tgoop.com/gibi_gubae/556
Last Update:
💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐
............የቀጠለ.........
#በሕማማት_የማይፈቀዱ
በዚህ በሰሙነ ሕማማት ሳምንትም ቅደስት ቤተ ክርስቲያን ለየት ያለ የአገልግሎት ሥርዓት ሠርታለች:: ከጸሎተ ሐሙስ በቀር ቅዳሴ አይቀደስም፡ ይህ ብቻም አይደለም፡ የዘወትር የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሆነው ሥርዓተ ጥምቀተ፤ ክርስትና፣ ሥርዓተ ፍትሐት፣ ሥርዓተ ማኅሌት፣ ሥርዓተ ተክሊልና ሌሎችም የተለመዱ አገልግሎቶች አይካሔዱም፡፡
👉በመስቀል መባረክ፣ ኑዛዜ መስጠትና መቀበል፣ እግዚአብሔር ይፍታህ ማለት የለም፡፡
በአጠቃላይ ከዓመት እስከ ዓመት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለምእመናን ይሰጡ የነበሩ መንፈሳውያት አገልግሎቶች አቁመው ወቅታዊ በሆኑ ማለትም የጌታችንን ሕማሙን፤ መከራውን፤ መከሰሱን፤ መያዙን፤ ልብሱን መገፈፉን፤ በጲላጦስ ዐደባባይ መቆሙን፣ መስቀል ላይ መዋሉን፤ ሐሞት መጠጣቱን እና ሌሎችንም ለኀጢአተኛው የሰው ልጅ ሲባል የተከፈለውን ዕዳ በሚያስታውሱ አገልግሎቶች ይተካሉ፡፡
እነዚህንም ሥርዓታዊና ምስጢራዊ የሰሙነ ሕማማት አገልግሎቶች እስከ ቀዳም ሥዑር ድረስ እንዴት እንደሚከናወኑ በአጭር በአጭሩ እንመለከታለን፡፡
ከትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ይኸውም በነቢዩ ኢሳይያስ ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማምነ፣ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንም ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ /ኢሳ. 5፤34-36/ ተብሎ በመንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተነገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ ለማስታወስ የወጣ ስያሜ ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት መስቀል መሳለምና እርስ በእርስ መሳሳም የለም፡፡ ይህም ይሁዳ ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠው ለማሰብ ነው፡፡
በዚህ ሣምንት ውስጥ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና በየአንዳንዳቸው ዕለታት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
✍ሰኞ
ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ በምትባል መንደር ያድራል በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ /ማር. 11፣11-14/ ቅጠል ያላትን በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፣ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዕለት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፡፡
👉በለስ የተባለች
ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች፣ ሃይማኖትና ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤልን ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡
👉በለስ ኦሪት ናት
ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡
👉በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች... እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ.21፣13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም ይባላል፡፡
💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐
@gibi_gubae
@gibi_gubae
@gibi_gubae
BY ✞ግቢ ጉባኤ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/gibi_gubae/556