tgoop.com/memhrochachn/1774
Last Update:
“በቤት ውስጥ በሚስትህ ምክንያት አንድ ደስ የማያሰኝ ስሕተት ቢፈጠር ‘አይዞሽ’ ልትላት ይገባል እንጂ ኀዘኗን ልታባብሰው አይገባህም፡፡ ኹሉንም ነገር ብታጣም እንኳን ከጎኗ ኹን፡፡ እርግጥ ነው ለባልዋ ደንታ ከሌላት ሚስት በላይ ምንም አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ በእናንተ መካከል ጸብ ክርክር ከሚፈጥር የሚስትህ ጥፋት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ስለዚሁ ዋና ምክንያት ግን ለእርስዋ ያለህ ፍቅር እጅግ ጽኑዕ ሊኾን ይገባዋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች አንዳችን የሌላችንን ሸክም እንድንሸከም የታዘዝን ከኾነ፥ ከዚህ በላይ ደግሞ አንተ የሚስትህን ሸክም ልትሸከም ይገባሃል፡፡ በመኾኑም ድኻ ብትኾን ስለዚሁ ምክንያት በፍጹም አትናቃት፡፡ ሰነፍ ብትኾን ስለዚሁ ምክንያት አስተካክላት እንጂ አታዋርዳት፡፡ እርስዋ አካልህ ነችና፤ አንተም አካልዋ ነህና፤ አንድ አካል ናችሁና፡፡ ‘ክፉ ነች፤ ቁጡ ነች፤ ራስዋን መቈጣጠር የማትችል ግልፍተኛ ነች’ ልትለኝ ትችላለህ፡፡ ስለዚሁ ጠባይዋ እጅግ ልታዝን ይገባሃል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን ጠባይ ያርቅላት ዘንድ ጸልይላት እንጂ አንተም መልሰህ አትቈጣት፡፡ ልታሳምናት ሞክር እንጂ ወደ ሙግት አትግባ፡፡ እነዚህን ክፍተቶችዋን ከእርስዋ ለማራቅ ኹሉንም ዓይነት በጎ ዘዴዎችን ተጠቀም፡፡”
“ይህን እንደማድረግ ሚስትህን የምትመታትና የምታሠቃያት ከኾነ ግን እነዚህ ሕመሞችዋ እንዲድኑ አታደርጋቸውም፡፡ ኃይለኝነት የሚወገደው በጭካኔ ሥራ ሳይኾን በየውሃት ነውና፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም ሚስትህ በየውሃት ስትይዛት ከእግዚአብሔር ዘንድ ሹመት ሽልማት እንደምታገኝ አስታውስ፡፡ ከአሕዛብ ፈላስፎች አንዱ ክፉ፣ መራራና ሥርዓት የለሽ ሚስት ነበረችው ይባላል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለምን ከእርስዋ ጋር እንደሚኖር (ለምን እንደማይፈታት) በተጠየቀ ጊዜ ጠቢቡ ሰው በገዛ ቤቱ ውስጥ የፍልስፍና ትምህርት ቤት እንዳለው ነበር የመለሰው፡፡ ‘ዕለት ዕለት በዚህ ትምህርት ቤት የምማር ከኾነ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ታጋሽ እኾናለሁ’ ነበር ያለው፡፡ በዚህ ተደነቅህን? እኔ ግን መላእክትን እንዲያውም ከእነርሱም በላይ የዋሃን ኾነን እግዚአብሔርን እንድንመስለው ከታዘዝነው ከእኛ ይልቅ አረማውያን ሰዎች ጠቢባን ኾነው ስመለከታቸው ፈጽሜ አለቅሳለሁ፡፡ ያ ፈላስፋ ሚስቱን እንዳይፈታት ምክንያት የኾነው የእርስዋ ክፉ ጠባይ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ‘ይህ ፈላስፋ ይህቺን ሴት ሚስት ትኾነው ዘንድ ያገባት ይህን ለማግኘት ብሎ ነው’ ይላሉ፡፡ አንተም ዕጮኛ ስትመርጥ በምርጫህ ተሳስተህ ክፉ ሚስት አግብተህ ከኾነ (ብታገባ) ቢያንስ ቢያንስ ይህን አረማዊ ፈላስፋ አብነት አድርገው፡፡ ሚስትህን ለማስተካከል የተቻለህን አድርግ፡፡ ክፋትዋን በሌላ ክፋት አትመልስላት፡፡ ከእርስዋ ጋር ኾነህ የትዳርን ቀንበር የምትሸከም ከኾነ ሌሎች ብዙ ረብ ጥቅሞችንም ታገኛለህና፤ መንፈሳዊ ተግባራትን ለመተግበር ቀላል ይኾንልሃልና፡፡”
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
@memhrochachn
BY የዕንቁ መምህሮቻችን ትምህርቶች🔥
Share with your friend now:
tgoop.com/memhrochachn/1774