tgoop.com/gibi_gubae/838
Last Update:
+ የሞት ሞት +
‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰሎሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት የሚሞትበት ጊዜው መች ይሆን?››
ነፍሳቸውን ይማርና ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ይህችን ጥልቅ ስንኞች ያሏት አጭር ግጥም ጽፈው ነበር፡፡ ጋሽ ከበደ ምናልባት በዚያኛው ዓለም ጠቢቡ ሰሎሞንን የማግኘት ዕድል ገጥሟቸው ይጠይቁት ይሆናል፡፡ ሆኖም እርሳቸው ‹ሞት የሚሞትበት ጊዜው መቼ ነው?› ብለው ወደኋላ ዘመን ተጉዘው የብሉይ ኪዳኑን ሰው ጠየቁ እንጂ ሞት እንኳን ከሞተ ድፍን ሁለት ሺህ ዓመታት አልፈውታል፡፡ ለዘመናት ባለሥልጣን ሆኖ ሲገድል ብቻ የኖረው ሞት በዕለተ ዓርብ ግን ‹የሞት ሞቱ› በሆነው በመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ኃይል ሞት ራሱ ፍግም ብሎ ሞቷል፡፡ አሟሟቱ ደግሞ እንዲሁ አልነበረም ፣ ‹ከሞቱ አሟሟቱ› እንዲሉ አበው ሞት እንደ አረጀ አንበሳ ጥርሶቹ ረግፈው ጽኑ ሥቃይ ተሠቃይቶ ፣ ተዋርዶ ፣ በሆዱ ያለውን ሁሉ ተፍቶ ነበር የሞተው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሞትን አሰቃቂ አሟሟት ከሆድ ሕመም ጋር ባለመሳሰለበት ‹ተምሳሌተ መብል ወከርስ› (Gastronomic Analogy) እንዲህ ይገልጸዋል ፡-
‹‹የክርስቶስን ሰውነት በመቀበሉ ሞት ታላቅ ስኅተት ሠራ፡፡ ይህ ሰውነት በእርሱ የገዥነት ሥልጣን ሥር ያለ ተራ ሰውነት ፣ ኃጢአተኛ የሆነና የሚሞት ሰውነት መስሎት ነበር፡፡ ከሰውነታቸው ጋር የማይስማማ ምግብን የበሉ ሰዎች ሲያስመልሳቸው የሚያወጡት አልስማማ ያላቸውን ምግብ ብቻ ሳይሆን የበሉትን ነገር ሁሉ ነው፡፡ በሞትም ላይ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሞት ፍጹም ንጹሕና የማይሞት የሆነውን የክርስቶስን ሥጋ ዋጠ ፤ የማይሞተው ሕያዉ ክርስቶስ ለአልጠግብ ባዩ ሞትና ሲኦል የሚመር እና የማይስማማ ምግብ ሆነበት፡፡ ሊስማማው ስላልቻለም ተፋው ፤ ከክርስቶስ ሥጋ ጋርም ሲኦል ሆድ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ውጦ የያዘውን ሙት ሁሉ አብሮ ተፋ፡፡ ለሞት የሚስማማው ብቸኛ ምግብ ኃጢአት ብቻ ነው፡፡ ኃጢአት የሌለበት የጌታ ሰውነት ለሲኦል የማይስማማ ምግብ ነው፡፡
ሞት ሊላመጥ የማይችልን ትልቅ ድንጋይ ዋጠ ፤ ይህ ድንጋይ የማይላመጥ ብቻ ሳይሆን በሆድ ውስጥ ቆይቶ የሚያፈራርስና የሚሰባብር ነው፡፡ ስለዚህ ሞት ‹የማዕዘን ድንጋይ› የሆነውን የክርስቶስን ፍጹም ቅዱስ የሆነ ሥጋ በዋጠ ጊዜ በታላቅ ሥቃይና ድካም ውስጥ ሆኖ ጥንካሬዎቹን ሁሉ አጣ፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለም› ያለው፡፡ (ሐዋ.፪፥፳፬) የትኛዋም ሴት ልጅ ለመውለድ ምጥን ባማጠች ጊዜ ሞት የክርስቶስን ሥጋ ይዞ የተጨነቀው ያህል ተጨንቃ አታውቅም ”
ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ደግሞ በሰውኛ ዘይቤ (Personification) በጻፈው ውብ ድርሰቱ ሞትን ስለ ክርስቶስ ከራሱ ጋር እንዲህ ያናግረዋል፡-
‹‹ሞት እንዲህ አለ ፡- ‹‹ይህ ማን ነው? የማንስ ልጅ ነው? እኔን ድል የነሣኝ ይህ [ኢየሱስ የተባለ] ሰው ከየትኛው ቤተሰብ የተገኘ ይሆን? የትውልዶች ሁሉ የዘር ሐረጋቸው የተዘረዘረበት መጽሐፍ በእጄ ላይ አለ፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩት ሰዎች ስም አንድ በአንድ ማንበብ ጀመርሁ፡፡ ከእኔ ያመለጠ [ያልሞተ] አንድም ሰው የለም፡፡ ነገድ በነገድ ሁሉም በክንዶቼ ላይ ተጽፈዋል…
…. በእርግጥ አልዋሽም ፤ የሁለት ሰዎች ስም ብቻ ከእኔ ዘንድ የለም ፤ ሄኖክና ኤልያስ ወደ እኔ አልመጡም … በመላው ምድር ሁሉ ዞሬ ፈለግኋቸው ፣ ዮናስ እስከ ወረደበት የዓሣ አንበሪው ሆድ ድረስ ወርጄ ፈለግኋቸው፡፡ በገነት ውስጥ ተሸሽገው ከሆነ እንዳልፈልጋቸው የሚያስፈራ ኪሩብ ጠባቂ ሆኖ ቆሟል፡፡ ያዕቆብ መሰላልን ተመልክቶ ነበር ፤ ምልባት ወደ ሰማይ የወጡት በዚያ መሰላል ይሆንን?››
ከዚህ ሁሉ መዘላበዱ በኋላም ሞት በሶርያዊው ብዕር እንዲህ ሲል የክርስቶስን ሞት ያማርራል፡-
‹‹ሞት እንዲህ አለ ፡- ወደ ሙሴ ዘመን ብመለስ ሳይሻለኝ ይሆን? ሙሴ እኮ በዓልን ደግሶልኝ ነበር፡፡ በግብፅ ፋሲካ የታረደው በግም ከእያንዳንዱ ግብፃዊ ቤት የበኩር ልጅን ሠጥቶኝ ነበር፡፡ በሙት ላይ ሙት በሲኦል ደጃፍ ተከምረውልኝ ነበር፡፡ ይኼኛው የፋሲካ በግ [ክርስቶስ] ግን ሲኦልን በዘበዘው ፣ ሙታንንም ከእጄ ነጥቆአቸው ወጣ፡፡ ሙሴ ያሳረደው የቀደመው በግ መቃብሮችን ሞላልኝ ፤ ይኼኛው በግ ክርስቶስ ግን ሞልተው የነበሩትን መቃብሮች ባዶ አደረገብኝ››
‹‹የኢየሱስ ሞት ለእኔ ሥቃይ ነው ፤ ከሞቱ ይልቅ ለእኔ በሕይወት እንዲቆይ በተውሁትና ወደ እርሱ ባልቀርብሁ ይሻለኝ ነበር፡፡ በሌሎች ሰዎች ሞት ደስ ይለኝ ነበር ፤ የእርሱን ሞት ግን ጠላሁት፡፡ በሕይወት ሳለ የሞቱ ሰዎችን አስነሥቶ ነበርና እርሱም ከሞት እንደሚነሣና ወደ ሕይወት እንደሚመጣ ገምቼ ነበር፡፡ እርሱ ግን በሞቱ ሙታንን ወደ ሕይወት ወሰዳቸው ፤ ይዤ ላስቀራቸው ስሞክርም በሲኦል ደጃፍ አሽቀንጥረው ጥለውኝ ሔዱ … ገና አሁን እኔም ስለ ወዳጆቻቸው ሞት የሚያለቅሱ ሰዎችን የኀዘናቸውን ጣዕም ቀመስሁት … ከሰዎች ላይ የሚወዷቸውን በመቀማት የማመጣባቸው ሥቃይ በተራው በእኔም ላይ ወደቀ …›› እያለ ሞት ‹እግዚአብሔር ያጽናህ› የማይባል ኀዘንን አዘነ፡፡
ተስፋ የቆረጠ መቼም ከሁሉ ጋር ጠበኛ መሆኑ አይቀርምና ሞት በደረሰበት ውርደት ከወዳጁ ከዲያቢሎስም ጋር ተጣላ፡፡ ዲያቢሎስ ሰውን ለሚያሠራው ኃጢአት ደሞዙ ሞት ቢሆንም በክርስቶስ ሞት ምክንያት ግን ሰይጣን ከደሞዝ ከፋዩ ሞት ጋር ተጣላ፡፡ ሶርያዊው ንብ ኤፍሬም በንጽቢን እያለ በጋገረውና ሳናካትተው ልናልፈው በማንችለው ውብ የኦርቶዶክሳዊ ሥነ ጽሑፍ የማር እንጀራ በመሰለ ዝማሬው ላይ እንዲህ ይላል ፡-
‹‹ሞትና ሰይጣንን ‹ከእኔና ከአንተ በሰው ላይ ኃይለኛ የሆነ ማን ነው?› እያሉ እየጮኹ ሲነታረኩ ሰማኋቸው፡፡ ሞት ሰዎችን ሁሉ መማረኩን በመግለጽ ኃይለኛነቱን አስረዳ ፤ ሰይጣን ደግሞ ሰዎችን ሁሉ ኃጢአት እንዲሠሩ የሚያደርግበትን ተንኮሉን አስረዳ፡፡
ሞት ፡- አንተ ክፉ ሆይ ፤ ለአንተ የሚታዘዙልህ እኮ መታዘዝ የፈለጉ ሰዎች ብቻ ናቸው ፤ ለእኔ ግን ወደዱም ጠሉም ይታዘዙልኛል፡፡
ሰይጣን ፡- አንተ እኮ በጉልበት አስገድደህ ነው የምትይዛቸው ፤ እኔ ግን የምይዛቸው የሚማርኩ ማማለያዎችንና ወጥመዶችን ተጠቅሜ ነው፡፡
ሞት ፡- ስማኝ አንተ ክፉ ፣ የአንተን ወጥመዶች ብርቱ ሰው ሊሰባብራቸው ይችላል ፤ ከእኔ ቀንበር ግን ማንም አያመልጥም ፤ ማንም!
ሰይጣን ፡- አይ ሞት! አንተ እኮ ጉልበትህን የምታሳየው በታመሙ ሰዎች ላይ ነው ፤ እኔ ግን በጤነኞቹም ላይ ኃይል አለኝ!
ሞት ፡- አንተ እኮ የሚቃወሙህን ሰዎች ትሸሻለህ እንጂ ድል የማድረግ ሥልጣን የለህም ፤ እኔ ግን በሚረግሙኝ ላይም ሥልጣን አለኝ ፤ የሰው ልጅ እየረገመኝ እንኳን እጄ ላይ ይወድቃል!
ሰይጣን ፡- ሞት ሆይ! አንተ እኮ ይህን ሥልጣን ያገኘኸው ከእግዚአብሔር ነው ፤ እኔ ግን ሰዎችን ወደ ኃጢአት ስመራ ማንም አይረዳኝም፡፡
ሞት ፡- እኔ እንደ ንጉሥ ሥልጣኔን ስጠቀም አንተ ግን ሥራህን የምትሠራው በደካማነትና በመልከስከስ ነው፡፡
ሰይጣን ፡- አይ ሞኙ! ምን ያህል ታላቅ እንደሆንሁ አታውቅም አይደል? እኔ እኮ ከፍተኛውን ሥልጣን ነጻ ፈቃድን ለመማረክ ብቃት ያለኝ እኮ ነኝ!
ሞት፡- አንተ እኮ ተንኮልህን የምትሠራው እንደ ሌባ በመሬት እየተሳብክ ነው ፤ እኔ ግን እንደ አንበሳ ሳልፈራ ሰባብሬ እጥላለሁ!
ሰይጣን ፡- ሞት ሆይ ፤ እስቲ ንገረኝ አንተን የሚያገለግልህና የሚያመልክህ ማን ነው? እኔን ግን ነገሥታት ሳይቀሩ እንደ አም
BY ✞ግቢ ጉባኤ✟
Share with your friend now:
tgoop.com/gibi_gubae/838