tgoop.com/melkam_enaseb/1326
Last Update:
ደስተኛ ለመሆን የሚያግዙ አምስት ልማዶች!
የስነልቦና ባለሙያዎች ማንኛውም ሰው በቀላሉ ተግብሯቸው ደስተኛ ሊሆንባቸው የሚችሉ በሚል የዘረዘሯቸውን አምስት ልማዶች እንመልከት፡፡
1. ለሰዎች ደግ መሆን ወይም በጎ ማድረግ
ሰዎች ካላቸው ነገር ላይ ቀንሰው ለሰዎች በጎ ነገርን ማድረግ ደስታ ከሚፈጥሩ የመኖር ትርጉም ጥያቄን ከሚመልሱ ልማዶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከመልካምነት በመነጨ ስሜት ለሌሎች ሰዎች የሚደረግ መልካምነት ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ አመስጋኝ እንዲሆኑ፣ በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ስለራሳቸው መልካም ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
በዚህ ምግባር ምክንያት በማህበረሰብ ውስጥ እና በሚገኙበት አካባቢ ሰዎች የሚሰጧቸው አክብሮት እና ተቀባይነት ስለሚጨምር በሰዎች ዘንድ መወደዳቸው ደስታን ይፈጥራል ተብሏል፡፡ ትንሽ የሚባል የደግነት ምግባር የለም የሚሉት የስነልቦና ተመራማሪዎቹ ሰዎች አካባቢያቸውን በደንብ ቢቃኙ መልካም ለመሆን ገንዘብ ማውጣት የማይጠይቁ ምግባሮችን ያገኛሉ ብለዋል፡፡
2. አመስጋኝነት
ምስጋና በሀይማኖታዊው ትእዛዛትም በጎ ምግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ስለተሰጣቸው ነገር የሚያመሰግኑ ሰዎች ስለጎደላቸው ስለማይጨነቁ እንዲሁም በቁሳቁሳዊ ጉዳዮች ራሳቸውን ለማነጻጸር ጊዜ ስለማይኖራቸው ደስተኞች መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ሰዎች ወደ መኝታቸው ከማቅናታቸው በፊት አልያም ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ሲወያዩ አመስጋኝ ስለሆኑባቸው፣ በሕይወታቸው ስለተሰጧቸው ነገሮች ማመስገንን ልማድ ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡ ለምሳሌ በነጻነት መንቀሳቀሳቸው፣ በህመም አልጋ ላይ ባለመዋላቸው፣ ሙሉ አካል እና ሙሉ ጤና ስላለቸው እንዲሁም ለሌሎች ውድ የሆኑ እነርሱ ጋር ግን ያሉ ነገሮችን በመቁጠር አመስጋኝ እንዲሆኑ ይመከራል፡፡
3. መልካም ግንኙነትን ከሰዎች ጋር መመስረት
የሰው ልጅ በምድር ላይ ብቸኛ ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፡፡ ከቤተሰብ፣ ከልጆች፣ ከጎረቤት፣ ከጓደኛ በአካባቢ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ግንኙነትን የተቃና ማድረግ የደስተኛነት ሚስጥር ከሆኑ ልማዶች መካከል አንዱ ተደርጎ ተጠቅሷል፡፡
ሰዎች ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር አካባቢያቸው ከጭንቀት እና ድብርት እንዲሁም ያለመፈለግ ስሜትን ስለሚያጠፋ ለመኖር ተጨማሪ ምክንያትን የሚያክል ነው ሲሉ የስነ ልቦና ተመራማሪዎች ተናግረዋል። በችግር እና ደስታ ጊዜ በአቅራቢያ የሚገኝ ሰው መኖር እንዲሁም በወዳጆች መከበብ ሰዎች ደህንነት እና በራስ መተማመን እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
4. መልካም ዜናዎችን በተገቢው መጠን ማጣጣም
በርካታ የጭንቀት እና የሀዘን ዜናዎች በሞሏት አለም ውስጥ መልካም ዜናዎች ከብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ የሚገኙ በመሆናቸው በልካቸው መከበር ይገባቸዋል፡፡ በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ መልካም አጋጣሚዎችን እና የስኬት ወሬዎችን ከቅርብ ሰዎች ጋር በመሰባሰብ ማክበር ህይወት አንድ አይነት እና አሰልቺ እንዳትሆን ከማገዙም በላይ በተሰፍ የተሞላ ነገ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በዚህም በስራ እና በህይወት ስላጋጠሙን ስኬቶች ደስታን በተገቢው መንገድ መግለጽ ይመከራል፡፡
5. ከሰዎች አለመጠበቅ
ለሰዎች ስኬት እና ውድቀት ቀዳሚ ሃላፊነቱን የሚወስዱት ራሳቸው ናቸው። መልካም ወዳጅነትን መመስረት ለደስተኛነት ወሳኝ ቢሆንም ደስተኛነት በሰዎች ላይ መንጠልጠል አይኖርበትም፡፡
ለሰዎች በሰጠናቸው መጠን ምላሽ የምንጠብቅ ከሆነ የታሰበው ሳይሆን ሲቀር ደስተኛ አለመሆንን እና ስለራስ መጥፎ ስሜት እንዲሰማ በማድረግ ከሰዎች መራቅን እና ብቸኝነትን ያስከትላል፡፡ በመሆነም ደስተኛ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች የደስተኘነት ምክንያታቸው በሰዎች ላይ መመርኮዝ የለበትም ይላሉ የሰነ ልቦና ባለሙያዎች።
Via: Alain
@melkam_enaseb
BY Psychology (ሥነ-ልቦና) Zone 🧠
Share with your friend now:
tgoop.com/melkam_enaseb/1326