Warning: Undefined array key 0 in /var/www/tgoop/function.php on line 65

Warning: Trying to access array offset on value of type null in /var/www/tgoop/function.php on line 65
- Telegram Web
Telegram Web
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖የካቲት ፲፰ (18) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+*" ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደገ:
የአረጋዊው ቅ/ዮሴፍ የመጨረሻ ልጅ : በንጽሕናውና
ድንግልናው የተመሠከረለት : ከጸሎትና ገድል ብዛት እግሩ
ያበጠ : የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ኤዺስ ቆዾስ ሲሆን
ቁጥሩም ከ72ቱ አርድዕት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-

=>ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል
ትልቅ ሞገስ የነበረውና የጌታችን ወንድም ተብሎ የተጠራ
ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ
(የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ ጥላው የሞተችው
እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም
ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ
የምትባል እህትም ነበረችው::

+እናቱ ማርያም ከሞተች በሁዋላ ዕጉዋለ ማውታ (ደሃ
አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ
ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ
መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ
ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት
የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው::

+እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ
አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው
ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ
ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም::
ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውሃ አምጥታ
የሕጻኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ
ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል!)

+እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ9 ወራት: ከተወለደ
በሁዋላ ደግሞ ለ2 ዓመታት ሕጻኑን ያዕቆብን
ተንከባከበችው::

ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ግን ድንግል ማርያም አምላክ
ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለ25
ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ
ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና::

+ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ
ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና
ወተትን) ብቻ ነው::

ስለዚህም:-
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል
መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል)

+ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ
በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ:-
1.ለ30 ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፡፡
2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ
በመሆኑ፡፡
3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች
በመሆናቸው፡፡
4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን
"ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ
ተገኝቷልና)

+ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ
ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት
ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር
ተከተለው::

¤ከ72ቱ አርድእት ተቆጠረ
¤3 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን ተማረ
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ
ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሳኤ ሳላይ እሕል አልቀምስም" ብሎ
ማክፈልን አስተማረ
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ዻዻስ ሆኖ አገለገለ
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት
ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ
¤ሙታንን አስንስቶ: ድውያንን ፈውሶ: የመካኖችን ማሕጸን
ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተእምራትን ሠራ::
እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ
መልካሙን ገድል ተጋደለ::

+በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ
ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ
ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት
ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው"
እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት!)

+በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ
ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት
ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ አብ ወልደ ማርያም: ሥግው ቃል: እግዚአብሔር
ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት
ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው::

+ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ
ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ
አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት
የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ
መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ
ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ::

+ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው
ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ
ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ: ጸጉሩን ተላጭቶ: ገላውን ታጥቦና
ልብሱን ቀይሮ አያውቅም::

"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ::
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ::
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ::" እንዲል::

+ከጾም: ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ
አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ
(ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ
"የያዕቆብ መልዕክት" የሚለውን ባለ 5 ምዕራፍ
መልዕክት ጽፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ
ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም
ምሕረትን ይላክልን::

=>የካቲት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (የቅዱስ ዮሴፍ ልጅ : ከ72ቱ
አርድእት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ መላልዮስ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት (በአንጾኪያ
ሊቀ ዽዽስና ተሹሞ በአርዮሳውያን ብዙ ግፍ የደረሰበትና
በስደት ያረፈ አባት ነው)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

=>+"+ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ
ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ
ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን
እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ
እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም
የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ
ሥራውን ይፈጽም:: +"+ (ያዕ. 1:1)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ✞

† ታላቁ አባ መርትያኖስ †

=>አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ዕለት የተጋዳይ መነኰስ የአባ መርትያኖስ ሥጋው ከአቴና አገር ወደ አንጾኪያ የፈለሰበት ሆነ። እርሱም ሽንግላ በኃጢያት ልትጥለው በወደደች ጊዜ ከአመንዝራ ሴት ከተፈተነ በኋላ እርሱ ግን መንኵሳ በገድል እስከ ተጸመደች ድረስ ስቦ ወደ ንስሓ መልሷታል።

«« ከዚህም በኋላ መኖሪያውን ትቶላት ከሀገር ወደ ሀገር የሚዞር ሆነ ከአቴና አገርም ደርሶ በዚያ ጥቂት ቀን ኖረ ጥቂትም ታመመና በሰላም አረፈ ዜናው በግንቦት በሃያ አንድ ቀን እንደተጻፈ።

የከበረ ቴዎድሮስም ለአንጾኪያ ሀገር በከሀዲው የፋርስ ንጉሥ ዘመን ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህ አባት የካህናት አለቆችንና ምእመናንን ልኮ ሥጋውን ከአቴና አፍልሰው ወደ አንጾኪያ ከተማ አመጡት በምስጋናም እየዘመሩ አክብረው ተቀበሉት ሊቀ ጳጳሳቱም ተሳለመው በሣጥንም አድርጐ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው። በዚችም ዕለት በዓልን አደረጉለት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

=>የካቲት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ታላቁ አባ መርትያኖስ (በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

=>+"+ . . . በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ:: በመጋዝ ተሰነጠቁ:: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: +"+ (ዕብ. 11:36)

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለጻድቁ "አቡነ ክፍለ ማርያም" እና ለሰማዕቱ ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" አቡነ ክፍለ-ማርያም "*+

=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ ክፍለ-ማርያም በሐዋርያዊ አገልግሎቱ የተመሠከረለት: ለበርካታ ዓመታት በጾምና በጸሎት በአቱን አጽንቶ የኖረ: ከቅድስናው የተነሳ መላዕክት ሰማያዊ ኅብስት ይመግቡት: ውሃም ከአለት ላይ ይፈልቅለት የነበረ አባት ነው::

+በዘመኑም ረሃብ ነበርና እርሷ ሳታውቀው እናቱን በረሃብ ጠውልጋ ቢያያት በጣም በማዘኑ እንዲባርከው ከቀረበለት የሰንበት ቁርስ ለእናቱ አድልቶ ብዙ ሰጣት:: በዚሕ ምክንያት መልዐኩም ሰማያዊ ኅብስቱን አስቀረበት: ምንጩም ደረቀች::

+ጥፋቱ የገባው አባ ክፍለ-ማርያም ለ11 ዓመታት ንስሃ ገብቶ እግዚአብሔር መልሶለታል:: ከብዙ የገድል ዓመታት በሁዋላም በዚህች ቀን ተሠውሯል::

+*" ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት "*+

=>ይህን ቅዱስ "ፊልሞን መዓንዝር" ብሎ መጥራቱ
የተለመደ ነው:: እርሱ በቀደመ ሕይወቱ አዝማሪ (ዘፋኝ)
ነበርና:: ዘፋኝነት (አዝማሪነት) ደግሞ በክርስትና
ከተከለከሉ ተግባራት አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ዘፈን
(ሙዚቃ) መስማትም ሆነ ማድመጡ ኃጢአት ነው::

+ነገር ግን ሁሉ እንዲድን የሚፈቅድ ጌታችን ጥሪውን ወደ
ሁሉም ሰው በየጊዜው ይልካል:: ቅዱስ ፊልሞንም
የክርስቶስ ጥሪ የደረሰው በከንቱ የዘፋኝነት (የአዝማሪነት)
ኑሮ ውስጥ ሳለ ነው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+በ3ኛው ክ/ዘ መጨረሻ (በ290ዎቹ) አርያኖስ የሚባል
ሹም በግብጽ (እንዴናው) ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ::
ባለማወቅም ክርስቶስን የሚያመልኩ ሚሊየኖችን በሰይፍ
በላቸው:: ከዚህ ድርጊቱ መልስ ደግሞ በጣዖቱ (አዽሎን)
ፊት እያስዘፈነ ከንቱነትን ይሰዋ : ይዝናናም ነበር::

+ከዘፋኞቹ መካከል ደግሞ ይህ ፊልሞን አንዱ ሆኖ
ለዘመናት በፊቱ ተጫወተለት:: አንድ ቀን ግን እንዲህ
ሆነ:: አስቃሎን የሚባል ቅዱስ ክርስቲያን ለጣዖት
እንዲሰዋ ታዘዘ::

+ይህ አስቃሎን (አብላንዮስም ይባላል) ወንድሙን
ፊልሞንን ያድነው ዘንድ ተጠበበ:: ወደ ፊልሞን ሒዶ "እኔ
ገንዘብ እሰጥሃለሁ:: የእኔን ልብስ ለብሰህ : እኔን መስለህ
ለጣዖት ሰዋልኝ" አለው:: አስቃሎን ይህንን ያለው
ለጥበቡ ሲሆን ፊልሞን ግን "ገንዘብ ካገኘሁ" ብሎ
የባልንጀራውን ልብስ ተሸፋፍኖ ወደ ጣዖቱ ፊት ቀረበ::

+ያን ጊዜ ተሸፍኖ መስዋዕት ማቅረብ ክልክል ነውና ሹሙ
አርያኖስ ግለጡት ሲል አዘዘ:: ቢገልጡት ፊልሞን ሁኖ
ተገኘ:: መኮንኑ ገርሞት "ምን እያደረክ ነው?" ቢለው "እኔ
ክርስቲያን ነኝ" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

+ለጊዜው ሁሉም እየቀለደ መስሏቸው ነበር:: ፊልሞን
ግን ይህንን ያለው ከልቡ ነው:: ምክንያት በቅዱስ
አስቃሎን ልብስ ተመስሎ መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦለት
ነበር:: ተገልጦ ቀና ሲልም ቅዱሳን መላእክት ከበውት
አይቶ ልቡ ጸንቶለታል::

+ሹሙ አርያኖስም የቀልዱን እንዳልሆነ ሲያውቅ
"ታብዳለህ?" ቢለው ፊልሞን "ምን አብዳለሁ! ዛሬ ገና
ከእብደቴ ሁሉ ዳንሁ እንጂ" ሲል መልሶለታል:: አሕዛብ
ሁሉ እያዩም በዚያች ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ በደመና
አምሳል ወርዶ አጥምቆታል::

+በሆነው ሁሉ የተበሳጨው ሹሙም ቅዱስ ፊልሞንን
ከክርስቶስ ፍቅር ይለየው ዘንድ ደበደበው : ገረፈው :
ጥርሱን አረገፈው : ደሙንም መሬት ላይ አፈሰሰው::
በዚህ ሁሉ ግን ጸና:: ቅዱስ አስቃሎንም ፈጥኖ መጥቶ
በመከራው መሰለው::

+በመጨረሻም 2ቱም ቅዱሳን በቀስት ተነድፈው ይገደሉ
ዘንድ ተፈረደባቸው:: ነገር ግን ለእነሱ የተወረወረ ቀስት
መንገዱን ስቶ የሹሙን (የአርያኖስን) ዐይን በማጥፋቱ
ወታደሮቹ በንዴት 2ቱንም ሰይፈው ገድለዋቸዋል::

+ዐይኑ የጠፋበት አርያኖስም ስቃዩ ሲበዛበትና
ከሚያመልካቸው የረከሱ ጣዖታት መፍትሔ ሲያጣ
ከቅዱሳኑ ደም ተቀባ:: ዐይኑም ፈጥኖ በራለት:: በዚህም
ምክንያት ምድራዊ ሹመቱን : ሃብት ንብረቱን : ትዳርና
ቤቱን : ጣዖት አምልኮውን ትቶ በክርስቶስ አምኖ
ለሰማዕትነት በቅቷል::

=>አምላከ ቅዱሳን በወዳጆቹ አማላጅነት
የምናስተውልበትን አዕምሮ አይንሳን:: በረከታቸውንም
ያድለን::

=>የካቲት 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ክፍለ-ማርያም ዘዲባጋ (የተሰወረበት)
2.አቡነ ገብረ-መርዐዊ ዘአግዶ (ኢትዮዽያዊ)
3.ቅዱስ ፊልሞን መዐንዝር (ከአዝማሪነት በክርስቶስ አምኖ ለሰማዕትነት የበቃ ቅዱስ ሰው)
4.ቅዱስ አስቃሎን አናጉንስጢስ (ሰማዕት)
5.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት (የታላቁ ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ደቀ መዝሙር)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
4.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ
5.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
6.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

=>+"+ ስትጦሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ . . . አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ: ፊትህንም ታጠብ:: በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ያስረክብሃል:: +"+ (ማቴ. 6:16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

+"+ እንኩዋን ለቅዱስ "አናሲሞስ ሐዋርያ" እና ለእመቤታችን "ቅድስት ድንግል ማርያም" በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" ድንግል ማርያም "*+

=>የአምላክ እናቱ እመ-ብርሃን ድንግል ማርያም:-
*በ3 ወገን (በሥጋ: በነፍስ: በልቡና) ድንግል
*በ3 ወገን (ከኀልዮ: ከነቢብ: ከገቢር) ንጽሕት
*ሳትጸንስ: በጸነሰች ጊዜና ከጸነሰች በሗላ ድንግል
*ጌታን ሳትወልድ : በወለደችው ጊዜና ከወለደችው በሗላ ድንግል ስትሆን እናትም ድንግልም መሆኗን አምነን እመሰክራለን::

+እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ በላይ ክብርትና ንዕድ ናት:: ሊቃውንት አበው እንዳስተማሩን በዚህ ዕለት እንዲህ ብለን እንጸልያለን::
"ረስዪ ፍና ትሕትና አእጋርየ ይሑሩ:
ትዕቢትሰ ለአምላክ ጸሩ"
(እመቤቴ ሆይ ትዕቢትን አምላክ ይጠላልና እግሮቻችን በትሕትና እንዲሔዱ አድርጊ)

+*" ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ "*+

=>በዘመነ ሐዋርያት ምስጉን ከነበሩ አበው አንዱ ቅዱስ አናሲሞስ ነው:: ስለ ቀና አገልግሎቱና መልካም እረኛነቱ አባቶቻችን ሐዋርያት አብዝተው በቀኖናቸው መስክረውለታል:: እርሱ ከኃጢአት ኑሮ ወደ ዘለዓለማዊ የቅድስና ሕይወት መጥቷልና::
¤ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

=>በሮም ከተማ የሚኖር ፊልሞና የሚባል አንድ ባለጸጋ ነበር:: ይህ ሰው በስብከተ ቅዱስ ዻውሎስ አምኖ ከርስቲያን ሆነና በመንፈሳዊ አገልግሎት ተጠመደ:: ነገር ግን ከአገልጋዮቹ መካከል ያላመነ አንድ ሰው ነበር:: "ተጽዕኖ አላደርግበትም" ብሎ ዝም ይለዋል:: ግን ክርስትና እንዲገባው ለተልዕኮ መንፈሳዊ በሚሔድበት ሥፍራ ያስከትለው ነበር::
+አገልጋዩ ግን በመለወጥ ፈንታ ሌብነትን ለመደ:: ይባስ ብሎም የአሳዳሪውን (የፊልሞናን) ገንዘብ ሠርቆ ወደ ሮም ጠፍቶ ተመለሰ:: ቅዱስ ፊልሞናም ለገንዘቡ ሳይሆን ለሕይወቱ አዘነ::

+ያ ሠርቆ የጠፋው አገልጋይ ግን በሮም ከተማ ሲመላለስ ስብከተ ወንጌልን ይሰማል:: ሰባኪው ደግሞ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ነበር:: ቁጭ ብሎ ሲማርም ልቡናው በርቶለት ተጸጸተ:: ከሐዋርያውም ዘንድ ቀርቦ ኃጢአቱን ተናዞ ተጠመቀ::
+ከዚያች ዕለት ጀምሮም ብርቱ ክርስቲያን ሆነ:: በጥቂት ጊዜም የተጋ ሰባኪ : ርሕሩሕ እረኛ ሆነ:: ፈጣሪውንም ደስ አሰኘ:: ነገር ግን ስለ አንድ ነገር ፈጽሞ ያዝን : ይተክዝም ነበር::

+የድሮ አሳዳሪው ቅዱስ ፊልሞና እንዳዘነበት እያወቀ ዝም ማለት ባያስችለው ለመምህሩ ቅዱስ ዻውሎስ ነገረው:: ያን ጊዜም ሐዋርያው በእሥራትና በግርፋት ይሰቃይ ነበር:: በሮም ሳለም አጭር ክታብ (ደብዳቤን) ጽፎ ለዚህ ደቀ መዝሙሩ ሰጠውና ወደ ቀድሞ አሳዳሪው ወደ ፊልሞና ላከው::
+ይህች ጦማር (ክታብ) ዛሬም ድረስ ከ81ዱ አሥራው መጻሕፍት : ከቅዱስ ዻውሎስ 14 መልዕክታት አንዷ ሆና ተቆጥራ እንጠቀምባታለን:: ክታቧ እጅግ አጭር ብትሆንም ምሥጢሯ ግን ሰፊ ነው::

+ያ የተላከ ክርስቲያንም ያችን ክታብ ወስዶ ለቅዱስ ፊልሞና (ለቀድሞ አሳዳሪው) አስረከበ:: ቅዱስ ፊልሞናም በደስታ አቅፎ ሳመው:: ቀድሞውንም ያዘነ በወጣቱ አገልጋይ የነፍስ እዳ እንጂ በገንዘቡ አልነበረምና:: ያ ተላኪ ሰውም በአካባቢው ሲያገለግል ቆይቶ ወደ ቅዱስ ዻውሎስ ተመልሷል:: ደቀ መዝሙሩ ሆኖም ብዙ አገልግሏል::
+#ቅዱስ_አናሲሞስ ማለት . . . የቀድሞ የሰው አገልጋይ . . . ዛሬ የክርስቶስ ባሪያ . . . ቀድሞ ሠራቂ . . . ዛሬ ግን ለመንጋው የሚራራ ሰው የሆነው ይህ ክርስቲያን ነው::

+በ67 ዓ/ም ቅዱስ ዻውሎስ መሰየፉን ተከትሎ እርሱንም አሳድደው : አሰቃይተው : ጭኑንም ሰብረው አሕዛብ ገድለውታል:: በሰማይም የሐዋርያነትና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጅቷል:: (ጢሞ. 4:6-8, ፊልሞና 1:1-25)
=>አምላከ ቅዱሳን የአናሲሞስን መመለስ : ንስሃና በረከት ያድለን::

=>የካቲት 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

1.ቅዱስ አናሲሞስ ሐዋርያ (የቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዝሙር ሲሆን ከ14ቱ መልዕክታት አንዱ የሆነው 'ወደ ፊልሞና' የተጻፈው በዚህ ቅዱስ ምክንያት ነው:: ፊል. 1:11)
2.አባ ዘካርያስ ዘሃገረ ስሃ
3.አባ አካክዮስ ጻድቅ
4.አባ ገብርኤል ሊቀ ዻዻሳት
5.አባ ገብርኤል (የኢትዮዽያ ዻዻስ)

=>ወርኀዊ በዓላት

1.ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

=>+"+ ስለ ጽዮን ዝም አልልም . . . አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ:: የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ:: በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ:: +"+ (ኢሳ. 62:1-3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† ሰማዕታተ ፋርስ †††

††† ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

ፋርስ (persia) በአሁን መጠሪያዋ "ኢራን" የምትባል: በቀደመው ዘመን የበርካታ እውነተኛ ክርስቲያኖች ቤት ነበረች:: ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ጨምሮ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን የመሰሉ አእላፍ ሰማዕታት በዚሕች ሃገር ውስጥ በ2ኛውና 3ኛው መቶ ክ/ዘመን የሰማዕትነት ጽዋዕን ጠጥተዋል:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም አባ ማሩና በተባለ ጻድቅ ሰው በዚህች ቀን ዐፅማቸው ተሰብስቦ ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል::

††† አምላከ ቅዱሳን ይራዳን: ይባርከን: ይቀድሰን:: ከወዳጆቹ በረከትም ያሳትፈን:: የቅዱሳኑን ግፍና መከራ አስቦም ከምንፈራው ጭንቅ ሁሉ ይሰውረን:: ለመንግስቱም ያብቃን::

††† የካቲት 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሰማዕታተ ፋርስ (ፍልሠታቸውና ቅዳሴ ቤታቸው)
2.ቅዱስ አባ ማሩና ጻድቅ ኤዺስ ቆዾስ (የፋርስ ሰማዕታትን አጽም የሠበሠበ)
3.ቅዱስ አባ ቡላ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
5.አባ ዻውሊ የዋህ

††† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ መራቆት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቆጠርን::'
ተብሎ እንደተጻፈው ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::" †††
(ሮሜ. 8:35-37)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞

❖የካቲት ፳፪ (22) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+" አቡነ አቢብ (አባ ቡላ) "+

+ይህን ታላቅ ቅዱስ በምን እንመስለዋለን!
*እኛ ኃጥአን ጣዕመ ዜናውን: ነገረ ሕይወቱን ሰምተን ደስ
ተሰኝተናል!
*ቅዱሱ አባታችን:- "ቡላ-የእግዚአብሔር አገልጋይ"
ብለን እንጠራሃለን::
*ዳግመኛም "አቢብ-የብዙኃን አባት" ብለን እንጠራሃለን::

+እርሱ ቅሉ አባትነትህ አንተን ለመሰሉ ቅዱሳን ቢሆንም
እኛን ኃጥአንን ቸል እንደማትለንም እናውቃለን::
*አባ! ማነው እንዳንተ የክርስቶስን ሕማማት የተሳተፈ!
*ማን ነው እንዳንተ በፈጣሪው ፍቅር ብዙ መከራዎችን
የተቀበለ!
*ማንስ ነው እንዳንተ በአንዲት ጉርሻ አማልዶ ርስትን
የሚያወርስ!
*የፍጡራንን እንተወውና በፈጣሪ አንደበት ተመስግነሃልና
ቅዱሱ አባታችን ላንተ ክብር: ምስጋናና ስግደት በጸጋ
ይገባሃል እንላለን::

+" ልደት "+

+አባታችን አቡነ አቢብ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/
ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ ሮሜ ናት::
ወላጆቹ ቅዱስ
አብርሃምና ቅድስት ሐሪክ እጅግ ጽኑ ክርስቲያኖች ነበሩ::
ልጅ ግን አልነበራቸውም:: ዘመነ ሰማዕታት ደርሶ ስደት በሆነ ጊዜ እነርሱም በርሃ ገቡ::

+በዚያም ሳሉ በቅዱስ መልአክ ብሥራት ሐሪክ ጸንሳ
ብሩሕ የሆነ ልጅ ወለደች:: ቅዱሱ ሕጻን ሲጸነስ ማንም
ሳይተክለው
የበቀለው ዛፍ ላይ መልአኩ እንዲህ የሚል የብርሃን
ጽሑፍ ጽፎበት ወላጆቹ ዐይተዋል::
"ቡላ ገብሩ ለእግዚአብሔር: ወቅዱሱ ለአምላከ ያዕቆብ:
ዘየኀድር ውስተ ጽዮን"

+" ጥምቀት "+

+ቅዱሱ ሕጻን ከተወለደ በኋላ ሳይጠመቅ ለ 1 ዓመት
ቆየ:: ምክንያቱም ዘመኑ የጭንቅ ነውና ካህናትን እንኳን
በዱር
በከተማም ማግኘት አይቻልም ነበር:: እመቤታችን ግን
ወደ ሮሙ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሰለባስትርዮስ ሒዳ
'አጥምቀው' አለችው::

+ወደ በርሐ ወርዶ ሊያጠምቀው ሲል ሕጻኑ ተነስቶ:
እጆቹንም ዘርግቶ:- "አሐዱ አብ ቅዱስ: አሐዱ ወልድ
ቅዱስ አሐዱ
ውዕቱ መንፈስ ቅዱስ" ብሎ አመስግኖ ተጠመቀ::
ከሰማይም ሕብስና ጽዋዕ ወርዶላቸው ሊቀ ዻዻሳቱ
ቀድሶ ሁሉንም
አቆረባቸው:: የሕጻኑ ወላጆች "ለልጃችን ስም አውጣልን"
ቢሉት "ቡላ" ብሎ ሰየመው:: እነርሱም ምሥጢሩን ያውቁ ነበርና አደነቁ::

+" ሰማዕትነት "+

+የቅዱሱ ቡላ ወላጆች ለ10 ዓመታት አሳድገውት ድንገት
ሕዳር 7 ቀን ተከታትለው ዐረፉ:: ሕጻኑን የማሳደግ
ኃላፊነትን
የአካባቢው ሰዎች ሆነ:: ሕጻኑ ቡላ ምንም የ10 ዓመት
ሕጻን ቢሆንም ያለ ማቁዋረጥ ሲጾም: ሲጸልይ ክፉ
መኮንን
"ለጣዖት ስገዱ" እያለ መጣ::

+በዚህ ጊዜ በሕጻን አንደበቱ አምልኮተ ክርስቶስን ሰበከ:: በዚህ የተበሳጨ መኮንኑ ስቃያትን አዘዘበት:: በጅራፍ ገረፉት: በዘንግ ደበደቡት: ቆዳውን ገፈፉት: በመጋዝ ቆራርጠውም ጣሉት:: ነገር ግን ኃይለ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና 2 ጊዜ ከሞት ተነሳ:: በመጨረሻ ግን ሚያዝያ 18 ቀን ተከልሎ ሰማዕት ሆኗል::

+" ገዳማዊ ሕይወት "+

+ቅዱስ ቡላ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል በአክሊላት አክብሮ ወስዶ በገነት አኖረው:: ከሰማዕታትም ጋር ደመረው:: በዚያም ቡላ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተመልክቶ ተደነቀ:: መንፈሳዊ ቅንዐትን ቀንቷልና "እባክህን ወደ ዓለም መልሰኝና ስለ ፍቅርህ እንደ ገና ልጋደል" ሲል ጌታን ለመነ::

+ጌታችን ግን "ወዳጄ ቡላ! እንግዲህስ ሰማዕትነቱ
ይበቃሃል:: ሱታፌ ጻድቃንን ታገኝ ዘንድ ግን ፈቃዴ ነውና ሒድ" አለው:: ቅዱስ ሚካኤልም የቅዱስ ቡላን ነፍስ ከሥጋው ጋር አዋሕዶ: ልብሰ መነኮሳትንም አልብሶ ግብጽ በርሃ ውስጥ አኖረው::

+" ተጋድሎ "+

+አባ ቡላ ወደ በርሃ ከገባ ጀምሮ ዐርብ ዐርብ የጌታን
ሕማማት እያሰበ ራሱን ያሰቃይ ገባ:: ራሱን ይገርፋል:
ፊቱን
በጥፊ ይመታል: ሥጋውን እየቆረጠ ለአራዊት ይሰጣል:
ከትልቅ ዛፍ ላይ ተሰቅሎ ወደ ታች ይወረወራል::

+በጭንቅላቱ ተተክሎ ለብዙ ጊዜ ጸልዮ ጭንቅላቱ
ይፈሳል:: ሌላም ብዙ መከራዎችን የጌታን ሕማማት
እያሰበ ይቀበላል::
ስለ ጌታ ፍቅርም ምንም ነገር ሳይቀምስ ለ42 ዓመታት
ጹሟል:: ጌታችንም ስለ ክብሩ ዘወትር ይገለጥለት ነበር::

+የሚታየውም እንደ ተወለደ: እንደ ተጠመቀ: እንደ
ተሰቀለ: እንደ ተነሳ: እንዳረገ እየሆነ ነበር:: አንድ ቀንም
ጌታችን መጥቶ "ወዳጄ ቡላ! እንዳንተ ስለ እኔ ስም
መከራ የተቀበለ ሰው የለም:: አንተም የብዙዎች አባት
ነሕና ስምህ
አቢብ (ሃቢብ) ይሁን" አለው::

"እስከ ይቤሎ አምላክ ቃለ አኮቴት ማሕዘኔ:
ረሰይከኑ ለባሕቲትከ ኩነኔ:
ዘመጠነዝ ታጻሙ ነፍስከ በቅኔ" እንዲል::

+" ዕረፍት "+

+አቡነ አቢብ ታላቁ ዕብሎን ጨምሮ በርካታ ደቀ
መዛሙርትን አፈራ:: ከእመቤታችን ጋርም ዕለት ዕለት
እየተጨዋወተ
ዘለቀ:: በተጋድሎ ሕይወቱም ከ10 ጊዜ በላይ ሙቶ
ተነስቷል:: በዚህች ቀን ሲያርፍ ገዳሙ በመላእክት
ተሞላ::
+ጌታም ከድንግል እናቱ ጋር መጥቶ "ወዳጄ ቡላ!
ስምህን የጠራውን: መታሰቢያህን ያደረገውን
እምርልሃለሁ:: አቅም ቢያጣ
'አምላከ አቢብ ማረኝ' ብሎ 3 ጊዜ በዕለተ ዕረፍትህ
የሚለምነኝን: በስምሕ እንኳ ቁራሽ የሚበላውን ሁሉ
እምርልሃለሁ"
ብሎት ነፍሱን በክብር አሳረገ: በሰማይም ዕልልታ
ተደረገ::

✞አምላከ ጻድቃን ወሰማዕት በቃል ኪዳናቸው እንዲምረን ቸርነቱ ይርዳን:: በረከታቸውንም አትርፎ ይስጠን::

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
††† እንኳን ለታላቁ ሐዋርያና ሰማዕት ቅዱስ ፖሊካርፐስ እና ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!†††

††† ቅዱስ ፖሊካርፐስ †††

†††ቅዱስ ፖሊካርፐስ:-
*ከ70 እስከ 156 ዓ/ም የነበረ::
*ዮሐንስ ወንጌላዊ በራዕዩ ከመሰከረላቸው 7ቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ (የሰርምኔስ) ዻዻስ የነበረ::
*ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቃል በቃል የተማረና ደቀ መዝሙሩ የነበረ አባት ነው::

ታላቁ አግናጥዮስ (ምጥው ለአንበሳ) የዚህ ቅዱስ ባልንጀራ ነበር:: ከ46 ዓመታት በላይ በፍፁም ትጋት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎ አረማውያን በ86 ዓመቱ በአደባባይ በእሳት አቃጥለው ገድለውታል:: አባቶቻችን "ሐዋርያዊ" ሲሉ ይጠሩታል::

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት በ1888 ዓ/ም በቅዱስ ጊዮርጊስ ምልጃና ረዳትነት አባቶቻችን አድዋ ላይ ጣልያንን ድል አድርገዋል:: ቅዱስ ጊዮርጊስን እና ደጉን ንጉሥ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን እናስባቸው ዘንድ ይገባል::

††† ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት †††

በቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር ከሆነ ቅዱሳን ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ አውሳብዮስ ነው:: ተወልዶ ያደገው በምድረ አንጾኪያ (ሶርያ) ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘ ነው:: አባቱ ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፋሲለደስ ነው:: እናቱም ቡርክት ሶፍያ ትባላለች::

ሰማዕቱ ቅዱስ መቃርስ ትንሽ ወንድሙ መሆኑም ይታወቃል:: ቅዱሳን እነ ፊቅጦር : ገላውዴዎስ : ቴዎድሮስ : ዮስጦስ : አባዲር . . . ባልንጀሮቹ ሆነው ኑረዋል::

ቅዱስ አውሳብዮስ የቅዱስ ፋሲለደስ ፍሬ ነውና ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር ሆነ:: በቤተ መንግስት ውስጥ ስንት የተደላደለና የተቀማጠለ ነገር እያለ እርሱ ግን እንደ ቡሩክ አባቱ ንጽሕናን መረጠ:: የወርቅ ካባ ደርቦ ሲሰግዱ ማደር ምን ይደንቅ!

ያ ዘመን እጅግ ግሩም የሆኑ ቅዱሳን በቤተ መንግስት የታዩበት ነበር:: ቅዱስ አውሳብዮስ በምጽዋት : በጾምና ጸሎት የሚኖር ቢሆንም በየጊዜው ወደ ጦርነት ይላክ ነበር:: ምክንያቱም እርሱ ኃያል የጦር ሰው : የሠራዊቱም ሁሉ አለቃ ነውና:: በሔደበት ሁሉም በእግዚአብሔር ኃይል ድል ያደርግ ነበር::

አንድ ጊዜም ከፋርስ ቁዝ ሰዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገቡ:: ይህንን ጦርነት በበላይነት እንዲመሩ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በኑማርያኖስ (ንጉሡ ነው) ተሹመው ወደ ሠልፍ ገቡ::

በጦርነቱ ጐዳና ላይ ሳሉ ግን አንድ አታላይ ሰላይ በጠላት እጅ እንዲወድቁ አደረጋቸው:: የተማረኩና የታሠሩ ዮስጦስና ሠራዊቱ ሲሆኑ ቅዱስ አውሳብዮስ ይህን ሰምቶ አለቀሰ:: ወደ ፈጣሪውም እየተማጸነ ለመነ::

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ አረጋጋው:: ድል መንሳትንም ሰጥቶት አደጋ ጥሎ ባልንጀራውን ዮስጦስን አስፈታው:: ጠላቶቻቸውንም እያሳደዱ አዋረዷቸው:: "ወመጠውከኒ ዘባኖሙ ለጸርየ" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ::

ከዚህ ሠልፍ በሁዋላ ቅዱሳን አውሳብዮስና ዮስጦስ በድል አድራጊነት ወደ አንጾኪያ ሲመለሱ ግን አንጀትን የሚቆርጥ ዜና ደረሳቸው:: አምላከ አማልክት ክርስቶስ ተክዶ ጣዖታት (እነ አዽሎን : አርዳሚስ) እየተሰገደላቸውም ደረሱ:: ይህንን ያደረገ ደግሞ የሰይጣን ታናሹ የሆነ ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ነው::

ቅዱሳኑንም ለጣዖት ስገዱ ሲል በአደባባይ ጠየቃቸው:: ድፍረቱ ያናደደው ቅዱስ አውሳብዮስ ግን ሰይፉን መዞ ወደ ንጉሡ ተራመደ:: ያን ጊዜ ንጉሡ ሸሽቶ ሲያመልጥ መሣፍንቱን ሜዳ ላይ በተናቸው:: አባቱ ቅዱስ ፋሲለደስ ባይገለግለው ኖሮ ኃያል ነውና ባላተረፋቸው ነበር::

ከቀናት በሁዋላ ግን ቅዱስ አውሳብዮስ በጾምና ጸሎት ሰንብቶ ሰማዕት ለመሆን ልቡ ቆረጠ:: ቅዱስ ሚካኤልና አባቱ ፋሲለደስም በምክር አበረቱት:: እርሱም በአጭር ታጥቆ በከሐዲው ንጉሥ አደባባይ ላይ ቆመ::

"እኔ ክርስቲያን ነኝ:: ክርስቶስን አመልካለሁ:: ለእርሱም እገዛለሁ:: ጣዖታት ግን ድንጋዮቸ ናቸውና አይጠቅሙም:: የሚሰግድላቸውም የረከሠ ነው::" ሲል አሰምቶ ተናገረ:: ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ እዚያው ሊገድለው ፈልጐ ነበር:: ቅዱሱ ተወዳጅ ሰው ነበርና ሁከት እንዳይነሳ አውሳብዮስ ወደ አፍሪቃ (ግብጽ) ሒዶ እንዲገደል ተወሰነበት::

በምድረ ግብጽም አረማውያን በእሳትም : በግርፋትም : በስለትም ብዙ አሰቃዩት:: ቅዱስ ሚካኤል ግን ገነትን አሳይቶ ከደዌው እየፈወሰ ተራዳው:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ገድለውት አክሊለ ክብርን ተቀዳጅቷል::

††† አምላከ ቅዱሳን ሰማዕታት ጽናታቸውን አድሎ ከበረከታቸው ይክፈለን::

††† የካቲት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ፖሊካርፐስ ሐዋርያዊ ሰማዕት (የሰርምኔስ ዻዻስ)
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት (አባቶቻችንን አድዋ ላይ የረዳበት)
3.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት (የቅዱስ ፋሲለደስ ልጅ)
4.ቅዱስ አውስግንዮስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
3.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
4.አባ ሳሙኤል
5.አባ ስምዖን
6.አባ ገብርኤል

††† "በሰርምኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልዐክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- ሞቶ የነበረው: ሕያውም የሆነው: ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል:-
'መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ . . . እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን: የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ::" †††
(ራእይ 2:8)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ አጋቢጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አጋቢጦስ †††

††† ቅዱስ አጋቢጦስ:-
*ይህንን ዓለም ንቆ ለበርካታ ዘመናት በፍፁም ምናኔ የኖረ::
*ምድራዊ ሃብትና ሹመት ሞልቶለት ሳለ ከሁሉ የክርስቶስን ፍቅር የመረጠ::
*ከደግነቱ ብዛት የተነሳ ምግብ ሲያዘጋጅ ሽምብራውን ከክቶ ለሌሎች ከሰጠ በሁዋላ ለራሱ የሚመገበው ገለባውን (አሠሩን) ነበር::

ሌሊቱን በጸሎት ለመትጋት ማታ ማታ አመድ ይመገብ ነበር:: በዚህም ቅዱስ ዳዊት "አመድን እንደ እህል በላሁ" ያለው በዚህ ቅዱስ ሕይወት ላይ ተገልጧል:: (መዝ. 101:9)

ቅዱስ አጋቢጦስ በዘመኑ ከሠራቸው ይህኛው እጅግ ይገርመኛል:: እርሱ በበርሃ የነበረበት ዘመኑ የሰማዕታት በመሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች በርጉማን መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ ተገድለዋል:: ቅዱሱን ግን በአካባቢው የነበረ ሃገረ ገዢ ከበዓቱ አስወጥቶ ወደ ውትድርና ሥራ አስገብቶታል::

ሰይጣን በዚህ ከተጋድሎና ከቅድስና ሕይወት እንደሚያርቀው ተማምኖ ነበር:: ቅዱስ አጋቢጦስ ግን በወታደሮች መካከል ሆኖም ተጋድሎውን ቀጠለ:: የጦር ሠራዊት አለቃ አድርገው ቢሾሙትም እርሱ ከበጐ ማንነቱ ፈጽሞ አልተለወጠም::

ክርስቲያን ማለት እንዲህ ነውና:: ክርስትና ሲመቸን : ሲመቻችልን : በአጋጣሚ ወይም በምክንያት የምንኖረው ሕይወት አይደለም:: ፍጹም ፍቅር የጊዜ : የቦታ : የሁኔታ ገደብ የለውምና አባቶቻችን በጊዜውም : ያለ ጊዜውም ጸንተው ክርስቶስ መድኃኒታችንን አስደሰቱ::

ከቅዱስ ዻውሎስ ጋርም እንዲህ ሲሉ ዘመሩ:- "መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ" (ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል!)

ወደ ቀደመው ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አጋቢጦስ ለዘመናት ሰው ሳይገድል : ፈጣሪውን ሳይበድል : ከጾም ከጸሎት : ከምጽዋትና ትሕርምት ሳይጐድል ኖረ:: በዚህም ሰይጣንን አሳፈረ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::

በዚህ ጊዜም ወደ በዓቱ ለመመለስ መንገድን ይፈልግ : ይጸልይም ገባ:: እግዚአብሔርም ወደ በርሃ የሚመለስበትን መንገድ በቸርነቱ አቀናለት::
ነገሩ እንዲህ ነው::
ዘመነ ሰማዕታት አልፎ ራትዕ (የቀና) ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ነገሠ:: ስደት ቆመ:: የታሠሩ ተፈቱ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጹ:: ለክርስቲያን ቀደምቶቻችንም ታላቅ ተድላ ሆነ::

ጊዜው ለሁሉ ክርስቲያን የተድላ ቢሆንም አንድ ወጣት በደዌ ሰይጣን ያሰቃየው ነበር:: ወጣቱ የንጉሡ የቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ባለሟል : ባለብዙ ሃብት : መልኩ ያማረ ነውና ሁሉ ያዝንለታል:: ይልቁኑ ቅዱሱ ንጉሥ ተጨነቀለት::

አንድ ቀን ግን ከወታደሮቹ አንዱ ያን ወጣት "አንተንኮ አጋቢጦስ ይፈውስህ ነበር" ይለዋል:: ወጣቱ ግን አላወቀምና "ከመቼ ወዲህ የጦር አለቃ እንዲህ አድርጐ ያውቃል?" ሲል በጥያቄ ይመልስለታል:: ወታደሩ ግን ቀስ አድርጐ ምሥጢሩን ይነግረዋል::

ይህ ነገር ሲያያዝ ከንጉሡ ደርሶ ቅዱስ አጋቢጦስን አስጠርቶ "እባክህ ፈውስልኝ?" ይለዋል:: "ካዳንክልኝም የፈለግኸውን አደርግልሃለሁ" ሲል ያክልለታል:: ቅዱስ አጋቢጦስም ወደ ፈጣሪው ለምኖ ሰይጣንን ይገስጸዋል:: በቅጽበትም በክርስቶስ ኃይል ወጣቱ ይድናል::

ቅዱስ ቆስጠንጢኖስም ከደስታው ብዛት "ምን ላድርግልህ?" ቢለው ቅዱሱ "ከሹመቴ ሻረኝ : ወደ በርሃ አሰናብተኝ" ብሎ መሻቱን ገለጸለት:: ቅዱሱ ንጉሥም በመገረም ቡራኬውን ተቀብሎ ወደ በርሃ ሸኝቶታል::

ወገኖቼ! . . . በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊው እርከን ስልጣንን የሚንቁ ሰዎችን ካላገኘን መፍትሔው ሩቅ ነው:: እኛም ከሥልጣን መሻት እንራቅ:: ማር ይስሐቅ እንደ ነገረን ሰይጣን ያደረበት ሰው ሹመትን (ሥልጣንን) በመሻቱ ይታወቃልና::

ቅዱሱ በፍፃሜ ዘመኑ እረኝነት (ዽዽስና) ተሹሞ ብዙ ኢ-አማንያንን ወደ ክርስትና መልሶ: ድውያንን ፈውሶ: እውራንን አብርቶ: በርካታ ተአምራትንም አድርጎ በዚህች ቀን አርፏል::

††† ልመናው በረከቱ ይደርብን::

††† የካቲት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
2.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት (ዘጋዛ)
3.ቅዱስ ሚናስ ዘቆዽሮስ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምሕረ ትሩፋት)
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)

††† "የሚያሳድዷችሁን መርቁ . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ:: ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ:: እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ:: የትዕቢትን ነገር አታስቡ:: ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ::" †††
(ሮሜ. 12:14-16)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡፋና እና ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አቡፋና †††

††† ታላቁ አባ አቡፋና፦
በምድረ ግብጽ ተጋድሏቸውን የፈፀሙ፣
በመዐልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊትም አምስት ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልዩ የነበሩ፣
በአርባ ቀን አንድ ጊዜ ብቻ እህል ይቀምሱ የነበሩና ሙሉ ዘመናቸውን በበርሃ በታላቅ ጽሙና የፈፀሙ አባት ናቸው።

ጻድቁ በጣም የሚታወቁት ከማበጡ የተነሳ እጅግ ግዙፍ በነበረ እግራቸው ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስለ መድኃኔ ዓለም ፍቅር አልቀመጥም፤ አልተኛም ብለው ለአሥራ ስምንት ዓመታት በመቆማቸው ነው።

አሥራ ስምንት ዓመት የመቆማቸው ዜናስ እንደምን ነው ቢሉ፦
አንድ ቀን "እኔ ግን ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ይሆን?" ሲሉ አሰቡ። በእርግጥ ይህንን ሐሳብ ብዙ ሰዎች ሊያስቡት ይችላል። ሐሳቡ ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው።
፩. "ጠቃሚ ነው።" ያልኩት አንድ ሰው ሞት እንዳለ ካወቀ ወይም 'መቼ ነው የምሞተው' ብሎ ካሰበ ንስሐ ይገባል፤ ክፋትን ይተዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ወገኔ ሁሉ እንደ አውሬ ሲባላ፣ ደም ሲያፈስ፣ ክፋትን ሲጐነጉን የሚውል "እሞት ባይ" ሳይሆን "እኖር ባይ" ሆኖ ነውና።
ግን ሞት በቅርቡ እንዳለ በኃያሉ አምላክ ፊት ራቁቱን ለፍርድ እንደሚቀርብ ለወገኔ ማን በነገረው!
፪. "ያልተፈቀደ ነው።" ያልኩት ደግሞ በሁለት ምክንያት ነው።
"ኢትበሉ ለጌሰም (ለነገ አትበሉ።)" የሚል አምላካዊ ቃል ስላለ።
ማቴ. ፮፥፴፬
ሰው (በተለይ ዓለማዊው) የሚሞትበትን ቀን ቢያውቅ አጭር ጊዜ ከሆነ ሽብር ጭንቀት ይበላዋል። ወዲህ ደግሞ ጊዜው ረዥም ቢሆን እንደ ሰብአ ትካት (ማለትም በኖኅ ዘመን እንደ ነበሩ ሰዎች) 'ብዙውን ልዝናናበት (ኃጢአት ልሥራበት')ና ንስሐ እገባለሁ።' ይላልና ነው።

በዚያውም ላይ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ሰውና የነቢያት አለቃ ቅዱስ ሙሴ የሞቱን ጊዜ ጠይቆ እጅግ መቸገሩን መጥቀሱ በራሱ በቂ ነው። ጌታ "ዓርብ ቀን ትሞታለህ።" ብሎት ለሁለት ዓመታት ዓርብ ዓርብ ሲገነዝ ሲፈታ ኑሯል።

በመጨረሻም ዓርብ ቀን ድንገት መልአከ ሞት መጥቶበታል። ስለዚህ "ወድልዋኒክሙ ንበሩ - ተዘጋጅታችሁ ኑሩ። መባላችንን አስበን ልንኖር ግድ ይለናል።
ማቴ. ፳፬፥፵፬

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አቡፋና ይህንን የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ "ተርፈከ አሠርቱ ወሰመንቱ - አሥራ ስምንት ቀርቶሃል።" አላቸው። እርሳቸውም "ጌታዬ አሥራ ስምንት ምን?" ሲሉ ቢጠይቁትም ሳይመልስላቸው ተሠወረ።

ከደቂቃ እስከ ኢዮቤልዩ ብዙ አሥራ ስምንቶች አሉ። እርሳቸው ግን "አሥራ ስምንት ቀን ነው!" ብለው ለጌታ ተሳሉ። ስዕለታቸውም "ከዚህ በኋላ አልቀመጥም።" የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ለአሥራ ስምንት ቀናት ቆሙ። ሞት አልመጣም።

"አሥራ ስምንት ሱባኤ ይሆን!" ብለው አሥራ ስምንት ሱባኤ (መቶ ሃያ ስድስት ቀናት) ቆመው ጸለዩ። አሁንም ሞት አልመጣም። "አይ! አሥራ ስምንት ወር ሊሆን ይችላል።" ብለው ለአሥራ ስምንት ወራት (ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር) ቆመው ተጉ። አሁንም ግን ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

ይህን ጊዜ ግን ወደ ፈጣሪ ለመኑ። "ጌታዬ! ያልከኝ ምን አሥራ ስምንት ነው?"
ቅዱስ መልአኩም መጥቶ "አቡፋና ሆይ! የቀረህ አሥራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና።" ብሏቸው ተሰወረ። ልብ በሉልኝ "እስክሞት አልቀመጥም።" ብለው ተስለዋል።

ቅዱሱ ገዳማዊ በቃላቸው የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያን ነበሩና ለአሥራ ስምንት ዓመታት እንደተተከለ ምሰሶ ቆመው ጸለዩ፣ ጾሙ። እንዲህ ያሉትን ቅዱሳን ሊቃውንት፦
"ሰላም ለከ ጽኑዕ ከመ ዓምድ
ዘኢያንቀለቅሎ ሞገድ።"
(ማዕበለ ዓለም የማያናውጸው ብርቱ ምሰሶ ሆይ! ምስጋና ይገባሃል።) የሚሏቸው።

ስለ ቅዱሱ የተጻፈ አርኬም፦
"ሰላም ለቁመተ አቡፋና ዘአልቦ ኑታጌ
እስከ ተመሰለ እግሩ ከመ እግረ ነጌ።" ይላል። ከመቆም ብዛት አካላቸው ደቆ እግራቸው የዝሆን እግር እስኪመስል ወፍሮ ነበርና።

††† አባ አቡፋና በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን አርፈዋል።

††† ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ እንጦኒ (Anthony) በትውልዱ ከሶርያ ዐረቦች ሲሆን በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ካህናትን ይደበድብ፣ አብያተ ክርስቲያናትንም ያቃጥል ነበር። እግዚአብሔር በንስሐ ሲጠራው ግን ደግ፣ ጻድቅና ምርጥ ዕቃ ሆኖ ተገኘ። በመጨረሻም ከብዙ መከራ በኋላ ለሰማዕትነት በቅቷል።

††† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ትጋት፣ ጽናት፣ ፍቅርና በረከት ያድለን። ከማስተዋልም አያጉድለን።

††† የካቲት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
፪.ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት
፫.ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞናና ሉቅያ ድንግል (የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዛሙርት)
፬.ቅዱስ ቶና ዲያቆንና ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሚናስ ዘሃገረ ቁስ

††† ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

††† "ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ። አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ። ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።" †††
(፩ጢሞ ፩፥፲፪-፲፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሆሴዕ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
¤15ቱ አበው ነቢያት:
¤4ቱ ዐበይት ነቢያት:
¤12ቱ ደቂቀ ነቢያትና
¤ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ::

"15ቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

"4ቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

"12ቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

"ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
ቅዱስ ሆሴዕ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ሆሴዕ 'ዖዝያ' በመባልም ይታወቃል:: ቅዱሱ ነቢይ የቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ-ቃል ባልንጀራ የነበረ ሲሆን በ4 ነገሥታት ዘመን (ዖዝያን : ኢዮአታም : አካዝና ደጉ ሕዝቅያስ) ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናግሯል:: የትንቢት ዘመኑም ከ70 ዓመት በላይ ነው::

ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሆሴዕ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራም በስፋት ተንብዩዋል:: 14 ምዕራፎች ያሉት የትንቢቱ ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል:: ሆሴዕ ማለት መድኃኒት ማለት ነው:: የመዳን ትምሕርትንና ትንቢትን ሊናገር ተመርጧልና::

††† ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::

††† የካቲት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሆሴዕ ነቢይ (ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት)
2.ቅዱስ ሳዶቅ ሰማዕት
3."808" ሰማዕታት (ከቅዱስ ሳዶቅ ጋር የተሰየፉ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንመለስ:: እርሱ ሰብሮናልና: እርሱም ይፈውሰናል:: እርሱ መትቶናል: እርሱም ይጠግነናል:: ከሁለት ቀን በሁዋላ ያድነናል:: በሦስተኛውም ቀን ያስነሳናል:: በፊቱም በሕይወት እንኖራለን:: እንወቅ:: እናውቀውም ዘንድ እንከተል . . . " †††
(ሆሴዕ 6:1-3)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †††

††† እንኩዋን ለታላቁ ሰማዕት "ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

+*" ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘሮም "*+

=>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

+ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

+እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

+እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

+በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

=>ቅዱስ ቴዎድሮስ በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው:: በወቅቱ መሪ የነበረው ክሀዲው መክስምያኖስ "ክርስቶስን ክደህ ለጣኦት ስገድና በከተማዋ ላይ እሾምሃለሁ" ቢለው "ለእኔ ሃብቴም ሹመቴም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" በማለቱ ንጉሡ ተቆጥቶ በብረት ዘንግ አስደበደበው::

+በመንኮራኩር አበራየው:: ለአናብስት ጣለው:: አካላቱን ቆራረጠው:: በእሳትም አቃጠለው:: ቅዱስ ቴዎድሮስ ስቃዮችን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በትዕግስት ተቀበለ:: በፍፃሜውም አንገቱን በሰይፍ ተመትቶ 3 አክሊላት ወርደውለታል::

+ከፈጣሪው ዘንድም ነጭ መንፈሳዊ ፈረስና ቃል ኪዳን ተቀብሏል:: ስሙን የጠራ: መታሠቢያውን ያደረገ ዋጋው አይጠፋበትም:: (ማቴ. 10:41)

=>አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት ይክፈለን:: አይተወን:: አይጣለን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን::

=>የካቲት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
2."6,304" ሰማዕታት (በቅ/ቴዎድሮስ አምላክ አምነው ሰማዕትነት የተቀበሉ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

=>+"+ እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን:: +"+
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. 73)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
†††እንኳን ለታላቁ ሊቅና ጻድቅ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ †††

††† ቅዱስ አንስጣስዮስ በ4ኛው ክ/ዘመን የተነሳ ሶርያዊ የነገረ መለኮት ሊቅ: ገዳማዊ ጻድቅና የመንበረ አንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ነበር:: ቅዱሱ ርጉም አርዮስን ካወገዙ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው:: በወቅቱ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ሱባኤውንና ጉባኤውን የመሩ ሲሆን አንዱ ይህ ቅዱስ ነው::

ከ 5 ዓመታት በሁዋላም ብዙ ድርሳናትን ጽፎ: ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ330 ዓ/ም አርፏል:: ያረፈው ግን አርዮሳውያን ባቀረቡት ክስ በሃሰት ተመስክሮበት በግፍ ተሰዶ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ውለታው የውዳሴ ድርሳን ጽፎለታል::

††† አቡነ ዓምደ ሥላሴ †††

††† እኒህ ታላቅ ጻድቅ ሐዋርያዊ አባት አቡነ ዓምደ ሥላሴ የትውልድ ሃገራቸው ጎጃም ሲሆን የተወለዱት በዚሁ ዕለት (የካቲት 27) ነው:: ጻድቁ በአጼ ሱስንዮስ (በ17ኛው መቶ ክ/ዘ) የነበሩ ድንቅ ሠሪ : ተአምረኛና ገዳማዊ አባት ናቸው::

የካቲት 16 ቀን መንኩሰው ወደ ተጋድሎ ገብተዋል:: በዋልድባ በነበራቸው ቆይታም እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እንድትከበር ማድረጋቸውም ይነገራል:: ጻድቁ በሌሎች ገዳማትም የነበሩ ሲሆን ዛሬም ድረስ ረድኤታቸው የሚደረግበት : ስማቸው የሚጠራበት ገዳም ግን ማኅበረ ሥላሴ ይባላል::

ገዳሙ የሚገኘው በሃገራችን ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ : በመተማ በርሃ ውስጥ ነው:: ይህንን ቅዱስ ገዳም የመሠረቱትም ራሳቸው አባ ዓምደ ሥላሴ ናቸው:: ገዳሙ ዛሬም ብዙ ምሑራንና መናንያን ያሉበት : በደህና ሁኔታም የሚገኝ ነው:: ግን በርሃውን የኔ ብጤ ደካማ ሰው የሚችለው አይደለም::

ስለ ጻድቁ ዓምደ ሥላሴ ከሚነገሩ ታሪኮች ቅድሚያውን የሚይዘው የተዋሕዶ ጠበቃነታቸው ነው:: በ1603 ዓ/ም ዼጥሮስ (ፔድሮ) ፓኤዝ የሚባል ካቶሊካዊ እሾህ ወደ ሃገራችን ገብቶ ነበርና ንጉሡን ሱስንዮስን አባብሎ ተዋሕዶን አስካዳቸው:: ነገሩ ውስጥ ለውስጥ ሲበስል ቆይቶ በ1609 ዓ/ም በመገለጡ እነ ራስ ዮልዮስ ለሃይማኖታቸው ጠዳ ላይ ተዋግተው ግንቦት 6 ቀን ተሰው::

ይህ ነገር ሲሰማ ወንድ ሴት : ትልቅ ትንሽ ሳይመረጥ በገጠሩም : በከተማውም : በገዳሙም ያሉት ሁሉ የተዋሕዶ ልጆች መንቀሳቀስ ጀመሩ:: 7 ዓመታት እንዲህ አልፈው በ1616 ዓ/ም ግጭቱ በይፋ ተጀመረ::

"ተዋሕዶን ካልካዳችሁ" በሚል በቀን እስከ 8,000 ሰው በሰይፍ ታረደ:: ይህን ያደረጉት ደግሞ አልፎንሱ ሜንዴዝ : ንጉሡ ሱስንዮስና ጀሌዎቻቸው ነበሩ::

በጊዜውም ከቤተ መንግሥት እነ ንግሥት ወልድ ሰዓላ (የሱስንዮስ ሚስት) : ከጻድቃን አበው ዘርዓ ቡሩክ ዘግሺ : ሐራ ድንግል ዘደራ : ምዕመነ ድንግል ዘጩጊ : ዓምደ ሥላሴ ዘማኅበረ ሥላሴ . . . ከቅዱሳት እነ ፍቅርተ ክርስቶስ : ወለተ ዼጥሮስ : ወለተ ዻውሎስ : እኅተ ዼጥሮስ . . . ለሃይማኖታቸው ተዋሕዶ ጥብቅና ቆመው ሕዝቡን አስተማሩ:: መከራም ተቀበሉ::

ብዙ ኢትዮዽያውያን የመከራ ጽዋን ተጐንጭተው ለክብር ከበቁ በሁዋላ የእግዚአብሔር ፍርድ ተገለጠ:: በጻድቃኑ እነ አባ ዓምደ ሥላሴ ሐዘን ንጉሡ ታመመ:: ምላሱ ተጐልጉሎ ወጣ::

በዚህ ጊዜ አቤቶ ፋሲለደስ ለአባ ዓምደ ሥላሴና ለሌሎቹ ቅዱሳን "አባቴን አድኑልኝ! ተዋሕዶም ትመለስ" አላቸው:: ጻድቁም ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጸልየው ንጉሡን አዳኑት:: በፈንታውም ይህንን አሳወጁ::

††† ፋሲል ይንገሥ!
ሃይማኖት (ተዋሕዶ) ይመለስ!
የሮም ሃይማኖት ይፍለስ! †††

ከዚህ በሁዋላ በ1624 ዓ/ም ፋሲል ሲነግሥ አባ ዓምደ ሥላሴ ለገዳማቸው ብዙ ቦታ አስከልለው : በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በቀናችው እምነት ተዋሕዶ ሁላችንም እስከ ፍጻሜ ዘመናችን ያጽናን:: ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን::

††† የካቲት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አንስጣስዮስ ርቱዓ ሃይማኖት (ዘአንጾኪያ)
2.አቡነ ዓምደ ሥላሴ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
5.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
6.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
7.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(1ዼጥ. 2:21-25)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †††

††† እንኩዋን ለታላቁ ሰማዕት "ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

+*" ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘሮም "*+

=>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

+ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

+እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

+እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

+በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

=>ቅዱስ ቴዎድሮስ በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው:: በወቅቱ መሪ የነበረው ክሀዲው መክስምያኖስ "ክርስቶስን ክደህ ለጣኦት ስገድና በከተማዋ ላይ እሾምሃለሁ" ቢለው "ለእኔ ሃብቴም ሹመቴም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" በማለቱ ንጉሡ ተቆጥቶ በብረት ዘንግ አስደበደበው::

+በመንኮራኩር አበራየው:: ለአናብስት ጣለው:: አካላቱን ቆራረጠው:: በእሳትም አቃጠለው:: ቅዱስ ቴዎድሮስ ስቃዮችን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በትዕግስት ተቀበለ:: በፍፃሜውም አንገቱን በሰይፍ ተመትቶ 3 አክሊላት ወርደውለታል::

+ከፈጣሪው ዘንድም ነጭ መንፈሳዊ ፈረስና ቃል ኪዳን ተቀብሏል:: ስሙን የጠራ: መታሠቢያውን ያደረገ ዋጋው አይጠፋበትም:: (ማቴ. 10:41)

=>አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት ይክፈለን:: አይተወን:: አይጣለን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን::

=>የካቲት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
2."6,304" ሰማዕታት (በቅ/ቴዎድሮስ አምላክ አምነው ሰማዕትነት የተቀበሉ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

=>+"+ እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን:: +"+
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. 73)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
† እንኳን ለኢትዮዽያዊቷ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† እመ ምዑዝ (እም ምዑዝ) †

††† ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ሐዋርያዊት: ጻድቅትና ሰማዕት ናት::
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-
=>ወር በገባ በ29 በቤተክርስቲያናችን ታስበው
ከሚውሉት እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳን ከገባላቸው
(ከሰጣቸው) እናቶች ኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅት
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ትገኛለች::
ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ማን ናት? ምን ቃል ኪዳን
ተሰጣት? ያደረገችውን ተጋድሎ በጥቂቱ እንመልከት:-
✞✞ ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ
ይወስዳል፡፡ (ማቴ. 10፡40) ✞✞

=>በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቂት ወረዳ ጥባ
ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና
ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ
ምዑዝ ኪዳነ ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት
ገዳም ትገኛለች፡፡

+ይህች ገዳም ከአዲስ አበባ በደሴ ወደ ጎንደር
በሚወስደው መንገድ 665 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በኋላ
ገራገር (ፍላቂት) ከምትባለው ከተማ በመውረድ በእግር
2፡30 እንደተጓዙ ከ370 ዓመት ባለይ ያስቆጠረችውን
እመ ምዑዝ ኪዳነምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በአንድ
ቀን የሠራቻትና ለጌታ በአራቱም አቅጣጫ የሰገደችውን
ታላቅና ድንቅ ቤተመቅደስ ያገኛሉ፡፡

+የዚህች ታላቅ ገዳም መስራች ኢትጵያዊት ሰማዕትና
ጻድቅ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ በደቡብ ጎንደር ደራ ፎገራ
አንበሳሜ ወረዳ ልዩ ስሙ አቡነ ሐራ ገዳም አዋሳኝ ከተታ
ማርያም ተብሎ በሚጠራ ቦታ በሚያዚያ 4 ቀን ተፀንሳ
ታህሳስ 29 በጌታ ልደት ቀን ተወለደች፡፡

+አባቷ ላባ እናትዋ ወንጌላዊት የተባሉ እግዚዘብሔርን
የሚወዱ ትዕዛዙን የሚከብሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡
መሀን ሆነው ልጅ ባመውለዳቸው እያዘኑ ተግተው ወደ
እግዚአብሔር በመፀለያቸው ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስን
የመሰለች ልጅ: በፀሎትዋ ለሀገር ለወገን የምትበቃ
ሰጥቷቸዋል፡፡

+ከዚያም 80 ሲሆናት ለልጅነት ጥምቀት ወደ ቤተ
መቅደስ በወሰዷት ጊዜ ከጥምቀት በኋላ ስጋ አምላክ
ስትቀበል (ስትቆርብ) "ሕይወት የሆነውን ቅዱስ ስጋህን
ክቡር ደምህን የሰጠኸኝ አምላኬ ክብር ምስጋና ይግባህ"
ብላ አመስግናለች፡፡ ስመ ክርስትናዋ ማርያም ፀዳለ
ሲሆን የአለም ስሟ 'ሙዚት' ነው፡፡ ፍቅርተ ክርስቶስ
የምንኩስና (የቆብ) ስሟ ነው፡፡

+እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አባ ዳንኤል ከሚባል
አባት መፅሐፍን እየተማረች ካደገች በኋላ ለአቅመ ሄዋን
ስትደርስ እናትና አባቷ ሊድሯት በመፈለጋቸው ዘርዓ
ክርስቶስ ለሚባል ከደጋግ ሰዎች ወገን ለሆነ ሰው
አጋቧት፡፡

+ማታ እንደ ሙሽሮች ደምብ ወደ ጫጉላ ቤት ሲገቡ
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ዘርዓ ክርስቶስን "ወንድሜ ሆይ!
እኔ የእናት አባቴን ፍቃድ ለመፈፀም ነው እንጂ ስጋዊ
ሙሽራ መሆን አልፈልግም ፡፡ ፍላጎቴ የእግዚአብሔር
ሙሽራ መሆን ነው" በማለት ብታማክረው ቅዱስ ዘርዓ
ክርስቶስም ፀጋ እግዚአብሔር የበዛለት ሰው ነበርና "እኔም
እናት አባቴን ላክበር ፈቃዳቸውን ለመፈፀም ነው እንጂ
የስጋ ፈቃድ የለኝም በማለት ተነጋገሩ::

+በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ ለቤተሰቦቻቸው: ለአገሬው
እንደ ባልና ሚስት ግን በንፅህና ለ40 ዓመት ሁለቱም
በድንግልና ኖረዋል፡፡

+ከዚያም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅዱስ ሚካኤል
መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቢግራቸውም ሁለቱም
"ይህስ አይሆንም" ብለው ለ40 ቀን በጾም: ፀሎት:
በትጋት ጸልየዋል፡፡ መልአኩ ተገልጦ "ይህ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ነው ሁለታችሁም ድንግልናችሁ አይፈርስም ብሎ
ነግሮአቸዋል፡፡

+ከዚያም ወንድ ልጅ ወልደዋል:: ህፃኑ በተወለደ በ7
ዓመቱ በቅዱስ ሚካኤል እቅፍ ገነትን ለ7 ቀናት ከጎበኛት
በኋላ ወደ ምድር ሲመልሰው "በእናት አባቴ አምላክ
ይዤሃለሁ ወደዚች ወደ ከፋች ዓለም አትመልሰኝ" ብሎ
ቢለምነው ቅዱስ ሚካኤልም ከአምላክ ጠይቆ በብሔረ
ህያዋን የህፃናት አለቃ ተብሎ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡
ስሙም ዳግማዊ ቂርቆስ ተብሏል፡፡

+ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶና ቅዱስ ዘርዓ ክርስቶስም ልጅ
ከወለዱ በኋላ እንደ ቀደሞው በቅድስና: በንፀህና ፀንተው
ኑረዋል፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ነግሶ የነበረው አፄ
ሱስንዮስ ሃይማኖቱን ለውጦ 'ሁለት ባህርይ የሚሉ
ካቶሊኮችን በመቀበሉ ክርስቲያኖችን እየገደለ ነው' የሚል
ወሬ ሰምተው ወደ ንጉሱ በመሄድ ሳይፈሩ ስለ ተዋህዶ
ሃማኖታቸው በንጉሱ ፊት መስክረዋል፡፡

+ንጉሱም በጣም የበዛ መከራን አድርሶባቸዋል፡፡ መከራ
በበዛ ቁጥር እነርሱም እየፀኑ ተከታዮቻቸውንና የንጉሱን
ሠራዎቶች ሳይቀር አሳመኑ:: 60,000 ክርስቲያኖችም
ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡

+ንጉሱም በጣም የበዛ መከራ አድርሶባቸዋል፡፡ መከራ
በበዛ ቁጥር እነርሱም እየጸኑ ተከታዮቻቸውንና የንጉሱን
ሰራዊቶች እያሳመኑ ቢያስቸግሩ በሰማዕትነት አንገታቸውን
አስቆርቷቸዋል፡፡ አንገታቸውም ሲቆረጥ ከሁለቱም ደም
ውሃ ወተት ፈሷዋል፡፡

+በዚያን ዘመን ከእነ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ጋር
ሰማዕትነት ከተቀበሉት ውስጥ የማህበረ ስላሴው ጻድቁ
አምደ ስላሴ: የጎረጉር ማርያም አባ መርአዊ: የመሲ
ኪዳነ ምህረት እመ ወተት እና ከ60 ሺ በላይ ክርስቲያኖች
ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡

+ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንገቷ ከተቆረጠና ሰማእትነት
ከተቀበለች በኋላ ወደ ምድር መልሶ አንገቷን ከቀሪው
የሰውነቷ ክፍል ጋር አዋህዶ ከአንቅልፍ አንደሚነቃ ሰው
ቀስቅሶ አስነስቷቷል፡፡
ከዚያም ከአቡነ ማርቆስ ስርዓተ ምንኩስናን በመቀበል
ዋልድባ ገዳም ለ4 ዓመት አገልግላለች፡፡

+ከዚህም ከ500 የሚበልጡ ተከታዮችዋን መነኮሳትን
አስከትላ በሰሜን ወሎ ቆቦ ወረዳ ወደምትገኘውና በፃድቁ
በአባ ጉባ ተመስርታ ጠፍታ ወደ ነበረችው ራማ ኪደና
ምህረት አንድነት ገዳም በመሄድ ገዳሟን አቅንታ: የወንድ
የሴት ብላ ስርዓት ሰርታ: ገዳሟን አስተካክላ: 500
የሚሆኑ አገልጋች መነኮሳትን አኑራ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ
ጀምራለች፡፡

+በመንገዷም ላይ ሰውን የሚበሉ ወደ ሚኖሩበት አካባቢ
በመድረስ እነርሱም እርሷንና 60 የሚሆኑ አገልጋዮችዋን
ዓይኖቻቸውን በጉጠት በማውጣት ለ4 ወራት በጨለማ
ቤት ውስጥ ዘግተውባቸዋል፡፡ ከአራት ወር በኋላም በዓል
አድገው ለመብላት ከቤት ቢያወጧቸው መልካቸው እንደ
ፀሐይ የሚያበራ ቢሆንባቸው "አንቺ ሴት ምንድን ናችሁ?"
ብለው ጠይቀዋታል፡፡

+እርሷም ክርሰቲያን መሆናቸውንና እነሱ የስላሴ ሕንፃ
የሆነውን የሰውን ልጅ መብላት እንደሌለባቸው
ብትመክራቸው "ምን አንብላ?" ብለዋታል፡፡ እርሷም
ከራማ ኪዳነ ምህረት ስትነሳ የእህል ዘርን በአገልጋዮቿ
አሲዛ ነበርና ስንዴውን በአንድ ቀን ዘርታ: በቅሎ: ታጭዶ:
ደርቆ: ተፈጭቶ ለምግብነት በቅቷል፡፡

+እርሷ ቀምሳ ብታቀምሳቸው እንደማር እንደ ወተት
የሚጣፍጥ ሆኖላቸው በደስታ ተመግበውታል፡፡ ከዚያም
እንደዚህ እያደረጉ እየሰሩ እንዲበሉ አስተምራ: አስጠምቃ
ከ6 የሚበልጡ አብያተ ክርስቲያናትን አስተክላላቸዋለች፡፡
+ከዚያም የተወሰኑ አገልጋዮችን አስቀምጣላቸው ወደ
ኢየሩሳሌም በመሄድ ለ7 ዓመታት በአየሩሳሌም ከኖረች
በኋላ የእመቤታችን በዓል ለማክበር ወደ ግብፅ በመሄድ
ላይ ሳለች በመንገድ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብታ
ስትፀልይ እመቤታችን በስዕሏ ላይ ተገልጣ: ቦታዋ
በኢትዮጵያ መሆኑን ነግራ: እጇን ዘርግታ "ወደ ኢትዮጵያ
ሂጂ" ብላ ነገረቻት::

+በኋላ በብርሃን አምድና በቅዱስ ሚካኤል እየተመራች
አሁን ወደ ምትታወቅበትና የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ወደ
ተገለፀበት እመ ምዑዝ ኪዳነ ምህረት ቅድስት ፍቅርተ
ክርስቶስ አንድነት ገዳም ደርሳለች፡፡
+በቦታው ስትደርስ የቦታው ልምላሜ የሚያስደስት ነበርና
"ይህች ቦታ ምን ታምር!" ብላለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን
ድረስ ምንታምር በመባል ይጠራል፡፡

+ምንታምር ላይ ከአገልጋዮቿ ጋር በመሆን አርፋ ሳለ
ከኢየሩሳሌም መርቶ ያመጣት የብርሃን አምድ በዚያ ቦታ
ላይ በስፋት ረቦ (ከምድር እስከ ሰማ ተተክሎ) ብታየው:
መልአኩም "ቦታሽ ይሄ ነው" ብሎ ቢነግራት በዚያው
ተቀምጣለች፡፡

+የቦታው ባለ አባት "ይህን ቦታ ልቀቂ" ቢሎ ቢጠይቃት
"እግዚአብሔር የሰጠኝ ቦታዬ ነው" ብላዋለች፡፡ እርሱም
ለክስ ወደ ጎንደር በመሄድ አፄ ሱስንዮስ አርፈው አፄ
ፋሲል ነግሰው ነበርና እሳቸውን ፍርድ ቢጠይቃቸው በዝና
ያውቋት ነበርና "ቤተ ክርስቲያን ካልተሰራ ትልቀቅልህ:
ከተሠራ ግን ሌላ ቦታ ይሰጥሃል" የሚል ፍርድ አስፈርዶ
ነበር::

+ሲመለስ ቅዱስ ሚካኤል ቀድሞ "ቶሎ ቤተ ክርስቲያን
ስሪ እንዲህ የሚል ፍርድ ተፈርዷል ብሎ ነግሯት ‹‹ታህሳስ
14 ቀን ከነግህ ፀሎት በኋላ በሰንሰልና በስሚዛ
ግድግዳዋን: በአይጥ ሀረግ ማገር አድርጋ: የግድግዳ
ቤተ መቅደስ በዕለተ አርብ: በአንድ ቀን ሰርታ ታህሳስ 16
ቀን እሁድ ታቦተ ኪዳነ ምህረትን አስገብታ ቅዳሴ
አስቀድሳለች::››

+ቅዳሴውም ከተፈፀመ በኋላ ጌታችን ከቅዱስ መንበሩ
ላይ እንዳለ ሆኖ ከእናቱ ከእመቤታችን ጋራ ታያቸው፡፡
ከመንበሩ ወርዶም ይህን ቦታ በባረከው ጊዜ የስሚዛው
ቤተ መቅደስ በአራቱም አቅጣጫ ለፈጣሪው ሰገደ፡፡

+የመሬት መናወጥም ሆነ:: ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም
"ልታጠፋን መጣህን? ቤተ ክርሰቲያኔንስ ልታፈርሳት
ነው?" ብላ ብትጠይቀው "ይህ የሰንሰል ቤተ መቅደስሽ
ዳግም እስከምመጣ ድረስ ሳይፈርስ: ሳይታደስ ፀንቶ
ይኖራል፣ በውስጡም እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ
የክሀድያንና ፣ መናፍቃን እግር አይገባበትም፣ በውስጧ
ቁርባንን የተቀበሉ ሁለ ኃጢያታቸው ይሰረይላቸዋል፣
ዘወትር ምህረቴ በረከቴ ከእነርሱ ጋር ይኖራል" በማለት
ተናግሮ ተሰወራቸው፡፡

+ከዚያም በኋላ መነኮሳትና መነኮሳይያት የቅድስት ፍቅርተ
ክርስቶስን የትሩፋት ዜናዋን ሰምተው ከየአቅጣጫው
ተሰበሰቡ፡፡ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም በአምላክ ሀይል
ተጋድሎአቸውን ይፈፅሙ ዘንድ ታስተምራቸው ፣
ትመክራቸው፣ በተግባርም እያሳየቻቸው ለብዙ ዘመናት
ከኖሩ በኋላ በገዳሙ ላይ የአጋንንት ፆር እንዳይነሳ
ወንዶቹን ለብቻ ሴቶቹን ለብቻ አደረገች፡፡

+ዘወትርም እንዳይተያዩ የእግዚአብሔር መልዐክ
በቅድስተ ፍቅርተ ክርሰቶስ ፀሎት ይጠብቃቸው ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ከዚህ
ኃላፊ ዓለም መለየቷ በቀረበ ጊዜ ሁለት መላዕክት ወደ
እርሷ መጥተው በብርሃን ሰረገላ ጭነው ወደ ደብረ ነባት
(ወደ ብሔረ- ህያዋን) ወስደው በዚያ ቅዱስ ቁርባንን
አቀብለው ወደ ቦታዎ መለሷት፡፡

+መልዐኩም "ከጻማ: ከድካም: ከመታረዝ: ከረሐብ
ከጥም: ከመትጋት: ከእንባ: ከዚህ ዓለም የምትለይበት
ጊዜ እነሆ ደረሰ" አላት፡፡ የካቲት 27 ቀንም ወደ ምስራቅ
እጇን ዘርግታ ቆማ ስትጸልይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ
ከደስታ ብርሀን ጋር ያማረ ሽታ መላ::

+ጌታችን ከአዕላፋት መላዕክትና ቅዱሳን ጋር ወደ እርሷ
መጣ፡፡ እናታችን ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ሰገደች፡
ተንበረከከች: እጅግም አለቀሰች፡፡ ከወደቀችበት ቦታ
አንስቶ ‹‹ላጠፋሽ አልመጣሁም ወዳጄ ላከብርሽ ነው
እንጂ›› አላት፡፡

+"የዘለአለም መንግስት አዘጋጅቼልሻለሁና ደስ ይበልሽ"፡፡
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስም ቃል ኪዳን እንዲገባላት
ተማጸነችው:: ጌታችንም ‹‹ሁሉም እንደ ቃልሽ ይሁንልሽ::
በስምሽ ስሜ ተጨምሯልና ለቤተ ክርስቲያንሽ መባ
የሰጠ፣ የተላከ ፣የተቀበረ፣ ቤተ መቅደስሽ መጥቶ
የተሳለመ ፣ እስከ 12 ትውልድ የምህረት ቃል ኪዳን
ሰጠሁሽ::

+በረከቴም በቤቱና በልጆቹ በገንዘቡም ላይ ይደር::
የገድልሽ መጽሐፍ ባለበት አጋንንት (ሰይጣናት)
አይቀርቡም:: በአዝመራ ስምሽን በጠሩት ጊዜ የለመለመ
ይሁን:: በጸሎትሽ የተማጸነ ሁሉ ባለጤና ይሁን::

+ስምሽን በእውነት የሚጠራ የከበረ ነው፡፡ ያለመጠራጠር
በቀናች ሐይማኖት የገድልሽን መጽሐፍ የጻፈ: ያጻፈ:
ያነበበ: የተረጎመ በሐይማኖት የሰማ: እስከ ቀዝቃዛ ውሃ
ድረስ የሰጠ ኃጢያቱ ይሰረይለታል::
ስለ ድካምሽ ስለ ትሩፋትሽ 7 አክሊሎችን እና ይህን ሁሉ
ቃል ኪዳን ሰጠሁሽ፡፡ ላልምረው ቦታሽን
አላስረግጠውም›› ብሏት ወደ ሰማይ አረገ፡፡

+በማግስቱ ትንሽ ህመም ታመመች ደናግል መነኮሳትን
ጠርታ የእረፍት ቀኗ መድረሱን ነገረቻቸው:: ከመካከላቸው
አንዷን ለገዳሙ አስተዳዳሪነት መርጣ በፍቅር ስም
ተሰናበተቻቸው፡፡ የዳዊት መዝሙርንም ስትጸልይ የካቲት
29 ቀን እሁድ አጥቢያ ጠዋት በጌታ በዓል አንቀላፋች
(ነፍሷ ከስጋዋ ተለየች)፡፡

+ጌታችንም ከእናቱ: ከቅዱሳኑ ጋር መጥቶ ነፍሷን
ተቀብሎ ወደ ዘለዓለም ገነት ወሰዳት፡፡ ቅዱሳንም
ከመላእክት ጋር እልል እያሉ እያመሰገኑ ወደ ዘለዓለም
ቦታ ገነት አስገቧት፡፡ ከቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ መቃብር
ላይ 40 ቀናት ብርሃን ሲበራበት ታይቷል፡፡

+በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት: በመቂት ወረዳ ጥባ
ማርያም ቀበሌ ውስጥ ምን ታምር በመትባል ቦታ ላይ
በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያዊቷ ሰማዕትና ጻድቅ
ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ የተመሰረተቸው እመ ምዑዝ
ኪዳነ ምህት ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ አንድት ገዳምም
በዓላቶቿ የሚከበሩት ታህሳስ 16 የቅዳሴ ቤቷ እንዲሁም
የካቲት 29 ቀን በዓለ እረፍቷ ይከበራል፡፡

††† ከቅድስት እናታችን በረከት አምላክ አይለየን::

††† የካቲት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
2.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)
3.ቅዱሱ ሕፃን (የፍቅርተ ክርስቶስ ልጅ)
4.ቅዱስ ቢላካርዮስ ዘሃገረ አርሞኒ (አረጋዊ: ደራሲ: ጻድቅና ሰማዕት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ

††† "መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ:: አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ::
ውበት ሐሰት ነው:: ደም ግባትም ከንቱ ነው::
እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች:: ከእጇ ፍሬ ስጧት:: ሥራዎቿም በሸንጐ ያመስግኗት::" †††
(ምሳሌ. 31:29)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!†††

††† ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ †††

††† ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል::
"ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

*የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ ደግሞ 100 ደርሶ ነበር::

*ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

*ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

*የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

*ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

*እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

*ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

*ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

*ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

*ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

*ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ "አጥምቀኝ" ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

*"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

*ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)*ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

*ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

††† አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች)
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም መጥምቁ ዮሐንስን አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::

††† የካቲት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
(ታላቁ ነቢይና ካህን መጥምቁ ዮሐንስ ሔሮድስ በግፍ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ ቅድስት ራሱ ለ15 ዓመታት ዙራ አስተምራ አርፋለች:: በዚህ ዕለትም በልሑክት (በሸክላ ዕቃ) የተገኘችበት በዓል ይከበራል:: በዓሉም "ተረክቦተ ርዕሱ" በመባል ይታወቃል:: )
2.አባ ሚናስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
2.አባ ሣሉሲ ክቡር
3.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
4.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

††† "ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም . . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ::" †††
(ማቴ. 11:7-15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኩዋን ከተባረከ ወር መጋቢትና ከሁለተኛው መንፈቀ ዘመን የመጀመሪያ ዕለት በሰላም አደረሳችሁ

=>ወርኀ መጋቢት መዐልቱና ሌሊቱ እኩል (12:00) ናቸው:: ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ ለሚቀጥሉት 6 ወራት (186 ቀናት) ከማይጠቅም ወሬ ተቆጥበን: ከክፋትም ርቀን መልካሙን የእግዚአብሔር ጐዳና ለመከተል ራሳችንን ልናዘጋጅ ይገባል::

=>በዚህ ዕለትም ከአዳም 8ኛ ትውልድ የሆነው አባታችን ማቱሳላ በዓሉ ይከበራል:: ቅዱስ ማቱሳላ የጻድቅ ሰው ኄኖክ ልጅ: የደጉ ላሜሕ አባት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ረዥም ዕድሜ (969 ዓመት) የቆየ ባለ ረዥም ዕድሜ አባት ነው:: ከአሥሩ ቅዱሳን አባቶች አንዱ ነው::

+10 ቅዱሳን አባቶች ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ ናቸው::

† ቅዱስ በርኪሶስ †

«« በዚች ቀን የኢየሩሳሌም አገር ኤጲስቆጶስ ቅዱስ በርኪሶስ አረፈ።ይህም አባት ክርስቲያኖችን በሚወዳቸው በቄሳር እለእስክንድሮስ ዘመነ መንግስት ተሹሞ ሳለ ሀዋርያት ሲጠብቋቸው እንደነበር በበጎ አጠባበቅ ህዝቡን ጠበቃቸው ።

«ከጥቂት ጊዜ በኃላ እለእስክንድሮስ ሞተ ከእርሱ በኃላ ቄሳር መክስሚያኖስ ነገሰ። ክርስቲያኖችውም በፅኑእ መከራ አሰቃያቸው ከእርሳቸውም ብዙዎችን ገደላቸው።

ሀገሮቻቸውን ትተው የተሰደዱም አሉ። ይህም አባት ሽሽቶ ወደ ገዳም ገባ ህዝቡም ፈልገው አጡት።

ከዚህም በኃላ ስሙ ዲዮስ የተባለ ሌላ ኤጲስቆጶስ በላያቸው ሾሙ። እርሱም በጥቂት ቀን አረፈ። ከዚህ በኃላ ስሙ አግርንዲኖስ የሚባል ሌላ ኤጲስቆጶስ ሾሙ።

የስደቱም ወራት በአለፈ ጊዜ ይህ አባት በርኪሶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ተመለሰ ።አግርንዲኖስ የሚባል ሌላ ኤጲስቆጶስ ሹመው አገኛቸው።

ወደርሳቸውም በደረሰ ጊዜ ህዝብ በመምጣቱ ደስ አላቸው አግርንዲኖስም ተመልሶ በመንበረ ጵጵስናው ላይ እንዲ ቀመጥ ለመነው በታላቅ ድካምም በወንበሩ ላይ አስቀመጡት። ከአግርንዲኖስም ጋራ አንዲት አመት ኖረ አግርንዲኖስም አረፈ።

አባ በርኪሶስም እጅግ እስኪያረጅና እስኪያረጅና እስኪደክም ድረስ ኖረ ወገኖቹንም ሌላ ኤጲስ ቆጶስ በላያቸው እንዲሾሙ ለመናቸው እነርሱም አይሆንም አሉ።

በዚያም ወራት የቀጰዶቅያ ኤጲስቆጶስ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። እርሱም በውስጥዋ ሊፀልይና ወዳገሩ ሊመለስ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።ስራውንም በጨረሰ ጊዜ የበአሉም ቀኖች በተፈፀሙ ጊዜ ወዳገሩ ሊመለስ ወደደ።

በመድኃኒታችን ትንሳኤ በአል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መግቢያ ወደ እገሌ ደጃፍ ውጡ ወደ ደጃፉ መጀመሪያ የሚገባውን ያዙት በጵጵስና ስራም ይረዳው ዘንድ ከበርኪሶስ ጋር አድርጉት የሚል ቃል እነሆ ተሰማ።

ወጥተውም ወደ ደጃፉ በደረሱ ጊዜ እለእስክንድሮስን አገኙት ይረዳውም ዘንድ ያለ ፈቃዱ ከአባት በርኪሶስ ጋራ አደረጉት። እስከሚአርፍበትም ጊዜ አብሮት ኖረ።

መላ የህይውቱ ዘመን አንድ መቶ አስራ ሰባት አመት ሆነ ኤጲስቆጶስነት ሳይሾም ሰማንያ አንድ አመት ኖረ በሹመቱም ላይ ሰላሳ ስድስት አምታትን ኖረ። እግዚአብሄርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

† ቅዱስ እለእስክንድሮስ †

በዚችም እለት የሰማእቱ የቅዱስ እለእስክንድሮስ መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ ሰማእት የሮም ሀገር ሰው ነው ለእርሱ ባለመታዘዙና ለረከሱ ጣኦቶቹ ባለመሰዋቱ ከሀዲው መክስሚያኖስ ፁኑእ ስቃይን አሰቃየው።

እጅግ ከባድና ታላቅ የሆነ ደንጊያ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ አስሮ ሰቀለው። ብዙ ግርፋትንም ገረፈው ጎኖቹንም ቀደደ በፊቱም ላይ የእሳት መብራት ጨመሩ።

ስቃዩንም ባልፈራ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።
በመንግስተ ሰማያትም የሰማእታትን አክሊል ተቀዳጀ።

=>ዕድሜ ማቱሳላን ለንስሃ አምላከ ቅዱሳን ይስጠን!

=>መጋቢት 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ማቱሣላ (በ969 ዓመቱ ያረፈበት)
2.ቅዱስ በርኪሶስ ዘኢየሩሳሌም
3.ቅዱስ እለእስክንድሮስ
4.ቅዱስ መርቆሬዎስ
5.አባ ሚካኤል ዘሃገረ አትሪብና አባ ዮሐንስ ዘሃገረ ቡርልስ
(ሃይማኖተ አበውን: ግፃዌንና ስንክሳርን ያዘጋጁ ናቸው)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

=>+"+ ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ:: ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቧልና:: ሌሊቱ አልፏል: ቀኑም ቀርቧል:: እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ:: +"+ (ሮሜ. 13:11)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት †††

††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሃገሩ ሮሃ (ሶርያ አካባቢ) ሲሆን ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን የተመለከተ) ይባላል::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ሃገር ይህ ቀረው የማይባል ኃጢአተኛ ሰው ነበር:: ታዲያ ምንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍፁም ልቡ ይወዳት ነበርና በመዳን ቀን ጥሪ ለንስሐ አበቃችው::

ከዚያች ዕለት ጀምሮም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው : ንጹሕ የቤተ ክርስቲያን መስዋዕት : ጽኑዕ የበርሃ ምሰሶ ሆነ:: ድንግል እመቤታችንም ከነሥጋው ወደ ሰማያት ወስዳ ገነትና ሲዖልን አሳይታ : ከአዳም : ኖኅ : አብርሃም : ሙሴ : ዳዊትን ከመሰሉ ቅዱሳን ጋር አስተዋውቃ : ከዚህም በላይ የሆነና በሰብአዊ አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢር አሳይታ ወደ ምድር መልሳዋለች::

ቅዱስ ጐርጐርዮስ በሰማይ (በገነት) በነበረው ቆይታ ክብረ ቅዱሳንን ተመልክቶ አድንቋል:: በተለይ በፍጹምነት ድንግልናቸውን የጠበቁ ቅዱሳንና ቅዱሳት ደናግል አኗኗራቸው ከአምላክ እናት : ከሰማይ ንግሥት : ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ጋር መሆኑን አይቷል::

"የለበሱት ልብስም በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የሚቻል አይደለም" ይላል:: የደናግል ፊታቸው ከፀሐይ 7 እጅ ያበራልና ግርማቸው ያስፈራል::

ቅዱሱ ሰው በዚያው በሰማይ ሳለ ደግሞ ይህንን ተመለከተ:: አንድ አረጋዊ : ጽሕሙ ተንዠርግጐ : የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሶ ይመጣል:: ቅዱሳን መላእክት በፊት በኋላ : በቀኝ በግራ ከበውት ሳለ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ጀመረ::

"እግዚኦ እግዚእነ : ጥቀ ተሰብሐ ስምከ በዲበ ምድር (አቤቱ ጌታችን : በምድር ሁሉ ስምህ የተመሰገነ ሆነ)" ሲል . . . መላእክቱ በዝማሬ አጀቡት:: በዚህ ጊዜም ታላቅ መናወጥ ሆነ:: ደናግሉም የቅዱሱን ሽማግሌ በረከቱን ተሳተፉ::

ይህ አመስጋኝ ሽማግሌ ልበ-አምላክ : ጻድቅ : የዋህና የእሥራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነበር:: በምን ታወቀ ቢሉ :- በበገናው:: አንድም እመቤታችን "አባቴ ዳዊት!" ብላ ስትጠራው ጐርጐርዮስ ሰምቷልና::

በመጨረሻም እመቤታችንን በፍጹም ክብርና ግርማ ተመልክቷት ሐሴትን አድርጓል:: እመ-ብርሃንም "ተወዳጅና ንጹሕ ሰው ነህ" ስትል ቅዱስ ጐርጐርዮስን አመስግናዋለች:: ስለዚህ ዓለምም እንዲህ የሚል መልእክትን ልካለች::

"ልጆቼ ሆይ! ከብርሃን ጨለማን : ከደግነት ክፋትን : ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን . . . ምነው መምረጣችሁ? እኔ ስለ እናንተ በየቀኑ እየለመንሁ እነሆ አለሁ:: ወደ ጨለማ ገሃነም እንዳትወርዱ እባካችሁ ንስሐ ግቡ!"

ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ለቅዱሱ ሰው ነግራው : ቅዱስ ዳዊትን አስከትላ : በግሩማን መላእክት ታጅባ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት (የእሳት መጋረጃዎች ወደ ተተከሉበት ድንኳን) ገባች:: በዚያም ተመሰገነች::

ለዛም አይደል ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ:-
"ይዌድስዋ መላእክት ለማርያም በውስተ ውሳጤ መንጦላዕት : ወይብልዋ : በሐኪ ማርያም ሐዳስዩ ጣዕዋ::" ሲል ያመሰገናት::

ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከሰማይ ቆይታ መልስ ያየውን ሁሉ ጽፎ ለአበው ሰጥቷል:: ስለዚህም ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን ያየ) ይሰኛል:: ቅዱሱ ተረፈ ዘመኑን በተጋድሎ ፈጽሞ በዚህች ቀን አርፏል::

††† የቅዱሱ እመቤት ድንግል እመ ብርሃን መዓዛ ፍቅሯን ታብዛልን::

††† መጋቢት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት (ዘሃገረ ሮሃ)
2.አቡነ መክፈልተ ማርያም ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
3.አባ መከራዊ ዘሃገረ ኒቅዮስ (አረጋዊ: ጻድቅ: ጳጳስና ሰማዕት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
4.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
7.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

††† "ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" †††
(፩ጢሞ. ፩፥፲፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ቆዝሞስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቆዝሞስ ሊቀ ጳጳሳት †††

††† "ጳጳስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ 3 ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ጵጵስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ 9 ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ጵጵስና ነው::

ጵጵስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር "ሸክም: ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ጵጵስናን አይመኝም::

ቅዱስ ጳውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ጵጵስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" (1ጢሞ. 3:1) ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የጳጳሱ ነው::

አንድ ጳጳስ ቢጾም ቢጸልይም እንኳ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" (ዮሐ. 10) ስለዚህም ክህነት ( ጵጵስና) ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው::

አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የጵጵስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ጵጵስናዎች አራቱ የበላይ ናቸው::

እነዚህም የቅዱስ ጴጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ጳውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው::

እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ 443 (451) ዓ/ም: ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው::

የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ጳጳሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች::

በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ ቅዱስ ቆዝሞስ የእስክንድርያ (የግብጽ) 58ኛ ሊቀ ጳጳሳት የነበረ አባት ነው:: ዘመኑ እስልምና የሰለጠነበት ነበርና በዚያ ጊዜ እረኝነት (ጵጵስና) መመረጥ እንደ ዛሬው ዘመን ሠርግና ምላሽ አልነበረም:: በከሃዲዎች እሳትና ስለት መከራን ለመቀበል መወሰን እንጂ::

ከ6ኛው መቶ ክ/ዘመን በኋላ በዓለማችን ከተነሱ ሊቃነ ጳጳሳት ለግብጻውያኑ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ቦታ አላት:: ምክንያቱም በወቅቱ በጎቻቸውን (ምዕመናንን) ለመጠበቅ ከግብጽ ከሊፋዎች የግፍ ጽዋዕን ጠጥተዋልና:: ከነዚህም አንዱ የእመቤታችን ፍቅር የበዛለትና በዚህ ቀን ያረፈው ቅዱስ ቆዝሞስ ነው::

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን::

††† መጋቢት 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ቆዝሞስ (የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት)
2.አባ በርፎንዮስ ክቡር

††† ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

††† "ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን: መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናቹሃለሁ:: ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ:: እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና:: በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ::" †††
(ሮሜ ፲፮፥፲፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
መጋቢት 4 (ድርሳነ መስቀል)

✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይ : ጠቢብና የእሠራኤል ንጉሥ "ቅዱስ ሰሎሞን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" #ቅዱስ_ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል "*+

=>መፍቀሬ ጥበብ::
¤ጠቢበ ጠቢባን::
¤ንጉሠ እሥራኤል::
¤ነቢየ ጽድቅ::
¤መስተሣልም (ሰላማዊ) . . . እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ #ቅዱስ_ዳዊት እና የቅድስት #ቤርሳቤህ (#ቤትስባ) ልጅ ነው:: ከ3ሺ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ 12 ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጉዋል::

+ቅዱስ ዳዊት 70 ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ : አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም:: #እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በ12 ዓመቱ ነገሠ:: ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው:: "ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ:: ፈጣሪህንም አምልክ" አለው::

+ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ:: ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን : ልቡናን ለመነ:: በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ : ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት : ከአንተም በሁዋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም : አይኖርም" ብሎት ተሠወረ:: ቅዱስ ሰሎሞን ለ40 ዓመታት በእሥራኤል ላይ ነገሠ::

+ግሩም በሆነ ፍትሑ : በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት:: እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ #ንግስተ_ሳባ / #አዜብ / #ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን (#እብነ_መለክን) ጸነሰች:: በሁዋላም #ታቦተ_ጽዮንና #ሥርዓተ_ኦሪት መጣልን:: ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን #ድንግል_ማርያም ከእነሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር::

+ነገር ግን:-
¤አንደኛ ሰው (ሥጋ ለባሽ) ነውና::
¤ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ #እመ_ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር:: ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ (ከፈርዖን ልጅ) ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው:: እግዚአብሔር እጅግ አዘነ::

+በራዕይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ #ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም" አለው:: ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ:: ማቅ ለብሶ : አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ:: ንስሃ ገባ:: መፍቀሬ ንስሃ ጌታችንም ንስሃውን ተቀበለው::

+የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን 5 መጻሕፍት ገለጠለት:: ተናገራቸው:: ጻፋቸው:: እሊሕም:-

1.መጽሐፈ ጥበብ
2.መጽሐፈ ተግሣጽ
3.መጽሐፈ መክብብ
4.መጽሐፈ ምሳሌ
5.መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው::

+ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን #ቤተ_መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል:: ደጉ ንጉሥ : ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በ52 ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል:: (እንደ ድርሳነ መስቀል ኢትዮጵያዊ ትውፊት)

=>ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን በረከት ይክፈለን፡፡
=>መጋቢት4 የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት።
1.መፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን

=>ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

=>+"+ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ : ፀሐይ : ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ : ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ : ከንቱ : ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል:: +"+ (መክ. 12:1-9)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
2025/03/13 05:30:56
Back to Top
HTML Embed Code: