tgoop.com/mahircomp123/6129
Last Update:
ስቅለት፥ ቁርኣን እና ታሪክ።
አምላካችን አላህ ❲ﷻ❳ ክርስቶስ ኢየሱስ እንዳልተሰቀለ በግልጽ ነግሮናል። በእርሱ ፈንታ አይሁዳውያን ‟ክርስቶስ” ነው ብለው ያሰቡትን አካል እንደሰቀሉ፣ መሲሑን ግን ወደራሱ እንደወሰደው በቅዱስ ቃሉ [ኒሳዕ 4፥157:-8] ላይ አስቀምጧል። ይህ ማለት ታላቁ ነቢይ ሳይሰቀል እና ሳይገደል ከነ ክቡር ሥጋው ወደሰማይ ዐርጓል። ነቢያችን ⎛ﷺ⎠ በሐዲስ እንዲህ ብለዋል:- ‟እርሱ ኢየሱስ አልሞተም፣ ትንሳኤ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ በመካከላችሁ ተመልሶ ይመጣል።” [አጥ-ጠበሪይ: ጃሚዕ አል-አሕካም 6፥ 455] አይሁዳውያን ነቢያትን የመግደል ልምድ እንዳላቸው ግልጽ ነው። አላህ ኢየሱስን ሲያስነሳ አስቀድሞ እንደሚያድነው ቃል ገብቶለት ነበር፣ ቃሉንም ፈፅሟል፣ [ኢምራን 3፥55]።
ስቅለት ለክርስትና መሰረታዊ ትምህርት ነው። እምነቱም የተገነባው በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ እንደሆነ ይታመናል። ለዚያም ነው ጳውሎስ ክርስቶስ (ሞቶ) ካልተነሳ እምነታችን 'ከንቱ' ናት ያለው፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥14። ይህ ነጥብ ለክርስትና የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ የእምነቱ ተከታዮች የብሉይ ኪዳንን ጥቅሶች ከማጥመም አንስተው ስቅለትን ለማረጋጋጥ ያገኙትን ሁሉ ሲጠቅሱ ይስተዋላሉ። በእርግጥ ያን ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነገርም ነው። ይህ ርዕስ በታሪክ "History" የተደገፈ እንደሆነ ስለሚያምኑ ምንም ሳያመናቱ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ለኃጢኣት ሲል በመስቀል ላይ ቤዛ መሆኑን ይሰብካሉ። እንደውም እስልምና ይህን "ታላቅ ታሪካዊ ክስተት" (የሚሉትን) ስቅላት ባለመቀበሉ ሐሰተኛ እንደሆነም ይናገራሉ።
[፨] በዚህ ዙርያ «ታሪክ» ምን ይላል፣ ስንት አቋምስ ነው ያለው ?
መሲሑ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ዘመነ-መንግስት እንደተሰቀለ በርካታ የታሪክ ምሁራን ይስማሙበታል። ለዚህም ከወንጌላት በተጨማሪ እንደ ታሲተስ፣ ጆሲፈስ፣ ሉሲያን እና ሌሎችን የታሪክ ጸሐፊያን እንደ መረጃ ይጠቅሳሉ። በተጨማሪ ሌሎች ጥንታውያን ሰነዶችም "ክርስቶስ ተሰቅሏል" የሚል እምነት አላቸው። ከዚሁ በተቃራኒ የመሲሑን ስቅለት «የማያምኑ» ጥንታውያን አካላት መኖራቸውም ግልጽ ነው። ለምሳሌ በ2ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ በአሌክሳንደሪያ መሰረት ያገኘው "Basilideans" በመባል የሚታወቁት ክርስቲያኖች በኢየሱስ ፈንታ የቀሬናው ስምዖን እንደተሰቀለ ያምናሉ። ይህንንም ሄራንዮስ በእንተ-መናፍቃን በተሰኘው ሥራው ገልጿል (Heresies Book I, Chapter 24 Verse 4)። አንዳንድ ዘመናዊያን ምሁራን የኢየሱስ ስቅላት ከታሪካዊ እውነታ ይልቅ አፈ-ታሪካዊ ይዘት ያለው ፈጠራ መሆኑን ይሞግታሉ። (Robert M. Deconstructing Jesus, NY: Prometheus Chapter 7)
በእርግጥ በታሪክ ውስጥ «አልተሰቀለም» ከሚለው ይልቅ «ተሰቅሏል» የሚለው ትርክት ሰፊውን ድርሻ ይዞ ቀጥሏል። ይህም የሆነው እነዚያ ክርስቶስ ኢየሱስ "አልተሰቀለም" ብለው የሚያምኑ አካላት "መናፍቃን" ተብለው እንዲወገዱ ስለተደረገ ነው። እንደሚታወቀው በ4ኛው ክ/ዘ የሮም ግዛት ንጉሥ የነበረው ቴዎዲዮሲዮስ (Theodosius l) የትኛውም የኑፋቄ እምነት በእግሩ ቆሞ እንዳይንቀሳቀስ ከፍተኛ አድማ በማስነሳት እምነታቸውን በአደባባይ እንዳይሰብኩ ከልክሏቸዋል። አቋማቸውን የሚያስተምሩበት መቅደስ (Temple) እንዳይገነቡ፣ የተገነቡትም እንዲፈርሱ ከፍተኛ ትዕዛዝ አስተላልፏል። በዚህ ምክንያት በኃይል አንድ አቋም ብቻ ገኖ እንዲወጣ ስለተደረገ "በምንፍቅና" የተወነጀሉ አቋሞች እንደ ልብ መስፋፋት አልቻሉም።
[Source:- Eliot, Samuel. "History of the Early Christians" Brown, 1853. Vol.2 p.200]
[፨] በታሪክ ውስጥ ሰዎች እንዲህ ማመናቸው ከምን የተነሳ ነው ?
ቁርኣን ስቅላት መኖሩን አልካደም። በእርግጥ የተሰቀለ አካል እንዳለ ያምናል። አይሁዳውያን የሰቀሉት ግለሰብ "ክርስቶስ" መሆኑን ያምናሉ፣ ያንንም እንደ ጀብድ አውርተዋል። መቼ ? ጥንት ዘመን። ነገር ግን...በዚህ ተግባራቸው "እርግጠኞች" አልነበሩም። ቁርኣን እንዲህ ይላል:- «እኛ የአላህን መልክተኛ የመርየምን ልጅ አልመሲሕ ዒሳን ገደልን በማለታቸው ረገምናቸው።» አክሎም «እነዚያም በእርሱ (መገደል) የተለያዩት በነገሩ በመጠራጠር ውስጥ ናቸው፡፣ በእርግጥም አልገደሉትም።" ❲ሱራ 4፥157❳
ታድያስ እነዚያ ጻፎችና ፈሪሳውያን በክርስቶስ አስተምህሮ ድል መነሳታቸው ታላቅ ውርደትና ቀውስ እንዳስከተለባቸው እሙን ነው። ይህም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እርሱን ለማስወገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፣ ❲ሱራ 3፥54❳። በዚህም ምክንያት አምላክ ወደ ሰማይ የወሰደውን ኢየሱስን «እንደገደሉት» አድርገው ማራገባቸው፥ ይህም በታሪክ ሰፍሮ መገኘቱ የሚጠበቅ ነገር ነው። ቁርኣንም ክርስቶስ በስቅለት እንደተገደለ ተደርጎ መወራቱን አላስተባበለም። ለዚያ ይህ 'ንግግር' በሰፊው በታሪክ ውስጥ ቢወራ ቁርኣንን እንዴት ሐሰት ያደርገዋል ? «ክርሰቶስ ተሰቅሏል» የሚለውን ወሬ በሰፊው ያራገቡት አይሁዳውያን ናቸው። ታሪክ በዋነኝነት እንደ መጀመሪያ ምንጭ (Primary source) የሚጠቀመው እነርሱን ነው። እነርሱ ደግሞ የዚህ ንግግር ባለቤት መሆናቸውን አልካድንም፣ እኛ ያልነው "እርግጠኞች አይደሉም" ነው።
ስናጠቃልል:- ኢየሱስ አልተሰቀለም። በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስምምነት ያለው የስቅለት ቅጣት መኖሩን እኛም አንክድም። ክርስቶስ መሆኑ ላይ ግን አንድ ወጥ አቋም ብቻ አልነበረም። ምንም ያኽል በፖለቲካዊ ተፅዕኖ ታሪክ አንዱን አቋም ብቻ በሰፊው ቢያቀርብም የእርሱ አለመሰቀል በጥንታዊያኑ ዘንድም ይታመን ነበር። ታሪክ ያን መናገሩም በወቅቱ ከነበረው ከአይሁዳውያን ንግግር የተነሳ በመሆኑ የሚጠበቅ ነገር ነው። ይህ ደግሞ የቁርኣኑን ሀሳብ የሚደግፍ እንጂ በፍጹም የሚቃረን አይደለም። የኢየሱስ አለመሰቀል በመለኮታዊው ራዕይ የተገለጠ ነው።
-------------------------------------------------
®Sαlαh Responds 🖋
▸ www.tgoop.com/mahircomp123
BY Sαlαh Responds ⛉
Share with your friend now:
tgoop.com/mahircomp123/6129