tgoop.com/mihret_debebe/211
Last Update:
ቋንቋችን “ጊዜ” ይባላል!
አንድን ሰው ከልባችሁ የምታከብሩት ከሆነ ቀላሉ መመዘኛ የዚያን ሰው ሰዓት ወይም ጊዜ የማክበራችሁና ያለማክበራችሁ ጉዳይ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ጊዜያችሁን ሰውታችሁ ለዚያ ሰው ስትሰጡት ያንን ሰው እንደምታከብሩት መልእክትን እያስተላለፋችሁ ነው፡፡ ገንዘብ፣ ቁሳቁስና የመሳሰሉት ነገሮቻችሁን ለማንም ሰው ልትሰጡ ትችላላችሁ፣ ጊዜያችሁን (በተለይም የተጣበበውን) ግን ለሚከበርና ለመወደድ ሰው ነው የምትሰጡት፡፡
አንድ ስራ በትክክል ከተከናወነ ወሳኝ የሆነ ጥቅም እንዳለው ስታምኑ ስራውን በሰዓቱ ጀምራችሁ በሰዓቱ ታጠናቅቁታላችሁ፡፡ ስለሆነም፣ ግድ ከማይሰጣችሁ ስራ ጊዜን እየወሰዳችሁ ለምታከብሩትና ጥቅም ላለው ታውሉታላችሁ፡፡
ማሰተካከያ ልናደርግበት የሚገባን ቀውሰ ያለው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፡፡ የአብዛኛዎቻችን የግንኙነት ቀውሶች፣ በስራ ስኬታማ ያለመሆንና የመሳሰሉት ቀውሶች መነሻቸው ለምንወደውና ለእኛ ወሳኝ ለሆነ ሰውም ሆነ ስራ ተገቢውን ጊዜ አለመመደብና አለመስጠት ነው፡፡ ይህ ቀውስ ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ሰዎችንና ስራዎችን ከእጃችን እንዲወሰዱ ያደርገናል፡፡
ይህንን አትርሱ፣ ማንኛውም ሰው ሆነ ስራ እኛ ተገቢውን ጊዜና ትኩረት ካልሰጠነው ተገቢውን ጊዜና ትኩረት የሚሰጡት ሰዎች “ላፍ” አድርገው ይወስዱታል፡፡
ጊዜያችሁን ለምትወዱት፣ ለምታከብሩትና ቅድሚያ ለምትሰጡት ሰው ስትሰጡ ተገቢውን ምላሽ ታገኛላችሁ፡፡ ተገቢውን ምላሽ ካላገኛችሁ ደግሞ ግንኙነታችሁን እንደገና ማጤንና ማስተካከያ ማድረግ የግድ ነው፡፡
ዋጋ ለምትሰጡት ስራም ቢሆን ጊዜ ስትሰጡት ስራው ውጤትን በመስጠት ይመልስላችኋል፡፡ ስራው ጊዜያችሁን እየወሰደ ውጤት የማይሰጣችሁም ከሆነ ደግሞ ስራው እንደገና ሊቃኝ ይገባዋል፡፡
ለዚህ ነው “ጊዜ” የመግባቢያ ቋንቋ ነው የምንለው፡፡@mihret_debebe
BY ዶ/ር ምህረት ደበበ
Share with your friend now:
tgoop.com/mihret_debebe/211