tgoop.com/kibirenaw/538
Last Update:
የማቆም ውሳኔ
አንድ የጀመራችሁት ነገር በፍጹም እንደማያስቀጥላችሁ እያወቃችሁ ለውጥ ማምጣት ካቃታችሁ . . . እንዲሁም ከአንድ ሰው ጋር ያላችሁ ግንኙነት ፍጹም ጤና ቢስ እንደሆነና እንደማያዛልቃችሁ እያወቃችሁት ደንዝዛችሁ እንደቀራችሁ ከተሰማችሁ፣ ችግራችሁ ነገሩን የማቆም ከመሆኑ ይልቅ አዲስ ነገር የመጀመር ጉዳይ እንደሆነ አትዘንጉ፡፡
1. እንደገና የመጀመር ፍርሃት
አንድን ነገር እንደገና የመጀመር ፍርሃት ካለብን አሁን ያለውና አላስኬድ ያለውን ነገር ማቆም እንዳለብን እያወቅነው እንኳን ያንን ማድረግ ያስቸግረናል፡፡ ሆኖም፣ የተበላሸ ነገር ይዞ የመቀጠል ሁኔታ ረጅም ርቀት የሚሄድን ችግር ይዞ እንደሚጠብቀን እናስታውስ፡፡
2. ግራ መጋባት
አንድን ነገር ማቆም እንዳለብን ብቻ አውቀን ያንን ካቆምን በኋላ ምን እንደምንጀምር ካላወቅነውና ግራ ከገባን ሁኔታው አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ እዚህ ጋር ማስታወስ ያለብን ነገር ቢኖር አንድን ነገር ስናቆም በቶሎ ሌላ ነገር መጀመር እንደሌለብን ነው፡፡ በተለይም ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እንዳቆምን ወዲያው ሌላ መጀመር እንዳለብን ማሰብ ወደሌላ አስቸጋሪ ግንኙነት ውስጥ እንድንገባ ሊያሳስተን ይችላል፡፡
3. ጊዜ እንዳባከንን መሰማት
አንድ ነገር አላስኬድ ሲለንና ማቆም ስንፈልግ፣ አንዳንድ ጊዜ የሚቆጨን በዚያ ነገር ላይ እስካሁን ያሳለፍነው (ያባከንነው) ጊዜ ነው፡፡ “ይህንን ያህል አመት ቆይቼ” እንላለን፣ ልክ በቁጭት ከተነሳን አሁን ያለው ነገር ይለወጥ ይመስል፡፡ አንድ ነገር ፈጽሞ እንደማያስኬደን ካወቅን በኋላ ብዙ ጊዜ አቃጥያለሁ ብሎ ማሰብ በማይሰራ ነገር ላይ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ በመቃጠል ወደፊት ለሚቆየን የከፋ ጸጸት ራስን ማዘጋጀት ማለት ነው፡፡
አስታውሱ . . .
• አዲስ የሚተክለውን ነገር በሚገባ ያወቀ ሰው አሮጌውን መንቀል አያስቸግረውም፡፡
• አዲስ የሚገነባው ነገር የገባው ሰው አሮጌውን ማፍረስ አይከብደውም፡፡
• አዲስ የሚጀምረውን ነገር የተረዳ ሰው አሮጌውን ማቋረጥ አያዳግተውም፡፡
ችግራችን አቅጣጫን ያለማወቅ እንደሆነ ተገንዝበን ስለነገው ጉዟችን ግልጽ የሆነ እይታን ስናዳብር በፊት ያስቸገረን ነገር ምን ያህል ቀላል እንደሆነ እንደርስበታለን፡፡
@kibirenaw
BY ማራናታ Maranata
Share with your friend now:
tgoop.com/kibirenaw/538