tgoop.com/medianews123/96
Last Update:
#Update
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ከመጋቢት 17 እስከ መጋቢት 18 የሚያካሂደውን 2ኛ መደበኛ ጉባኤው ዛሬ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምራል።
በዛሬው ዕለት በነበረው የጉባኤው ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር የሆኑት ፕ/ር መረራ ጉዲና ንግግር አድርገዋል።
ፕ/ር መረራ በንግግራቸው " በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ የኦሮሞ ወጣት (ቄሮና ቀሬዎች ) የደም ዋጋ ከፍሎበታል። ብዙዎችን አጥተንበታል " ብለዋል።
" ለውጡ መጥቶ አዲስ መንግስት ተመስርቶ ወንድሞቻችን ወደ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ሲገቡ ትንሽ ስራቸው አሳስቦኝ በግፋ በለው ባይሄዱ አልኩኝ " ያሉት ፕ/ር መረራ " በዚያ በግፋ በለው መንገድ በመሄዳቸው በእነዚህ አራት ዓመታት ሀገራችንንም ሆነ ህዝባችንን ብሎም ፓርቲያችንን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለዋል " ሲሉ ተደምጠዋል።
" ከምንም በላይ ደግሞ ምርጫውን ያለ ብሄራዊ መግባባት ብናደርግ ሰላም እና መረጋጋትን እድገት እና ብልፅግናን ብሎም ዴሞክራሲን አያመጣም በፈጣሪ ስም ወደ ብሄራዊ መግባባት እንሂድ ብለን ጠይቀን ነበር " ብለዋል።
" ነገር ግን በእንቢተኝነት ተሄደበት ውጤቱ ደግሞ የምታዩት ነው ፤ ኃይል በእጃቸው ያለው አይሆንም እኛ በቀድሞ ህግ መሰረት ነው የምንሄደው ብለው ምርጫ አካሄዱ ያ ደግሞ ጦርነት መዘዘ " ሲሉ ተናግረዋል።
ፕ/ር መረራ " ጦርነቱ እንዳይጀመር ተማፅነናል " ያሉ ሲሆን " ከተጀመረም እንዳይቀጥል በተደጋጋሚ ነው የጠየቅነው አሁን ያ ሁሉ ህይወትና ንብረት ወድሞ ወደእርቅ ተመጥቷል " ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ ፤ 2014 ዓ/ም ላይ ከተካሄደው ምርጫ ተገፍተው መውጣታቸውን ገልፀው የፓርቲያቸው ጥያቄ የነበረው እውነተኛ የምርጫ ቦርድ ፣ ምህዳሩ የሰፋ የፖለቲካ ስርዓት እንደነበር አስረድተዋል።
የሃጫሉን ህልፈት ተከትሎ የፓርቲው አባላት እና አመራሮች ወደ እስር ቤት መታጎራቸውን ፤ ከ206 ፅህፈት ቤቶችም 203ቱን መዘጋታቸውን ይህን ተከትሎ ተገፍተው ከምርጫ መውጣታቸውን ገልፀዋል።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ በትግራይ ምርጫ እንዳልተካሄደና በኦሮሚያም አንድ ፓርቲ ከራሱ ጋር መወዳደሩን አንስተዋል።
በመጨረሻ ፕሮፌሰር መረራ " ሰሞኑን መንግስት ከህወሓት ጋር ጦርነቱን አቁሞ ወደ ብሄራዊ መግባባት እንሂድ እየተባለ ነው የሚገኘው የኛዎቹስ ? ኦነግ ሸኔ የተባሉትን በአንድ ወር እናጠፋለን እያሉ ነው በጦርነቱ ማንም ያሸንፍ ማን የኦሮሞ ህዝብ ግን የከፋ ዋጋን ያስከፍለዋል በፈጣሪ ስም አስቡበት በሏቸው። " ሲሉ ተደምጠዋል።
ፓርቲያቸው ለሰላም በሚደረገው ትግል፣ ለሀቀኛ ዴሞክራሲ በሚደረገው ትግል፣ ይሄን ሀገር ለመለወጥ እና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
BY MEDIA NEWS
Share with your friend now:
tgoop.com/medianews123/96