tgoop.com/gibi_gubae/474
Last Update:
እንኳን ለሰባተኛው_ሳምንትና ለኒቆዲሞስ፤ በዓል በሠላም አደረስዎ
#የዕለቱ_ምንባባትና_መዝሙራት፤
ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ይባላል፤ በዚህ ሳምንትም ይህ ይታሰብበታል፡፡
‹‹ኒቆዲሞስ››፤ * አይሁዳዊ ሲሆን ከፈሪሳውያን ወገን የነበረ ነው
* በኢየሩሳሌም በሀብት ቢሉ በዕውቀት እንዲሁም በሥልጣን የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡
* ማታ ማታ ጌታችን ዘንድ እየተገኘ ይማር ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እንዲህ አስቀምጦልናል፦
፨ ‹‹ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ ‹‹መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህ ተዓምራቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን›› አለው፡፡
⊚ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።
፨ ኒቆዲሞስም፦ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።
⊚ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። #ከሥጋ_የተወለደ_ሥጋ_ነው፥ #ከመንፈስም_የተወለደ_መንፈስ_ነው።›› /ዮሐ. ፫፥ ዘ፩-፲፭/
፨ለምን በሌሊት ይመጣ ነበር?
⊚ አይሁድ ‹‹ማንም ከእኛ ወገን የሆነ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከሆነ ሀብት ንብረቱ ይወሰድ፣ በቤተመቅደስ አይግባ፣ መሥዋዕት አይሠዋ›› ብለው ነበርና አይሁድን ፈርቶ፥ ሀብት ንብረቱን ወዶ፥ እንዳይታወቅበት በሌሊት ይመጣ ነበር፡፡
⊚ በሌላ በኩል ደግሞ የቀን ልብ ባካና ነው፤ ዓይን ብዙ ያያል፥ ሐሳብ ይበታተናል፡፡ በተሰበሰበ ልብ ለመማር፤ በተጨማሪ ‹‹ሊቅ ነኝ›› እያለ ‹‹እስከ ዛሬ ትምህርት አልጨረሰም›› እንዳይሉት በሌሊት ይመጣ ነበር፤ ይህንንም የቀድሞ ሊቃውንት "ረቢ ሰገደ በመንፈቀ ሌሊት ለረቢ፤ አኮኑ አጽባሕት እምነ አጽባሕት የአቢ።" በሚል ጕባኤ ቃና ቅኔ አራቅቀውታል፤ ይህ ቅኔም ለተማሪዎች የቅኔ ሀሁ ነው።
⊚ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳን ለመማር የመጣውን እራሱ እየሄደ ያስተምር ነበርና ኒቆዲሞስ ምንም በሌሊት ቢመጣም ማወቅን ፈልጎ ነውና ስለዳግም መወለድ (ስለጥምቀት) በእግዚአብሔር ልጅ ስለማመንና ስለ ጽድቅ ስራ በዝርዝር አስተምሮታል፡፡
⊚ ኒቆዲሞስ ከአርማትያው ዮሴፍ ጋር በመጨረሻው ቀን በዕለተ ዐርብ ጌታችንን በስቅለቱ ጊዜ፤ ከመስቀል ላይ ሥጋውን ለማውረድና ገንዞ ለመቅበር ቀድሞ ተገኝቷል፡፡ /ዮሐ. ፲፱፥፴፰/
ከኒቆዲሞስ ሕይወት የምንማረው፡-
፩. #ትሕትና፦ ኒቆዲሞስ በትምህርት፣ በሹመት፣ በባለጸግነት የአይሁድ አለቃ ሲሆን፤ አለቅነቱ ግን ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ እርሱ ተገኝቶ ለመማር አልከለከለውም፡፡ (የቅኔውን ትርጕም ከመምህራን ይጠይቁ)
፪. #አለማመካኘት፦ ከመጀመሪያ ሰዎች ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ ሰዎች በምክንያተኝነት በአመፅ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ ኒቆዲሞስም ወደ ጌታ በመቅረቡ የጸሐፍት ፈሪሳውያን አድማና ግርግር ታላቅ እንቅፋትና ምክንያት መሆን እንደሚችል ያውቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት እንደማያዋጣ አውቆ የሚያዋጣውን አደረገ፡፡
፫. #ጥበብ፦ በክርስትና ጉዞ ውስጥ ጥበብ የመጀመሪያ ቦታ ትይዛለች፡፡ ኒቆዲሞስም ጕዞውን በጥበብ አደረገ፡፡ በሌሊት ያደረገበት ምክንያት፡- ራሱ መምህር ሆኖ ሌላ ትምህርት አስፈለገው ብለው ሌሎች እንዳይሰናከሉበት፣ የመዓልት ልቦና ስለሚሰበሰብ በቂ ዕውቀት ለማግኘት፣ መንፈሳዊ ፍሬ ለማፍራት በመዓልትም በሌሊትም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንዳለብን ለማጠየቅ፣ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ያሉ ነፍሳት በሲዖል ይገኛሉ ሲል፣ በመዓልትም በሌሊትም ብትፈልጉ ትገኛለች ሲል ነው፡፡ በእውነት ግሩም ጥበብ!
፬. የተነገረውን አምኖ በመቀበሉ፡- ጸሐፍት ፈሪሳውያን ብዙ ምክንያቶች እየደረደሩ የጌታን አምላክነት አምኖ መቀበል ሲያቅታቸው እርሱ ግን ጌትነቱን ለመቀበል ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
፭. ለእውነት መመስከር፡- እነርሱ ሲክዱ ጌታ ላይም ትርፍ ቃል ሲናገሩ፤ በድፍረት መክሰሳቸውን እየነገራቸው የጌታችን አምላክነቱን በግልጽ ይመሰክር ነበር፡፡
፮. ጽንዓት፡- ብዙዎች በመከራ ጊዜ ላይለዩት ቃል ቢገቡም መጨረሻ ላይ ያኔ በመከራ ሰዓት ከመስቀሉ ሥር ሊገኙ የቻሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ኒቆዲሞስም በዚች ሰዓት ያንን መከራ ታግሶ በጽነዓት ከዮሴፍ ጋር የጌታን ሥጋ ከመስቀል አውርደው በአዲስ መቃብር ቀብረውታል፡፡
ምንጭ፤ የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ
፠፨፠ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ፠፨፠
@gibi_gubae
@gibi_gubae
@gibi_gubae
BY ✞ግቢ ጉባኤ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/gibi_gubae/474