tgoop.com/gibi_gubae/2419
Last Update:
ቂርቆስና ኢየሉጣ በሰማዕትነት የጸኑ ቅዱሳን
በዛሬ ዕለት ቅዱስ ቂርቆስ ከእናጹ ጋር ሰማዕትነት ተቀብለው ከዚህ ዓለም የተለዩበት ነው። አገራቸው አንጌቤን ነው። መምለኬ ጣዖት የነበረው የአገራቸው ንጉሥ እለ እስክንድሮስ ቅድስት ኢየሉጣን “ለጣዖቴ ስገጂ” ባላት ጊዜ ሰማይንና ምድርን ለፈጠረው ለእግዚአብሔር እንጂ ለጣዖት አልሰግድም አለችው። ኢየሉጣም የሦስት ዓመት ሕፃን ፈልግና እርሱ የተናገረውን እፈጽማለሁ አለች። ንጉሡም የሦስት ዓመት ልጅ ፈልጉ ብሎ አዘዘ። ወታደሮቹ ሕፃን ሲፈልጉ ከከተማ ውጭ ቅዱስ ቂርቆስን አግኝተው ወደ ንጉሡ ወሰዱት። ንጉሡ ሊሸነግለው ቢፈልግም ቅዱስ ቂርቆስ ግን ለጣዖት መስገድ እንደማይገባ ነገረው።
ቅዱስ ቂርቆስም በከሐዲው ንጉሥ ፊት የአምላኩን ክብር ገለጠ። ንጉሡ እለ እስክንድሮስ ቂርቆስና ኢየሉጣ የሚሰቃዩበትን መሣሪያ እንዲዘጋጅ አዘዘ። ወታደሮችም ማሰቃያ መሣሪያው ተሠርቶ እስከሚያልቅ ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ከእስር ቤት አስገቧቸው፡፡ የተዘጋጀውን ማሰቃያ መሣሪያ ስትመለከት ቅድስት ኢየሉጣ በጣም ስለፈራች ንጉሡ አድርጊያ ያላትን ለመፈጸም ደርሳ ነበር። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ"እናቴ ሆይ የተዘጋጀውን መሣሪያ አትፍሪ” በማለት አረጋጋት። እናቱን ከማረጋጋት በተጨማሪ የእናቱን ልቡና እንዲያጸናላት እግዚአብሔርን በጸሎት ጠየቀው። እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፍርሃቷን አስወገደላት። ቅድስት ኢየሉጣም “ልጄ ስትሆን የጽድቅ መሪ ሆንከኝ። ለመንግሥተ ሰማያት አበቃኸኝ” አለችው። ሁለቱ ቅዱሳን እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ነደደው እሳት ቢገቡም እሳቱ አልጎዳቸውም።
ሕፃኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ለብዙ ጊዜ መከራ ሲቀበሉ ቆዩ። በመጨረሻም ተጋድሏቸውን ፈጽመው ጥር 15 ቀን ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡ ከቅዱሱ አንገት ደም፣ ውኃና ወተት ወጣ። ስለተጋድሎውም ሦስት አክሊሎች ወረዱለት፡፡ ጌታችንም ቅዱሱ የተቀበለውን የመከራ ጽናት፣ የትዕግሥቱን ብዛት አይቶ ቃልኪዳን ገባለት። “ስምህ በተጠራበት፣ ቤተመቅደስህ በታነፀበት፣ ሥዕልህ ባለበት ቦታ ሁሉ የሕፃናት ሞት፣ የእንስሳት እልቂት፣ የእህል መታጣት፣ አባር፣ ቸነፈር አይደርስም” አለው፡፡ በዘመኑም ዓሥራ አንድ ሺሕ አራት የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር አብረው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ የቅዱስ ቂርቆስ አብረውት ሰማዕትነትን የተቀበሉ በረከት ይደርብን፤ ጸሎታቸው በሃይማኖት እንድንጸና ያግዘን። አሜን!!
BY ✞ግቢ ጉባኤ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/gibi_gubae/2419