tgoop.com/mahiberekidusan/1509
Last Update:
🕯 💛 🕯
† እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።
🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ †
" የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።" [መዝ.፴፬፥፯]
🕊 ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት 🕊
† በቤተ ክርስቲያን ክቡር ከሆኑ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ገብርኤል ብዙ የክብር ስሞች አሉት:: በተለይ ግን:-
† ሊቀ አርባብ
† መጋቤ ሐዲስ
† መልአከ ሰላም
† ብሥራታዊ
† ዖፍ አርያማዊ
† ፍሡሐ ገጽ
† ቤዛዊ መልአክ
† ዘአልቦ ሙስና . . . እየተባለ ይጠራል::
በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ስሙ በብዛት ተጠቅሷል:: ስለ ረዳትነቱና አማላጅነቱም ቤተ ክርስቲያን በስሙ ታቦት ቀርጻ : መቅደስ አንጻ በሥርዓት ክብሩን ትገልጻለች::
ከእነዚህም አንዱ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነደው እቶን አሳት ማዳኑ ታስቦ የሚከበርበት በዓሉ ዛሬ ነው::
"ለዝንቱ ዜናዊ መልአከ ኃይል::
በዛቲ ዕለት ከመ ይትገበር በዓል::
መምሕራን አዘዙ ወሠርዑ በቃል::" እንዲል:: [ አርኬ ]
ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ::
ምንም እንኳ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ: ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::
አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::
ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር ስድሳ ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ አርባ ዘጠኝ ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::
ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳ አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::
ዳን 3፥17 ጀምሮ ያንብቡ
ቅዱሳኑን ያዳነ ቅዱስ መልአክ እኛንም ያድነን ዘንድ እንደ አባቶቻችን ፦
"አድኅነኒ ዘአድኃንኮሙ በአክናፊከ ምንትው::
አመ ውስተ እሳት ተወድዩ ሠለስቱ እደው::" እያልን እንለምነው:: [ መልክዐ ገብርኤል ]
የቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ቃል ኪዳን አይለየን፡፡
#ሼር
@mahiberekidusan
🕯 💖 🕯
BY ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)
Share with your friend now:
tgoop.com/mahiberekidusan/1509