tgoop.com/infokenamu/1889
Last Update:
እንደዋዛ የነበረን ሁሉም ነገር መትነን ጀምሯል። የማንመለሰውን መንገድ ብዙ ርቀት ተጉዘናል። "ለይስሙላ ነው" እያልን የምንኮንነው ማህበራዊ ወገንተኝነትና እዝነታችን ሳይቀር አሁን ቢጠሩት አይሰማም። ለካ ባለ ነገር ላይ ነው ኩነኔ፣ ትችትና ወቀሳ። የሰብአዊነት ወዛችንን ደጋግመን አጠብነው። ማጠባችን ሳያንስ ርዝራዥ እንዳይቀር ጨምቀንና ጠምዝዘን አሰጣነው። "ሃገሬን በሃዘን" የተሰኘው የሱራፌል ወንድሙ ግጥም ላይ በባዕድ ሃገር የሚኖር ሰው ሃዘን በገጠመው ጊዜ "ኡኡ" ብሎ ማልቀስ አለመቻሉ ምን ያህል ሰቀቀን እንደሆነበት የሚያሳዩ ስንኞች አሉ። አሁን ያገር ሰው በሃገሩ የለም፣ ከእዝነት ልቡ ሸሽቷል።
ሰሞነኛውን የጎፋ ህዝብ ህመም በተመለከተ በየቢሮው በየቡናው ላይ የሚሰሙ ድምጾችን ላስተዋለ፣ የወትሮው ያገር ሰው በቦታው እንደሌለ ያመላክታል።
"ኧረ በስማም አንተ የሞቱት እኮ ቁጥራቸው 150 አለፉ ተባለ"
"እንዴ የመቼህን? ገና ማታ ላይ 170 እንደደረሱ አንብቤያለሁ"
"ገበያ ነበር እንዴ፣ ይሄ ሁላ ሰው እንዴት አንድ ቦታ ላይ ተገኘ"
"በየሱስ ስም፣ 260 አለፉ የሚል ነገር ተጽፎ አየሁ"
መሰል፣ መሰል ዘገባዎች ከዚያና ከዚህ ይወራወራሉ። በአንዱም ውስጥ ሃዘኔታ የለም። በአንዱም ውስጥ "እኔን 💔" የሚል ድምጽ የለም። አስመሳይ ሃዘኔታችን ለዛ ነበረው። ለወትሮው ስንሰበር ደረት የሚደልቅልን አይቸግርም ነበር። ዛሬ እሱ ብርቅና ሩቅ ነው። እንደማህበረሰብ ሰው ሟች መሆኑን አለቅጥ አምነናል። አለቅጥ ተፅናንተናል። Trauma ሸሽቶናል። ሃዘን የሚጎዳቸውንና የሚበረታባቸውን ሰዎች ሳይ ብርቅ እየሆኑብን ነው። ሁሉም Move on ላይ ጡንቻ አውጥቷል። ይሄ ይሄ ያስፈራል ሲበዛ።
አንዱ ጓደኛዬ ምን አለኝ፣ "ከንፈር የሚመጡ እናቶች የት ገቡ"
አዎ እንዴት ነው ግን ፣ ከንፈር መምጠጥ እንኳን ብርቅ የሆነብን። አዎ ከተለማመዱት ሁሉም ነገር ይለመዳል። በሞት አለመደንገጥን ያለልክ ተለማመድን። የሞት ዜና ሰዓት የማብሰሪያ ድምጽ ያህል ትኩረት እስኪያጣ ተጋትነው።
በርግጥ ይሄ ይሄ እንደሚመጣብን ደራሲው አዳም ረታም "ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ" መጽሐፉ ላይ የሚከተለውን ከትቦልን ነበር።
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
" . . . እውነቴን ነው፤ እናቶች ተትረፍርፈዋል፡፡
ነጠላ ደርበው 'ልጄ' የሚሉ፣
መንገድ ላይ የውሸት የሚቆጡ
(መቆጣት የሚችሉ ይመስላቸዋል ግን)
ለጠማው መንገደኛ ፈልሰስ እያሉ (ስለ ወፈሩ ወይም ስለ ደከሙ) ጠላ በጣሳ የሚያቀርቡ
(ይህችን ይህችን እወዳለሁ)
ጠዋት ጎሕ ሳይቀድ ለቤተክርስቲያን የሚታጠቁ፣ ፀሎታቸው ሩቅ የሚሰማ……
ዓይኖቻቸውን ከድነው በፍቅር የሚስሙ
(ጨርቅ የለበሰ ጠበል ያቀፈ ገንቦ)……
'እሰይ የእኔ ልጅ' ሲሉ ትንፋሽ የሚያጥራቸው……
ትልልቅ ጡቶች ያላቸው
(ከአምስት በላይ ያጠቡ)
ቡና እያፈሉ ነጠላ የሚቋጩ
(ሰነፍ ይጠላሉና)
ከሽሮ ወጥ ፋሲካ የሚሠሩ
(ከፍትፍቷ ፊቷ)
በቆሎና በንፍሮ ሽር ጉድ የሚሉ፤ ጋብዘው የማይጠግቡ
የውሸት የሚቆነጥጡ
ሲደነግጡ ነጠላ ጥለው ደረት የሚመቱ
ያለ መሐረብ የሚናፈጡ (በማሽቀናጠር ስላደጉ---- ከወንዝ ወንዝ የሚወረወሩ)
በነጠላቸው ጥለት ዓይኖቻቸውን የሚያብሱ
እነኚህን ዓይነት እናቶች ይጠፉ ይሆናል
('ኋላ ቀር' ብለናቸው)
ብዙ መልካሞችና መልካምነቶች እንደጠፉ ሁሉ……
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
በቅጽበት ላጣናቸው የአንድ ቀበሌ ህዝቦች ለነፍሳቸው ምህረት ይስጥልን። የሚወዷቸውን ላጡ ሁሉ መጽናናትን በቅጡ ይስጥልን። ያጡት ይበቃልና ዳግመኛ ማጣት እንዳይጎበኛቸው በምንችለው እናቋቁማቸው።
©ገረመው ፀጋው @gere_perspective
BY ኢንፎክን የመጻሕፍት እና የመረጃ ማዕከል
Share with your friend now:
tgoop.com/infokenamu/1889