tgoop.com/mez_tewahedo/2587
Last Update:
+ + + "እመቤታችን የያዘችው፡ የወደቀውን የአዳም ሥጋ ነው" ስለተባለው ጉዳይ፦
* * *
የቲክ ቶኩ ውዝግብ መነሻ፡ በዋናነት አክሊል የተባለ መምህር መኾኑን ሰሞኑን ተገንዝቤያለሁ። አክሊል ሳያውቅ ሊያጠፋ ይችላል። እንዲያ ከኾነ በሊቃውንት ይታረማል፤ ችግር የለውም። ችግሩ ዐውቆ እያጠፋ ከኾነ ብቻ ነው። ያ ደግሞ፡ በቅድሚያ አደጋነቱ ለራሱ ነው። እኔ ስላልተከታተልኩት ምንም ማለት አልችልም። ሊቃውንት መልስ እየሰጡበት ይመስለኛል። መልካም ውይይት ይኹንላቸው።
* * *
ይልቅ፡ በዚች አጭር ጽሑፍ ላካፍላችሁ የፈለግሁት፡ "ጥንተ አብሶ" እና "የወደቀ ሥጋ" በሚለው ዙርያ፡ በአንድ ወቅት፡ ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ፡ በኅዋ ሰሌዳቸው ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን መልስ ስላስታወስኩ፡ እሱን ላካፍላችሁ ነው። እሳቸው በረዥሙ ነው ያብራሩት። እኔ ግን፡ በማስታውሰው መጠን፡ በአጭሩ፡ በራሴ አገላለጽ ነው መልሳቸውን የምጽፍላችሁ።
* * *
"ቅድስት ድንግል ማርያም፡ የአዳም የውርስ ኃጢአት አለባት"፣ ወይም በሰሞነኛው አገላለጽ "ሞት የተፈረደበትን የወደቀውን የአዳም ሥጋ ይዛለች" የሚለው አባባል "ትክክል ነው ወይ?" ተብለው ተጠይቀው፡ ሲመልሱ፡ እንዲህ አሉ፦
"እመቤታችን፡ እንደሌላው የአዳም ዘር ኹሉ፡ እሷም 'ጥንተ አብሶ፥ ወይም አንዳች ከኃጢአት ጋር የተያያዘ እንከን አለባት' የምንል ከኾነ፥ አልያም 'መጀመሪያ ኖሮባት ከዚያ፡ አምላክ፡ እንዳይኖርባት አድርጎ ቀደሳትና፡ አደረባት' የምንል ከኾነ፡ አንድ ከባድ ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል። እሱም፦ 'ከቅድስት ድንግል ማርያም በፊት ብዙ የተባረኩና ምሳሌዋም የኾኑ ቅዱሳን ሴቶች፡ ለምሳሌ፦ ሣራ፣ ርብቃ፣ ልያ፣ ወዘተ እንደነበሩ ይታወቃል። እነርሱም እንዲሁ፡ የአዳምና ሔዋን ሥጋን የያዙና የውርስ ኃጢአት ያለባቸው ባለ እንከኖች ስለኾኑ፡ ከነርሱ መካከል አንዲቱን አንጽቶና በድንግልና አጽንቶ ሊያድርባት እየቻለ፡ ለምን፡ ድንግል ማርያም እስክትወለድ ድረስ፡ አዳምንና ልጆቹን በሲዖል 5,500 ዘመን ሙሉ ማስጠበቅ አስፈለገው?' የሚለው ጥያቄ ነው። ለዚህ መልሱ፡ ቅድስት ድንግል ማርያም፡ በሕይወት ዘመኗ ኹሉ፡ ፍጹም ፈጣሪዋን ብቻ ምርጫዋ አድርጋ በመኖሯ፡ ለአምላክ እናትነት በቅታ የተገኘች፡ ምንም የውርስ ኃጢአት የሌለባት ንጽሕት እሷ ብቻ ስለኾነች፡ እርሷ እስክትወለድ መጠበቅ ስለአስፈለገው ነው" የሚል ሃሳብ ነበረው፡ መልሳቸው።
* * *
ስለዚህ፡ ቅድስት ድንግል ማርያም የያዘችው ሥጋ፡ "ሞት የተፈረደበትን የአዳም ሥጋ" ሳይኾን፡ በአዳም ላይ ሞት ከመፈረዱ በፊት የነበረውን ንጹሕ ሥጋ ነው ማለት ነው። እንዲያ ባይኾን ኖሮ፡ "ቤዛዊተ ዓለም" አትባልም ነበር። አንድ ሰው፡ "ቤዛ" ለመባል፡ ቤዛ ከሚኾንላቸው ኹሉ የበለጠ ንጹሕ መኾን አለበት። አለዚያማ፡ "እሱም የሌላው ዕጣ ፈንታ ደረሰበት" ይባላል እንጂ፡ "ቤዛ ኾነ" አይባልም። ቅድስት ድንግል ማርያምም፡ በስደቷም፣ በኀዘኗም፣ በሞቷም፡ እንደልጇ፡ ለዓለም ሕዝብ "ቤዛ" ልትባል የቻለችው፡ የዓለም ሕዝብ የተካፈለው የውርስ ኃጢአት ተካፋይ ስላልኾነችና ከደረሰባት ነገር ኹሉ፡ አንዱም እንኳ ሊደርስባት የሚገባት ስላልኾነች ነው። ልክ እንደልጇ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ።
"ፀጋን የመላብሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ! ከሴቶች ኹሉ ተለይተሽ፡ አንቺ የተባረክሽ ነሽ" እንዳለው ቅዱስ ገብርኤል።
ምንጭ፡ ዶክተር መስከረም ለቺሳ በራሷ ዩቲዩብ ገጽ ላይ ካሰፈረች ጽሁፍ ሙሉ ለሙሉ የተወሰደ
https://www.tgoop.com/mez_tewahedo
BY የሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ መዝሙሮች

Share with your friend now:
tgoop.com/mez_tewahedo/2587