tgoop.com/kibirenaw/541
Last Update:
ቅደም ተከተልን የማወቅ ጥበብ
“የሚያጣድፍ ነገር ሁሉ አስፈላጊ ነገር አይደለም” - Stephen Covey
አንድ ቀን አንድ የማኔጅመንት ሳይንስ ሊቅ ለተማሪዎቹ ንግግር በማድረግ ላይ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለእነዚህ በጣም ለተነሳሱና ብሩህ አእምሮ ላላቸው ተማሪዎች በመናገር ላይ እያለ አንድን ነገር አደረገ፡፡ አንድ ባሊ አመጣና ጠረጴዛው ላይ ካስቀመጠ በኋላ ድንጋዮችን በማምጣት ባሊውን አፉ ድረስ ጢም አድርጎ በድንጋይ ሞላው፡፡ ይህንን ካደረገ በኋላ፣ “ይህ ባሊ ሙሉ ነው የሚል እጁን ያውጣ” አለ፡፡
በክፍሉ ያሉ ተማሪዎች በሙሉ እጃቸውን አወጡ፡፡ “እርግጠኛ ናችሁ?” አላቸው፡፡ “አዎን” በማለት እርግጠኝነታቸውን አረጋገጡለት፡፡ ከዚያም ከጠረጴዛው ስር አስቀምጦት ወደነበረው ሌላ ባሊ አጁን ዘርግቶ አነሳውና በውስጡ ያለውን ጠጠር ወደዚያ ድንጋይ ሞልቶበት ወደነበረው ባሊ አፈሰሰው፡፡ ጠጠሮቹ ሹልክልክ እያሉ ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ገቡ፡፡
“አሁንስ ባሊው ሙሉ ነው የምትሉ ስንት ናችሁ?” አለ መልሶ፡፡ አሁን አሰልጣኙ ምን ሊል እንደፈለገ በመጠኑ እየገባቸው ስለመጣ በማንገራገር የተደባለቀ ምላሽ ሰጡት፡፡ አንዳንዶቹ፣ “አሁን ሙሉ ነው” ሲሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ፣ “አሁንም አልሞላም” አሉ፡፡ አሁንም በመቀጠል እጁን ወደ ጠረጴዛው ስር ሰደድ በማድረግ ሌላ ባሊ አነሳ፡፡
ይህኛው ባሊ በአሸዋ የተሞላ ነው፡፡ ወዲያውኑ አሸዋውን ወደዚያ ድንጋይና ጠጠር ሞልቶበት ወደነበረው ባሊ አፈሰሰው፡፡ አሸዋዎቹ ሹልክልክ እያሉ ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ገቡ፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ፣ “አሁንስ ባሊው ሙሉ ነው የምትሉ ስንት ናችሁ?” አሁን ተማሪዎቹ በሙሉ በአንድ ቃል፣ “ባሊው አሁንም አልሞላም” ብለው መለሱለት፣ አካሄዱ ገብቷቸው፡፡ አሰልጣኙ እንደገና ሌላ ውኃ የሞላበት ባሊ ከጠረጴዛው ስር በማንሳት ድንጋይ፣ ጠጠርና አሸዋ ሞልቶበት ወደነበረው ባሊ አፈሰሰውና በባሊው ውስጥ ሌላ ምንም ነገር መጨመር እስከማይቻል ድረስ ሞላው፡፡
የመጨረሻው ትምህርታዊ ጥያቄ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “ከዚህ ምሳሌ የምናገኘው ዋና ቁምነገር ምንድን ነው?” አላቸው፡፡ አንዱ ሰልጣኝ አጁን አውጥቶ፣ “ምንም እንኳ ጊዜህ በብዙ ነገር ቢጨናነቅ፣ አሁንም ሌላ ነገርን አጨናንቀህ ማድረግ እንደምትች ነው” አለው፡፡
አሰልጣኙም፣ “ተሳስተሃል! የዚህ ምሳሌ ዋነኛ ትምህርት በመጀመሪያ ትልልቆቹን ድንጋዮች ባሊው ውስጥ ባትጨምር ኖሮ ትንንሾቹን ጠጠሮች፣ አሸዋውንና ውሃውን መጨመር አትችልም ነበር፡፡ ትልልቆቹ ድንጋዮች የሚወክሉት በሕይወትህ ያሉትን ዋና ዋና የሕይወት አላማዎችና ግቦች ነው፡፡
ቤተሰብህ፣ ጤንነትህ፣ የትምህርትህ አቅጣጫ፣ ዋነኛ ሕልሞችህና የመሳሰሉት … ዋና ዋና ከሚባሉት “ድንጋዮች” መካከል ይገኛሉ፡፡ በመጀመሪያ በእነዚህ ነገር ካልተደላደልክና የሕይወትህን አቅጣጫ ካልሞላኸው፣ በጥቃቅን ነገሮች ተጨናንቀህ ሕይወትህን ታባክናለህ፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጊዜን በአግባቡ የመጠቀምን ጥበብ ማዳበር በራሱ እጅግ አድካሚ ስራ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ሁኔታው የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ የሕይወቴን ዋና ዓላማ በመለየትና ቅድሚያን ለእርሱ በመስጠት መልክ የያዘ ሕይወት ለመኖር ማቀድ ካልቻልኩ ነገ በዚህና በዚያ የባከነውን ጊዜዬን መለስ ብዬ ከማየትና ከመቆጨት ውጪ ምንም ነገር ለማድረግ ያስቸግረኛል፡፡
“የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ መጽሐፍ የተቀነጨበ፡፡
@kibirenaw
BY ማራናታ Maranata
Share with your friend now:
tgoop.com/kibirenaw/541