስ ተፈታ!

ለኃያል እውነታ መሸነፍ ተስኖት ፥ ላሸንፍ ባይ ገንኖ
የእንኪ እንካው ጉነጣ በቅብብል ሆኖ
መንፈስ አጥቶ መቅኖ ፥
ፍቅር የነፍስ አምላክ በቀፎ ስጋ ስብ ፥ ላያሸንፍ ዳምኖ
ከውስጠት መሻሻት የላይ መተሻሸት በፍቃድ ሠልጥኖ
መኖር ሆነ ተክኖ!

ማዳመጥ ካለብን ፥ ማዳመጥ 'ምንሻው እስከበለጠብን
ማየት 'ሚገባንን ፥ መመልከት ካለብን እስካልለያየን
ሕይወትን በኑሮ ፥ ፍቅርን በጉሮሮ እስከለካካን
ልብ ከልብ ጋር እንደተተጣጡ መኖር ነው ግዳችን ፤
ስናሳዝን!

( በይቅር
አይቅር
ለማይቀር
አይገደብ ፍቅር! )

A.P.N.K -- የሜሮን
ስጦታ
"""""""""
መዘሞት ሃጥያት ነው፥
አይኔ አያመነዝር
በፍቃደኝነት ካልሰጡኝ በስተቀር!

ፍቅር!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ብቻዬን መጣሁኝ
************
ከልቤ ዙፋን ላይ
በሰጠዋት ሞገስ፣
አምራና ተውባ
በኑሮዬ ብትነግስ፥
ብዬ በተውኩላት
ሕይወት ማንነቴን፣
ታሾፍበት ጀመር
የልጅነት ፍቅሬን።
እኔ ብከፋባት
ስታረገኝ ከንቱ፣
እንደኔ ሚያፈቅራት
የለምና ብርቱ፥

ሌላ ሰው ያጋጥምሽ ፦

ኑሮሽም ይሙላልሽ
ብዬ አየረገምኳት ፣
ብቻዬን መጣሁኝ ፡
እስከዘላለሙ እሷን
መንገድ ትቻት።

ቤተልሔም አባይ(ሰንፔር) ፋና ብዕር
ሰው...
"""""""""

ቀን ዘንበል ያለ'ለት ፥ ለቀን የሚያጋድል
ዘላለም የማያውቅ ከልኩ ሚጎድል፤

ከህሊናው ሙግት ፥
ተጋጥሞ ሚሸነፍ
ሰው እኮ ጤዛ ነው፥
በቅፅበት የሚረግፍ!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ማን ይሆን?
"""""""""""""""

ቅናት አቅል አሳተው ፥ንፁህ ፍቅሩን ካደ
ጭምቱ ኦቴሎ ፥ጨርቁን ጥሎ አበደ፤

ምስኪን ዴዝዴሞና ፥ ፍቅሯ ሞትን ገዛ
ምን ታምና ብትኖር ፥ ተቆጥራ እንደዋዛ፤

ኢያጎም በትሩ እጥፍ ተዘረጋ
ለስልጣን አደረ ፍቅር እያናጋ፤

ዴዝዴሞና ትሆን፥አልያስ ኢያጎ ነው
ኦቴሎ ከርታታው
እውነት የሞት ሞትን ፥
ማን ይሆን የሞተው?


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ጤዛ
""""""

ቃል ወድቋል ይሉኛል፥
ሌት በጠፍ ጨረቃ
ሰው የለም ባገሩ
ለቃሉ ሚበቃ።

ይሉኛል...ይሉኛል...

እኔ ግን እላለሁ፥
ከህሊናው ሙግት፥
ተጋጥሞ ሚሸነፍ
ሰው እኮ ጤዛ ነው
በቅፅበት የሚረግፍ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ትሳመኝ
"""""""""""

ሲያምርባት የምለው፥
የጥርሷን መፈገግ
ባይኔ ስላየሁ ነው
ሀዘን ሲያፈገፍግ!

አጃኢብ የምለው፥
የከንፈሯን ቃና
ስድን ስላየሁ ነው
ተይዤ በጠና!

ስለዚህ ልታመም ፥
በየዕለት ይመመኝ
በፈዋሽ ከንፈሯ
ስማ እንድታድነኝ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
* ፈልጉት! *
--------------
የበሰለ ጥሬ -- የነቃ እንቅልፋም
የቆመ ተራማጅ -- የድንጋይ ቅቅላም!
.
.
.
በሦስት ነጠብጣብ ፥ በብዙዎች ዓለም
ኑረትን በዙረት ፈልጉት ግዴለም!

A.P.N.K. -- የሜሮን
ልምጭ
""""""""""
ከተማሪው አይደል፣
ከትምህርቱም አይደል፣
አልያም ከጠመኔው ከጥቁሩ ሰለዳ፥
ዕውቀት የሚያጣመም
የሚሆን ወልጋዳ።

ይልቅስ...
የየኔታ ልምጭ ያልሞካከረችው
በጀርባው ላይ አርፋ፣
የጊዜው ምሁር ነው
በሸውራራ ዕውቀት ተማሪ ሚያጠፋ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
በምን ይሆን?
""""""""""""""""""
አንድ እልፍኝ ተጋርቶ
ባንድ አልጋ ተኝቶ፥
ባንድ ዋንጫ ጠጥቶ
ባንድ ቃል አውግቶ፥

እልፍ አመት የኖረ...

አንድ ነው ያሉት ነብስ ሁለት ሆኖ ቢገኝ
በየትኛው ችሎት ፥ በም'ነው የሚዳኝ?


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
ጥመት!
""""'""""

አንዴ ለመከራ ለፈተና ጥፎኝ
እንኳን የነገድሁት ፥ ዋናዬም አይተርፈኝ!

ተፈርዶብኝ እንጂ ፥በ'ጣፈንታ ችሎት
ለተድላ ስጠበቅ ፥ ሃዘን የማነጉት!

ባይሆንለት እንጂ...

ባሳብ በትካዜ ፥ ማን ወዶ ያነጋል
እንባና ሳቅ መሃል ፥
ምን ሲል ያንጎላጃል?

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
እኔን!
"""""""

እኔ እንባዬ ይፍሰስ ፥ ያንክተኝ መከራ
የኔ ልብ ይሰየፍ ፥ ይሸለት በካራ፤

እኔ እንባዬ ይፍሰስ ሃዘን ያጨምተኝ
ተሰብረሽ ከማይሽ ያንቺን ለኔ ይስጠኝ።

ባሴት በተድላ እንጂ ፥ ተከፍተሽ አትኑሪ
ማየት ነው ምኞቴ እንደ ወፍ ስትበሪ!

አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
* ሴት አላምንም! *
-------------------
ዘጠኝ ወር አርግዤ
አምጬ ወልጄው
ፈግጌም ተክዤ
በልቤ አቅፌው ፤
( ፍቅርን ላሞህረው )
በመውጣት ፥ በመውረድ
ስዬ አሳድጌው
ክፋት ሳላናግድ
በጎነት ሸልሜው ፤
( ከ'ምነት ላዋህደው )
በህይወት ሳያድግ
በ'ድሜ አደገና
በስሜት ሲፋተግ
በልቡ ሳይጠና --
( ለሚኖርለት ሃቅ
መሞትን ሳይሰንቅ ፥
ለሞተለት እውነት
ሳይቆም ሊኖርለት )
""እማዬ አሁንስ በጣም ነው ያስጠላኝ
ከ'ንግዲህ በኋላ ሴት አላምንም"" አለኝ!
( እጅግ የደነቀኝ
መጥሬቱ የገባኝ )
የፍቅር ፥ የእምነት ምሳሌው የሆንሁት እናቱን አስቀምጦኝ
ሴት እንደማያምን ለሴቷ ነገረኝ!

A.P.N.K. -- የሜሮን
ተዋት!
"""""""""

ከሃሜታችሁ ፅዋ ስላልተካፈለች
ከእኩይ ምግባራችሁ ስላልተሳተፈች፥

አላችኋት አሉ ኢቺ ሴት ነውር ነች!


ማነው ነውረኛ?
ማነው በደለኛ?
ለምን አዘነ ነው እኔን ባይ አንጀቷ?
ለምን ተደቃ ነው ምስኪኑ ደረቷ?

ተዉ...!
እንባም አይን ይመርጣል
አይፈስ በዝምታ፥
የትም አይገኝም
ሀዘን አለው ቦታ።

እስኪ ለቀቅ አርጓት፥
ትጨምት ብቻዋን ሀዘን ተቀምጣ
ፈገግታ ሚመልስ ውብ ቀን እስኪመጣ!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
እምነትና ብሔር
""""""""""""""""""""

ቋንቋ ተቀይሮ
ማውራት ብንጀምር በሰናፍጭኛ
ትግረ ኦሮምኛ ቢቀር ብሔርተኛ
ፈቅ ይሉ ነበረ ጥል ተራሮች ከኛ።

ዶ/ር ነጋ ፍቅሬ ባህርነሽ
(በመረሳት ፍርሃት)
አጥፊ በቀል
""""""""""""""""

ተዘጋ ደጃፏ
ጠቆረ መዳፏ፥
አቄመ ስስ ልቧ
ሸፈተባት ቀልቧ፤
ወርቅ ላበደራት ጠጠር ሆነ መልሷ
መጥላት ግብሯ ሆነ ያደባባይ ክሷ።

ሸሸች ከሴትነት ፥ ሸፈተች ርቃ
በረረች እንደ ወፍ ፥ ተሰበረች ወድቃ።

በደልና ቅጣት ሆኖባት ለየቅል
ቅስሟን አነከተች ፥ በግለሰብ ጥፋት
ሀገር ብትበቀል!


አረጋኸኝ መንገሻ(ፋና ብዕር)
* "ሌላ ሰው!" *
--------------
ነገሩ ሲጀመር ሌላ ሰው ቆሰለ
ሌላው ተገደለ!
ብሶ ሲባባስም ሌላ ሰው ታፈነ
ሌላው ተበተነ!
አደጋው ቀጠለ ሌሎች ሰዎች ሞቱ
ሌሎች ተራቆቱ!
ጭከናው ሲፋፋም ሌሎችም አለቁ
ሌሎች ተላለቁ!
ግፍ ተበራከተ ሌላው ተደፈረ
ሌላ ሰው አረረ!
ስቃይ ገደብ ጣሰ ሌላ ሰው ታረደ
ሌላ ሰው አበደ!

ይኼ ሁሉ ሲሆን እኛ አለን በሕይወት
ነግደን ስናተርፍ በሌሎች ሰዎች ሞት!

ባዛኝ ቅቤ አንጓች ፥ በወንበር ፍቅር ኃይል
በተሰራ ድል ሳቅ ፥ ገዳይ ልብ ሲወድል
በሸንጋይ ጀግንነት መንበር ሲደላደል
በሌላ ሰው ሞት ርቅ መንቀባረር መቄል!

በሴተኛ አዳሪ የዕለት እስባት ፊት ብቻ ቀባብቶ
ከጀርባ ጉዳጉድ ፥ የመከራ ስቀት በየቦታው ሞልቶ ፤
ፌሽታና ዳንኪራ ተጧጡፏል ደምቆ
ኩራታችን ከፊት ፥ ውርደታችን ኳላ በቀይ ተደብቆ!
ምክንያቱም
አሁንም
እኛ "አልተነካንም" በደከመው ብርቱ
ሌሎች ሰዎች ናቸው ያሉት እየሞቱ!

የተለመደ ነው የሌላ ሰው መሞት መነገሩ መርዶ
ለካሜራ ለቅሶ ፥ ለታይታ ዋይታ እንባ መቼ ገዶ!
እስካልመጡ ድረስ በዙፋናችን ላይ እያጉረጠረጡ
ሺህ ሌላ ሰው ቢሞት አንጨክን በቁርጡ!
እኛ
ስቃይና ሞትን እያየን መጨከን የተለማመድነው
ሁሌም የሚሞተው ሌላ ሰው ሆኖ ነው!
ግና
ጽዋው ሞልቶ ሞልቶ የፈሰሰ ለታ
ወየው ዝም ላለው በምቾት ለሽታ!
ወየውለት ወየው
የሌላ ሰው አሳር ነግ በኔ ላላለው!

A.P.N.K. -- የሜሮን
2024/12/20 17:31:34
Back to Top
HTML Embed Code: