tgoop.com/kinexebebe/9615
Last Update:
#እናስተዋውቃቹ
#ቅዱስ_ሚናስ (#ማር_ሚና)
ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው። በግብጻውያን ልዩ ቦታ አለው ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም። ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም ድረስ ለጆሮና ለዐይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ ነው። በተለይ ለታመመ ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ ደራሽ ባለ በጎ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው።
ቅዱስ ሚናስ ትርጉሙ ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው። በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ፣ በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ፣ በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ፣ ሃብትን ክብርን ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ፣ በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ በአላውያን ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ ህዳር 15 በሰማዕትነት ያረፈበት ሲሆን ሰኔ 15 ደግሞ ቤተ ክርስቲያኑ መርዩጥ በተባለ አገር የከበረችበት ነው።
#በአንድ_ወቅት፦
ዐሥራ ስምንት ቀሳውስት በሥራ ጉዳይ አቡነ ቄርሎስ ፮ኛን ለማነጋገር መርዩጥ ወደ ሚገኘው የቅዱስ ሚናስ ገዳም ጉዞ ጀመሩ። ቀሳውስቱ በጉዞአቸው መንገድ ስተው ሲባዝኑ ከአንድ የበረሓ ሰው ጋር ተገናኙ።
የበረሓው ሰው መርዩጥ የሚገኘው የቅዱስ ሚናስ ገዳም ለመሄድ መንገድ እንደሳቱ ቀድሞ ተረድቶ ነበርና "የማር ሚናስን ገዳም ነው የምትፈልጉት? በማለት ይጠይቃቸዋል። እነርሱም ችግራቸውን እንዴት እንዳወቀ በልባቸው እያደነቁ "አዎን" አሉት። የበረሓው ሰውም እየመራ ከገዳሙ አደረሳቸው አቡነ ቄርሎስ ፮ኛም ወደ በር ወጥተው ተቀበሏቸው።
ከዚያም "ምነው ዘገያችሁ? መንገድ ሳታችሁ እንዴ?" ብለው እንደ ቀልድ ጠየቋቸው። እነርሱም "አዎን! በጣም ተቸግረን ሳለን ይህ የበረሓ ሰው ደርሶልን መንገዱን አሳየን" ብለው ወደ ሰውየው ለማመልከት ዘወር ሲሉ እርሱ በአካባቢው የለም። አቡነ ቄርሎስም "መንገድ እንደጠፋችሁ ስለተረዳሁ ሚናስን ልኬላችሁ ይዟችሁ የመጣው እርሱ ነው" አሏቸው።
አምላካችን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከትን ይክፈለን!!
@kinexebebe
BY መንፈሳዊ ኪነ ጥበብ ብቻ
Share with your friend now:
tgoop.com/kinexebebe/9615