tgoop.com/kinexebebe/9520
Last Update:
++++++ጠባቧ_መንገድ++++++
"በተጨባጭ እውነታ ሰፊውንና ልቅ የኾነውን መንገድ ይዘን ሳለ ጠባቡንና የቀጠነውን መንገድ እየተከተልን እንደ ኾነ በማሰብ እንዳንታለል በራሳችን ላይ ቅርብ ትኲረት እናድርግ። ቀጥሎ የሰፈረው ነገር ጠባብ መንገድ ማለት ምን እንደ ኾነ ያሳይሃል፦ ሆድን ማጎስቆል (ስስትን መግደል)፣ ትጋሃ ሌሊት (ሌሊቱን ሙሉ መቆም)፣ ጥቂት ውኃ መጠጣት፣ ቍራሽ ዳብ መብላት (ከፊለ ኅብስት)፣ በተዋርዶ ድርቅ መንጻት፣ መናቅ፣ ፌዝን መቀበል፣ መሰደብ፣ የገዛ ፈቃድን ቆርጦ መጣል፣ በሚያስቆጣ ነገር መታገሥ፣ ባለ ማጉረምረም ንቀትን መታገሥ፣ ስድቦችን ቸል ማለት፣ ያልተገባ ጠባይን ጸንቶ መታገሥ፤ ሲታሙ አለመቆጣት፣ ሲዋረዱ አለመቆጣት፣ ሲነቀፉ ትሑት መኾን ነው። የገለጽናቸውን ጎዳናዎች የሚከተሉ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ማቴ 5፡3-13።" እንዲል ዮሐንስ ዘሰዋስው። (ሳሙኤል ፍቃዱ (ተርጓሚ)፣ ምዕራግና ድርሳን፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ 102)።
በዚህ አባት ጽሑፍ ውስጥ አንደኛ ራሳችንን መመርመር እንዳለብን ተገልጿል። ልቅ በኾነው ሰፊ መንገድ በተባለው የዓለማዊነት መንገድ ላይ መኾን አለመኾናችንን በትኩረት እንድናስተውል ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። ኹል ጊዜም ቢኾን ትክክለኛ ወደ ኾነው መንገድ ለመግባት አስቀድሞ የቆምንበትን መንገድ እና በዚያ መንገድ እንድንጓዝ ያደረገንን ውስጣዊ ፍላጎት መረዳት ያስፈልጋል። ምን ያህልስ ጊዜ ልቅ በኾነው የኃጢአት መንገድ ተጉዘን ይኾን? ምን ያህልስ የዚያ መንገድ ጣዕም በውስጣችን ቀርቶ ይኾን? እንዴትስ ከዚያ መንገድ መውጣት እንችላለን። እያልን በእርጋታ ለራሳችን ጥያቄ እያቀረብን ራሳችንን እንመርምር።
ኹለተኛው መሠረታዊ ነገር ጠባብ መንገድ ማለት ምን ማለት እንደ ኾነ የተገለጸበት ነው። ጥቂት መመገብን ከመለማመድ ጀምሮ ማንኛውንም ክፉ የተባሉ ነገሮችን የሚያደርጉብንን መታገሥ ተገቢ መኾኑን ያስረዳል። መንገዱን ጠባብ ያሰኘውም፥ የተገለጹትን ነገሮች ለመተግበር እጅግ የሚከብዱ ስለ ኾነ ነው። ጽድቁንና መንግሥቱን እያሰብን የምንኖር ከኾነ ግን ከባድ ሊኾኑ አይችሉም። ጠባቡ መንገድ ጣዕመ መንግሥተ እግዚአብሔርን እያሰቡ ኃጢአትን መጥላትን ማዕከል ያደረገ ነውና። የሚንቁንን፣ የሚሰድቡንን፣ የሚያሙንን መታገሥ ለብዙዎቻችን አስቸጋሪ ነው። በእውነትም የሚጠሉንን ላለመጥላት እየታገልንን ኹሌ ራሳችንን ትዕግሥትን ብናለማምድ እግዚአብሔር ይረዳናል። ትዕግሥት በእኛ ጥረት ብቻ ሳይኾን ከእግዚአብሔርም ጸጋ ኾኖ የሚሰጥም ነገር ነውና። እኛ ከልባችን ክፉን በትዕግሥት ስንቀበል እግዚአብሔር ጽናቱን ይሰጠናል። የጠባቡ መንገድ መድረሻው መንግሥተ እግዚአብሔር መኾኑን በሕሊናችን ውስጥ አስቀምጠን፥ መንግሥቱን እያሰብን እንኑር። አንድ ሯጭ ትኲረቱን በሙሉ የሚያደርገው ቀድመውት ያሉ ተወዳዳሪዎች ላይ እንደ ኾነ ኹሉ እኛም ትኲረታችንን ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር አቅጣጫ ካደረግን በእኛ ላይ የሚደረጉ ክፉ ነገሮችን ኹሉ ሳናያቸው ማለፍ እንችላለን።
ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው
https:/www.tgoop.com/kinexebebe
BY መንፈሳዊ ኪነ ጥበብ ብቻ
Share with your friend now:
tgoop.com/kinexebebe/9520