tgoop.com/mahircomp123/6098
Last Update:
ነገረ-እኩይ ❲Problem of Evil❳ ?
የአምላክን ሕልውና (Existence) ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት አብዛኛውን ጊዜ በኢ-አማንያን 'Atheist' ከሚነሱት ሙግቶች መካከል አንዱ 'ነገረ-እኩይ' ግንባር ቀደሙ ነጥብ ነው። 'እኩይ' የሚለው የግዕዝ ቃል "ክፋት፣ መከራ፣ ስቃይ፣ ችግር" ወዘተ የሚል ትርጉም ይሰጠናል። ይህም ሁሉን ቻይ 'Omnipotent፣ በሁሉ ሥፍራ የሚገኝ 'Omnipresent'፣ ፍጹም ቸር፣ ቅን እና አዛኝ 'Omnibenevolent'፣ እንዲሁ ሁሉን አዋቂ 'Omniscience' የሆነው አምላክ ባለበት ዓለም ውስጥ እንዴት ይህ ሁሉ ክፋት ሊኖር ቻለ የሚል ጥያቄ አዘል ሙግት ነው።
ከቀደምት ግሪክ ፈላስፋዎች መካከል አንዱ የሆነው "ኤጲቆሮስ" Epicurus ❲341 BC) የነገረ-እኩይን ጥያቄ እንዲህ በማለት አዋቅሯል:- ‟እርሱ (አምላክ) ክፋትንና ስቃይን መግታት እየፈለገ ነገር ግን ማስቆም ካልቻለ እርሱ አቅመ-ቢስ እና ደካማ ነው። ስቃይን መግታት እየቻለ ግን ማስቆም ካልፈለገ ደግሞ ጨካኝ ነው። እንዲሁ አምላክ ክፋትን ማስቆም እየፈለገ ያንን የሚያጠፋበት አቅሙም ካለው ታድያስ ስለምን መከራን ከዓለም አላጠፋም ?።” ❲David.'Dialogues Concerning Natural Religion' p.186❳ የሚል ነው። ከዚህ በመነሳት ኢ-አማንያን የሆኑ ምሁራን 'ነገረ-እኩይ' በፍጹም ሊመለስ የማይችል እና ከባድ ቋጥኝ እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ። እርግጥ ነው፥ ጥያቄው ሲታይ ፈታኝ ይመስላል። በተለይ ደግሞ ስለ እምነት እምብዛም እውቀት ላሌለው ሰው እነርሱም እንዳሉት ከባድ ቋጥኝ ሆኖ ሊታየው ይችላል።
ለዚህ ርዕስ ❲Problem of Evil❳ መልስ በመስጠት ረገድ አማኞች 'theists' በሁለት ጎራ ይካፈላሉ። የመጀመሪያዎቹ «አምላክ ክፋትን አልፈጠረም» ብለው የክፋትን መንስኤ ለሰው ልጆች የሚሰጡ ሲሆኑ ሁለተኞቹ ደግሞ «ከክፋት ጀርባ የአምላክ ጥበብ አለ» በማለት የሚያስረዱ 'Theodicist' ናቸው። በእርግጥ በባይብልም ሆነ በቁርኣን ውስጥ "ክፋትን" የፈጠረው እራሱ አምላክ መሆኑን በማያሻማ መልኩ በግልጽ ተጽፏል፣ ❲ሱራ አል-ፈለቅ 113፥2 | ትንቢተ ኢሳይያስ 45፥7❳።
የነገረ-እኩይ ዋንኛው ሙግት መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኹት፣ ይህ ፍፁም የሆነው አምላክ ከክፋት ጋር አብሮ ሕልው (Co-exist) መሆን አይችልም የሚል ነው። በእርግጥ ይህ ሙግት ብቻውን ሕልውናን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ብቁ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ባሕሪያተ-መለኮት ላይ ያተኮረ ነው። ሙግቱ ድል ቢነሳ እንኳ አጽናፈ-ዓለሙ እንዲሁ ያለ አስገኝ ተፈጠረ ወደሚል ድምዳሜ በፍጹም አይወስድም። እርግጥ ነው "ባሕሪያቱ" ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፣ አስነስቷልም። ታድያስ...ይህን ጥያቄ እንዴት እንረዳለን ? ሙስሊም እንደመሆናችን ደግሞ ከእስልምናው አንጻርስ እንዴት እናየዋለን ?
[፨] 'አምላክ መከራን (Evil) ፈቅዷልን ?' አጭሩ መልስ «አዎ በሚገባ» የሚል ነው። ግን ለምን ?
□ ለፈተና ነው:- ጌታ አምላካችን የሰው ልጆችን ሲፈጥር በተለያዩ መከራዎች ይፈትናቸዋል። ይህንንም እንዲህ ይገልጻል:- ‟በገንዘቦቻችሁና በነፍሶቻችሁ በእርግጥ ትፈተናላችሁ ❲ሱራ 3፥186❳ በተጨማሪ ‟ከፍርሃትና ከረኃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን ❲ሱራ 2፥155❳፣ በሌላም ቦታ እንዲህ ይላል:- ‟ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊሞክራችሁ ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው። ❲ሱራ 67፥2❳።
ስለዚህ ያ ፍፁም የሆነው አምላክ በዚህ ዓለም መከራን የፈቀደው የፈጠራቸውን ፍጥረታት ለመፈተን መሆኑን እንረዳለን። ይህም ከጀርባው ድንቅ የሆነ መለኮታዊ ጥበብ "Divine wisdom" አለው። አምላክ የሰው ልጅን ለመጉዳት ወይም ለመበደል ምንም አያደርግም። አንድ መምህር ተማሪዎቹን የሚፈተንው ሊያጠናክራቸው እንጂ ሊጎዳቸው እንዳልሆነ ሁሉ አምላክም እኛን በተለያዩ መከራዎች የሚፈትነው ለመንፈሳዊ ጥንካሬ፣ ነፍስን በግብረ-ገብነት ለማበልፀግ እና የታገሱትን ለመሸለም ነው።
ይህ "Soul-making theodicy" ይባላል። በአጭሩ ስንቃኘው፥ አምላክ መከራን በመፍቀዱ ጀርባ ያለው ጥበብ የሰው ልጆች ሕይወት ላይ ከፍተኛ የነፍስ ግንባታ አስተዋፅኦ ለማድረግ ነው። ሰው በትክክል የሰውነትን ዋጋ የሚረዳው በመከራ ነው። ለምሳሌ ጤና ምን ያኽል አስፈላጊ እንደሆነ ያወቅነው በበሽታ ነው። የሃብት ጥቅም የሚታወቀው በማጣት ነው። የአምላክ ፀጋ እጅግ ውድ እንደሆነ ልናውቅ የምንችለው ያንን ፀጋ ስናጣው ነው። «ችግር ያስተምራል» የሚባለውም ለዚሁ ነው።
[፨] ፍፁም የሆነ ክፋት ❲Pure evil❳ በትክክል አለ ?
□ ኢብኑል ቀይም አል-ጀውዚያ ‟ፍፁም የሆነ ክፋት የለም።” ይላሉ። ይህ የመምህሩ የኢብኑ ተይሚያም አቋም ነው። "Evil is relative, not absolute" የሚለው ፅንሰ-ሀሳብ መከራ በአንድ በኩል ክፉ ቢመስልም በሌላኛው እይታ ደግሞ መልካም ነገር ስለሚኖረው "ፍጹም ክፋት" ተብሎ አይገልጽም የሚል ነው። ይህ ሀሳብ መለኮታዊ መሰረት አለው፥ ❲በሱራ 2፥216❳ ላይ አላህ ለእኛ መጥፎ የሚመስል ነገር መልካምን፣ እንዲሁ መልካም የሚመስለን ነገር መጥፎ ሊሆን እንደሚችል ይገልጽና ለእኛ የተሻለውን ግን እርሱ እንደሚያውቅ ያስቀምጣል። ለምሳሌ ህመም ! በሽታ በራሱ ክፉ ነገር ነው፣ ማንም መታመም አይፈልግም። ነገር ግን በሽታ መልካም ጎንም አለው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከአምላኩ ጋር ይበልጥ ቀረቤታ የሚኖረው ሲታመም ነው። ያጋጠመው ህመም ከአምላክ ጋር ያለውን ግኑኝነት በማጠናከር ወደ እምነት ይመልሰዋል። ይህ ደግሞ የመጨረሻው ስኬት ነው።
● ስለዚህ አንድን ነገር በአንድ በኩል ብቻ አይቶ "ይህ ክፋት ነው፣ እንዲህ መሆን የለበትም" ብሎ መቃወም ተገቢ አይደለም።
ምን እኩይ "Evil" ምንስ መልካም "Good" እንደሆነ የምናውቅበት መለኪያውስ ምንድነው ? በእርግጥ እኛ በአምላክ ሕግ የምንተዳደር እንደመሆናችን መልካም እና ክፉው ተለይቶ ተቀምጦልናል። ኢ-አማኙ (Atheist) ወገን እንዴት ይህን ይለያል ? ከምንስ ተነስቶ ነው "ይህ ክፉ ነው" የሚለው ?፥ ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላኛውን ሲገድል ክፋት ሆኖ ፍየልን ለመብላት ሲገድላት ግን "ጥሩ" የሚሆነው እንዴት ነው ? የመጥፎነት መለኪያው ይህ ነው ለማለት መሰረት ያስፈልጋል። ይህ መሰረት ደግሞ በፍጹም ኢ-አማንያን ዘንድ የለም፣ ሊኖርም አይችልም።
[፨] ነጻ ፍቃድና ሀላፍትና (Free will and moral responsibility)
□ በሰዎች የሚፈፀሙ ችግሮች (ግድያ፣ ስርቆት፣ ዝሙት) እነዚህ ሁሉ የሰው ልጆች ፍፁም የሆነ ነጻ ፍቃድ እንዳላቸው የሚያሳዩ ነጥቦች ናቸው። የሰው ልጅ መሰል ተግባራትን እንዳይፈፅም ተደርጎ ቢፈጠር ሰው "ነጻ ፍቃድ አለው" የሚባለው እንዴት ነው ?። ድርጊቶቹ ትክክል ናቸው እያልኹ አይደለም። ነገር ግን መልካምም ሆነ ክፋት በአንድነት ያሉበት ዓለም ያለ ነጻ-ፍቃድ (Free will) እንዲሁ ከሚኖርበት ዓለም ይልቅ ትርጉም ይሰጣል። ስናጠቃልል:- ፍፁም ፍትሓዊ የሆነው አምላክ መከራ ይኖር ዘንድ ፈቅዷል። መከራ አንጻራዊ (Relative) እንደመሆኑ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ተመልክቶ መቃወም ትክክል አይደለም።
-------------------------------------------------
®Sαlαh Responds 🖋
▸ www.tgoop.com/mahircomp123
BY Sαlαh Responds ⛉
Share with your friend now:
tgoop.com/mahircomp123/6098