tgoop.com/kinexebebe/7722
Last Update:
🕊
✞ እንኩዋን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ዕርገት በሰላም አደረሳችሁ ✞
🕊 ዕርገተ እግዚእ 🕊
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን ፪ [2] ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል": ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል::
የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ [በሕማሙ: በሞቱ] ዓለምን አድኖ: ፵ [40] ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል::
በ፵ [40] ኛው ቀን ፻፳ [120] ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው: ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጉዋል::
ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን እርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ፵ [40] ኛው ቀን ዐረገ::
አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል::
" ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ:: ወእግዚእነ በቃለ ቀርን:: ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ::" [መዝ.፵፮፥፮] (46:6)
ከበረከተ ዕርገቱ ይክፈለን::
"እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ::" [ሉቃ.፳፬፥፶] (24:50-53)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
@kinexebebe
BY መንፈሳዊ ኪነ ጥበብ ብቻ
Share with your friend now:
tgoop.com/kinexebebe/7722