tgoop.com/gibi_gubae/781
Last Update:
የቤተ ክርስቲያኑ በር ነገ ወለል ብሎ ቢከፈትም ትናንት ግን ዝግ እንደነበር አንርሳው።
በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንባችንን ሊያብስ አድባራት ክፍት እንዲሆኑና አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ወስኗል። አያይዙም የማስተባበሩን ሃላፊነት አድባራት እና ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲወስዱ አደራ ብሏል።
እናም.....
1 ትናንትና መዘጋቱን ረስተን ነገ መከፈቱን ብቻ አይተን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን እርስ በርስ ቡድን መድበን እገሌ እገሌ ለመባባል አንሂድ ከነገ ወዲያም ሊዘጋ እንደማይችል እርግጠኞች አይደለንምና!
2 ከምስጢራት ለመሳተፍ ማለትም ንስሃ ለመግባት ለመቁረብ ቀጠሮ አናስረዝም ትናንት ዝግ ነበር ከነገ ወዲያም ላለመሆኑ ፈጣሪ ብቻ ነው ማስተማመኛችን!
3 የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ የሚያስከብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትን አንተች ጥንቃቄውን እንደ መጠራጠር አንውሰድ እምነታችንን ትናንት ቤተ ክርስቲያን ተዘግቶ ቤት ስንውል አይተነዋልና!
4 ምንም አይነት አገልግሎት ላይ ብንሆን ጸሎትንም ጨምሮ በቸልታ በማፌዝ አናድርገው ትናንት ባደረግነው ፌዝና ቸልታ ቤተ ክርስቲያን ተዘግቶ ነበርና!
5 ይሄን እድል ፈጥነን እንጠቀምበት ቤተ ክርስቲያናችንን እናክብራት የማይታዩ ጠባቂዎቿን መላእክትን ስንረሳ ፈጣሪ አለማውያኑን ከበሩ ላይ አቆመ ፣ በሰው መብዛት ስንመጻደቅ ቁጥራችን ምንም እንደማይረባው ሊያሳየን ቀነሰን ፣ እርሱ የሚፈልገውን ህይወት ሊያመለክተን ቆራቢ ብቻ እንዲገባ ተፈቀደ ፣ የእምነታችንን ድክመት ለሁላችንም ገለጸልን ፣ እንዲያ የቀበጥንበት የእግዚአብሔር ቤት እስኪናፍቀን ድረስ ባለመግባት ተቀጣን ፣ እንዲያ ለመታያ ብቻ ያደረግነው አገልግሎት ቆሞ መስዋዕትነት የሚጠይቅ አገልግሎት ሰጠን ፣ ብዙዎቻችንም ይሄ አገልግሎት ከብዶን ከቤተ ክርስቲያን ራቅን ጠፋን ፣ ራሴ ማለት ትተን ነበርና ራሳችንን እንድናይ ጊዜ ሰጠን ፣ በጣም ብዙ ነገር ተደረገልን
ይሄን ሁሉ ነገ ቤተ ክርስቲያን ሲከፈት እንዳንዘነጋው ቤተ ክርስቲያኑ ሲዘጋ አቁመንበት ከነበረው ሁኔታ ዛሬም ከቀጠልን ከነገ ወዲያም እንደሚዘጋ እርግጠኞች እንሁን። ያዘጋው ምንም አይደለም የኛ ችግር ነው።
ነገ እንዳይዘነጋ በተለይ ሰንበት ተማሪዎች እንደ ስማችን የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ሆነን የማስተባበሩን ስራ እንከውን። ይሄ እንደ ትናንቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውስጥ የምንፈልገውን ሰምተን ሰንበት ተማሪን የሚመለከተውን ውሳኔ ባላየ ማለፉ አይጠቅመንም።
እንደ ምዕመንም ወደ ሌላ ነገር አንግባ በቃ ምንም ስሌት አያስፈልገውም ትናንትና ተዘግቶ ነበር። ነገም ሊዘጋ ይችላል። ግን እንዳይዘጋ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳዘዘን የታዘዝነውን ጥንቃቄ እንፈጽም ስለ ተቀራረብን የውስጥ አንድነት አለን ማለት አይደለም ስለተራራቅንም እንዲሁ።
እኛ ልጆች ነን ልጅነታችን ደግሞ ለእግዚአብሔር ነው ሰማያዊው አባታችን እግዚአብሔር ደግሞ ምድራዊ አባት ጳጳሳትን ሰጥቶናል። ከዚያም ደግሞ አባትህን እና እናትህን አክብር ብሎናል።
ነገም ዳግመኛ የቤተ ክርስቲያን በሮች እንዳይዘጉ እኔም አንተም አንቺም ሁላችንም ከራሳችን የሚጠበቀውን ነገር እናድርግ።
ዲያቆን ዳዊት ናሁሠናይ (ዘብሥራት)
ግንቦት 5 2012 ዓ.ም
ወለቴ
👇👇👇👇👇
👉 @zebisrat 👈
👆👆👆👆👆
BY ✞ግቢ ጉባኤ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/gibi_gubae/781