tgoop.com/gibi_gubae/557
Last Update:
💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐💐
👉#ማክሰኞ
የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡
ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፡፡
ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታት በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? የሚል ነበር ይህንስ ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው? አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ነው ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም? ይለናል፡፡ ከሰው ነው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፤ እንደ መምህርነቱም ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እኔም አልነግራችሁም አላቸው፡፡ ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፡፡ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂ፡፡
🌿በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምር ነው፡፡
👉#ረቡዕ
ይህ ዕለት የምክር ቀን ይባላል፡፡
የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሓፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ወይም የያዙበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑ ብዙውን ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጥር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፤1-5፣ ማር. 14፤1-2/
የሐዲስ ኪዳን ካህናት ምእመናን በዚህ ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከእህልና ውኃ ተለይተው፣ መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው፣ የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ስለዚህ ታሪክ የሚያወሳውንም በማንበብ እስከ ኮከብ መውጫ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡
🌿መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት ከእንግዲህ በኃጢአት ተጎድቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚሁ መልካም ሽቶ ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስላቀረበች ነው፡፡
🌿የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ይህም ይህችው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፤6-13፣ ማር. 14፤3-9፣ ዮሐ. 12፤1/
❄️ ከዚህም እያንዳንዳችን ልንማር የሚገባን ነገር አለ፡፡ ይኸውም የራሱን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ነው፡፡
💐.............👇👇👇...............💐
@gibi_gubae
@gibi_gubae
@gibi_gubae
BY ✞ግቢ ጉባኤ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/gibi_gubae/557