tgoop.com/kinexebebe/9369
Last Update:
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †
† ስንክሳር ዘወርኀ ጥቅምት ፲፭ †
=>አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥቅምት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን ከኒቆምድያ አገር ቅዱስ ቢላሞን በሰማዕትነት አረፈ።
የዚህም ቅዱስ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናት ጥበብንም አስተማሩት ከዚህም በኋላ ስሙ አርማላስ ከሚባል ቄስ ጋር ተገናኘ። እርሱም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የቀናች ሃይማኖት አስተማረው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው ታላቅ የሆኑ ድንቆች ታምራትን የማድረግ ሀብትን እግዚአብሔር እስከ ሰጠው ድረስ በጾም በጸሎት ታላቅ ገድልን ተጋደለ።
በአንዲት ቀንም ለዓይኖቹ መድኃኒትን እንዲአደርግለት አንድ ዕውር ሰው ወደርሱ መጣ ቅዱስ ቢላሞንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያለ በዕውሩ ዐይኖች ላይ የመስቀልን ምልክት አደረገ ያን ጊዜ ዐይኖቹ ድነው አየባቸው ጤነኛም ሆነ።
ንጉሥም ዐይኖቹ የተገለጡለትን የዚያን ዕውር ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረበውና ዐይኖችህን ማን አዳነህ ብሎ ጠየቀው እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት ቅዱስ ቢላሞን ፈወሰኝ እርሱ እጁን በዐይኖቼ ላይ አድርጎ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያለ በመስቀል ምልክት አማተበብኝ ያን ጊዜ አየሁ ይህንንም ብሎ እኔ ክርስቲያን ነኝ እያለ በንጉሡ ፊት በግልጽ ጮኸ። ንጉሡም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ከዚህም በኋላ ወታደር ልኮ ቅዱስ ቢላሞንን አስቀረበው ስለ ሃይማኖቱም በጠየቀው ጊዜ እርሱም ክርስቲያን ነኝ ብሎ በፊቱ ታመነ ንጉሡም ብዙ ሽንገላን በመሸንገል አባበለው። ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት ባልሰማውም ጊዜ በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ ካልሰማኸኝ እኔ ጽኑ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ አለው። ቅዱስ ቢላሞንም እኔ ከሥቃይህ የተነሣ ፈርቼ ሃይማኖቴን ለውጬ ፈጣሪዬን አልክድም አለው።
ከዚያችም ቀን ጀምሮ በብዙ አይነት ሥቃይ በብዙ ቀኖች ውስጥ ማሠቃየትን ጀመረ። በግርፋት በስቃላትም፣ በባሕር ስጥመትም፣ ወደ እሳት በመወርወርም የሚያሠቃይበት ጊዜ አለ። በዚህም ሥቃይ ውስጥ ሳለ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጠመቀው ቄስ በአርሜላዎስ አምሳል ተገልጾለት እንዲህ የሚል የደስታ ቃል አሰማው። የመረጥኩህ ቢላሞን ሆይ ደስ ይበልህ እኔ ሰማያዊ መንግሥትን አዘጋጅቼልሃለሁና።
የንጉሡ ጭፍሮችም ይህን የደስታ ቃል ሰሙ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው እነርሱ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የአመኑ መሆናቸውን በንጉሡ ፊት ገለጡ በዚያንም ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ ንጉሡ አዘዘ። ቅዱስ ቢላሞንንም እንዲቆርጡት አዘዘ ከእሊህ ጭፍሮች ጋርም እንዲህ ገድሉን ፈጸመ ቁጥራቸውም መቶ ኀምሣ ስምንት ነው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሰማዕት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
፨፨፨
=>በዚችም ቀን የቢላሞን ማኅበር የሆኑ የመቶ ሃምሣ ስምንት ሰማዕታት መታሰቢያቸው ነው ደግሞ የሰላትዮን፣ የአጥራኪስ፣ የኢናፍር፣ የአድራኒቆስ፣ የአርሞሊስ፣ የአርሞቅስ፣ የአድማንያ፣ የአርሚስ፣ የቅድስት ጾመታ፣ የአባት ኢሳይያስ፣ የጳውሎስ ረድ የሲላስና የሐዋርያትም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
፨፨፨
አርኬ
ሰላም እብል ለርክበተ ዐፅምክሙ ወርቅ። አዝቂር ወኪርያቅ። ወሰላም ለሲላስ ረድአ ጳውሎስ ማዕነቅ። ዘጸለለ በጌጋይ እምነጽሮታ ለጽድቅ። ዐይነ ሐሊናየ ፈውሱ በምራቅ።
ሰላም ሰላም ሐዋርያቲሁ ለአብ ዘአኀዙ ዮም በቃለ ጥበብ። በቤተ ክርስቲያን አሐቲ እንተ አሕዛብ። ያስተጋብኡ መጻሕፍተ እምባሕረ መለኮት ርኂብ። ከመ ጽጌያተ ያስተጋብእ ንህብ።
፨፨፨
=>ጥቅምት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1."12ቱ" ቅዱሳን ሐዋርያት
2.ቅዱስ ቢላሞን ሰማዕት
3."158" ሰማዕታት (የቅዱስ ቢላሞን ማሕበር)
4.ቅዱስ ሲላስ ሐዋርያ
5.ቅድስት ጾመታ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና
=>+"+ በዚያን ጊዜ ዼጥሮስ መልሶ:- 'እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?' አለው። ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- 'እውነት እላችኋለሁ እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት: የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። +"+ (ማቴ. 19፥27)
፨፨፨
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
፨፨፨
( ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
@kinexebebe
BY መንፈሳዊ ኪነ ጥበብ ብቻ
Share with your friend now:
tgoop.com/kinexebebe/9369