tgoop.com/nahuseman25/619
Last Update:
✝✝✝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤፤ ✝✝✝
✝ መስከረም 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
+" ቅድስት ሐጊያ ሶፍያ "+
✝ዘመነ ሰማዕታት በሚል በሚታወቀው 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ብዙ ቅዱሳት እናቶቻችን ስለ ፍቅረ ክርስቶስ አንገታቸውን ሰጥተዋል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ሕይወታቸው እጅግ የሚያምር ነበር:: ከእነዚህ ቅዱሳት እናቶቻችን አንዷ ዛሬ የምናከብራት ሐጊያ ሶፊያ ናት::
+በዚህ ስም ከሚጠሩት አንዷ ስትሆን በቀደመ ሕይወቷ ክርስቶስን አታውቅም ነበር:: ጣዖትን የሚያመልኩ ወላጆቿ አሳድገው አጋቧት:: ከትዳሯም 2 ቡሩካት ሴቶች ልጆች ወልዳለች:: ስማቸውም አክሶስናና በርናባ ይባላል:: ልጆቿ ልብ እያገኙ በሔዱ ጊዜ ቅድስት ሶፍያ ስለ እውነተኛው አምላክ ትመራመር ገባች::
+በወቅቱ የነበሩ ብዙ ሃይማኖቶችን መዘነች:: ከክርስትና በቀር ግን ሌሎቹ ሚዛን እንደማይመቱም አስተዋለች:: "እውነኘተኛው አምላክ ሆይ! ምራኝ: እርዳኝም" ስትል ጸለየች:: መድኃኔ ዓለም ለጠሩት አያሳፍርምና ፈጥኖ በጐውን ጐዳና አሳያት::
+ድኅነት ለልጆቿም ይሆን ዘንድ ሁለቱንም ጠርታ ስለ ክርስትና አማከረቻቸው:: ደስ ብሏቸው ተቀበሏት:: እርሷም ጊዜ ሳታጠፋ ወደ ዻዻስ ሒዳ ማሕተመ ክርስትና: ሃብተ ውልድናን ትቀበል ዘንድ ከልጆቿ ጋር ተጠመቀች:: በቅድስናና ደስ በሚያሰኝ አኗኗርም እስከ መከራ ቀን ቆየች::
+የመከራ ጊዜ ሲደርስም ልጆቿን ጠርታ "ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንሙት" አለቻቸው:: ቡሩካቱ አክሶስናና በርናባም ደስ እያላቸው "እሺ" አሏት:: ወዲያውም በመኮንኑ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ከመካድና ከስቃይ ሞት የትኛውን እንደሚመርጡ ቢጠየቁ እነርሱ መሞትን መረጡ:: ወደ እሥር ቤትም ከተቷቸው::
+ቅድስት ሶፍያ 2 ልጆቿ ይጸኑላት ዘንድ አዘውትራ ገድለ ሰማዕታትን እና ክብራቸውን ትተርክላቸው ነበር:: በተለይ የታላቁዋን አንጌቤናይት (እመቤት) ሶፍያንና የ3 ልጆቿን (ዺስጢስ: አላዺስና አጋዺስ) ተጋድሎ እየነገረች ታጸናቸው ነበር::
+ከእሥር በኋላ ግርፋት ታዞባቸው እናት ራቁቷን ስትገረፍ መልአክ ወርዶ ሲጋርዳት ልጆች በማየታቸው ደስ አላቸው:: ቅድስት ሐጊያ ሶፍያና 2 ልጆቿ እጅግ የበዛ ስቃይን ስለ ቀናች እምነት ተቀበሉ:: ምላስ እስከ መቆረጥም ደረሱ:: በመጨረሻ ግን በዚህች ቀን ተገድለው አክሊለ ሰማዕታትን ገንዘብ አደረጉ::
+የመከራ ዘመን ካለፈ በኋላ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ የሁሉን ቅዱሳን ቤት ሠርቶ የእርሷን በመዘንጋቱ ለራሱ ባሰራው ቤተ መንግስት ላይ ተአምር ታይቷል:: ለ3 ያህል ጊዜ ስሙን ሲያስቀርጽ መልአክ እየወረደ ይፍቀው: የሶፍያንም ስም ይጽፈው ነበር::
+በመጨረሻም ንጉሡ ልጁን እስከ መገበር ደርሶ ቤተ መንግስቱ የቅድስት ሶፍያና የ2 ልጆቿ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል:: ምንም ለ3 ጊዜያት ያህል ሙሉ እድሳት ቢደረግለትም ዛሬ አሕዛብ የያዙትን ይህንን ቅርስ ንጉሡ የሠራው ከ1700 ዓመታት በፊት ነው::
+" ቅዱስ ማማስ ሰማዕት "+
✝የሰማዕቱ ወላጆች ቴዎዶስዮስና ታውፍና ሲባሉ ማማስ የሚለው የስሙ ትርጉም 'ዕጉዋለ ማውታ - እናት አባቱ የሞቱበት' ማለት ነው:: ለምን እንደዚህ ተባለ ቢሉ:- በዘመነ ሰማዕታት ስደት በሆነ ጊዜ ወላጆቹ ይዘውት ተሰደው ነበር:: ማምለጥ ባይችሉ ይዘው አሠሯቸው::
+በእሥር ቤትም ከስቃዩ ብዛት 2ቱም ልጃቸውን ማማስን እንዳቀፉት ሕይወታቸው አለፈች:: ሕጻኑ ሲያለቅስ የተመለከተች አንዲት ሴትም ራርታ እነርሱን አስቀብራ: እርሱን አሳድጋዋለች:: ስሙንም 'ማማስ' ብላዋለች::
+ቅዱሱ ባደገ ጊዜ የወላጆቹን ጐዳና በመከተሉ ተይዞ ለፍርድ ቀረበ:: ክርስቶስን አልክድም በማለቱም ብዙ ስቃይን አሳልፎ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል:: ቅዱስ ማማስ ከዐበይት ሰማዕታት አንዱ ሲሆን በአንበሳ ጀርባ ላይም ይቀመጥ ነበር::
+" አቡነ አሮን መንክራዊ "+
✝ኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ አሮን በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ኢትዮዽያዊ ሲሆኑ በገዳማዊ ሕይወታቸው: በሐዋርያዊ አገልግሎታቸውና ነገሥታቱን ሳይፈሩ በመገሰጻቸው ይታወቃሉ:: በተለይም ሕይወታቸው በተአምር የተሞላ ስለነበር 'አሮን መንክራዊ' (ድንቅ አባት) ተብለው ይጠራሉ::
+አንዳንድ ጊዜም 'አሮን ዘመቄት /ዘደብረ ዳሬት/' በሚልም ይጠራሉ:: የአቡነ አሮን ወላጆች ገብረ መስቀልና ዓመተ ማርያም የሚባሉ ሲሆን ከልጅነታቸው ጀምረው በቅዱስ ቃሉ የታነጹ ነበሩ:: ምናኔን በደብረ ጐል: ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጀምረው ብዙ ገዳማትን መሥርተዋል:: በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፍርተዋል::
+ለወንጌል አገልግሎት በወጡበት ጸሐይን አቁመው: ሕዝቡን ድንቅ አሰኝተዋል:: እንኳን ሰዉ ይቅርና አጋንንትም ያደንቁዋቸው ነበር:: ነገሥታቱንም ስለ ኃጢአታቸው በገሰጹ ጊዜ ራቁትነት: እሥራት: ግርፋትና ስደት ደርሶባቸዋል::
+ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ በዚህች ቀን ወሎ መቄት ውስጥ በሚገኘው ገዳማቸው ዐርፈው ተቀብረዋል:: ገዳሙ እስካሁን ያለ ሲሆን ድንቅ ጥበበ እግዚአብሔር የሚታይበት ነው:: ጣራው ክፍት ሲሆን ዝናብ አያስገባም::
+" አፄ ልብነ ድንግል "+
✝እኒህ ንጉሥ ኢትዮዽያን ለዓመታት (ከ1500 እስከ 1532 ዓ/ም) ቢያስተዳድሩም 15ቱ ዓመት ያለቀው በስደት ነው:: ከደጋጉ አፄ ናዖድና ንግሥት ወለተ ማርያም ተወልደው: በሥርዓቱ አድገው ቢነግሡም: በክፉ መካሪዎች ጠንቅዋይ ወደ ቤታቸው ገብቶ ሃገሪቱን ለመከራ ዳርጉዋታል::
+ዛሬም ድረስ ጠባሳው ያለቀቀው የግራኝ ወረራ ለ15 ዓመታት ሃገሪቱን ያለ ካህንና ቤተ ክርስቲያን አስቀርቷት ነበር:: ብዙ ክርስቲያኖችም ሰልመው ቀርተዋል:: አፄ ልብነ ድንግል ግን ደብረ ዳሞ ገዳም ውስጥ ገብተው ንስሃ ጀመሩ: አለቀሱ: ተማለሉ::
+እመቤታችን ተገልጣም "ይቅርታን በነፍስህ እንጂ በሥጋህ አታገኝም" አለቻቸው:: እርሳቸውም ሱባኤውን ቀጥለው: 'ስብሐተ ፍቁርን': 'መልክአ ኤዶምን' የመሰሉ መጻሕፍትን ደርሰው በዚህች ቀን በ ዓ/ም ዐርፈዋል:: እኛ ክርስቲያኖችም እናከብራቸዋለን::
+የቅዱሳኑ አምላክ የወዳጆቹን ፈተና አስቦ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቡንም ከስደት ይሰውርልን:: ከበረከታቸውም አይለየን::
+መስከረም 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
2.ቅዱሳት አክሶስናና በርናባ
3.ቅዱስ ማማስ ሰማዕት
4.ቅዱሳን ቴዎዶስዮስና ታውፍና
5.አቡነ አሮን መንክራዊ
6.አፄ ልብነ ድንግል
በ 05 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
++"+ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን: ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን:: ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን:: +"+ (ሮሜ. 6:5)
‹‹‹‹ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ››››
BY ናሁ ሰማን(Nahu seman)
Share with your friend now:
tgoop.com/nahuseman25/619