tgoop.com/markonalfikru/858
Last Update:
በዚህ መሆን ለኛ መልካም ነው⛪️
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ሰላም ላንተ ይሁን ፥ የታቦር ተራራ
የተገለጠብህ ፥ የአምላክ ድንቅ ስራ
ቅዱሱ ተራራ ፥ የምስጢራት ደብር
ግርማው የታየብህ ፥ በገናና ክብር
ልብሱ ነ....ጭ ሆነ ፥ ድንገት ተለወጠ
አንደ ፀሐይ በራ ፥ ምስጢር ተገለጠ
ቡሄ ቡሄ በሉ ፥ ሰዎች ተደሰቱ
ጨለማ ሲገፈፍ ፥ ሲነጋ ሌሊቱ
ከክህደት የሚያድን፥ ከጥርጥር መንፈስ
እውነት በዚያ ታይቷል፥ ልብን ሞልቶ ሚፈስ
ለፈሪሳውያን ፥ ለአዋቂ ነን ባዮች
በሙሴ ህግ አለን ፥ ተከራካሪዎች
እነሙሴ መጥተው ፥ ለርሱ መሰከሩ
ኋላ መገለጡን ፥ ቀድመው እንዳወሩ
አንድም ስለሰው ልጅ፥ ስለ ማንነቱ
ልባቸው ለሚስት ፥ ስለ አምላክነቱ
ኤልያስ ነህ ለሚሉት፥ ኤልያስ መጣላቸው
ሙሴ ለሚሉትም ፥ ሙሴን ጠራላቸው
የሚያነሳ የሚያኖር ፥ ፈጣሪ አምላካቸው
ከያሉበት ጠርቶ ፥ በዚያ አስቆመላቸው
ኤልያስም አለ..............
ዮርዳኖስን ብከፍል፥ ሰማይን ብለጉም
ምልክትን ባደርግ ፥ እሳትን ባወርድም
ኃይልን ብጎናፀፍ ፥ ጠላትን ባርድም
አምላኬን በኔ ስም ፥ ሲጠሩት አልድም
ብሎ መሰከረ ፥ ልቡ እየተነካ
ጌታው በርሱ መጠን ፥ ስለማይለካ
ሙሴም እንዲህ አለ ...........
በሲና በረሃ ፥ ከላይ መና ባወርድ
ከአለት ውሃ ባፈልቅ ፥ ደመናን ብጋርድ
ታምራትን ባደርግ ፥ ባህርን ብከፍልም
የአባቶቼን አምላክ ፥ ጌታን አላኽልም
የአብርሐምን አምላክ ፥ በርሱ ልክ አሎንም !!
አንኳን መሆን ቀርቶ ፥ ያሰቡት ለምን ነው ?
ጌታን #ማየት እንኳን ፥ እጅግ መታደል ነው
ብሎ ተናገረ...... ፥ ስለ አማኑኤል ክብር
በአምሳለ ተዋህዶ ፥ በምጢሩ ደብር
አንድም አሮን እና ፥ ማርያም እህቱ
በሲፓራ ዮቶር ፥ በኢትዮጵያዊቱ
ሙሴን ቢያቆጣቸው፥ ጥቁሯን በማግባቱ
እግዚአብሔር አለ.........
ባርያዬን በቤቴ ፥ እኔ ሹሜዋለሁ
ነብያት ባስነሳ ፥ ምሳሌ እሰጣለሁ
አልያም በራእይ ፥ ሆኘ አገለጣለሁ
ሙሴን ግን ዝምበሉት ፥ እኔ እታየዋለሁ
አፍለአፍ በግልጥ ሆኜ፥ አናግረዋለሁ
ብሎ ስለነበር ፥ ትንቢት ተፈጸመ
አፍለአፍ ተናገሩ ፥ በግልፅ አብሮት ቆመ
አንድም የህያዋን ፥ የሙታን አምላክ ሲል
ኤልያስ ከህያዋን፥ ሙሴን ከመቃብር
የነብያት እና ፥ የሐዋርያት ጭምር
ጥንት የነበረና፥ ዘለዓለም የሚኖር
በአልፋና ኦሜጋ ፥ በ'ውነተኛው ባ'ንዱ
ብሉይና ሐድስ ፥ እዚያው ተዋሐዱ
በአንድ እምነት ሆነው፥ በፊቱ ሰገዱ
አንድም የስላሴ ፥ ምስጢር ተገለጠ
በብሩህ ደመና ፥ አብ ድምፁን ሰጠ
እኛም ከወልድ ጋር፥ ባንድ ቆመን ሳለን
የምወደው ልጄን ፥ እርሱን ስሙት አለን
በብርሃን አምሳል ፥ መንፈስ ቅዱስ ታየን
ልጅም በአባቱ ዘንድ፥ ያለውን ክብር አየን
ለማይጠፋ እርስቱ ፥ ለመንግሥቱ ለየን
አንድም ነገረ ጾም ፥ ለሚጠራጠሩ
አርባ ቀንና ሌት ፥ በጾም የከበሩ
ሙሴና ኤልያስ ፥ ሁለቱ ተጠሩ
የተራራው ምስጢር ፥ ተገልጦ ያየነው
ቢቀኙት አያልቅም ፥ እጅግ የበዛ ነው
ቢነገር > > >> >> >> !
ከአለም ተረት ተረት፥
ከሌለው መሰረት
ከይሆናል ግምት ፥
ውልየለሽ መላ-ምት
ከይምሰል ብልሃት ፥ ከልብ-ወለድ ትርክት
ኑ በዚህ ተራራ.........!!
ኑ ቃሉን እንስማ ፥ እንኑር በርሱ እቅፍ
ከወጀብ ማዕበሉ ፥ ከነፋስ እና ጎርፍ
በአለም ከምናየው.. ..
ከጥፋት ርኩሰት ፥ እንሽሽ እንትረፍ
ከሚጋየው መቅሰፍት ፥ እናምልጥ እንለፍ
በማደሪያው ገብተን ፥ በቅዱሱ መቅደስ
ከዘርፋፋው ልብሱ ፥ ዳስሰን እንፈወስ
ኑ በዚህ ተራራ.... ...
ከቅዱሳን ጋራ ፥ አንቁም በኅብረት
ቤተ ክርስቲያንን ፥ ቅጥሯን እንሙላት
ለጥያቄያችን መልስ፥ ወደ የሚገኝባት
የሚያለቅሱት እምባ ፥ የሚታበስባት
የታመሙት ሁሉ ፥ የሚፈወሱባት
ያቀረቀሩትም ፥ ቀና የሚሉባት
ጥላቻ ያይደለ ፥ ፍቅር የነገሠባት
ከሁከት የራቀች ፥ ሰላም የበዛበት
በዚች መሆን ለኛ ፥ መኖሩ መልካም ነው
አምባ መጠጊያችን ፥ክርስቶስ በርሷ ነው
ኑ በዚች ተራራ........
ልባችሁ አይፍራ!
ከሊቅ እስከ ደቂቅ
ትንሽ እስከ ትልቅ ፥ ከእቅልፍ ተነሱ
የእምነት ጋሻችሁን ፥ ሰይፋችሁን አንሱ
ተቃዋሚው በዝቷል ፥
ፍቅር ከአለም ጠፍቷል
ገንዘብ አምላኪና ፥ ርኩሰቱም ታይቷል
አሳዳጃችንም ፥ ጠላት አፉን ከፍቷል
ኑ በዚች ተራራ ...........
ልባችሁ አይኩራ
ለሰላሟ መርከብ ~ ለዚች ላ'ማናዊት
ካባችሁ እስኪወድቅ ~ እንደ ቅዱስ ዳዊት
እንዘምር ለጽዮን~ለመአምላክ ለእናቱ
አድስ ቅኔ እንቀኝ ~ እንውደቅ በፊቱ
ማደርያውን እና ~ ስሙን እናወድስ
የጠላትን ቅጥር ~ በእልልታ እንደርምስ
እምዬ ኦርቶዶክስ ፥ እናት ተደፍራለች
በጠላት እጅ ወድቃ ፥ ልጆቼን ትላለች
ንፁሐን ልጆቿ ፥ እምነቴን ስላሉ
ደማቸው ፈሰሰ ፥ በገፍ ተገደሉ
የቀጥተኛዋን ፥ መንገድ የሚያፈርሱ
የዳቢሎስ ልጆች ፥ አጥፊዎች ተነሱ
በግፍ የሚጠሏት ፥ አሳዳጆች በዙ!
የገዛ ልጆቿም ፥ እንደ እርብቃ ማህፀን
እኔ'በልጥ እኔ'በልጥ፥ ብኩርና ሽተን
ባ'ንድ እትብቷ ታስረን ፥ በሆዷ ተኝተን
ለማያልፈው መንግሥት ....
ህዝብ የምንሆነውን ፥ ዓላማ ዘንግተን
ለዚያውም ትልቁን ...
የሰማይ አርማውን ፥ መስቀሏን አንግተን
በምድራዊ ሀሳብ ፥ ክልል እና ወሰን
ላላፊ እና ጠፊ ፥ ለማትረባዋ አለም
በቅድስቲቱ ምድር ፥ በዳግማዊት ሳሌም
ያልተሰማ ሮሮ ፥ ያልታየ ጉድ የለም
አቤቱ ዝም አትበል!!
ጌታ ሆይ ዝም አትበል ፥ ይህ እስከመቼ ነው ?
የቀድሞ ምህረትህ፥ ይቅርታህ ወደትነው?
ለያህዌ ለአዶናይ......
ለእግዚአብሔር ኤልሻዳይ፥ ሁሉ ለሚቻለው
እባክህ አሁን አድን ፥
አሁን አቅና እያልን ፥ እንድንማፀነው
በአንድ ልብ ሆነን ፥ እንድንለምነው
በዚህ መሆን ለኛ ፥ መኖሩ መልካም ነው።
✍️,,,,,,,,,,,, ማሩ አብዬ
ነሐሴ 12/2012 ዓ.ም
BY 📜መንፈሳዊ ግጥሞች📜MENFESAWI GITMOCH
Share with your friend now:
tgoop.com/markonalfikru/858