tgoop.com/memhrochachn/1762
Last Update:
"ጋብቻ ለመመስረት ያሰበ አንድ ወጣት ከቤተሰብና ከጓደኞቹ ጋር ተማክሮ ከጨረሰ በኋላ የመንፈስ አባቱ ዘንድ በመሔድ ይህንን ውሳኔውን አስረዳቸው፡፡ ጥበበኛውም አባት ለማግባት ያለውን ጉጉት በልጁ ፊት ላይ እያስተዋሉ አሳቡ መልካም እንደሆነ ገልጸው ማስታወሻና ብዕራቸውን በማውጣት “ስለ ልጅቷ ትንሽ ነገር ንገረኝ” በማለት ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ እርሱም እንዲህ አለ “ትውልዷ ከነገስታት ዘር እድገቷም በምቾት መሐል ነው” አለ፡፡ እኚህም አባት በሙሉ ልብ ሆነው በያዙት ማስታወሻ ላይ ዜሮ ጻፉ፡፡
ወጣቱም ስለ ልጅቷ ማብራራቱን ቀጠለ፡- “በጣም ውብ ናት” አለ፡፡ እርሳቸውም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡ “በጣም ዝነኛ ናት” አለ፡፡ ደግመው ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡ “በጣም ሀብታም ናት” አለ፡፡ ጥበበኛውም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ምሁር ናት” አለ፡፡ አሁንም ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡
“በጣም ዘመናዊ ናት” አለ፡፡ ተጨማሪ ሌላ ዜሮ ጻፉ፡፡ በመጨረሻ ግን የረሳውን አንድ ነገር ነገራቸው “ልባም እንዲሁም ሕይወቷ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የተሰጠ ነው” አላቸው፡፡ ጥበበኛውም አባት ፊታቸው ላይ ፈገግታ እየተነበበባቸው አስቀድሞ ከጻፉአቸው ስድስት ዜሮዎች ፊት አንድ ቁጥርን ጽፈው “በል ሂድና አግባት” አሉት፡፡ ወጣቱም በደስታ ከፊታቸው ሄደ፡፡
ጋብቻ ብዙ ጊዜም በሌላው ሰው አካላዊ ገጽታና ውጫዊ አቋም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአካላዊ ውበት መማረክ ወደ ፍቅር የሚመራ አንደኛው መንገድ ቢሆን እውነተኛ ፍቅር ግን በአካላዊ ውበት፣ በአፋዊ መስፈርት ከመሸነፍ ያለፈ ነው፡፡ አካላዊ ውበት የጊዜያዊ ጉጉት መገለጫ ሲሆን ፍቅር ግን በሌላው ውስጥ ያለውን መልካሙን ነገር በመሻት ትዕግስትን መሰረት የሚያደረግ ነው፡፡ይህም የትኛውንም ልብ የመንካት፣ በላቀና በጠለቀ መንገድ የመግዛት ጉልበት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በዘመኑ የሚያሳልፋቸው ትልልቅም ይሁን ትንን ውሳኔዎች አሉ፡፡ ሕይወትም በዚህ የዕለት ተዕለት ቋሚ የመምረጥና የመወሰን ተግባር ላይ የተመሰረተች ናት፡፡ ጋብቻ የእኛን ትልልቅ ውሳኔ ከሚፈልጉ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ የምናመልከውን እንመርጣለን፣ የምንኖርበትን አካባቢ እንመርጣለን፣ የልባችንን የምናካፍለው ባልንጀራ እንመርጣለን፣ በትዳር አጋር የሚሆነንን እንመርጣለን፣ በአጠቃላይ መሆን የምንፈልገውን እንመርጣለን፡፡ በእርግጥ ምርጫችንን ከምንኖረው በላይ ተጽእኖ ወደ ኑሮአችን የሚያመጣውን መኖራችን ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህም ውስጥ ከእውነት ጋር ያለን ትስስር ሊደበዝዝ አይገባም፡፡ ምርጫችን ውስጥ ሞትም ሕይወትም፣ ደስታም ሀዘንም፣ ክብርም ውርደትም አለ፡፡ መርጠን ዘመናችንን የእንባ ልናደርገው መብቱ የእኛ ነው፡፡"
BY የዕንቁ መምህሮቻችን ትምህርቶች🔥
Share with your friend now:
tgoop.com/memhrochachn/1762